እንደ መግቢያ
ሥራው አጥጋቢ ባለመሆኑና የቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻላቸው ትዳራቸው መፍረሱ ልባቸውን ያደማዋል። አሁን እየኖሩት ያለው ሕይወት ቤተሰቦቻቸውን ትተው በመጡ ጊዜ እንግዶቼ ብሎ በተቀበላቸው በረንዳ ላይ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ከበረንዳ ተነስተው ተመልሰው ወደ በረንዳ ሲገቡ ብዙ ተፀፅተናል ይላሉ። ኑሮ የጭካኔ በትሯን በእኛ ላይ ስለማበርታቷ እማኝ ሳንቆጥር ትዳራችን ፈርሶ፤ ቀድሞ ምርር ብሎን ወደ ነበረው ሕይወት መመለሳችን ሕያው ምስክር ነው ይሉታል – በመቆጨት ስሜት። ጥላሁን እና ተሾመ በትዳርም ሆነ በኑሮ መዛባት ክፉኛ ተፈትነዋል። ወዲህ ደግሞ ፈተናዎችን ለማለፍ ከኑሮ ጋር ግብግብ ገጥመዋል በሚችሉት ሁሉ።
ጥላሁን እና ተሾመ
ጥላሁን ሸዋ ፈረጃ በጉራጌ እነሞር በሚባል አካባቢ የተወለደ ሲሆን 41 ዓመት ሞልቶታል። ለመጀመሪያ ጊዜ እግሩ አዲስ አበባን የረገጠው በ1985 ዓ.ም ነበር። ያኔ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ጠንክሮ ሰርቶ የራሱንም የቤተሰቡንም ሕይወት ለማሻሻል ነበር። በተለይም ደግሞ ሱቅ ከፍቶ ሌሎች ሥራዎችን ደግሞ እያስፋፋ መሄድ ያስብ ነበር። ይሁንና ነገሮች እንደታሰቡት ሳይሆኑ ቀርተው ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ሊገፋ ተገደደ። በሰዎች ግሮሰሪ እና ሱቅ ውስጥም ተቀጥሮ ሰርቷል። በሂደት ደግሞ ትንሽ ሳንቲም ይዞ በራሱ መንቀሳቀስ ጀመረ። አትክልትና ፍራፍሬም ይሸጥ ነበር። ግን የንግድ ፈቃድ ስለሌለው ደንቦች ሊያሰሩት አልቻለም። ነገሮች አልሆን ሲሉት የሥራውን ዘርፍ ለመቀየር ፈለገ። ይሁንና አሁንም ኑሮን ማሸነፍ አልቻለም፤ ለበረንዳ ሕይወትም ዳርጎታል። ይህን ሥራውን አቋርጦ ከሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ ቄጠማ ይሸጥ ጀመር።
ጥላሁን በትምህርት ብዙ መግፋት ይፈልግ ነበር፤ በኑሮ ጫና የተነሳ ከሦስተኛ ክፍል በላይ መዝለቅ አልቻለም። ጥላሁን ትዳር መስርቶ ሦስት ልጆች አፍርቷል። ትልቁ ልጁ 19 ዓመት ሲሆን ከታናሽ ወንድሙ ጋር ቃሊቲ አካባቢ ሱቅ እየሰራ ነው። ባለቤቱ ኳስ ሜዳ በሚባለው ሰፈር ዘመድ ዘንድ ናት። እርሱ ደግሞ ከኑሮ ጫና የተነሳ ትዳሩን በትኖ በረንዳ ላይ ወድቋል። ቀደም ብሎ ትዳር ሳይመሰርት በረንዳ ላይ ሳለ ለረጅም ዓመታት በጓደኝነት ያሳለፈና እንደ እርሱ የተጎሳቆለ ሕይወት የሚመራ ተሾመ ጎሳዬ የሚባል ሰው ተዋውቆ ነበር።
ተሾመ ጎሳዬ የ27 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ የተወለደው በደብረብርሃን መስመር ላይ በምትገኘው ሸኖ ከተማ ነው። ገና በልጅነቱ እናት እና አባቱ በመሞታቸው በሐዘን የመዋጥና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ ይገባል። ነገሮችን ቢያወጣም ቢያወርድም ለእርሱ አንዳች ብሩህ ነገር በወቅቱ አልታይ ይለዋል። የእናትና አባት እንክብካቤ እና ፍቅር ቢመኝም ተፈጥሮ ፊቱን አዙራበታለች። ወንድሞቹና እህቶቹም የዚህን ልጅ መብሰልሰል በሚገባ ሊረዱት አልቻሉም። በቅርብ ያሉ ዘመድ አዝማድም አይዞህ! ብለው የነገ ተስፋን ሊሳዩት አልሞከሩም።
በቃ በዚህን ጊዜ ተሾመ አንድ ነገር ወሰነ። ዳግም ላያመነታ ቆረጠ። ከዚያም ራቅ ብሎ ለመስራትና እራሱን ለመለወጥ፤ አንድም ደግሞ የእናትና አባቱን ናፍቆት በቄያቸው ሆኖ ጠዋትና ማታ ከመብልሰል ደጁን ጥሎ ትዝታን ብቻ በልቡ ይዞ ለመኖር። በመጀመሪያ ከደጅ ሲጠፋ በአዲስ አበባ አቆራርጦ ወደ ጅማ ለማምራት ነበር። ግን እንዳሰበው ሳይሆን ቀርቶ ኑሮውን በጎጃም በረንዳ አካባቢ አደረገ፤ የበረንዳ ሕይወትንም ተላመደ። በዚህ ስፍራ ሆኖ ከወዛደርነት ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ሞክሯል፤ ምንም እንኳን ስኬት ብትርቀውም። ቀደም ሲል አዲስ ከተማ ክፍለከተማ 32 ክበብ በሚባል አካባቢ የቄጠማ ንግድ ጀምሮ ነበር። ግን ይህንንም ደንቦች ሊያሰሩት አልቻሉም። ንግድ ፈቃድ ሳይኖርህ ቄጠማ አትነግድም፤ አካባቢው እየቆሸሸ ነው አሉት።
እርሱ ግን ለቄጠማ ንግድ እንዴት ብዬ ንግድ ፈቃድ ላውጣ፣ ሥራውም ወቅት ለይቶ የሚመጣ ከመሆኑ የተነሳ እንዴት ሊሆን ይችላል ሲል ይጠይቃቸዋል። ግን ሰሚ አላገኘም። ተደራጅቶ ሊሰራም ቢሞክርም የሚያደራጀው ሰው አጣ። እንዲያውም የአካባቢው ደንብ ጽሕፈት ቤት ቄጠማ ንግድ የሚሰራ ከሆነ እንደሚታሰር አስፈረመው። ይህኔ ተሾመ የቄጠማውን ሥራ እርግፍ አድርጎ ትቶ ሰፈር ቀየረ። ወደ አዲሱ ገበያ መጥቶ የሁልጊዜ የልብ ወዳጁ ከሆነው ጥላሁን ጋር እየሠራ ነው።
ተሾመ ትዳር መስርቷል፤ አንድ ልጅም ወልዷል። ይሁንና እርሱም ልክ እንደ ጓደኛው ሁሉ በትዳሩ ስኬታማ አይደለም፤ ከትዳር አጋሩ ጋር ተለያይተዋል። ለትምህርት ከፍተኛ ጉጉት ቢኖረውም ከአምስተኛ ክፍል በላይ ሊጓዝ አልቻለም።
ትዳር ያልታደጉ ጥረቶች
ሁለቱም ትዳራቸውን ከመፍረስ ለመታደግ ብዙ ጥረት አድርገዋል፤ ግን አልተሳካም። አማራጮችን ሞክረው ስላልተሳካላቸው ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ተለያይተዋል። ቀድሞ ምርር.. ብሏቸው የነበረውን የበረንዳ ሕይወት ለመግፋት ዳግም ከቤታቸው ወጡ። በአሁኑ ወቅት ቀድሞ በጋራ ይጋሩት የነበረውን ሕይወት ተመልሰውበታል- የኑሮ ጫናን መሸከም ባለመቻላቸው። ምንም እንኳን አሁንም ፈተና ቢበዛባቸውም የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን ደፋ ቀና ይላሉ።
ነገሮቻችን ሁሉ እየተመሳሰሉ መጡ የሚለው ተሾመ ነው። እኔም ሆንኩ ጥላሁን ትዳራችንን በልፋታችን መታደግ አልቻልንም። ለዚህ ሁሉ ፈተና የዳረገን ደግሞ ቤት አልባ መሆናችን ነው። ቤት ቢኖረን እንዴት ቤተሰቦቻችን እፎይ ይሉ ነበር ይላል። የቄጠማ ንግድ ቢጀምሩም አሁንም ፈተና ማለፍ አልቻሉም። «አንዳንድ ከምንሠራው በላይ የምንከስረው ይበልጣል። ገዢ ከሌለ ሳሩ ይጠወልጋል፤ ቀስ እያለም ይደርቃል። በዚህ ጊዜ ያለው አማራጭ ቄጠማውን መጣል ነው።» ይላል የኪሳራውን አስከፊነት ሲናገር።
ተሾመ እና ጥላሁን ቄጠማ የሚገዙት ከጎጃም በረንዳ ነው። ጎጃም በረንዳ ቄጠማ የሚያከፋፍሉ ሰዎች ደግሞ ከቃሊቲ የሚያመጡ ናቸው። ታዲያ ይህን ቄጠማ ከጎጃም በረንዳ በታክሲ አስጭነው ወደ አዲሱ ገበያ ያመጣሉ። በእርግጥ አሁንም እየተንቀሳቀሱ ያሉት ከሰዎች ተበድረው ነው። ከምንም በላይ የሚያስከፋቸው ነገር ቢኖር በብድር እየሰሩ ኪሳራ ሲደርስባቸው ሌላ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸው ነው። ወዲህ ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን በሚገባ ማገዝ ባለመቻላቸው ጠዋትና ማታ ይሳቀቃሉ።
ገጠመኞች
ተሾመ ከቤተሰቡ ከራቀ 15 ዓመት ሞልቶታል፤ ምንም እንኳን አልፎ አልፎ ቢጠይቃቸውም። ጥላሁንም ከትውልድ መንደሩ ከራቀ 26 ዓመታት አስቆጥሯል። ታዲያ በረንዳ ላይ አብረው በነበሩበት ወቅትና አሁንም ብዙ ገጠመኞችን እየተመለከቱ ነው። በረንዳ ላይ አንድ ፎጣ ለሁለት ለብሰው ተኝተዋል። ተኝተው ኪሳቸው ውስጥ ያላቸውን ሳንቲም ተወስዶባቸው ምግብ መቅመሻ ቤሳቢስቲን አጥተዋል።
የሌሊት ድምጾች፤ የመንገድ ላይ ዝርፊያዎች እና ሌሎች ድርጊቶችን ተመልክተው አዝነዋል። ወዲህ ደግሞ በጎዳና ሕይወት በመተሳሰብና በመተዛዘን ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ጠንካራና ታታሪ የሆኑ ሰዎችን አይተው ተደስተዋል፤ ምንም እንኳን ለእነርሱ ኑሮ ቀዳዳዋ በዝቶ ሽንቁሯን መድፈን ቢያቅታቸውም።
ተስፋ
በዚህ ሥራ ውስጥ ብዙ ገጠመኞች አሳልፏል። እነዚህ ጓደኛሞች አሁንም ተስፋችን አልተሟጠጠም ይላሉ። ጥላሁን እና ተሾመ በአዲስ መንገድ በአዲስ ወኔ ሠርተን እንቀየራለን ብለው ያስባሉ። ሁለታችንም ተመካከርን በአንድ ላይ 2000 ብር አስቀምጠናል። ግን በዚህ ምንም ሊሰራበት አይችልም። እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ነገሮች ይለወጣሉ ብለን እናምናለን ይላሉ። ሁለቱም ትዳራቸውን መታደግና ከልጆቻቸው ጋር መኖር ይፈልጋሉ። ኑሮ ወገባቸውን አጉብጦ፤ አንገታቸውን አስደፍቶ ሕይወታቸውን ሲበጠብጥ ቆመው ለማየት አልፈልጉም፤ በተቻላቸው መጠን ሁሉ እየተፍጨረጨሩ ነው።
ከልጆቻቸው ጋር መጫወት፣ ከትዳር አጋራቸው ጋር ሃሳብ መለዋወጥ እንደ አዲስ ሕይወታቸውን ማቃናት ይሻሉ። ዛሬ በኑሮ ጫና እና በፈተና የተበተነ ቤታቸውን መልሰው መልክ እንዲይዝ ይፈልጋሉ። በተለይ ተደራጅተው የመስራት ምኞት አላቸው ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸውና የሚመለከተው የመንግሥት አካል ድጋፍ ካደረገላቸው። መንግሥት እጅ አጠር ለሆኑ ዜጎች የሚያርገው ድጋፍ እነርሱንም ቢደርሳቸው ይመኛሉ። ብቻ ማንም ይሁን ምንም በተቻለ መጠን ትዳራቸውን የሚታደግ፤ ቤተሰቦቻቸውን የሚሰበስብና ሃሳባቸውን የሚጋራ አካል ይፈልጋሉ። ሕይወት እንደ ገብስ ቆሎ ፍትግ አድርጋ ከበረንዳ ላይ ስትወረውራቸው አይዟችሁ ብሎ የሞራል ስንቅ የሚሆናቸው ሰው ይፈልጋሉ-ጓደኛሞቹ።
ግን እውን ይህን ትዳር የሚታደግ ቤተሰባቸውን የሚሰበስብ ማን ይሆን? ጓደኛሞቹ ጥላሁን እና ተሾመ ጠንክረው ትዳራቸውን ይታደጋሉ ወይስ ህልማቸው እንዲሁ እንደ ጉም በኖ ይቀር ይሆን? የዝግጅት ክፍላችን እነዚህ ሰዎች በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በሥነ ልቦና ምክር ጭምር ሊታገዙ እንደሚገባ ለመጠቆም ይወዳል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር