የዛሬ ትጋታችን የነገ ትሩፋታችን ነው

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ በጥንታዊነታቸው ከሚታወቁ ጥቂት ሀገሮች አንዷ ነች፡፡ ይህም ጥንታዊነቷ የሰው ልጅ መገኛ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ከዚህም ባሻገር የራሷ የሆነ ፊደል እና የዘመን አቆጣጠር ባለቤት እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የግብርና ስራን ከጀመሩ ጥቂት ሀገራትም አንዷ እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያትቱትም ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝና እና በቀይ ባሕር አማካኝ ስፍራ ላይ የምትገኝ ሀገር በመሆኗ የአካባቢው አውራ ሆና ለዘመናት ኖራለች፡፡

የሀገሪቱን እድገት የማይሹ አካላት ለዘመናት በሰሩት ደባ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና አካባቢ የነበራት ሚና እያሽቆለቆለ መጥቶ የኢሕአዴግ ዘመን እስኪያበቃ ድረስ ተሰሚነቷ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል፡፡ ይህም ሀገራዊ ቁጭት ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ የኢሕአዴግን መውደቅ ተከትሎ በተፈጠረው ሀገራዊ መነሳሳት እና የመንግስት ለውጥ ሀገሪቷ በአዲስ መነቃቃት ውስጥ ጥገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ዳግም እያበቡ ነው፡፡ በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ገናናነት የሚመልሱ አስተሳሰቦች እና ተግባራት መድረክ እየተቆጣጠሩ ነው። በተለይም ለጋሽ እንጂ ተመጽዋች አትሆንም የሚለው አስተሳሰብ እየጎለበተ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት ያህል ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ብትሆንም በምግብ ሰብል እራሷን ባለመቻሏ ነጻነቷን በሚገባ ሳታጣጥም ኖራለች፡፡ በአድዋ የተገኘው ድል በቅኝ ገዢዎች የፈረጠመ ኢኮኖሚ ሲጠመዘዝ ኖሯል፡ ፡ የኢትዮጵያ ኩራትና ድል በስንዴ ልመና ኮስሶ በዓለም መድረኮች ሁሉ ለምናቀርበው ጥያቄና ለምናሰማው ድምጽ መጀመሪያ ሆዳችሁን ሙሉ የሚል ምላሽን ስናገኝ ኖረናል፡፡

ዛሬ ግን የአድዋ ድል በተገቢው ቦታው ላይ እንዲነግስ የሚያስችል አኩሪ ታሪክ መጻፍ የምንችልበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስላል። ኢትዮጵያ ዳግም ነጻነቷን ልታውጅ፤ በስንዴ ምርት ራሷን ችላ ወደ ውጭ ገበያ ልትልክ፤ ከስንዴ ለማኝነት ወደ ስንዴ ላኪነት ልትሸጋገር ዳር ዳር እያለች ነው፡፡ ሀገሪቱ በዓለም ላይ ስንዴ ሸማች ከሆኑ ሀገራት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምትታወቅ ስትሆን፤ በየዓመቱም እስከ 107 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማስገባት 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ስታወጣ ቆይታለች፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት መንግስት ለስንዴ ምርት በሰጠው ትኩረትም ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ከማቆሟም በሻገር ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች፡፡ ይህ ጥረቷም በዓለም ላይ ስንዴ በማምረት ተጠቃሽ ከሆኑ 18 ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል፡፡ ኢትዮጵያ ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት እራሷን በመለወጥም ታሪክ ሰርታለች፤ ለቀጠናው ሀገራትም ኩራትና ተስፋ ሰርቶ የመለወጥ ተምሳሌትም ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ስንዴው ሁሉ ለሩዝ ምርት ትኩረት በመስጠት ከሀገራዊ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለመላክ በትኩረት በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ በተለይም ሀገሪቱ ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይና ምቹ መሬት ያላት መሆኑ ያቀደችውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደማያዳግታት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለከትውም በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በሩዝ መልማት የሚችል መሬት ቢኖርም በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች፡፡

በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርዓት መተግበር ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ፊቱን ወደ ሩዝ ምርት በማዞር በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል፡፡ ከሩዝ አኳያ አምና ከስምንት ሚልዮን ኩንታል ያልበለጠ ነበር የተመረተው ዘንድሮ በአንጻሩ 38 ሚልዮን ኩንታል ማምረት ተችሏል። በተለይ በአማራ ፎገራና በጅማ እንዲሁም በሶማሌ ክልል እየተከናወነ ያለው የሩዝ ምርት ኢትዮጵያን ከሩዝ ተቀባይ ሀገርነት ወደ ላኪነት የሚያሸጋግራት ነው፡፡

በፍራፍሬ ዘርፍም ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ እነዚህ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ኢትዮጵያ በአጭር ግዜ ውስጥ ከተረጂነት ተላቃ እራሷን በምግብ እንደምትችል አመላካቾች ናቸው፡፡ መንግስት ‹‹ተረጂነት ይብቃ›› በሚል መርህ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ከተመጽዋችነት ለማላቀቅ አዲስ ዕቅድ ይዞ መጥቷል፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እስከ 250 ሺ ሄክታር በማረስ ኢትዮጵያ በቂ እህል ለማምረትና ከእርዳታ ተቀባይነት ለመላቀቅ አቅዳ እየሰራች ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከእርዳታ እሳቤ እራሱን ማውጣትና እራስን በምግብ ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ ይገባል፡፡ ሁሉም እርዳታ መቀበልን ከተጸየፈ ኢትዮጵያ ከተረጂነት ወደ ሰጪነት የምትሸጋገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። በአጠቃላይ በለውጡ ዘመን በግብርና ምርታማነት ላይ የተሰሩት ስራዎች ነገን በተስፋ እንድንጠብቀው የሚያደርገን ነው፡፡

በለውጡ መባቻ ዘመን በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የነበረው የምርት መጠን 300 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 600 ሚሊዮን ኩንታል ሊያድግ ችሏል፡፡ በ2017 መጨረሻም ከ800 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚጠበቅ ሲሆን በ2018 የምርት ዘመን ወደ 1 ቢሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን እንድትችል ከማድረጉም በሻገር ስንዴ፤ ሩዝ እና የፍራፍሬ ምርቶችን በስፋት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም የሚፈጥርላት ይሆናል፡፡

እንደ ግብርና ስራው ሁሉ የኢትዮጵያን ነገ ከሚያሳምሩት ውስጥ በኃይል አቅርቦት በኩል የተሰራው ስራ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የአባይ ግድብ የስራ አፈጻጸም ነገን ቀና ብለን እንድንመለከት የተስፋ ወጋገን ያጎናጸፈን ነው። የአባይ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ማህተም ነው፡፡ ሆኖም ይህ ግዙፍ ግድብ በነበረው የአሰራር እና የአመራር ብልሽት ወደ መስተጓጎሉ ደርሶ ነበር፡፡ በኢህአዴግ የመጨረሻ ዘመናት ጀምሮ ግድቡ ሲመራበት የነበረው ሂደት ለሙስና እና ብልሹ አሰራር ተጋልጦ የነበረ በመሆኑ በሂደት ግንባታው የሚቆምበት እድል የሰፋ ነበር፡፡

እንደ ዕድል ሆኖ በኢትዮጵያ የመንግስት ለውጥ እውን በመሆኑ የግድቡ ግንባታ ከመስተጓጎል ሊተርፍ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሲቪል ስራው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን የኤሌክትሮሜካኒካል ስራውም እየተፋጠነ ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹትም ‹‹ዛሬ የሕዳሴ ግድብ ወደ ኋላ ከ205 እስከ 210 ኪሎ ሜትር ተኝቷል። ዛሬ የሕዳሴ ግድብ ወደታች ጥልቀቱ መቶ 133 ሜትር ደርሷል።

ዛሬ ሕዳሴ ግድብ የጣናን ሀይቅ እጥፍ አድጓል። ጣና እስከ 30 ቢሊዮን ነው። ይሄ 62 ነጥብ አምስት ነው፤ ደብል አድርጓል። የጣና ውሃ ስፋቱ ብቻ ሳይሆን በጣም ሻሎው ነው። 13፣ 14 ሜትር ነው ጥልቀቱ። ይሄ 133 ገደማ ሜትር ጥልቀት አለው። በጣም ጥልቅ ነው ማለት ነው። ወደታችም ወደኋላም ወደጎንም በጣም ሰፊ ስለሆነ የጣናን እጥፍ/ደብል ውሃ ሆኗል።›› ሲሉ የአባይ ግድብ የደረሰበት ደረጃ አብራርተዋል። ይህ ደግሞ የአባይ ግድብ ዛሬን አድምቆ ነገን ብርሃን ፈንጥቆ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማወጅ መዘጋጀቱን የሚያመላክት ነው፡፡

ሌላኛው ከዛሬ አልፎ የነገ ተስፋ የሆነን ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን እየሄደችበት ያለው መንገድ ፍሬ እያፈራ መምጣቱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በትኩረት ከሰራባቸውና ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች አንዱ የባሕር በር ጥያቄ ነው፡፡ መንግስት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባሕር በር ጣያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ለ27 ዓመታት ያህል ፈርሶ የቆየውን የባሕር ኃይል እንደገና በማደራጀት ኢትዮጵያ እንደገና የባሕር ኃይል እንዲኖራት አድርጓል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከ33 ዓመታት በኋላ የባሕር በር የምታገኝበት አማራጭ ተገኝቷል፡፡ ሰላማዊ አማራጭን ሲከተል ቆየው የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን ከሶማሊ ላንድ ጋር የባሕር በር የሚገኝበትን መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) ተፈራርሟል፡፡ ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሲተገበር አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ አለኝ የምትለውን የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲገኝ በር የሚከፍት ነው። ቀጠናዊ ሰላምን በማስፈን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የተረጋጋ እንዲሆን በር ይከፍታል፡፡

ሌላኛው የነገን ተስፋ ብሩህ ከሚደርጉት ሀገራዊ ክንውኖች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአረንጓዴ መርሃ ግብር ነው፡፡ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት እየተተገበሩ ካሉ ፕሮግራሞች አንዱ ነው። በየዓመቱም በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚሳተፍበት ሀገራዊ ንቅናቄ ለመሆን በቅቷል፡፡ ሰሞኑን ይፋ በተደረገው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ሪፖርት እንደተመላከተው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011 ዓመተ ምህረት ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን በ2016 ዓ.ም ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሏል።

እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የተቻለው በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ30 ሚሊዮን ሰዎች በላይ የሚሳተፉበት የችግኝ ተከላ በማካሄድ ነው። የችግኝ ተከላው በአንድ ጀንበር በሚሊዮኖች የሚተከሉ ችግኞችን በመትከል ዓለም አቀፍ እውቅና ማትረፉን ጭምር ያካተተ ነው። ለዚህም ባለፈው ነሃሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 615.7 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ቀደም ሲል በራሳችን ተይዞ የነበረውን ዓለም አቀፍ ሪከርድ ማሻሻል ችለናል፡፡

ከእነዚህ ግዙፍ ስራዎች ጎን ለጎንም በቱሪዝም፤ በኮሪደር ልማት፤ በዲፕሎማሲ፤ ጠንካራ ሀገራዊ ሰራዊት በመገንባት እና በመሳሰሉት ዘርፎች እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ነገን በተስፋ አሻግረን እንድንመለከት የሚያደርጉን ናቸው፡፡ ከወዲሁም ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ዛሬ ኢትዮጵያ በምስራቅ ቀዳሚዋ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። ተጽዕኖ ፈጣሪነቷም እያደገ መጥቷል። ይህ ደግሞ አሁን ላለነውም ሆነ ለልጆቻችን ነገን ብሩህ ቀን የሚያደርግ ጅማሬ ነው፡፡

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You