
ሁሉም ፍጥረት ሰላምን ይፈልጋል። አይደለም የሰው ልጅን ቀርቶ በጫካ የሚኖሩ እንስሳት እንኳን ሰላም ፈላጊ ናቸው። አይደለም ሰው እና እንስሳት ቀርተው ዕፅዋቶችም ሰላም ናፋቂዎች ናቸው። ሰላም የዚህን ያክል አስፈላጊ የሆነበት ዋና ምክንያት ከሕልውና ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ነው።
ሕይወት ከተፈጥሮ ጋር ተፈጥሮም ከሰላም እና ከሕይወት ጋር ያላቸው ትስስር ጥልቅ ነው። ትስስሩ አንዱ ለሌላው ከመኖር የሚጀምር፣ የአንዱ መኖር ለሌላው ዋስትና እስከመሆን የሚደርስ ነው። አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል እንደሚባለው የአንዱ ጉዳት የአንዱን ቤት የማንኳኳት አቅም አለው። የሰላም አለመኖር ሕይወትን ጨምሮ ተፈጥሮን እንዲያናጋ ሆኖ የተበጀ ነው።
አሁን አሁን የሰላም ጉዳይ ለሰው ልጅ የሕልውና ጉዳይ ሆኗል። ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኗል፣ በዓለም ላይ ካሉ ወሳኝ እና አስፈላጊ ሰላም አመንጪ እውነታዎች አንዱ እና ዋነኛው ውይይት እና ንግግር ነው ነው። አንዳንድ ጥናቶች በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ ትልቁ ሥልጣኔ ውይይት እንደሆነ ያመለክታሉ።
በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱ ጥናት ሆነ ዓለም አቀፍ እውነት እንደ ሀገር ለዘመናት ይዘን ከመጣነው የይለይልን ይዋጣልን ባህል አኳያ ለኛ እንደቀልድ የሚታይ ነው። በመነጋገር ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን፤ ዋጋ እየከፈልን ለለመድናቸው ለኛ ብዙም ትኩረታችንን የሚስቡ አይደሉም ።
እንዳለመታደል ሆኖ ለዘመናት የመጣንበት የግጭት ትርክታችን፤ የመነጋገር ባህል ቢኖረን ኖሮ እስከ ዛሬ የከፈልነውን ያልተገባ ዋጋ ባላስከፈሉን ነበር። ተነጋግረን ቢሆን የተፈጠሩም ሆነ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮቻችን፤ ችግር ሆነው አይፈትኑንም ነበር። እንደአለመታደል ሆኖ ጀግንነታችንም ሆነ ቆፍጣናነታችን እልህ በመጋባት የሚፈተን ነው። እልህ የደነደነ ልብ መገለጫ ነው። ንግግር እና ውይይት ከስክነት የሚቀዳ ማንነት ነው። የሰከነ ልብ ለአስተውሎት ዕድል ይሰጣል።
በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ገርበብ ያለ በር በጊዜ ካልተዘጋ በሚነፍሰው ቀላል ሆነ አውሎ ንፋስ በሩን በሂደት ሆነ በድንገት መከፈቱ የማይቀር ነው። የበሩን መከፈት በስክነት ማየትን እና መዝጋት ካልቻልን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር በሩ ሙሉ በሙሉ ተከፍቶ ጓዳችንን ብቻ ሳይሆን፤ ውስጣ ውስጣችንን አደባባይ ማድረጉ የማይቀር ነው። “የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል” እንደሚባለው በፉክክር ያልተዘጉ ብዙ በሮች አሉን።
ያልተዘጉ ብዙ በሮች አሉን። በጊዜ መዝጋት እየተቻለ በፉክክር ገርበብ ብለው የቀሩ ደጃፎች ብዙ ናቸው። የእከሌ የእከሌ በሚል ስም ወጥቶላቸው በጎጥ የሚጠሩ ተከፍተው የቀሩ በሮቻችን ጥቂቶች አይደሉም። እነኚህ ሁሉ ያልተዘጉ በሮች ነገ ላይ ተከፍተው የፈተና እና የችግር ምንጮች እንደሚሆኑ ለመገመት አይከብዱም።
በሩም ለመዝጋት ፉክክሩ ለምን አስፈለገ? ለሀገር ዘብ መቆም ያልተዘጉ በሮችን በያገባኛል መዝጋት ካልሆነ በምን ይገለጻል? የሀገር ፍቅር ከዚህ ስሜት ውስጥ ካልመነጨ ምንጩ ወዴት ይሆናል? አንዳንዴ ወንዝ አድርቀን ምንጭ እንፈልጋለን። ሌላ ጊዜ ውቅያኖሱን ንቀን ለኩሬ እንደክማለን።
እንደ አንድ ከፍ ያለ ማኅበረሰባዊ እሴት እንዳለው ሕዝብ፤ እየተረትን ለተረቶቻችን ባዕድ የምንሆንበት እውነታ ብዙ ነው። ‹ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል› እንላለን፤ አባባሉ ለትላንቷም ሆነ ለዛሬዋ ለወደፊቷም ኢትዮጵያ ወሳኝ የሆነ ተራማጅ እሳቤ ነው። ግን ደግሞ ከእኛው መንጭቶ እኛኑ እየጠቀመ አይደለም።
መነጋገር ጥሩ እንደሆነ እናምናለን ግን ደግሞ ባለመነጋገር መከራ ጠማቂዎች ሆነናል። ባለመነጋገር አያሌ የክብር ደጃዝማችነት ቀርቶብናል። ተነጋግረን ቢሆንና ስለፍቅር ጠቦቻችንን በይቅርታ ፈተን ቢሆን እነዛ ሁሉ የተናዱ የወርቅ ካቦቻችን አሁን ላይ የትውልዱ ኢንፓየር በመሆን መጠሪያዎቻችን በሆኑ ነበር።
ካለፈው ተምረን ነገን እናድን። የትላንቱን አርመን ዛሬን እንቀድስ። እንደሀገር በእርቅ እና በተግባቦት የበለፀጉ በርካታ እሴቶች አሉን። ዕሴቶቻችን ለብዙ ዓመታት አስታርቀው፣ አዋደው፣ አስተቃቅፈው እና አከባብረው አኑረውናል። እነዚህ ዕሴቶቻችን ዛሬም ካሸለቡበት ነቅተው ሰላም ወዳድነታችንን ሊያረጋግጡልን ይገባል።
አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች ማክበር እና መታዘዝ ማኅበረሰባዊ ዕሴቶቻችን ናቸው። በኢትዮጵያዊነት የበለፀግንባቸው የሰብዓዊነት መልኮቻችን ናቸው። እነዚህን ዕሴቶቻችንን ከወደቁበት አንስተን አክብረን ልናቆማቸው እና ልናጸናቸው ያስፈልጋል። የሰላም ግንባታ አንድ አቅም አድርገን ልንወስዳቸው ይገባል።
ሰላም በፍለጋ የሚገኝ አይደለም፤ ሰላም አማጭ ለሆኑ ዕሴቶቻችን ትኩረት መስጠትን ይጠይቃል። ለሰላም ዋጋ ሳይከፍሉ ስለሰላም ማውራት ትርጉም የለውም። ስለሰላም አስፈላጊነት ማወቃችን በራሱ ሰላም አያመጣም፤ ስለሰላም ዋጋ መክፈልን መለማመድ ያስፈልጋል።
የጦርነትን አስከፊነት ማወቃችን ለሰላማችን ማስተማመኛ አይሆንም፤ስለጦርነት ያለንን አመለካከት መግራት እና ጦርነት አማጭ የሆኑ ጉዳዮችን መሸሽ ይፈልጋል። የሰላምን አስፈላጊነት ልክ ተረድቶ የሰላም ሐዋሪያ መሆን ይፈልጋል። ሰላምን በኃይል ለማምጣት ከሚደረግ ስር የሰደደ ል ምምድ መውጣት ያስፈልጋል።
ሰላም በኃይል መጥቶ በማያውቅባት ወደፊትም በማይመጣባት ዓለም ላይ ነን። ሰላም በኃይል ካልመጣ የእኛ ኃይለኝነት ታዲያ ከየት የመጣ ነው? ሳናውቅ እንደመልካም ቅርስ የተዋሓድናቸው አላስፈላጊ ልምምዶች ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ።
ነፃነቶቻችን ያሉት ከአፈሙዝ በሚወጡ ገዳይ ጥይቶች ሳይሆን ከአፍ በሚወጡ የምክክር ቃሎቻችን ነው። ሰላም በጠመንጃ የሚገኝ ቢሆን ኖሮ ከነዴንማርክ እና ከነአየርላንድ በልጠን በምድር ላይ ሰላማዊቷን ሀገር በፈጠርን ነበር። ጉዟችን እንደግመል ሽንት ወደኋላ ባልሆነ ነበር።
የዓለም ሥርዓት ከቃታ ወደእርጋታ፣ ከትጥቅ፣ ወደመጠይቅ፣ ከፉክክር ወደምክክር፣ ከሰይፍ ወደሰልፍ ተቀይሯል። ዓለም ስለሰላም እና ስለሰብዓዊነት ሲያወራ እኛ ስለጦርነት እና ስለእርስ በርስ ጥላቻ እያወራን እንገኛለን። ሰላምን መውለድ ለምን አቃተን? ሞት የፀነሱ ገዳይ ቃታዎቻችን ደምን በደም ከሚል መርዘኛ እልህ ባለፈ ምን ሰጥተውን ያውቃሉ?
ሕይወት ከሰላም ጋር በጥብቅ ተሳስራለች። ሀገር የሚሏት ሰምናወርቅ ቅኔም ያለሰላም ቅኔዎቿን የደበቀች ናት። በጽኑ ተጋድሎ የጸኑ ምሰሶዎቻችን የሕያው አምላክን ስም እንደጻፉ ታቦታት የኢትዮጵያን ስም የከተቡ ናቸው። ባለፀጋ ሳለን ከደኸየንበት፣ ባለክብር ሳለን አንገት ከደፋንበት ከሞት ፖለቲካ እንላቀቅ። በውይይት እና በንግግር ወደ ምንደምቅበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ በዕውቀት እና በእውነት እንጓዝ።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም