“በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር አንደራደርም”- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ላይ አንደራደርም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሉዓላዊነት ቀን “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ በመከላከያ ሚኒስቴር ጠቅላይ መምሪያ ትናንት ሲከበር እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ማንንም ነክታ አታውቅም፤ ከነኳት ግን በሉዓላዊነቷና በክብሯ አትደራደርም፡፡

ለኢትዮጵያውያን ማንንም አለመንካት ተግባራችን፣ ማንነታችንና መለያችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሰላም ለልማትና ለብልጽግናችን መሠረት በመሆኑ ማንንም የመንካት ፍላጎትና ዓላማ የለንም ብለዋል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከተነካች አሳፍሮ የመመለስ ታሪክ እንዳላት ገልጸው፤ የሀገር ክብር የሆነው ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር እንዲሁም የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ በአስተማማኝ የዝግጁነት ቁመና ላይ ይገኛል ሲሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፍላጎት ከልመና መገላገል፣ ከዕርዳታ መላቀቅ፣ ምርት በስፋት ማምረትና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግቡን ለማሳካት በውስጥ ሆነ በውጭ ሰላም ያስፈልገናል ብለዋል። በትብብር መንፈስ አብሮ ማደግ

ፍላጎት አለን፤ ሳንነካቸው የሚነኩን ካሉ ግን አሳፍሮ የመመለስ ከታሪካችን የወረስነው ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሉዓላዊነታችንን ጠብቀን መኖራችን ያኮራናል። የግዛት ሉዓላዊነት ብቻውን እንደማይቆም ግን ተረድተናል ብለዋል።

ሉዓላዊነት ሁለንተናዊ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ፣ የበጀት ሉዓላዊነት፣ ታላቁን የሀገር ሉዓላዊነት በጽናት የሚያቆሙ መሆናቸውን አስረድተዋል። እነዚህን የሉዓላዊነት ዘርፎች ለማስከበር አዲሱ ዓይነት ዐርበኝነት ያስፈልገናል ነው ያሉት።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያና በቀጣናው ሰላም የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን ልማትን የሚያካሂድ፣ ኢንዱስትሪ የሚያስፋፋ፣ ከችግር የሚያወጣ፣ የሚመራመርና የሚፈጥር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን የኢትዮጵያ ሁለተናዊ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ ይኖርብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመርሀ ግብሩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለዋል። ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ለተሰዉ ጀግኖች የጧፍ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

በጌትነት ምህረቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You