በአንድነት የተጣመረ፣ በጥንካሬ ድር የተጋመደ ማንነት በዋዛ ፈዛዛ አይበጠስም:: አንዱ በአንደኛው ህብር ተጣምሮ ዘመንን ይሻገራል እንጂ፤ ይህን እውነት ወደ ኢትዮጵያዊነት ቀለም ስናመጣው ደግሞ ትርጓሜው ይደምቃል :: ኢትዮጵያዊነት ምንጊዜም በአንድነት ተምሳሌት ይገለጻል:: ህብሩ የጠበቀ አንድነቱ የተሳሰረ ነውና መሰረቱ በጸና ካብ ላይ ተገንብቷል::
ሰዎች በባህርይና በውሎ ተመሳስለው በተገኙ ጊዜ የዓላማቸው ግብ በአንድ ይቃኛል:: ይህን እውነት ለሀገር በጎ ፍጆታ ሲያውሉት ደግሞ ወገኖቻቸው ጠቅመው፣ በደማቅ አሻራ መልካም ታሪክን ያኖራሉ:: ይህ በህብር የተጣመረ ማንነት እርምጃው ሰላማዊ ሲሆን፤ በብዙ ያተርፋል::
ሰላም ለአንድ ሀገር ህልውና ወሳኝና ግድ የሚባል ሀሴት አለው:: ሰላም ህይወት ላላቸው ፍጥረታት ሁሉ አስፈላጊ እንደመሆኑ ዓላማው በህብር ሲቃኝ ፍሬያማነቱ ይጎመራል:: በሰላም ውሎ ያደረ ሕዝብ ነገ ለትውልዱ የሚያኖረው መልካም ታሪክ አይደበዝዝም:: በዚህ ምሪት የተጓዘ ትውልድም ዛሬ ላይ በሚገነባው ማንነት የወደፊት ታሪኩን ይሰራል:: የኋላ አሻራውን ይጠብቃል:: ይህ እውነታ በተናጠል ሲሆን ግን ፈጽሞ አይደምቅም:: ሁሌም በግል ሲታሰብ በነጠላ ሲራመድ ኃይሉ ይደክማል፣ ሃሳቡ ይሳሳል:: የሰላም ጉዳይ ውጥኑ የጋረ ሲሆን ህብረብሄራዊነት ዕውን ይሆናል::
ሰላም የአንድና የሁለት ሰዎች ጉዳይ ብቻ አይደለም:: ይህ እውነት ለሁሉም የሚያስፈልግ ለመኖር ግድ የሚል እስትንፋስ ነው:: ሰላም ባለበት መንደር ልጆች በጤና ያድጋሉ:: በወጉ ከትምህርት ውለው ይገባሉ:: የሰላም አየር ሲኖር ማንም ከራሱ ዓለም አይናጠብም:: አዕዋፍ በዛፎቻቸው፣የዱር እንስሳት በጫካቸው፣ ያለ ሥጋት ይኖራሉ::
አራዊቶች በአንድ ሲያብሩ አጥቂያቸው ይሸሻል:: ጠላታቸው ይሸነፋል:: መንጋቸው ሲበተን ለብቻ ሲገኙ ግን ከክፉ ጥርስ ይወድቃሉ:: ለሌሎች ሲሳይ ይሆናሉ:: የሰው ልጆች የሰላማቸው ዋጋም እንዲሁ ነው:: ይህ ታላቅ እሴት በመሀላቸው በሰፈነ ጊዜ ዕቅድ ዓላማቸው በበጎ ይመነዘራል:: ሀገርን በአንድ ለማልማት፣ ወገንን በዕውቀት ለመድረስ ይፈጥናሉ:: የድህነት ታሪክን ሽረው አዲሱን የህይወት ምዕራፍ ለመጀመር ይጣደፋሉ::
በሰላማዊ ጉዞ በህብረብሄራዊ ዓላማ የተወጠነ መልካምነት ሃሳቡ በወግ ይከወናል:: የ‹‹ነበር›› ሪክ ተሽሮም አዲስ ምዕራፍ በአዲስ እርምጃ ይጀመራል:: የሰላም ልቦች አንድ ሲሆኑ እጆች በእኩል ይዘረጋሉ:: የተጣመረ፣ ኅብረት፣ በእኩል የሰመረ አንድነት ደግሞ ህብራዊነቱ ደማቅና ብሩህ ነው::
ስለ ሰላም በህብር የሚጣመር ማንነት ሀገርን ለመገንባት ትውልድ ላይ ለመሥራት የዘገየ አይደለም:: በኅብረት ተዛምዶ ስለሰላም የዘመረ አንደበትም መልካምነትን ለመስበክ የሰላ ነው:: በጎ አመለካከት ሰላምን ለማምጣት ህብሩ የደመቀ አንድነቱ የተገመደ ሆኖ ይቀጥላል::
ኢትዮጵያ የትናንቱን የአብሮነት መልክ ዛሬም ታጎለበት ዘንድ በሕዝቦቿ መሀል ውሎ የሚያድር፣ ኖሮ የሚዘልቅ እውነተኛ ሰላም ያሻታል:: ከራስ የሚተርፍና ፣ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ማንነትን መገንባቷም ብሄራዊ ገጽታዋን ለማጉላት ያግዛል :: መልካም ሥሟን ይገነባል፣የወደፊት ህልሟን ይፈታል:: ይህ ዕውን የሚሆነው ሰላማዊ ልቦና ባላቸው ሰላምን ኖረው በሚያሻግሩ ዜጎቿ ነው::
ሀገራችን አብሯት የኖረው የእንግዳ ተቀባይነትና ፣ የአብሮነት እውነታ በህብር ተጣምሮ ይዘልቅ ዘንድ ሰላሟን የሚጋፉ፣ የሕዝቦቿን በህይወት መኖር የሚቃረኑ እንቅፋቶች ሊወገዱላት ግድ ይላል:: እንደዋዛ የሚነሱ አለመግባባቶች ፣ ወንዝ የሚሻገሩ ግጭቶችም ከስሩ ሊደርቁ፣ ሊከስሙ ያስፈልጋል:: ህይወት የሚያጠፉ፣ ቤት ንብረት የሚያወድሙ፣ካገር ከቀዬው የሚያሰድዱ ጦርነቶች እንዲቆሙም ሁሉም ስለ ሀገሩ ዘብ ሊቆም ይገባል::
አንድነት ካለ የማይቻል የለም:: ችግሮች ቢከሰቱ ከመነሻው ይፈታሉ፤ ግጭቶች ደም መፋሰሶች ከመፍትሔ ይደርሳሉ:: ሁሌም ስለሰላም የሚጣመር ህብር ግማዱ የጠነከረ፣ ኃይሉ የበረታ ነው:: በቀላሉ እንዳይፈታ ሆኗል፤ ጠብቋልና ያለ ልዩነት ሕዝቦችን አስተሳስሮ ለመጓዝ የሚያግደው የለም::
በአንድነት የተጣመሩ ክንዶች ሰላምን ለመፍጠር ፣ውህደትን ለማምጣት የበረቱ ናቸው:: መልካም አዕምሮ ገንብቶ ፣ብቁ ዜጋን ለማፍራት ፣ በልማት ጎዳና ዘልቆ መልካም እመርታን ለማየት ደግሞ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ሊረጋገጥ ያስፈልጋል::
የዚህ ጥብቅ ትስስር ዕውንነት የሚጎላው መሰረቱ በሰላም ላይ ሲገነባ ነው:: የሕዝቦች አንድነት ፣ የመልካም እሳቤ ማንነት የሚተገበረውም ይኸው ታላቅ እሴት በወጉ ሲከበርና በአግባቡ ሲያዝ፣ሲጠበቅ ይሆናል::
ዓለማችን ዛሬ በአስፈሪ ግጭቶች፣በማይጠፉ የጦርነት እሳቶች እየጋየች ፣ እየተናጠች ነው:: ጦርነት ያፈረሳቸው አለመግባባት የፈታቸው ሀገራት ሕዝቦችም በስደት እየተንገላቱ፣ የመከራ ፅዋን እየተጋቱ ነው:: ትናንት በቴክኖሎጂው ምጥቀት ዓለም ያደነቃቸው ሀገራት ዛሬ ዕውቀታቸውን ለጦርነት ፍጆታ አውለውታል::
አስቀድመው ስለሰላም ህብራዊ ፣ አንድነትና መግባባት ያልነበራቸው አካላት አሁን ላይ ስለትናንቱ ጉድለት የህይወት ዋጋን እየከፈሉ ነው:: የሰው ልጅ በራሱ እጅና አዕምሮ በፈጠረው ቴክኖሎጂ የራሱን ህይወትና ንብረት እያጋየ፣ እያጠፋ ይገኛል:: ህብራዊ አንድነት ተግባራዊ ባልሆኑባቸው ሀገራት የሰላም ክንዶች ታጥፈዋል:: የመግባባት አንደበቶች ተዘግተዋል::
ስለሰላም ያልተከበሩ ሕጎች፣ስለአብሮነት ያልተዘረጉ እጆች ውጤታቸው ጦርነትና ስደት መሆኑ ተረጋግጧል:: በህብር ያልተጣመረ ሀገራዊ እሴት፣ በመግባባት ያልተፈታ የግጭት አጀንዳ የሰው ልጆችን የመኖር መብት የሚጋፋ ለሚታይ ግልጽ ኪሳራ የሚዳርግ ነው::
እኛ ኢትዮጵያውያን ከጥንት እስከዛሬ መገለጫ አርማችን ብሔራዊ ማንነታችን ነው:: አንድ ስንሆን ዓላማችን ይጣመራል:: በእኩል ስንራመድ ሩጫችን ይፈጥናል:: ስለሀገር በአንድ አዕምሮ ስናስብ የጋራ ጠላታችን ይወድቃል:: ስለማንነት ታሪካችን ዓለም በአንድ ድምጽ የሚመሰክርልን በምክንያትና በማስረጃ ተመርኩዞ ነው::
ከዘመናት በፊት የሀገር ድንበር ሊወር፣ ሕዝብን በቅኝ ሊገዝ የመጣን የውጭ ኃይል የመከተው ትውልድ ደም በዛሬው ማንነት ውስጥ ይመላለሳል:: የዛኔ ጠላትን አባሮ የሀፍረት ሸማን ያከናነበው፣ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ፤ የሰለጠነ ጦር ያሰለፈ ኃይል አልነበረም:: የወቅቱ ሀቅና እውነታ ህብራዊ አንድነት፣ የማይበገር ኢትዮጵያዊ ማንነት መኖሩ ነው:: ይህ ከራስ አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራት የሆነ ድል መነሻና መድረሻው በአንድ ቃል ይታሰራል:: በ ‹‹ህብራዊ አንድነት:: ››
ዛሬም ይህ አይፈዜ እውነታ በእኛው ዘመን ባለንበት የትውልድ ሀረግ ሊመዘዝ አፎቱ ተጋልጧል:: በህብር አንድ ስንሆን የቀደመው ታሪካችን ይደምቃል:: ያለንበት ዘመን ይልቃል:: የወደፊቱን ዓለም ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ለማድረግ ያለፈውን ጊዜ መተረክ አያሻንም:: አሁንም ዕድል በእጃችን ነው:: በህብር ስንጣመር የሰላም ዋጋው ይገዝፋል:: የቃሉም ኃይል ይበረታል::
ዓለማችን በቴክኖሎጂ ምጥቀት ተራምዳ አሁን ለምትገኝበት ደረጃ የበቃችው በርካታ እሾህ ጋሬጣዎችን ተራምዳ ነው:: በእኛም ማንነት ጥቂት የማይባሉ ገደሎችን አልፈናል:: ፈተናዎችን ተሻግረናል:: ሻካራማው መንገድ አልፎ ምቹው ጎዳና እስኪመጣ ግን አንድ የመሆን ክንዳችን አይቀጭጭም:: ለእኛ የአዲሱ ዓመት አደይ አበባ የተጣመረው ኃይላችን ነው:: በዚህ ህብር ተስፋችን ያብባል፣ አድዮአችን ይፈካል:: አዎ! ዛሬ ‹‹ህብራችን ለሰላማችን›› ብለን እንዘምራለን:: ዜማችን ከእኛ አልፎ በመላው ዓለም ያስተጋባል:: እልፍ ጆሮና ዓይኖች ወደእኛ ይዞራሉ:: ስለሰላማችን! ስለህብራችን ድምቀት ሲሉ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም