እኛ ማን ነን? …እኛ ኢትዮጵያውያን ነን! ኢትዮጵያውያን የሆነው ግን “ኢትዮጵያ” ከምትል ሀገር ላይ “…ውያን” የምትል ምዕላድ ስለተቀጠለልን ብቻ ይመስለን ይሆን? አይምሰለን! ምናዊ እንደሆን ብቻ ሳይሆን ማን እንደሆን የሚናገሩ ህልቁ መሳፍርት ቃላት ከስሙ ጋር ተቀጽላ ሆኖው በማይታይ የፊደላት ቅርጽ፣ በውስጠ ታዋቂነት ብቻ የሚነበቡ ማንነቶች አሉ።
ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉም እነዚህን በቃላትና በቁጥሮች ብቻ የማይገለጸውን ማንነት ተሸክሟል። የዚህ መሸከሚያ፤ የዚህ ስልቻስ ምን ይሆን ያልን እንደሆን፤ እሱም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ካስማ የሆነው ህብራዊ አንድነታችን ነው። በተናጠል የምንወዳት፣ በተናጠል ቆመን የምንዋጋላት፣ በተናጠል ኖረን በተናጠል የምንታወቅባት፣ በተናጠል ሠርተን በተናጠል የምንበለጽግባት፣ በተናጠል ጠግበን በተናጠል የምንራብባት ኢትዮጵያ የለችም።
የመሰለን ዕለትም ያን ህብራዊ ማንነት አጥተነዋል ማለት ነው። ህብረ ብሔራዊነት ውበት፣ የፍቅር ማሠሪያው አንድነት ነው። ያለ አንድነት የምትሠራ ኢትዮጵያ፣ ያለፍቅር የሚቆም ኢትዮጵያዊነት የለንም። ይህም የኢትዮጵያን መልክ ለያዘ ሁሉ የኢትዮጵያዊነቱ ዶግማና ቀኖና ናቸው። ኢትዮጵያዊ የምንሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተወለድን ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያዊነት ምስጢር ሲገባን ነው። ከሚስጥራቱ አንዱ የሆነውን ህብረ ብሔራዊነትን ከማንነታችን አንገት ላይ እንደ ማህተብ ልናስረው፣ በሄድንበት ሁሉም ከልባችን የማይፋቅ የእምነት ቃል ኪዳናችን አድርገን መታየት ግድ ነው።
ከ2016 መካከል 6 ወጥቶ ሰባት ሊተካ ነው። ይሁንና 2016ዓ.ም ሄዶ 2017ዓ.ም ሊመጣ ነው እንላለን እንጂ ቁጥሩን በተናጠል ለውጠን አንጠራውም። የሚቀየረው 6 በሰባት ብቻ ቢሆንም የአንዱ ለውጥ የሌላውም ለውጥ፣ የአንዱም መነካት የሌላው መነካት መሆኑን በዚህ ስናይ እንዴትስ ኢትዮጵያዊነት ትዝ አይለን…ዛሬ ጳጉሜ አራት ነው። ዛሬ ግን ጳጉሜ 4 ብቻም ሳይሆን ህብራዊ አንድነታችንን ከፍ የምናደርግበት ዕለትም ጭምር ነው።
በህብረ ብሔራዊ አንድነት ተጸንሰን የተወለድን ስለመሆናችን፤ ሁላችንም በሀገር አቀፍ ደረጃ የምናስብበትና የምንተሳሰብበት ነው። ካለፈ የጠለሸ ትዝታ ይልቅ በፍቅር ወደፊት እየፈነጠቅን የነገውን ውጋጋን ሌሊትና የቀኑን ብሩህ ሰማይ የምንመለከትበት ነው። አንድ ሆነን በምንቆምበት ጊዜ የቱ ጋር እንደምንቆምም ጭምር የምናሰላስልበት ነው። ነገር ግን ይኼ የአንድ ቀን ግብራችን አይደለም።
በ365 ቀናት ውስጥ ሁሉ በእያንዳንዱ ደቂቃና ቅጽበት የምንኖረው፣ የሚጠብቀን ሕይወት ነው። የዛሬዋ ጳጉሜም በየትኛውም ዓለም ውስጥ የሌለች ብቸኛው የተፈጥሮ ጸጋችን እና ልዩ የሆንባት ልዩነታችን ናትና እርሷን ለማድመቅ ስንል ልዩ ከሆንባቸው ነገሮች መካከል መርጠን ለልዩ ቀን እንሰጣለን።
እንኳንስ ኢትዮጵያዊው ሰውና ተፈጥሮዋ ራሱ የቆመው በኢትዮጵያዊ ማንነት ነው። ልዩና የዘለዓለም በረከታችን የሆነው ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን በተፈጥሮ ውስጥም ትልቁን ሚና ይጫወታል። እኛ ልጆቿ ከዓለም ሕዝቦች ሁሉ ለየት የሚያደርጉን መገለጫዎች እንዳሉን ሁሉ ተፈጥሮዋም ከዓለም ተፈጥሮ ለየት የሚያደርጋቸው ልዩ የጸጋ መገለጫዎች አሏቸው።
ዋናው ኢላማዬ መኖራቸው ላይ ሳይሆን ያላቸው ነገር ከኛ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ መሆኑ ነው። በኢትዮጵያዊነት ዶግማና ቀኖና ውስጥ ሚስጥራተ ኢትዮጵያዊነትን ጠብቆ የሚኖርን አንድን ግለሰብ፤ ስለኢትዮጵያውያን የሰማ፣ ያነበበ በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ ያለ እንዲሁ በደሙ፣ በምግባሩና በግብሩ ለይቶ ያውቀዋል። ቃሉም “ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን…” የሚለውስ ለዚሁ አይደል። ልክ እንደዚሁ ሁሉ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱትን ጨምሮ ግእዙ ተፈጥሮዋም የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የረበባቸውና የራሳቸው ብቻ የሆነ መገለጫዎችን መያዛቸው ነው።
ከዓለም ሁሉ በተለየ መንገድ የ 13 ወር ጸጋ ባለቤት ስንሆን መነሻው ተፈጥሮ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ጠቢባን አባቶቻችን ተጠበው ያገኙት ያንን ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ብቻ የሆነውን የተፈጥሮ ቀመር በማስላት ነው። ቀመሩን በአሜሪካን አሊያም በራሺያ ተፈጥሮ ላይ በቀጥታ ብንተገብረው ፈጽሞ ልክ አይመጣም። ምክንያቱም ይህ ቁጥር የተሰጠው ለኢትዮጵያዊው ተፈጥሮ ብቻ ነው። ኢትዮጵያውያን ከተፈጥሮ ጋር ልዩ ስበት የኖረንም በባህሪ ብዙ የሚያመሳስለን ነገር በመኖሩ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከተፈጥሮና ከሰብ ሰብአዊነት ጋር የተዋሃደ መለኮታዊ ቀመር ያለው መሆኑንም ማወቅ ያሻል። ቀናት፣ ወራትና ዓመታት በተፈጥሮ ምህዋር ስር የሚኖሩ ናቸው። እያንዳንዳቸውን በህብር በማስተሳሰር ተፈጥሮ ይዘውራቸዋል። በዚህ ውስጥ ይመሻል፣ ይነጋል፣ ይጨልምና ደግሞ ብርሃን ይሆናል። ደመናማ የጭጋግ ቀን ጸሐያማ ብሩህ ቀን፣ የጽልመት ምሽት፣ ደግሞ የጨረቃ ምሽት ይታያል።
ክረምት፣ በጋና በልግ እንዲሁም ጸደይ በአንዲት ዓመት ውስጥ የሚኖሩ፣ በዘመናት መካከል ያልተቀየሩና የማይቀየሩ የተፈጥሮ ማንነቶች ናቸው። ክረምት ዝናባማ፣ በጋማ ብራ…ይህ ማነንታቸው ነው። ያለክረምት በጋ፣ ያለበጋ ክረምት አይኖርም። ማንም ማንንም አይመስልም ነገር ግን፤ በልዩነት ውስጥ አንድነት አላቸው። ስለዚህ የህብረ ብሔራዊ አንድነትን መገለጫ ይዘዋልና አመክንዮው ልክ ይሆናል። ኢትዮጵያዊ በደም ተፈጥሮዋም በመልክ ተሳስረዋል።
አያድርገውና ለአብነት በጋ አሊያም ክረምት ከሁለት አንዱ 365ቱም ቀናት ይገባኛልና አሻፈረኝ ቢሉ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስኪ ለአፍታ አስቡት… በቀን መውጣት ያለባት ጸሐይ በማታ ካልወጣሁ ብትልስ? ጉዳዩ የብርሃንና የጨለማ ብቻ መስሎ ከታየን በእርግጥም ህብረ ብሔራዊነት አልገባንም። የአንዲት ክረምት ማፈንገጥ ከሰው ልጆች ጀምሮ መላውን ተፈጥሮ ያቃውሳል። የማያባራ እልቂት ተከፍቶ መቋጫው ይጠፋል። ጸሐይም ከጨረቃ ጋር ተነካክታ ብቻ አታቆምም። ጦሱ በምድር ላይ ላለ ሰውና ተፈጥሮ ነው። ይህ ከገባን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ማለት ለሀገራችን ምን ማለት እንደሆን እንረዳለን።
ህብረ ብሔራዊነት ለኢትዮጵያ የምርጫ አሊያም የውዴታ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ህብረ ብሔራዊነት የመኖርና ያለመኖር፣ በህልውና የመቀጠልና ያለመቀጠል ነው። ህብረ ብሔራዊነት የሚለው ቃል ብዝሃነትን የሚገልጽ ስለሆነ ብቻ አንድነታችንን ለመጠበቅ የግድ በብሔር፣ ቋንቋና ጎሳ ደረጃ መድረስ አይጠበቅብንም። ጎሳንም ሆነ ብሔርን ቀጥሎም ሀገርን የሠራው እያንዳንዱ ግለሰብ ነውና የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን መሠረቱ ያለው በግለሰቦች ላይ ነው።
እያንዳንዱ ግለሰብ እላይ በሀገር ደረጃ ከማሰቡ በፊት ከራሱ መጀመር ይኖርበታል። እኛ ማን ነን? ለሚለው ምላሽ ከመፈለጉ በፊት እኔ ማን ነኝ ይቀድማል። እኛነት ደረጃ ላይ ከደረስን በኋላ ወደኋላ ተመልሰን እኔነት የሚያጠቃን አስቀድመን ይህን ባለመከተላችን ነው። አጠገባችን ያለን አንድ የሌላ ብሔር ግለሰብ፤ ነገረ ሥራው ሁሉ የሚያስጠላንና የማይመቸን እንደሆን ከብሔሩ ማንነት ጋር ወስደን የምንለጥፍበት አጋጣሚ ቀላል አይደለም። “እነርሱ እኮ እንዲህ ናቸው…አመላቸው ይኼው ነው…ከራሳቸው ዘር በስተቀር የማያስጠጉ…” ወዘተ ወዘተ…ዐረፍተ ነገሮችን ያላሰማን ወይም ያልሰማን የለንም። ዛሬ ለዚህ ያበቃን አንድም ይኼው የጅምላ ፍረጃችን ነው።
ትልቁ ችግራችን እኛ ውስጥ ያሉትን እነርሱን እንጂ፤ እነርሱ ውስጥ ሆነን ራሳችንን አንመለከትም። ብዙዎችን ይህን ፍርድ የሚፈርዱት ወደዚያ ማኅበረሰብ ሄደው ከማኅበረሰቡ ጋር ኖረው ሳይሆን፤ ከዚያ ማኅበረሰብ ወጥተው በእነርሱ ውስጥ የኖሩትን በጣት የሚቆጠሩትን ዋቢ በማድረግ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ጅምላ ፈጅ ንግግር ሲያደርጉ በግሌ ብዙዎችን ሰምቻለሁ።
ነገር ግን፤ በዚያ ከእነርሱ ጋር ኖረው ስለኖሩበት ማኅበረሰብ በክፋት ሲያነሱ የሰማኋቸው እንዳሉ ትዝ አይለኝም። ይህ ማለት በነፈሰብን ንፋስ ሁሉ እንደ ፔንዱለም ዥዋዥዌ የምንጫወት መሆናችንን ያሳያል። እንዲህ ዓይነቱን የጅምላ አመክንዮ የምንከተል ከሆነ በግለሰብ ደረጃ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለመጠበቅ ይከብደናል። ለሞት የመርዝ ጠብታም በቂ ነውና… እያለ ሄዶ የግለሰቦች መመረዝ ሀገርን ያጠፋል። ስለዚህ ህብረ ብሔራዊነት ከአንድ ግለሰብ ዛሬ፣ አሁን ይጀምራል።
ህብረ ብሔራዊነት ዶግማ፣ ህብረ ብሔራዊነት ቀኖና ነው። ያለ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነት፣ ያለ ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያ አይኖሩም። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የምናደርጋቸው የምናገኛቸው ነገሮች ኢትዮጵያን ይሠሯታል። ኢትዮጵያዊነት አንድም በተግባር ሥርዓት ይገለጣል። ሁለትም በልባዊ እምነት እያጸኑ በስጋና በደም ከማይታይ መንፈስ ጋር ይረብባል።
ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብ፣ መደጋገፍ፣ መከባበር…የሚሉ ነገሮች ሁሉ ሚስጥራተ ኢትዮጵያዊነት ናቸው። እኔ ኢትዮጵያውያን ነኝ! ስንልም ከዶግማና ቆኖናው መካከል የሆነውን ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እየጠራን ነውና አሳ ያለውሃ ለመኖር በማይቻለው መጠን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊም ከዚህ ዶግማ፣ ከዚህ ቀኖና በላይም በታችም ሆነው መኖር እንደማይችሉ ማወቅ ሀገር አድን ዕውቀት ነው።
ዶግማውን ያላወቀ ዜጋ፣ ቀኖናውን ያላጤነ ትውልድ ከወንዝ ውስጥ እንደጣሉት መርፌ ማለት ነው። መቼ እንደሚወጋ፣ መቼ የት እንደሚገኝ አይታወቅም። ኢትዮጵያዊነት በደም ብቻ የሚገኝ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት በልብና በሥራ የሚገለጽ የተፈጥሮና የሠብዓዊነት ድምር ውጤት ነው። ሀገራችን በብዙ ልዩነቶች መካከል አንዲት ህብር አጽንታ ዛሬም ድረስ ለመኖሯ ምክንያት፤ በየዘመናቱ የነበሩ ሁሉ ለዚህ ዶግማና ቆኖና ተገዝተውና አክብረው በመኖራቸው ነው። ኢትዮጵያ በህብራዊ አንድነት ተጽና የተወለደች፣ በአንድነት ቢከፋትም ቢደላትም በአንድነት ኖራ በአንድነት አደባባይ ቆማ የታየች ሀገር ናትና ከዚህ ወዲያም ያለዚህ ህላዊ እስትንፋስ አይኖራትም።
እኛ በጥቁር ሕዝቦች ግንባር የታተመን አርማ ነን። እኛ የነጻነት አውድማ፣ የፍቅር ሐይቅ ጀልባ፣ የሰላም ውቅያኖስ መርከቦች ነን። ያለምንም የቀለም ጠብታ የጥበብን ካስማ አቁመን ዓለምን ሁሉ ያስከተልን፣ ያለምንም ቀለም ሠብዓዊነትን ከተፈጥሮ የተቸርን፣ ብዙ ሆነን እንደ አንድ የተፋቀርን፣ አንድ ሆነን እንደ ብዙ የተፋጀን፣ ለወደደን ልባችንን ለጠላን ክንዳችን ስንሰጥ ሁሉ የዚህ ምስጢራዊ ሃይል፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ነበር። ዓድዋ ላይ እንኳን ታንክ ነበራቸው እንጂ አነበረንም። መድፍ ነበራቸው እንጂ እኛ አልነበረንም።
እኛ የነበረን እነርሱ ያልነበራቸው ነገር ቢኖር ያ ብሔራዊ አንድነታችን ነው። ሰሜን ከደቡብ፣ ምሥራቅ ከምዕራብ የቆመው ለአንዲት እናት ሀገሩ፣ አንድ ሆኖ ብቻ ነበር። “አንድነት ሃይል ነው!” ያለው ለምን ይመስልሃል? ምላሹ ለቀባሪ መርዶ እንደማርዳት ነው።
ታዲያ ዛሬስ እንዴት ነን? በ2016 የዳኝነት ሸንጎ ቆመን፣ በ2017 የታዛቢነት ሠገነት ላይ አሻቅበን እየተመለከትን እስቲ ራሳችንን እንጠይቀው። እስቲ ጥቂት እናስብ። እስቲ ጥቂት እናሰላስል። አንድ ሆነን አንድ ምድራዊ ባቢሎን የገነባን ሕዝቦች ነበርን። አብረን ተነስተን አብረን ስንሠራ ምን ያህል ብርቱና ጠቢባን እንደነበርን የዓለም ሕዝብ ሁሉ ምስክር ነው። ግን መቼ? እንዴትና የቱ ጋር ነው ያ ባቢሎናችን የፍርስራሽ ክምር የሆነው? እኛው የሠራነውን የአንድነት ባቢሎን እኛው እያፈረስነው መሆኑ እርግጥ ነው።
ፍቅርና ነገር በዓይን እርግብግቢት የሚገባን ሰዎች ቋንቋችን ተደበላልቆ፤ ከመግባባትም መስማማት የጠፋን እንዴት ይሆን? አዎን…ይህ ሁሉ የሚከተለው ህብረ ብሔራዊነት የራቀ ዕለት ነው። አዎን…ይህን የምናመጣው ለአንዲት ሀገር አንድ ሆኖ በአንድነት መታየት ባስጠላን ቅጽበት ነው። በዚያን ማግስት የኦሞራ የኑስ ዝናብ ይዘንባል። ከምድር በላይ አውሎንፋስ፣ ከምድር ላይ ሱናሚ ይነሳል። የውቅያኖሱ ማዕበል እየተቀሰቀሰ የባህሩ ሞገድ በወጀብ ያናውጣል።
ማንም በውሃው ላይ ሃይል አይኖረውምና ብቻውን ዋኝቶ ለማምለጥ አይቻለውም። ከመርከቦች ቀድመው ጀልባዎች ይሰምጣሉ። ከትናንሾች ይልቅ ትላልቆች ሃይል አላቸው። ሞገዱም ሆነ አውሎንፋሱ አስቀድመው በቀላሉ ሊያጠፉት የሚችሉት ትንሽ ሆኖ ለብቻው ያገኙትን ነው። በታሪክ ብቻውን ቆሞ ብቻውን የጀገነ፣ አንድነትን ገፍቶ አንድ ለራሱ የነገሠባት ማንም የለም። አንዱ ወጀብ፣ አንዱ ሱናሚ የተነሳ ዕለት ነጥሎ የሚመታው ማንም የለምና አንዱ ዳፋው ለሁሉም ነው። ህብረ ብሔራዊነታችን ለማንም ብለን ሳይሆን ራሳችንን ለማዳን የምንሠራት የኖህ መርከብ ናት።
አሁን ዛሬ እየሄደ፣ ነገ እየመጣ ነው። ከታዘብናቸው ጋር በሃሳብ ወርደን በላ! ልበልሃ! ከምንባባል፤ ህብር ባፈካ የፍቅር ቅላጼ ልባቸውን እናቅልጠው። የቀለጠን ነገር ማቃናት እዳው ገብስ ነውና። ሁሌም ካለፈው ለሚመጣው መማርን እንልመድ። ሕይወት ደግሞ ሁሌም የትምህርት ናትና። 2016ዓ.ም የሚል አንድ ደብተር ጽፈንና ሞልተን ልናልፍ ነው። የምናልፈው በፈተና ቢሆን ኖሮ ስንቶቻችን እንደምናልፈው ግን እንጃ…ይሁንና 2017 ዓ.ም የሚል ቀጣዩ አዲስ ደብተር ቀርቧል።
የአዲሱ ሕይወት ትምህርት ቤት ሊከፈት ተቃርቧል። እና ገና በመጀመሪያው የመስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በመጀመሪያው ገጽ ላይ የምንጽፈው ነገር ምን ይሆን? መቼም ታጥቦ ጭቃ መስለን ከአምናው ደብተር ላይ መገልበጥ ከጀመርን ወደኋላ ፊደል መቁጠር ሊያስፈልገን ነው። የምንሰርዘው አሊያም የምንደልዘው ታሪክ ባይኖርም የምንደግመው መጥፎ ታሪክ ግን አይኑረን። መድገም የሰነፎችና የወደቁት ነው። ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ፣ ጎበዝ የሕይወት ተማሪ ሁሌም ዶግማና ቀኖናውን አይረሳምና አይወድቅም። ሁሌም እያስታወስን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በእምነት፣ በተስፋ፣ በፍቅርና በቅንነት አጽንተን እንኑር!!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም