‹‹ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ የሚደራደር ትውልድ ኖሯት አያውቅም›› ሻምበል ዋኘው ዓባይ ወልደ ማርያም (የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል)

ሻምበል ዋኘው ዓባይ ወልደ ማርያም ይባላሉ። የተወለዱት በ1449 ዓ.ም መስከረም አንድ ቀን በጎንደር ከተማ ጨዋ ሰፈር በሚባለው አካባቢ ቆብ አስጥል በምትባል ቦታ ነው። አባታቸው የወገራ አውራጃና አካባቢው የነጭ ለባሽ ጦር አዛዥ፤ የበየዳ፤ የአርማጭሆ፤ የጠለምት፤ የሰሜን ደባርቅ ወረዳዎች ገዢ እንዲሁም የአውራጃው ረዳት ገዢ ሆነውም ለዓመታት አገልግለዋል።

በእነዚህ ጊዜያትም ሻምበል ዋኘው ከአራት ዓመታቸው ጀምሮ አባታቸው በአስተዳደር በተመደቡባቸው ቦታዎች ሁሉ እየተዘዋወሩ የልጅነት ጊዜያቸውን የቤተክህነት ትምህርት በመማርና በድቁና በቤተክርስቲያን በማገልገል አሳልፈዋል። ዘመናዊ ትምህርት ቤትን ሲቀላቀሉም በቤተክርስቲያን የቀደመ ትምህርት ስለነበራቸው የጀመሩት ከአራተኛ ክፍል ነበር።

በዚህ ሁኔታ ከቆዩ በኋላ በ1967 ዓ.ም የሰባተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አቋርጠው ኢህአፓን በመቀላቀል በርሃ ገብተው በወቅቱ የነበረውን የደርግ መንግሥት በመቃወም ለሶስት ዓመት ተኩል በታጋይነት ቆይተዋል። ከዚህ በኋላ ግን በአባታቸው ጥያቄና ትእዛዝ መሠረት መንግሥትን ምህረት ጠይቀው ሰላማዊ ኑሮ ለመጀመር በቁ።

በዚህ ሁኔታ እስከ 1972 ዓ.ም ከቆዩ በኋላ የኢትዮጵያን ሠራዊት በመቀላቀል በአስራ ስምንተኛው ተራራ ክፍለ ጦር ሰላሳ አምስተኛ ብርጌድ በመመደብ አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን በታጠቅ እና በሀረር ሁርሶ ማሠልጠኛዎች በመግባት ወታደራዊ እና የፖለቲካ ትምህርት ሥልጠናዎችን ተከታትለዋል። ከዚህ በኋላ በወቅቱ በትግራይና ኤርትራ ክፍለ ሀገራት በተለያዩ ቦታዎች በአውደ ውጊያዎች እስከ 1976 ዓ.ም ተሰልፈዋል። በ1976 ዓ.ም ወደ ሀረር ጦር ትምህርት ቤት በመመለስ የመቶ አለቅነት ኮርስ ካዴት በመውሰድ በምክትል መቶ አለቅነት ተመርቀው እስከ ሻምበል ማዕረግ በመድረስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በውትድርና ሳይንስና በፖለቲካ ትምህርት አሠልጣኝነት ለማገልገል በቅተዋል።

ከዚህ በኋላም ወደ ሩስያ ለከፍተኛ ትምህርት የተላኩ ቢሆንም ከአስር ወራት ቆይታ በኋላ የእናት ሀገር ጥሪ በመደረጉ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በውትድርናው ቀጥለዋል። ከመንግሥት ለውጥ በኋላም ወደ ላይቤሪያ በመሄድ ለጥቂት ወራት በምግብ ቤት ሠራተኝነት ሲሠሩ ቆይተው ሁኔታዎች ስላልተመቿቸው ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል። ከዚህ በኋላ በሀገር ቤት በነበራቸውም ቆይታ የተለያዩ ሥራዎችን ከመሥራት በተጓዳኝ ያቋረጡትን ትምህርት በመከታተል በማኔጅመንት የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመያዝ፤ ትዳር በመመስረትም የአራት ልጆቸ አባት ለመሆን በቅተዋል።

የሻምበል ዋኘው አባት የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሲመሠረት ተመራጭ በመሆን የሥራ አስፈጻሚ ሆነው አገልግለው ነበር ። በዚህም ምክንያት በ2006 ዓ.ም የአርበኛ ልጆች ማህበሩን እንዲቀላቀሉ መወሰኑን ተከትሎ ሻምበል ዋኛው በጊዜያዊ ዋና ጸሀፊነትና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ለሰባት ዓመታት አገልግለዋል።

ከ2013 ዓ.ም ጀምሮም በማህበሩ የበጎ ፈቃደኛ የነጻ አገልግሎት ሰጪ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። እኛም ለዛሬው የሕይወት አምድ እትማችን ከሀገር ሉዓላዊነት መጠበቅ ጋር ያላቸውን ተሞክሮ እንዲያጋሩን እንግዳችን አድርገን አቅርበናቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የኖረች ሀገር ናት ። ኢትዮጵያውያንም በሀገራቸው ሉዓላዊነት አይደራደሩም ይባላል ይህንን እንዴት ያዩታል ?

ሻምበል ዋኘው፡- ኢትዮጵያ ሉዓላዊነታቸውን አስጠብቀው ዘመናትን ከተሻገሩ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ኖሯል ስንል ግን አንድነቷን ለማፍረስ ሕዝቦቿን ለመበታተን በርካታ የተሸረቡ ሴራዎችና ሳይሳኩ የቀሩ ሙከራዎች እንደነበሩ ሳንዘነጋ ማለት ነው። እነዚህ ዛሬም ድረስ ተሻግረው ስጋት እየሆኑ ያሉ ሀገር የማፍረስ እና ሕዝብን የመበታተን ሙከራዎች ሳይሳኩ የቀሩት ደግሞ በእድል ወይንም በአጋጣሚ አልነበረም። ይልቁንም ቀደምት ኢትዮጵያውያን አባቶች በከፈሉት ዘመን ተሻጋሪ የጀግንነት መስዋእትነት ነው። እነዚህ ቀደምት ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ የውጭ ወራሪዎችና ሀገር በታኞችን ሲመክቱ የነበሩት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ጥቅም በማስቀደም የጠነከረ አንድነት በመፍጠር ነበር። የሀገርን ዳር ድንበር የሀገርን ሉዓላዊነት የሚነካ ጉዳይ ሲፈጠር የውስጥ ችግርን ቅሬታና ግጭትን ወደጎን በመተው በአንድ መሰባሰብ ለኢትዮጵያውያን የተለመደና ሀገር ያቆየ መለያቸው ነው። ይህንን የተረዱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የማይተኙ ሀገራትም ምንም እንኳን ባይሳካላቸውም ዛሬም ድረስ እየሞከሩ ያሉት የውስጥ አንድነትን በመረበሽ ዓላማቸውን ለማሳካት ነው።

ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ የሚደራደር ትውልድ ኖሯት አያውቅም። ለዚህ ጥሩ ማሳያ እንዲሆን የቅርብ ጊዜውን ታሪክ ማነሳት እንችላለን። ይህም ኤርትራ አንደ ሀገር ከቆመች በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር አድርጋው የነበረው ጦርነት ነው። በወቅቱ ኢትዮጵያ የነበራት የአስተዳደር ሥርዓት ብሄር ተኮር ማለትም ቋንቋን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት በመሆኑ በውጭ ሃይሎች ዘንድ ከፍተኛ መከፋፈል እንዳለ ተደርጎ ይወራ ነበር። በእርግጥም እስከ ጦርነቱ መጀመር ድረስ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የነበረው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ ከሚለው መገለጫ ይልቅ ቋንቋን መሠረት ያደረገውን ማንሳት ተስፋፍቶ ነበር። ይህንን ያስተዋሉ አንዳንዶች ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ቀሪው የሀገሪቱ ክፍልም የመበታተን የመገነጣጠልና የእርስ በእርስ ጦርነትም ይፈጠራል የሚል ስጋት ነበራቸው።

ይህ ስጋት ደግሞ በውጭ ሃይሎች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በቅጡ ባልተረዱ ሀገር እንድትፈርስ በሚፈልጉ ጥቂት የሀገር ልጆችም ውስጥ የነበረ ነው። ነገሩ ግን እንደተጠበቀውም እንደተፈራውም ሳይሆን ቀርቶ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ጦርነቱ ተጠናቆ ሀገሪቷም ዛሬ ለይ ለመድረስ በቅታለች። ዛሬም አሁን ያለውን መንግሥት የሚቃወሙ አካላት እንዳሉ ይታወቃል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ረገድ ማንም ጥያቄ ሲያነሳ ሰምተን አናውቅም። ይህ ደግሞ ከውጭም ሆነ ከሀገር ውስጥ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጉዳይ ገብተው ለመፈትፈት ለሚያስቡ አካላት ጥሩ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያውያን ለሉዓላዊነታቸው ያላቸውን ቀናኢነት እንዴት ይመለከቱታል ?

ሻምበል ዋኘው፡- የሉዓላዊነት ጥያቄ የሀገርና የሕዝብን ጥያቄ መሠረት ያደረገ ነው። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ሁለት ጉዳዮችን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች እንደሆነ እረዳለሁ። እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ጥርስ ያጋቡንም ናቸው። አንደኛው የህዳሴው ግድብ ነው። በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለማቆም በኢትዮጵያ የነበሩ መንግሥታት በሙሉ ሃሳብም ጅምርም የነበራቸው ቢሆንም ዛሬ የደረስንበትን ያሳዩን ግን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው።

እሳቸው ግድቡን በጀመሩበት ወቅትም በርካታ የሀገሪቷን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ ነገሮች ከግድቡ ጋር በተያየዘ ገጥመው ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም አልተሳኩም። በቅርቡም ሃያል የተባለችው ሀገር አሜሪካ መሪ ሳይቀሩ የህዳሴው ግድብ በግብጻውያን በቦምብ ለሚታ እንደሚችል ነግረውን ነበር። ግን እውን የሆነ ነገር የለም። የህዳሴው ግድብ እዚህ መድረስ ለሀገሪቱ የልማት ጅማሮ መሠረት የጣለ ነው። ከዚህ በኋላ የሚሠሩ በርካታ ሥራዎችም እንደሚኖሩ ተስፋ አለኝ ። እኛ አንድ ሆነን ትልቅ ሥራ ሥንሰራ ጠላቶቻችን ከሴራ መታቀባቸው አይቀርም።

ሁለተኛው ኢትዮጵያን የባሕር በር እንድታገኝ መንግሥት የጀመረው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው። ይህ ብዙዎችን ያስደነገጠ ሃሳብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጠየቀችው የባህር በር ጥያቄ የማንንም ሉዓላዊ ሀገር በጉልበት ለመጠቅለል የሚደረግ ሙከራ አይደለም። በዚህ ረገድ አሁን ጣልቃ እየገቡ ያሉት ሀገራት የሚሠሩት ሥራ ግን የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን ሉዓላዊነትም የሚገዳደር ነው። በዚህ ረገድ እኔ የምለው ነገር ቢኖር በመንግሥት በኩል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን መላው ኢትዮጵያዊ መደገፍ እንዳለበት ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ስላሴ በዲፕሎማሲው መስክ እየሠሩ ያሉትን አኩሪ ሥራዎች እየተመለክትን ነው። በመንግሥት በኩል ይህ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። እንደ ዜጋም ይህ ጅማሮ ውጤት እንዲያመጣ በያለንበት ከመንግሥት ጎን ልንቆም ይገባል። ይህንን የምለው ለግለሰቦች ብቻ አይደለም። በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት በተቋውሞ ጎራ ለተሰለፉትና የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉትም ነው። በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጉዳይ የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሆደ ሰፊ ሆኖ ነገሮችን መቻልም ይጠበቃል። ያለንን ልዩነት ወይንም ግጭት የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት እስከሚፈታተን ልናደርስ አይገባም።

አዲስ ዘመን፡- እስካሁን የቆየውን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስጠብቆ ለመቀጠል ከማን ምን ይጠበቃል ?

ሻምበል ዋኘው፡- የሉዓላዊነት ጉዳይ ሲነሳ ከድንበር ጋር ብቻ መያያዝ የለበትም ። በእርግጥ በዋናነት የሀገርን ድንበር መጠበቅ ወራሪዎችን ሽንፈት አከናንቦ መመለስ የግድ የሚል ቢሆንም ሉዓላዊነት ግን ከዚህም በዘለለ በኢኮኖሚውና በውስጣዊ አንድነት በማጠናከሩም ረገድ ብዙ መሥራት ይጠበቃል። ይህ ማለት ደግሞ የሀገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሁሉም ዜጋ በየደረጃው በያለበት ሃላፊነት አለበት ማለት ነው።

የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባው ጠመንጃ ይዞ የመጣ ወራሪ ሲከሰት ብቻ ሳይሆን በድህነት እጅን ለልመና መዘርጋት ሲጀመርም ነው። ወጣቶች ሥራ አጥ ሆነው ከሀገር ሀገር መሰደድ ሲጀምሩ ሉዓላዊነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ መግባቱ አይቀርም። ባጠቃላይ ኢኮኖሚው ሲዳከምና የውስጥ አንድነት ሲናጋ ሉዓላዊነትን በሚጋፋ መልኩ የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት መከሰቱ አይቀሬ ነው።

በመሆኑም ስለ ሉዓላዊነት ስናነሳ ስለ እድገት ስለ ብልጽግና ማሰብ የግድ የሚል ይሆናል። በሌሎች ሀገራት እንደምናየው ሉዓላዊነታቸውን አስከብሮ ለመኖር ከሌሎች የሚጠይቁት የሚለምኑት ነገር እንዳይኖር ጠንክረው ይሠራሉ። እኛ ሀገር ያለውም ሁኔታ ከዚህ

ጋር የሚመሳሰል ሊሆን ይገባል። ብዙ ጊዜ የሌሎች ሀገራት ጣልቃ ገብነት ሲከሰትብን የምናየው አንድም በመሀከላችን ያለ ክፍተትን አለ ብለው ሲያምኑ ያንን በመጠቀም ነው። አልያም ያለብንን የኢኮኖሚ ችግር መነሾ በማድረግ የርዳታ እጃቸውን በመዘርጋት ነው።

በመሆኑም ሥራ በመሥራት ራስን መቻልና ሀገርን ማልማት በሌላ በኩል ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ መሆኑን ልናውቅ ይገባል። ዛሬ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ችግር እያለም እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች የሉዓላዊነታችን ማስጠበቂያ አንድ መንገድ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። በአዲስ አበባ በስፋት እየተሠራ ያለው የኮሪዶር ልማት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። እኔ በአዲስ አበባ ከአርባ ዓመት በላይ ስቆይ ሁሉም መንግሥታት በየዘመናቸው የሠሯቸውን የተለያዩ የከተማ ልማት ሥራዎች አይቻለሁ ። በዚህ ፍጥነት በዚህ ያህል መጠነ ሰፊ ደረጃ ልማት ሲካሄድ ግን አይቼ አላውቅም ። ልማቱ የከተማዋን ነዋሪ አልያም ቀሪውን ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንና ሌሎችንም የሚያስደንቅ እንደሚሆን እገምታለሁ። ይህ ዐሻራ የዚህ ትውልድ አንድ ክፍል ነው ።

የኮሪዶር ልማቱ ሲሠራ የተፈናቀሉ እና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የሚዳረጉ ዜጎች እንደሚኖሩ ግልጽ ነው። ይህም ቢሆን ግን የትም ሊከሰት የሚችልና ለሀገርና ለሕዝብ ሲባል የሚደረግ መስዋእትነት እንደሆነ ሊታሰብ ይገባል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ብቻ አለመሆኗን በመገንዘብ ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ከላይ እንደጠቀስኩት የሀገር ሉዓላዊነት ከሀገር ልማት ጋር በቀጥታ ይገናኛል። ብዙ የልማት ሥራዎችን ስናከናውን ብዙ የሥራ እድል የመፈጠር አጋጣሚ ይኖራል። በዚህ ሂደት ተጠቃሚ የሚሆን ማህበረሰብ ደግሞ ሀገሩን የሚወድና የሚጠበቅ መሆኑ አይቀርም። ይሄ ማለት የሀገር ሉዓላዊነትን የሚነካ አጋጣሚ ሲፈጠር መከታ የሚሆን ሕዝብ እና ትውልድ አለ ማለት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ረገድ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) ምን ይጠበቃል?

ሻምበል ዋኘው፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት በሀገር ውስጥ የሚኖረው ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ማለት ነው። በዚህ መሠረት በውጪው ዓለም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብዙ ይጠበቃል። በአንድ በኩል ጠላቶቻችን የሀገር ሉዓላዊነትን ለማደፍረስ ብዙ ጊዜ እንደ መልእክተኛ የሚጠቀሙት በየሀገራቸው በስደት በትምህርትና በሌሎች ምክንያቶች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ነው። አንዳንዶቹ ለውጭ ጠላቶች የመረጃ ምንጭ ሲሆኑ አይተናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን በአውሮፓና አሜሪካ ሆኖ መቃወም የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል።

በሀገር ውስጥ የተለየ ሃሳብንና የራስ የሆነ የፖለቲካ አመለካከትን ለማራመድ ምቹ ሁኔታ አለ እያልኩ አይደለም። ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ችግሮች ደግሞ ዛሬ የተፈጠሩና አዲስ አይደሉም። ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ በሀገር ውስጥ ያሉ ችግሮችን እንፈታለን ያሉ አካላት በአውሮፓና አሜሪካ ፓርቲ ሲመሠርቱ በስፋት ሲንቀሳቀሱም ነበር። በተመሳሳይ በደርግም በቀደመው የኢህአዴግ ዘመንም በመንግሥት ላይ የሚደረጉ ተቃውሞዎች ከሀገር ውስጥ ይልቅ በእነዚህ ሀገራት የበረቱ ናቸው። በግልጽም ማእቀብ በማስጣል የመንግሥትን ሃሳብ ለማስቀየር የሚሠሩት ሥራዎች ዛሬም ድረስ አሉ።

ምንም ይሁን ምን ግን የሀገር ሉዓላዊነትን ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ከባእድ ጋር ሊመክር አይገባም። የሀገር ሉዓላዊነት ለችግር በመጋለጡ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አይሆንም። አነሰም በዛ በታቃውሞ ጎራ የተሰለፉትም እንታገልለታለን የሚሉት ማህበረሰብ የገፈቱ ቀማሽ መሆኑ አይቀርም።

ስለዚህ የሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ኢትዮጵያዊ የሆነን ሁሉ የሚመለከት ነው። ለምሳሌ የህዳሴው ግድብ ሲገነባ ከተፋሰሱ እና ከአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ጋር በነበረው ግንኙነት የሀገር ሉዓላዊነትን የሚነኩ አጋጣሚዎች ተፈጥረው ነበር ። በወቅቱ በዚህ ጉዳይ የመንግሥትና የሕዝቡ አንድነት ጠንካራ ስለነበር ሁሉም ነገር አልፎ ግድቡ ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅቷል። በዛን ጊዜ ብዙ ተቃውሞ ሲቀርብበት የነበረው የኢህአዴግ መንግሥት ዛሬ በሥልጣን ላይ የለም፡፡ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ሕዝብና የህዳሴው ግድብ ጥቅም ግን አሉ፤ ወደፊትም ይቀጥላሉ።

በአሁኑ ወቅትም ከባህር በር ጋር በተያያዘ በመንግሥት በኩል የተጀመረው ሥራ ተመሳሳይ ውጤት የሚኖረው ይሆናል። አንድነታችንን አጠናክረን የባሀር በር ባለቤት ለመሆን ከበቃን መንግሥት ቢቀያየርም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም የመጪው ትውልድ ተጠቃሚነት የተረጋገጠ ይሆናል። በመሆኑም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ምንም ያህል ችግር ገጥሟቸው ተቃውሞ ቢያሰሙም በሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ መደራደር የለባቸውም።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ሂደት የውስጥ ችግሮች መሰናክል እንዳይሆኑ ምን ሊሠራ ይገባል ?

ሻምበል ዋኘው ፤ በመጀመሪያ ደረጃ የውስጥ አለመግባባቶች ለሀገር አንድነት መጠበቅ እና ለሉዓላዊነት እንቅፋት እንዳይሆኑ መፍትሄው ተቅራርቦ መነጋገር ብቻ ነው። በንግግር የማይፈታ ጉዳይ የለም። በውስጥ ችግራቸው እርስ በእርስም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር እሰጥ አገባ ገብተው ጦርነት የገጠሙ ሀገራት መጨረሻቸው የሚሆነው ድርድር እና ውይይት አድርጎ መስማማት ነው። እኛም ጋር ሊሆን የሚገባው ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ተቀራርቦ መነጋገር ነው።

በዚህ በኩል በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን ብዙ የሚጠበቅ ይሆናል። የምክክር ኮሚሽኑ በመላው ሀገሪቱ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ እናውቃለን። ለዚህ ውጤታማነት ሁላችንም ሃሳባችንን ልንሰጥ፤ የሌሎችንም ልንሰማ ይገባል።

የምክክር ኮሚሽኑን እየመሩ ያሉ አካላትም ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው። እኛ ባለን አቅም አብረናቸው ከሆንን በተለይም የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያራምዱ አካላት ራሳቸውን ለድርደር ለውይይት ዝግጁ ካደረጉ ነገሮች ሁሉ በቀላሉ ሊፈቱ ይችላሉ። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሚለያያቸውና ከሚያቃቅራቸው በላይ በህብረት በአንድነት ያሳለፉት ጊዜና የሠሩት ሥራ ትልቁን ደርሻ የሚይዝ ነው። የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ መሆን ይህን አብሮነት አንድነትና መተሳሰብ ሊያስቀጥል የሚያስችል ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻችንን እየፈታን ህብረታችንን ማጠናከር ከቻልን የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ትልቁን ድርሻ ወሰድን ለማለት ይቻላል።

በሁለተኛ ደረጃ ወጣቱ ትውልድ ለሰላም ያለው ምልከታ የተስተካከለ ሊሆን የገባል። ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው። ሰላም ከሌለ ምንም ጥሩ ነገር ሊኖር አይችልም። የሀገር ሉዓላዊነት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ግለሰብ የእያንዳደንዱ ቤተሰብ ደህንነት አደጋ ለይ መውደቁ አይቀርም። ይህ እንዲሆን የሚፈልግ ደግሞ ይኖራል ብዬ አላስብም። በወጣቶች በኩል የተለያዩ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ሊኖሩ ይችላሉ። የሚታገሉለት ማህበረሰብም ሊኖር ይችላል። ሁሉንም ነገር ግን በሰላም ጥላ ስር ሆነው ማካሄድ እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል። ብዙ ጊዜ የሰላም መደፍረስ ለችግርና ለስቃይ የሚዳርገው መብቱን እናስክብርለታለን ፤ ፍላጎቱን እናሳካለታለን፤ ጥያቄውን እንመልስለታለን ብለው የተነሱለትን ሕዝብ ነው።

ይህንን እውነታ የፖለቲካ ልሂቃን ነን፤ የተወሰነን ማህበረሰብ እንወክላለን የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሊገነዘቡትና ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። በመሠረቱ እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ሳይከበር በተናጥል መብትና ጥቅሙን ሊያስከብር የሚችል ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሊኖር አይችልም። በመሆኑም በአንድ ሀገር ጥላ ስር እስካለን ድረስ ጥያቄዎች ሁሉ መቅረብ ያለባቸው በሰላማዊ መንገድ በንግግር ብቻ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር መሆኗን የሚያውቁ ፤ ነገር ግን በጠላትነት የፈረጇት ሀገራት ባይሳካላቸውም ሉዓላዊነቷን ለመፈታተን የሚሞክሩት የውስጥ ልዩነቶችን በማጋነንና በማጋጋል ነው። በመሆኑም በዚህ ረገድ የመላው ዜጋ በተለይም የወጣቶች ምላሽ ሊሆን የሚገባው ከሀገር ሰላምና የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ ልዩነት እንደማይኖር አሳይቶ አሳፍሮ መመለስ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር መጠበቅ የትውልዱ ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል ?

ሻምበል ዋኘው ፤ በአንድ በኩል አሁን ያለው ወጣት ትውልድ የራሱ ግል ሕይወት ብቻ ሳይሆን የነገዋ ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በእጁ መሆኑን መረዳት አለበት። ምንም ይሁን ምን የሉዓላዊነት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ሊሆን አይገባም። በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የተለያዩ ልዩነቶች እንዳሉን ይታወቃል። ልዩነቶች ድሮም አባቶቻችን ዳር ድንበር አስከብረው ኖረዋል በምንልበት ዘመንም ነበሩ። ነግር ግን እነሱ ልዩነታቸውን ጉዳታቸውንም ሆነ ጥያቄያቸውን ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስቀድመው አያውቁም። የዘመነ መሳፍንት የእርስ በእርስ ግጭት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ይህም በመሆኑ አባቶቻችን ዛሬ ድረስ የተሻገረ ሀገርም ታሪክም ለማስቀጠል በቅተዋል። የአሁኑ ትውልድም ምንም የውስጥ ልዩነት ቢኖር ዛሬ እሱ ስለሚኖርባት ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩም ትውልድ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ከነሙሉ ክብሯና ሉዓላዊነቷ የማስተላለፍ ሃላፊነት እንዳለበት ሊገነዘብ ይገባል።

በዚህ ረገድ ስለውጪ ጣልቃ ገብነት መታወቅ ያለበት ኢትዮጵያን በጠላትና በስጋትነት ያስቀመጡ ሀገራት አጋጣሚውን ባገኙ ቁጥር መሞከራቸው እንደማይቀር ነው። ውጤታቸው የሚወሰነው ግን በእኛ አንድነትና በምንሰጠው የህብረት ምላሽ ብቻ ይሆናል። በመንግሥትም በኩልም ቢሆን የውስጥ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚጠበቅበትን ሁሉ ማድረግ አለበት። በተጨማሪ ሥራ የማይሠራ ወጣት ሊኖር አይገባም። የቻለ ራሱ ሥራ እየፈጠረ መሥራት ያልሆነለት ደግሞ በመንግሥትና በሌሎች አካላት የሚፈጠሩ የሥራ እድሎችን እየተጠቀመ ራሱንና ሀገሩንም ሊያሸጋግር ይገባል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሁን ስላለው ትውልደ ስናወራ ትውልዱን መቅረጽ ስላለበት ያለፈው ትውልድ ማንሳታችን የግድ ይሆናል። ሀገር የምትጠበቀውም የምትጸናውም በትውልድ ቅብብሎሽ ነው። በዚህ ሂደት ለሀገሩና ለወገኑ የሚያስብ ሀገር ተረካቢ ወጣት እንዲፈጠር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል። ቤተሰብና ማህበረሰብ በየደረጃቸው ከሚኖራቸው ድርሻ በዘለለ የትምህርት ተቋማት ሃላፊነት አለባቸው።

ድሮ የነበረው የትምህርት ሥርዓት ሁሉንም ጥያቄ ከሀገር የሚያስቀድም አልነበረም፡፡ አሁንም ቢሆን ማንኛውም ጥያቄ ከሀገር ሊቀድም አይገባም። ትውልዱ ይህንን ሃሳብ እንዲያውቀውና አምኖ እንዲቀበለው የማድረግ ሥራ ከትምህርት ተቋማትና ከመምህራን ይጠበቃል። ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ተማሪዎችን ስለልዩነታቸው ሳይሆን ስለአንድነታቸውና ስለህብረታቸው፤ ስለመከባበርና መዋደዳቸው ደጋግሞ በማስተማር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

ሻምበል ዋኘው፡- አመሰግናለሁ ።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

 

አዲስ ዘመን እሁድ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You