ለሌሎች በመኖር – ትርጉም ያለው ሕይወት እንዴት እንፈጥራለን?

ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ደስታን በገንዘብ፣ በሥልጣን ወይም በዝና ለማግኘት ይሞክራሉ። ነገር ግን ብዙዎች እነዚህን ነገሮች ካገኙ በኋላም በውስጣቸው አንድ ነገር የጎደለ እንዳለ ይሰማቸዋል። እርሱም እውነተኛ እርካታ ነው። ለመሆኑ እውነተኛ የመኖር ትርጉምና እርካታ እንዴት በሕይወታችን ላይ ልንፈጥር እንችላለን? የዛሬው ርእሰ ጉዳዬ ከዚህ ጥልቅ የስሜት ቁርኝት ካለው ጉዳይ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ይሆናል። በምድር ላይ ስንኖር ትርጉም ሊሰጡን ስለሚችሉና ከተፈጥሮ ጋር ጥልቅ ትስስር ስለሚፈጥሩልን ጉዳዮች በስፋት እናነሳለን። ለመሆኑ እውነተኛ የሕይወት ትርጉምና እርካታ እንዴት ሊኖረን ይችላል?

እውነተኛ የመኖር ትርጉምና እርካታ ብዙ ጊዜ የሚመጣው ከሰዎች በምንወስደው ሳይሆን በምንሰጠው ነገር ነው። ለሌሎች መኖር ለሕይወታችን ጥልቅ ትርጉም እና ዘላቂ ደስታን ያመጣል። ለቤተሰባችን፣ ለልጆቻችን እና ለማኅበረሰባችን ስንኖር የበለጠ መኖራችን ትርጉም ይኖረዋል፤ ከሁሉም በላይ ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እና እርካታ ይሰማናል። ይህ የአኗኗር ዘይቤ ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ለሁላችን የሰው ልጆች በእጅጉ ይጠቅመናል።

ለሌሎች መኖር ማለት እንደ ሰው የማደግ መንገድ ነው። አጠገባችን ላሉ ሰዎች ስንኖር ደግ፣ ታጋሽ እና አስተዋይ እንድንሆን ያስተምረናል። ጠንካራ ግንኙነት እንድንፈጥር ይረዳናል። ለሌሎች ጊዜን፣ ፍቅርን እና ድጋፍን ስንሰጥ የበለጠ ሕይወታችን ትርጉም እንዳለው ይሰማናል። ሕይወታችን አስፈላጊ እንደሆነ እንዲሰማን ያደርጋል። በዚህ ዓለም ብቻችንን አይደለንም፤ እኛ የትልቁ ዩኒቨርስ አካል ነን። ምድራችን ላይ ያለው ከባቢ፣ ተፈጥሮ፣ መንደራችን፣ ጎረቤቶቻችን ሁሉ የእኛው አካል ናቸው። ለዚህ ነው ሌሎችን መርዳት ጠንካራ ማኅበረሰብ ይገነባል የምልህ። ጠንካራ ማኅበረሰብ ለመገንባት የግልህን አስተዋጽኦ ስታደርግ እያንዳንዱ ሰው ያለ እንከን በሕይወት መንገድ ላይ ስኬታማ እንዲሆንና እንዲያድግ ይረዳል።

ለሰው መኖር አስተሳሰብ ወይም እምነት ብቻ አይደለም። በእውነተኛ ጥናቶች የተደገፈ ነው። ለምሳሌ አንድ ጠቃሚ ጥናት ጂነስ በተባለው መጽሔት ላይ በቅርቡ ታትሟል። ጥናቱ ጥብቅ መተሳሰብና መደጋገፍ ያለበት ጓደኝነት የሕይወት እርካታን እንደሚሰጥ ያትታል። የቅርብ ጓደኞች ያሏቸው እና ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች የበለጠ ደስተኛ እንደሆኑም በሳይንሳዊ ጥናት ያረጋግጣል። በዚህ ከባቢ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሕይወት የበለጠ ደስተኝነት ይሰማቸዋል። በመልካም መንገድ የመሠረትናቸው ግንኙነቶች አዎንታዊና ስሜታዊ ድጋፍ ይሰጡናል። የጂኒየስ መጽሔት ጥናት እንደሚያመለክተው ሰዎች ችግሮችን እንዲፈቱ እና ውጥረት እንዲቀንስ ከሰዎች ጋር ያላቸው መልካም ግንኙነት ቁልፍ ነው። ጥናቱ እንደሚያሳየው ለሌሎች መኖር የደስታ ቁልፍ ነው።

በአሜሪካ የሥነ ልቦና ማህበር የታተመ ሌላ ጥናት የሰዎችን ጥልቅ ስሜት በርህራሄ ልክ እንደ ራሳችን መረዳት ስላለው ጠቀሜታ ያትታል። ርህራሄ ማለት ሌላ ሰው የሚሰማውን ስሜት መገንዘብ፤ ራስህን በሌላ ሰው ቦታ ማስቀመጥ ነው። ይህ ችሎታ ሰዎች በጥልቅ የስሜት ትስስር እንዲገናኙ ይረዳል። አንተ ሩህሩህ ስትሆን ሰዎችን በደንብ መረዳት ትችላለህ። አጠገብህ ያሉ ሰዎች ንግግርን ዝም ብለህ አትሰማም፤ ሕመማቸው ይሰማሃል፤ ደስታቸው ደስታህ ይሆናል። ይህ ግንኙነቶችዎን የበለጠ ጠንካራ እና የበለጠ ትርጉም ያለው ሕይወት እንድትመራ መንገድ የሚከፍትልህ ነው።

መተሳሰብ የበለጠ ለሰዎች ቦታ እንድንሰጥና እንድንጨነቅ ይረዳናል። ርህራሄ ሲኖረን ሌሎችን የመርዳት እድላችን ሰፊ ነው። ቅያሜ በሚፈጠር ሰዓት በቶሎ ይቅር የማለት እድላችን ሰፊ ይሆናል። በተጨማሪ በሰዎች ላይ እጃችንን ከመቀሰርና ከመፍረድ እንቆጠባለን፤ መተሳሰብ ልባችንን ይከፍታል። ሌሎችን እንደ እንግዳ ሳይሆን እንደ ራሳችን አድርገን እንድንመለከት ያስችለናል። ሰዎችን የመረዳት አቅም ሲኖረን በቀላሉ ግጭትን ለመቀነስ እና በሕይወታችን ላይ የበለጠ ሰላምን ለማምጣት ምክንያት ይሆናል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከፍ ያለ የመተሳሰብ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በቡድን ውስጥ በስኬት በመሥራት እና ችግሮችን በመፍታት የተሻሉ ናቸው።

መተሳሰብ ለግል እድገታችንም ይረዳል። ለሌሎች ስንጨነቅ በራስ መተማመናችን ያድጋል፤ የራሳችንን ስሜት ለሌሎች በቀላሉ የማጋራት እና ተመሳሳይ ድጋፍ የማግኘት እድላችን ሰፊ ይሆናል። የበለጠ ታጋሽ እና ሰላማዊ እንሆናለን። ከሁሉም በላይ ማዳመጥ እንማራለን፤ መስጠትን እንማራለን፤ በምላሹም መተማመን እና ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ እያደገ ይመጣል።

ለሌሎች መኖር ጠንካራ ያደርገናል። በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ስናልፍ ብዙ ጊዜ የሚረዳን የሌሎች ፍቅር እና ድጋፍ ነው። ሌላውን ስንረዳ ደግሞ የራሳችንን ሕመም ለጊዜው እንረሳዋለን። በሕይወት ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ እኛ ብቻ እየታገልን እንዳልሆን እናያለን። ይህ ጥንካሬ ይሰጠናል፤ በፍጥነት የማገገም ዓላማ ይሰጠናል።

ለሰዎች መኖርና ርህራሄን ማሳየት በመወለዳችን ብቻ የምናገኘው ችሎታ እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፤ ይልቁኑ የምንማረው ነገር ነው። ልክ ማንበብ ወይም መጻፍ እንደምንማረው ሁሉ የበለጠ ለሰዎች ማሰብና መተሳሰብን መማር እንችላለን። በየቀኑ ለሌሎች መኖርን መለማመድ እንችላለን። ይህንን ችሎታ ለማዳበር በትንሹ መጀመር እንችላለን።

ርህራሄን በተግባር መገንባት ይቻላል። አንዱና ዋንኛው ርህራሄን የምንለማመድበት መንገድ በጥልቅ ማዳመጥ ነው። አንድ ሰው ሲያናግርህ ንግግራቸውን ብቻ አትሰማ። ምን ዓይነት ስሜት እና መጎዳት እንደሚሰማቸው ለመረዳት ሞክር፣ ፊታቸውን ተመልከት፣ የሰውነት ቋንቋቸውን ተገንዘብ። በህሊናህ እነዚህ ሰዎች ምን እየደረሰባቸው ሊሆን እንደሚችል አስብ። ይህ ከእነሱ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖርህ ያግዝሀል።

ርህራሄን ለመገንባት ሌላኛው መንገድ በራስህ ስለደረሰብህ የአንድ ወቅት ጉዳት እና ጥልቅ የሀዘን ስሜት ማሰላሰል ነው። ሀዘን፣ ፍርሃት ወይም ብቸኝነት የተሰማህ ጊዜያትን መለስ ብለህ አስብ። ከዚያም ከዚያ ስሜት ውስጥ ስትወጣ አንድ ሰው ሲረዳህ ምን እንደተሰማህ አስታውስ። ይህ ትውስታ ለሌሎች ተመሳሳይ ስሜት እንዲኖርህ ያደርጋል፤ ልብህን ከፍቶ የበለጠ አሳቢ እንድትሆን፤ ለሰዎች አንተም ደራሽ፣ አዛኝና ደጋፊ እንድትሆን ያደርግሃል።

ማንበብ ሰዎችን በቀላሉ ለመረዳትና ርህራሄን ለማዳበርም ይረዳል። ለምሳሌ የልቦለድና እውነተኛ ታሪኮችን ስናነብ ወደ ገጸ ባሕሪያቱ አዕምሮ ውስጥ በጥልቀት እንገባለን። ሕመማቸው እና ደስታቸው ይሰማናል። ስለ የተለያዩ ባሕሎች፣ ባሕሪያት እና ሕይወት እንማራለን። ይህ የበለጠ በሰዎች ላይ ፈራጅ እንዳንሆን ያደርገናል።

ለሌሎች መኖር ለማኅበራዊ ግንኙነታችንን ብቻ የሚጠቅም አይደለም። ለአእምሯችን እና ለአካላችንም ጠቃሚ ነው። ሌሎችን የሚረዱ ሰዎች ረጅም ዕድሜ እንደሚኖሩ ጥናቶች አረጋግጠዋል። በቀላሉ ጭንቀትና ውጥረት ውስጥ አይገቡም፤ በድብርት የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ ነው። ሌሎችን መርዳት የሕይወት ግፊቶችን የመቆጣጠር አቅም ይሰጠናል። ጠቃሚ እንደሆንንና የምንኖረው ሕይወት ትርጉም እንዳለው እንዲሰማን ያደርጋል። ይህ ስሜት ደግሞ ሰላም እና ጥሩ ጤንነት ያመጣል።

በስሜታዊነት እና በስኬት መካከል ጥብቅ ግንኙነት አለ። ስኬት ምን ያህል ብልህ እንደሆንክ ብቻ አይደለም የሚያሳየው። አንተን ምን ያህል የሚያግዙህ እና በከፍታም ሆነ በዝቅታህ ወቅት በርካታ ሰዎች በዙሪያህ እንዳሉ የሚያሳይ ነው። በሥራ፣ በአመራር እና በንግድ ግንኙነት ወቅት መተሳሰብ መገንባት፣ ሰዎችን ልክ እንደ ራስ ማገዝ በእጅጉ ጠቃሚ ነው። በፎርብስ ላይ የታተመ ዘገባ እንደሚያመለክተው በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች ርህራሄ የሚያሳዩ የአመራር ችሎታቸው ከፍተኛ ነው፤ ርህራሄን የሚያሳዩ መሪዎች ጠንካራ አጋርና ቡድኖችን ይገነባሉ። በሥራቸው የሚገኙ ሠራተኞች የበለጠ ታማኝ፣ ፈጣሪ እና ውጤታማ ናቸው። ይህ የሚያሳየው ሌሎችን መንከባከብ በግል ሕይወት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሙያዊ ሕይወት ውስጥም እንደሚረዳ ነው።

በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከራሳቸው አልፈው ሰዎችን ስለመርዳትና ስለ ርህራሄ የሚማሩ ልጆች በሕይወታቸው ትርጉም ያለው ጊዜንና ስኬትን የሚያገኙ ናቸው። በማንኛውም ማኅበራዊ ግንኙነት ላይ ከሌሎች ጋር በደንብ መስማማት ይችላሉ። ልጆቻችንን መተሳሰብ እና አብሮ መኖርን ማስተማር ደግ እና አሳቢ ማኅበረሰብን ይገነባል። ልጆች ሰዎችን አክባሪ እና ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ያደርጋል።

ለሌሎች መኖር በሕይወት ላይ “እኔ” ብቻ የሚለውን ግለኝነት ማስወገድ እና “እኛ” በሚለው የአብሮነት ተግባር መተካት ነው። እኛ ማለት ከራሳችን ፍላጎት በላይ መመልከት እና የሌሎችን ፍላጎት ማየት ማለት ነው። ጊዜያችንን እና ችሎታችንን ተጠቅመን ሌሎችን ሰው ማድረግ ማለት ነው፤ እኛ ማለት ከራስ ወዳድነት ይልቅ ፍቅርን መምረጥ ማለት ነው።

ይህ የሕይወት መንገድና መርህ መጀመሪያ ላይ ከባድ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ተፈጥሯዊ ማንነታችን ይሆናል። በተለማመድነው መጠን ቀላል ይሆናል። የበለጠ ለሰዎች በኖርንና አጋር በሆንን ቁጥር የተሻለና ትርጉም ያለው ስሜት እንዲኖረን ያደርጋል። ለሌሎች መኖር ራስን መርሳት ማለት አይደለም። በልባችን፣ በእለት ተእለት ኑሯችን ውስጥ ለሌሎች ቦታ መፍጠር ማለት ነው።

እስቲ አንድ ጊዜ ለሰዎች ስለመኖር በኅሊናህ አስተውል። ሁሉም ሰው እርስ በርስ የሚተሳሰብበት ዓለም በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፤ ሰዎች የሚረዳዱበትና የሚያደማመጡበት ዓለም። ያ ዓለም ሰላም፣ ብርታት እና ደስተኝነት የሚያጎናጽፍህ መሆኑን ትጠራጠራለህ? ደግነት እንደ ዘር ነው፤ በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ስንተክለው ያድጋል፤ ወደ ሌሎችም ይተላለፋል። ይህንን ለልጆችህ ማስተማር አለብህ። ልጆች ደግነትን ካሳየናቸው ደግ መሆንን ይማራሉ።

ለዚህ ነው በዙሪያህ ላሉ ሰዎች ችግርና በሕይወት ውስጥ ስለሚያደርጉት ትግል ዓይኖችህን መክፈት ያለብህ። የተቸገረን ሰው ስታይ ርምጃ መውሰድ የሚኖርብህ። በጊዜ ሂደት እነዚህ ድርጊቶች ይለውጡሃል። የበለጠ ሰላማዊ ትሆናለን፤ የበለጠ ፍቅር ይሰማሃል። ሕይወትን በአዲስ መንገድ ማየት ትጀምራለህ። ሕይወት ትርጉም ያለው፣ ደስታ እና ግንኙነትህ የተሟላ ይሆናል። ዞሮ ዞሮ ጥያቄው ከሰዎች መጠበቅ ሳይሆን የምትሰጠው ምንድነው የሚለው ነው። ብቻህን የምትሄድበት የስኬት ርቀት ሳይሆን ማንን ይዘን እየሄድክ ነው የሚለው ነው። እናም ይህ የአብሮነት ጉዞ ከሁሉም የበለጠ ውብ እና ሰላም ያለው መሆኑን አስተውል። ሰላም!!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You