
ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተቀየረች ባለችው ዓለም ውስጥ አእምሮን ለአዳዲስ ሀሳቦች እና እውቀቶች ክፍት ማድረግ የአማራጭ ጉዳይ አይደለም፤ ግዴታም ጭምር ነው። በዓለማችን ላይ ቴክኖሎጂ፣ ሳይንስ፣ ንግድ እና ባሕል በፍጥነት እየተሻሻሉ ይገኛሉ። ከዚህ ለውጥ ጋር እራስን ለማዋሃድ የሰው ልጆች ያለማቋረጥ እንዲማሩ እና እራሳቸውን እንዲያሻሽሉ ይጠበቃሉ።
በቅርቡ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ባወጣው ሪፖርት መሰረት ዛሬ ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሚገቡ ሕጻናት 65 በመቶ የሚሆኑት በወጣትነት እድሜያቸው አሁን በጭራሽ በማናውቃቸው የሥራ ዘርፎች ላይ እንደሚሰማሩ ይጠቁማል። ይህ እውነታ ለአዲስ እውቀት ክፍት ሆኖ መኖር እና ለውጥን የሚሻ አስተሳሰብን ማዳበር ጠቀሜታው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያመለክተናል።
አዳዲስ እውቀቶች ማዳበር አስፈላጊ የሆነውን ያህል ‹‹አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ እንዴት ማዳበር ይችላል? በተለይ በፈጠራና በለውጥ ማዕበል በምትታመሰው ምድራችን ላይ ድርሻችንን አጥተን ወደ ኋላ እንዳንቀር እራሳችንን እንዴት እንለውጣለን?›› የሚል ጥያቄ ሊያጭርብን ይችላል። በዛሬው መጋቢ አዕምሮ አምዳችን ለዚህ ምላሽ ይዘን መጥተናል። በዚህ ዳሰሳ ላይ ግለሰቦችን በተለይም ወጣቶች አእምሯቸውን በእውቀት እንዲያዳብሩ፣ ከአዳዲስ መረጃዎች ጋር መላመድ እንዲችሉ እና ይህንን እውቀት ለግል እና ለሙያዊ ስኬት ሊጠቀሙባቸው የሚችሉበትን ስልቶችን፣ በጥናት በተደገፉ መረጃዎች አዋዝተን እንደሚከተለው ለመመልከት እንወድዳለን።
የማወቅ ጉጉት– የዕድሜ ልክ ትምህርት
የማወቅ ጉጉት ከእያንዳንዱ ታላላቅ ግኝቶች በስተጀርባ ያለ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው። የሰው ልጅ ግዜንና ቦታን መሰረት አድርጎ በነገሮች ላይ የሚመራመርበት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚፈጥርበት ለምድራችን መሻሻል አስተዋፆ የሚያደርግበትን ድንቅ እውቀት የሚያገኘው ለማወቅ ካለው ጉጉት ተነስቶ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የማወቅ ጉጉት መማርን ከማጎልበት በተጨማሪ የማስታወስ ችሎታን ያሻሽላል። ኒውሮን በተባለው ጆርናል ላይ የወጣ አንድ ጥናት ሰዎች ስለ አንድ ነገር የማወቅ ጉጉት ሲኖራቸው አእምሯቸው የበለጠ ለመማር ዝግጁ ይሆናል፤ ረዘም ላለ ጊዜ መረጃን የመያዝ ችሎታንም ያዳብራል።
የማወቅ ጉጉትን እንዴት ማዳበር ይቻላል
የማወቅ ጉጉትን አንድ ወጣት ማዳበር ሲፈልግ በቅድሚያ ጥያቄዎችን ያለማቋረጥ መጠየቅ ይኖርበታል። አዲስ ፅንሰ-ሀሳብ ሲያጋጥሙህ በርእሰ ጉዳዩ ዙሪያ “ለምን? እና እንዴት?” ብለህ ለመጠየቅና ከጀርባ ስላለው ሚስጢር ለመረዳት ሞክር። “እንዴት ሆነ” እና “ ይህ ቢሆንስ?” የሚሉ አመራማሪ ጥያቄዎችን ሳትዘነጋ ደጋግመህ መርመር። በተለያዩ ውይይቶች ውስጥ ተሳተፍ፤ አዳዲስ አመለካከቶችን ለማግኘት ከተለያዩ አካባቢ ከመጡና ልዩ ሙያ ካላቸው ሰዎች ጋር ውይይቶችን አድርግ።
አዲስ እውቀትን ለማግኘት ያልታወቁ ነገሮችን የማሰስ ልምድ ይኑርህ። መጽሃፎች አንብብ፣ ዘጋቢ ፊልሞችን ተመልከት፤ ለአዳዲስ ሀሳቦች ወደሚያጋልጡህ ቦታዎች ጉዞ አድርግ። የማወቅ ጉጉትን ማጎልበት አንጎልህ የበለጠ አዳዲስ ክስተቶችን እንዲላመድ እና ለአዲስ መረጃ ክፍት እንዲሆን ያበረታታል።
ማንበብ እና አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅ የማሰስ ፍላጎት በጣም የተሳካላቸው ሰዎች ልማድ ነው። ብዙዎቹ የዓለማችን በጣም ስኬታማ ሰዎች ስኬቶቻቸውን ያገኙት በማንበብ ነው። በጣም ስኬታማ ከሆኑ ባለሀብቶች አንዱ የሆነው ዋረን ባፌት 80 በመቶ የሚሆነውን እያንዳንዱን ቀን በንባብ ያሳልፋል። የማይክሮሶፍት መስራች የሆነው ቢል ጌትስ በዓመት 50 መጽሃፎችን ያነባል። ከእነዚህ ሰዎች ብዙ መማር ትችላለህ።
ማንበብ እውቀትን ያሰፋል። መጽሃፎች፣ መጣጥፎች እና ትምህርታዊ መጽሔቶች ካለህበትና ከምታውቀው እውነታ እና ከአካባቢህ እውቀቶች በላይ ለሆኑ መረጃዎች ያጋልጡሀል። አስተሳሰብህን ያሻሽላል፤ የተለያዩ አመለካከቶች የሚያሳዩ መጽሐፍትን ማንበብ የራስህን ምልከታ እንዲሁም አስተያየት እንድትመረምር እድል ይሰጥሀል።
ልዩ ልዩ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ንባብ ፈጠራን ያሳድጋል። ለመሆኑ ምን አይነት መጽሐፍትን ምን ማንበብ ለአዳዲስ እውቀቶች እራስህን እንድታዘጋጅ ይረዳህ ይሆን?
በዚህ ፈጣን ለውጥ በሚታይበት ዓለም ላይ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ይዘት ያላቸው መፅሀፍት ማንበብ በቀላሉ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እንድትዋሀድ ያግዝሀል።
የእለት ከእለት ሕይወትህን የሚያቀልሉ ቴክኖሎጂዎች ጋር በቀላሉ እንድትግባባና ሥራህን እንድታቀላጥፍ ያግዝሀል። ሌላው ታሪክ እና ባሕል ነክ መጽሐፍት ናቸው። በእነዚህ መጽሐፍት ውስጥ ስላለፉት ክስተቶች እና ዓለም አቀፍ የሆኑ ብዝሀ ባሕሎች ለመማር እና ምልከታህን ለማስፋት እነዚህን ማንበብ ምርጫህ ማድረግ ይኖርብሀል። ንግድ እና ኢኮኖሚክስ ጽንሰ ሀሳቦችን የያዙ መፅሀፍትም እንዲሁ ምንም እንኳን በንግድ ሥራ ላይ ባትሆንም የየእለት ኑሮህ ጋር ግንኙነት ካላቸው ጉዳዮች ጋር በቀላሉ እንድትግባባ ይረዳሃል፤ ወደ ንግዱ ዓለም ከገባህም ጥልቅ እውቀትና የመወሰን አቅም ይሰጥሀል።
አእምሮዎን ከአዳዲስ ሀሳቦች ጋር ለማያያዝ ማንበብ ፍቱን መድሀኒት ነው። እመነኝ በብዙዎች ዝቅተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነገር ግን እራስህን ለመለወጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለው አማራጭ መንገድ ነው። ስለዚህ ሳትግደረደር እራስህን ለንባብ አዘጋጅ።
የተለያዩ አመለካከቶችን የመረዳት ጥበብ
ለአዳዲስ እውቀቶች ክፍት መሆን ማለት ሁሉንም ነገር ማግበስበስና ባገኘኸው ነገር ሁሉ መስማማት ማለት አይደለም፤ ዝግጁነትህ የሚያሳየው ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆንህን እና ለሌሎች አመለካከቶች ለማወቅ ራስህን ማዘጋጀት ማለት ነው። በመሆኑም አመለካከቶችህን ለማስፋትና የመረዳት ክህሎትህን ለማሻሻል ሁሌም ዝግጁ ሁን። በሃርቫርድ ቢዝነስ ሪቪው የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያካትቱና በስራዎቻቸው ላይ የሚያበረታቱ ድርጅቶች 87 በመቶ የተሻሉ ውጤቶችና ስኬታማ ውሳኔዎችን ያደርጋሉ። አንተስ? በሕይወትህ ውጤታማ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምን ያህል የተለያዩ አመለካከቶችን ለመያዝ ትሞክራለህ?
የማዳመጥ ክሕሎት አዳብር
እውቀትንና መረዳትን ለማዳበር አንዱ መንገድ የማዳመጥ ችሎታን ማዳበር ነው። በመሆኑም አንተም ንቁ ማዳመጥን ችሎታህን ለማሳደግ ጥረት አድርግ። በውይይት ወቅት የአንተን ምላሽ ከማሰብ ይልቅ ተናጋሪው በሚናገረው ላይ አተኩረህ ሁሌም አዳምጥ። ግብዝ ፍርድን አስወግድ፤ በተከፈተ ልብ አዳምጥ፣ ምንም እንኳን አመለካከቱ ከአንተ የተለየ ቢሆንም በጥሞና ሀሳቡን እስኪጨርስ አዳምጥ። ይህ አመለካከትህንና እውቀትህን የሚያሰፉ መረጃዎችን ለማግኘት ያግዝሀል።
ለዚህ ነው ትርጉም ባላቸው ውይይቶች ውስጥ ለመሳተፍና በንቃት ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን ያለብህ። ይህ ማለት ግን የተባለውንም ሆነ የተነገረውን ሁሉ ተቀበል አይደለም፤ ሁሌም ከማዳመጥ በኋላ ሀሳቦችን በራስህ እውነት ከመሞገት አትቦዝን። ምክንያቱም ታላላቅ መሪዎች እና የሥራ ፈጣሪዎች ከሚናገሩት በላይ ያዳምጣሉ። ለዚህ ነው አንተም የተለያዩ አመለካከቶችን በትክክል በመረዳት፣ እራስህን ለአዲስ የአስተሳሰብ በማዘጋጀት እድሎችን መክፈት የሚጠበቅብህ።
አዳዲስ ነገሮችን መሞከር–ከምቾትህ ውጣ
ሁሌም እድገት ያለው ከምቾት ዞን ውጭ መሆኑን ልብ በል። ብዙ ሰዎች ውድቀትን በመፍራት ለውጥን ይሸሻሉ። ነገር ግን በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ራሳቸውን አዘውትረው ለአዳዲስ ነገር የሚያዘጋጁና ሁሌም ፈተና የሚወዱ ሰዎች “የእድገት አስተሳሰብ” አላቸው በቶሎም ወደሚፈልጉት ስኬት ይደርሳሉ። ታዲያ እንዴት ነው አንተም ከምቾት ከባቢህ የምትወጣው?
ለዚህ ቀላል ምላሽ አለኝ። አዲስ ክህሎቶችን ተማር፤ ሶፍትዌር ለመገንባት፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማምረት፣ የማሕበረሰብ ችግር የሚፈቱ ፈጠራዎችን ለመስራት ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ በአደባባይ በመናገር ሰዎችን ማሳመን የሚያስችል የንግግር ክህሎት ማዳበርም ይሆናል። ስለዚህ ከምቾት ከባቢህ ወጥተህ እነዚህን እውቀቶች ለመማር ዝግጁ ሁን። ሌላው በማታውቃቸው ልምዶች ውስጥ መሳተፍ ይኖርብሀል። ለምሳሌ ጉዞ አድርግ፣ አዲስ ምግቦችን ሞክር፣ ወይም የተለየ ማሕበረሰብ ባሕልን ለማወቅ እራስህን አዘጋጅ።
ብዙዎች ውድቀትን ይፈራሉ። በተለይ ውድቀት ለትችት እንዳያጋልጣቸው ይጠነቀቃሉ። ነገር ግን ውድቀትን እንደመማሪያ መሳሪያ ነው። ማንኛውም ውድቀት የመሻሻል እድል ይፈጥራል። ለዚህ ነው ከምቾት ከባቢህ ወጥተህ በድፍረት አዲስ ነገር መሞከር የሚኖርብህ። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ብዙውን ጊዜ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ለመቆየት እራሳቸውን ዝግጁ የሚያደርጉ ሰዎች የበለጠ ውጤት ያገኛሉ።
በጣም ስኬታማ ሰዎች ለውጥን በፍጥነት የሚላመዱ ናቸው። እንደ ኔትፍሊክስ እና አማዞን ያሉ ኩባንያዎች ያለማቋረጥ አዳዲስ ነገሮችን ስለሚፈጥሩ ያድጋሉ። የግዴታ ግለሰቦች አንድ ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ የለባቸውም። አንተም እራስህን ለአዲስ እና ልዩ ነገር አዘጋጅ። ከለውጥ ጋር ለመላመድ ደግሞ የሚከተሉትን መንገዶች ተከተል።
ሁሌም ከዘመኑ ጋር ተራመድ፤ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ለውጦችን እና የቴክኖሎጂ እድገቶችን ተከታተል። እራስህን ከሁኔታዎች ጋር የሚያላምድና ተለዋዋጭ ሁን። ለውጥ የማይቀር መሆኑን ተቀበል። ሁሌም መማርህን ቀጥል፤ አሁን ዘመኑ ቀላል አማራጭ ይዞ ከተፍ ብሏል። የኦላይን ኮርሶችን ተከታተል፣ ሴሚናሮች ላይ ተሳተፍ። ለውጥን የመላመድ ባህሪን ማዳበር ያለማቋረጥ ተቀያያሪ በሆነችው ዓለም ውስጥ ተፎካካሪና ስኬታማ ሆነህ እንድትቆይ ያግዝሀል።
እውቀትህን ተግብር
እውቀት ብቻውን ‹‹የአባ እከሌ ልጅ›› አያሰኝም። ማወቅህ ብቻ ስኬት ላይ አያደርስህም። አብሮት ተግባር መኖር አለበት። ለዚህ ነው እውቀት ብቻውን በቂ አይደለም የምልህ። ብዙ ሰዎች መጽሐፍትን ያነባሉ፣ ሴሚናሮችን ይሳተፋሉ ነገር ግን የተማሩትን ፈጽሞ በሕይወታቸው ላይ ተግባራዊ አያደርጉትም። በተሳካላቸው እና ስኬትን በተራቡት መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት የተግባር ነው። ለዚህ ነው በዚህ ፈጣን ዓለም ያከማቸኸውን የእውቀት ኃይል ለለውጥህ ኃይል እንዲሆን ተግባር ላይ ማዋል ያለብህ። የተማርከውን አዳዲስ እውቀት ግቦችን አውጥተህ ወደ ተግባር መቀየር ትችላለህ። መጀመሪያ ሙከራ አድርግ ውጤት ካሳየህ በሙሉ አቅምህ ግባበት
እውቀትህንና ተግባርህ ሌሎችን አስተምር። ይህንን ማድረግህ ወዳጆችህን ብቻ አይጠቅምም እውቀትን ማካፈል ለራስ መማርን ያጠናክራል፤ የበለጠ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲኖርህ ያደርጋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንዲሆን እንዳትጠብቅ። አዳዲስ ሀሳቦችን እና እውቀቶችን ስትቀበል በዙሪያህ ያሉ ሰዎች ተጽእኖ ሊያሳድሩብህ፣ ሊተቹህና ሀሳብህን ውድቅ ሊያደርጉ ይችላሉ። ስለዚህ ይህንን ተግዳሮት መጋፈጥ ይኖርብሀል።
አእምሮህን ለአዳዲስ ሀሳቦች እና እውቀቶች ክፍት ማድረግ የአንድ ጊዜ ሥራ አይደለም፤ የሕይወት ዘመን ጉዞ ነው። ብዙ በተማርክ ቁጥር ለራስህ ብዙ እድሎችን እንደምትፈጥር እወቅ። የማወቅ ጉጉት፣ ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ ሂስ አለመፍራትንና አዳዲስ አመለካከትና አስተሳሰብ መላመድ በፍጥነት እየተቀየረች ባለችው ዓለም ውስጥ የማይበገር ችሎታ እንዲኖርህ ባለ እድል ያደርግሀል። አልበርት አንስታይን በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር ‹‹የአእምሯዊ እድገት የሚጀምረው ስንወለድ ነው የሚያበቃውም ስንሞት ብቻ ነው። መማርህን ቀጥል፣ ጥያቄ ጠይቅ እና ማደግህንና ለውጥህን አታቋርጥ። የወደፊት ዕጣህ በእሱ ላይ የተመሰረተ ነው›› የሳምንት ሰው ይበለን። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም