ቅናት የሳለው ሰይፍ

ሮባ አበበ እና ባለቤቱ ካሳነሽ ሙላት ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ለዓመታት ያድርጉ እንጂ ትውውቃቸው በዚያ በተወለዱበት የወንዶ ገነት አነስተኛ ከተማ ነው:: ሮባ በአስተዳደር ሥራ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን ባለቤቱ ካሳነሽ በወንዶ ገነት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎችን የሳይንስ ትምህርት ዓይነት መምህርት ናት::

ሮባ ከሌላ ትምህርት ቤት በዝውውር እሷ የምታስተምርበት ትምህርት ቤት ሥራውን ሲጀምር ሊተዋወቁ ችለዋል:: ካሳነሽ በቀላሉ ከሰው ጋር የምትግባባ እና በትምህርት ቤት ውስጥ ረጅም ዓመት ያስቆጠረች በመሆኗ ከብዙዎች ተማሪዎች ጋርም ሆነ መምህራን ጋር ጥሩ የሚባል ተግባቦት ያላት ናት:: በባህሪዋም በብዙ ተማሪዎች ዘንድ ተወዳጅ ናት::

መምህር ሮባም ወደዚህ ትምህርት ቤት ሲመጣ ቀድመው ዓይኑ ውስጥ ከገቡ የሥራ ባልደረቦቹ ውስጥ የመጀመሪያዋ ናት:: ከሁሉ ጋር ተግባቢነቷን፣ ተጫዋችነቷ ለእሱም በእንኳን ደህና መጣህ መልኩ ስላጋራቸው አዲሱን የሥራ ቦታውን በይበልጥ እንዲለምደው እና እንዲወደው አድርጋዋለች::

አቶ ሮባ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚማረውን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ እንዲያመቸው ወደ ወንዶ ገነት ትምህርት ቤት የሥራ ቦታ ዝውውር ጠይቆ ሊመጣ ችሏል:: ሕይወት በትምህርት ቤት ውስጥ ቀጠለ፤ ሮባም ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተዋውቆ እና የሥራ ባሕሉን ተላምዶ ሥራውን፣ ትምህርቱን እና ሕይወቱን አብሮ ማስኬድ ጀመረ::

በጊዜ ሂደትም ከትምህርት ቤቱ ድምቀት ከሆነቸው ካሳነሽ ጋር ይበልጥ መግባባት እና አብረው ጊዜ ማሳለፍ ጀመሩ:: ሮባ ከሰዎች ጋር ለመግባባትም ቢሆን ያን ያህል የሚከብድ ባሕሪ ያለው አይደለም፤ ይልቁንስ በቶሎ የሚቆጣ እና ግልጽ በመሆኑ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር በሚኖረው ጊዜ በሚሰነዝራቸው ሃሳቦች እና በሚፈጥራቸው ጨዋታዎች ከሰዎች ጋር ጥሩ መግባባትን ፈጥሯል::

ከሥራው ባሻገር የልብ ጓደኛው አደረጋት ቢሆንም የእሱም ሆነ የሌሎች ዓይን ያረፈባትን መምህርት ካሳነሽን ከጓደኝነት ባለፈ ማንም ሳይቀድመው የራሱ ሊያደርጋት አስቧል፤ በማሰብ እና በማሰላሰል ጊዜ ማጥፋት ባለመፈለጉም ጥያቄውን አቅርቦ የፍቅር ጥያቄ ብቻም ሳይሆን በትዳር አብረን እንኑር ጥያቄም ጭምር አቅርቧል::

መምህርቷም እንደወጉ ላስብበት የሚል ምላሹዋን ከሰጠችው በኋላ መልሷን በእሺታ ገልጻለታለች:: ጓደኝነታቸውና የሥራ ባልደረቦች መሆናቸው ወደ ፍቅር ግንኙነት ሲቀየር አብረው በትዳር ለመኖር ያሰቡት ፈጥነው ነበር:: ይህም በብዙዎች ወዳጆቻችው ዘንድ ጥያቄና ትችትን ያስነሳ ነበር:: ሮባ እና ካሳነሽ በቅርብ ያሉ ጥያቄዎችን በመመለስ የሩቅ ትችቶችን እንዲሁ ችላ ብሎ በማለፍ ቀጣይ ሕይወታቸውን በመነጋገር እና በማቀድ አነስተኛ የሠርግ ፕሮግራም አድርገው አዲስ ጎጇቸውን መመሥረት ችለዋል:: አዲስ ሙሽራ በመሆናቸው የእንኳን ደስ አላችሁና የመልካም ትዳር ምኞት ተቀብለው ሕይወታቸውን መምራት ጀመሩ::

የካሳነሽ ባለቤት ሮባ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪውን ካጠናቀቀ በኋላ ትምህርቱ በፈጠረለት እድል አማካኝነት አዲስ የሥራ ቦታ በአዲስ አበባ በማግኘቱ ባለትዳሮቹ አስበውና ወስነው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሕይወትን እንደ አዲስ ጀመሩ::

ሮባ ባገኘው የሥራ እድል በአንድ ቢሮ ውስጥ በአስተዳደር ሥራ ዘርፍ ላይ ሥራውን ጀመረ:: ባለቤቱ ካሳነሽም ጥቂት ጊዜ አካባቢውን ለመልመድ ጥረት ካደረገች በኋላ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ሥራ ለማግኘት ቻለች:: በዚያም የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን የማስተማር ኃላፊነት ተሰጥቷት ሥራዋን ቀጠለች:: አሁን ላይ እሷም ሆነ ባለቤቷ እንደ ከዚህ ቀደሙ አብረው አይውሉም የሚገናኙትም ማታ ከሥራ መልስ ሆኗል:: ነገር ግን ሮባ የመምህርነት ሙያውን ባለመልቀቁ ባለቤቱ በምታስተምርበት ትምህርት ቤት ውስጥ በትርፍ ሰዓት በማስተማር ሥራ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበትን መንገድ ፈጥሯል:: በዚያ ሲሄድም ባለቤቱን የመመልከት እድል አለው:: መምህርት ካሳነሽ እንደ ሁልጊዜዋ ተጨዋችና ተግባቢ በመሆኗ የሥራ ቦታዋን ለመልመድም ሆነ ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር ለመግባባት ጊዜ አልወሰደባትም::

አንዳንድ ጭምጭምታ

የካሳነሽ ባለቤት ሮባ በባሕሪው ቶሎ ቁጡ እና ስሜቱን መደበቅ የማይችል በመሆኑ የሰማውን ፊት ለፊት የሚናገር ሰው ነው:: ባለቤቱ መምህርት ካሳነሽ ይህ ባሕሪው እሷ በትዕግስት እና ባላት ችግሮችን በቶሎ የመፍታት ችሎታ በመጠቀም ታረግበዋለች:: ከጊዜ በኋላ ግን ይህ ባሕሪው በቶሎ ቁጡ ከመሆኑ ወደ ንጭንጭ እና ምክንያት የለሽ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ተናዳጅ ሲሆን እየተመለከተችው ነው:: ችግሩን ለመፍታት አንዳንዴ ዝምታ፣ አንዳንዴም ነገሮችን ወደ ፍቅር በመቀየር ለማግባባት ብትሞክርም ባስ ያለ ቀን ሲመጣ ደግሞ ጉዳዩን በንግግር ለመፍታት ቁጭ ብለው እንዲነጋገሩ ታደርጋለች::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሮባን እያናደደው የመጣወ ጉዳይ ካሳነሽ ከሰዎች ጋር ያላት ተግባቦት ቅናት ቢጤ እያሳደረበት መጥቷል:: ካሳነሽ በምትሠራበት ትምህርት ቤት ውስጥ አብዛኛዎቹ መምህራን ወንዶች በመሆናቸው ባለቤቱ ካሳነሽም ከሥራ ውጭ ያለ የምሳ ሰዓት እና የሻይ እረፍቷን የምታሳልፈው ከእነዚሁ የሥራ ባልደረቦቿ ጋር ነው:: በሳምንት ውስጥ አንድና ሁለት ክፍለ ጊዜን ወስዶ በትርፍ ሰዓቱ ለማስተማር ባለቤቱ ወዳለችበት ትምህርት ቤት የሚያመራው ሮባ ባለቤቱን ሲያገኛት አብረዋት ለሚሠሩ መምህራን መልካም አመለካከት የለውም:: ይህ ባሕሪው ፊት ለፊት የሚታይ በመሆኑም ካሳነሽን ምቾት የሚነሳት ጉዳይ ከሆነ ውሎ ሰነባብቷል::

ችግሩን ለመፍታት እና ካሳነሽ የባለቤቷ ቅናት ከምን የመነጨ እንደሆነ ለማወቅ እና ጉዳዩ ትክክል እንዳልሆነ ለማድረግ ብትጥርም ችግሩ ግን የሚቀረፍ አልሆነም:: ለማስተማር በሚመጣበት ወቅት አብሯት አንድ ጠረጴዛ ከሚጋራው የሥራ ባልደረባዋ መምህር ናኔሳ በመጥፎ ዓይን ሲተያዩ ታስተውላለች:: ባለቤቷ በምናቡ በፈጠረው ነገር ምክንያት ያደረበት ስሜት እና የሚያሳየው መጥፎ ባሕሪም እሷን ማሸማቀቁ አልቀረም::

ታዲያ ችግሩን ለመፍታት በቤታቸው በሚነጋገሩበት ጊዜ ካሳነሽ ከባለቤቷ ያልጠበቀችው ጥያቄ መጣላት ሥራዋን እንድታቆም እና ሌላ ሥራ እንደሚፈልግላት ነበር:: ይህ ካሳነሽ ፍጹም የማትቀበለው እና ያናደዳት ጉዳይ ነበር:: በዚህ ሃሳብ ሳይስማሙም ንግግራቸውን ቋጭተው ጠዋት ወደ ሥራ ለመሄድ ተነሱ፤ ነገር ግን ባለቤቷ ሮቤ ያለወትሮው በጠዋት ነበር ከቤቱ የወጣው፤ ካሳነሽም ሰዓቷ ሲደርስ ወደምታስተምርበት ትምህርት ቤት ቀጣዩ ጉዳይ ምን ሊሆን እንደሚችልና መፍትሔውን በማሰብ አቀናች::

ያልታሰበ ዱብ እዳ

ትምህርት ቤቱ በር ላይ ግርግሮች ይስተዋላሉ:: ወደ ውስጥ እየዘለቀች ስትሄድ የጸጥታ አካላት ባለቤቷን ይዘውት ከግቢው ሲወጡ አየች:: ምን እንደተፈጠረ ያልገባት መምህርት ጉዳዩን ለማጣራት ባለቤቷን ትጠይቀዋለች:: በተደጋጋሚ የሚያስረዳትን ሰው ብትፈልግም ማግኘት አልቻለችም:: ነገር ግን በአጠገቧ እሷን ለማረጋጋት ከሚጥሩ ሰዎች እና በዙሪያዋ ከሚንሸኳሸኩ ሰዎች ባለቤቷ የሥራ ባልደረባዋን ከባለቤቴ ጋር ግንኙነት አለህ በማለት በስለት ወግቶ ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጉን ሰማች:: ካሳነሽ ባለቤቴን አውቀዋለሁ ብትልም እንደዚህ ዓይነት ሰው መሆኑን ግን ፈጽሞ አታውቅም ነበር::

ጉዳዩ ያልገመተችው ጉዳይ በመሆኑም ምን ምላሽ መስጠት እንዳለባትም አላወቀችም:: ተከትላው ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመራች::

የወንጀል ምርመራ

ፖሊስ በደረሰው መረጃ መሠረት በቦታው ተገኝቶ በቁጥጥር ሥራ በማዋል ጉዳዩን የማጣራት ሥራውን ጀምሯል:: አቶ ሮባ አበበ ባደረሰው ጉዳት የሰው ሕይወት እንዲልፍ ያደረገ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቷል:: ምርመራውንም ቀጥሏል::

ዐቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ ሮባ አበበ የተባለው ተከሳሽ በተለያየ 3 ክሶች የተከሰሰ ሲሆን በአንደኛ ክሱ ላይ ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት ከ25 ላይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ጎፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመምህራን ማረፊያ ክፍል ውስጥ ሟች ናኔሳ በሻዳ የተባለውን ግለሰብ ከሚስቴ ጋር ግንኙነት አለህ በማለት ቂም በመያዝ የተለያዩ የስለት ዓይነቶች ባሉት ስለታማዋ ቢላዋ ሟችን በስለት በመውጋት ጉዳት በማድረሱ ምክንያት ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል::

በመሆኑም ተከሳሽ ሮባ አበበ በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል፤ እና በተመሳሳይ በ2ኛ እና በ3ኛ ክሱ ላይም ተከሳሽ በያዘው ስለት በመውጋት በሁለት ግለሰቦች ላይ ጉዳት ያደረሰባቸው በመሆኑ በፈፀመው ተራ የሆነ የሰው ግድያ ሙከራ ወንጀል በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው ወንጀል ክስ አቅርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል::

በክርክሩ ወቅትም ዐቃቤ ሕግን ክሴን ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በቦታው የነበሩ ምስክሮች፣ የሟች አስከሬን የምርመራ ውጤት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንዬም ሜዲካል ኮሌጅ በማቅረብ ጥፋተኛ ብሎታል::

ውሳኔ

ተከሳሽ ሮባ አበበ ከሚስቴ ጋር ግንኙነት አለህ በማለት ቂም በመያዝ ናንሴ በሻዳ የተባለን ግለሰብ በስለት በመውጋት ሕይወቱ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ እና ሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረሱ በፍርድ ቤት በቀረበበት ክስ ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል፡፡ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት ከጥፋቱ እንዲማር እና ሌሎችን ሊያስተምር ይችላል በሚል የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You