በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና ችግር ሲያገጥማቸው ወደ ሐኪም ቤት ሄደው መታከም አይችሉም። ከፍተኛ ህመም ከገጠማቸውማ የሚሞቱበትን ጊዜ ከመቁጠር ውጭ ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም። እንዲያም ሆኖ ግን በጤና መድህን አገልግሎት አማካኝነት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚያገኙት ገቢ ላይ በመጠኑ በመቆጠብ ህመም ሲያጋጥማቸው ወደ ሐኪም ቤት ሄደው የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን ችለዋል። ይህ ለእነርሱ ጥሩ እፎይታን የፈጠረ ቢሆንም ከፍተኛ ምርመራ የሚጠይቁ ህመሞች ሲያጋጥሟቸው ግን አሁንም መቸገራቸው አልቀረም።
በተለይ እንደ ሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ፣ አልትራሳውንድ፣ ራጅና ሌሎችም መሰል ምርመራዎችን በአቅም ውስንነት ምክንያት ለማድረግ ሲቸገሩ ይስተዋላል። ይህን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ነው ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ላለፉት አስራ አራት ዓመታት ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› በሚል መሪ ሃሳብ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የሕክምና ምርመራ አገልግሎት ዘመቻ ሲያካሄድ የቆየው። አልፎ አልፎም በምርመራ ውጤት ለሚገኙ ህመሞች ሕክምናና መድኃኒት ለህሙማን እስከ ማቅረብ የሚደርስ ሥራ አከናውኗል። ይህም ህብረተሰብን የማገልገል ትልቅ ተግባር ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ጊዚያት ወደ ድርጅቱ ከሚመጡ ተገልጋዮች መክፈል ያልቻሉ ታካሚዎችን በመለየት አገልግሎቱን በነፃ እንዲገኙ አድርጓል። ባለፉት አሥራ አራት ዓመታትም በ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› የሕክምና ምርመራ አገልግሎት ዘመቻ እስካሁን ድረስ ከ54 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የነፃ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።
በሌላ በኩል ማዕከሉ ድንገተኛ አደጋ ለደረሰባቸው ወገኖች አምቡላንሶችን በመላክና ተጎጂዎችን ወደ ሕክምና ተቋም በማድረስ ከተጎጂዎች ጎን በመቆም ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ማዕከሉ በሚገኝበት አራዳ ክፍለ ከተማ ላሉ ነዋሪዎች መታወቂያቸውን በማየት ብቻ ለምርመራ ሲመጡ በፐርሰንት ቅናሽ በማድረግ የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል። ዘንድሮም 15ኛ ዓመቱን በማስመልከት አምስቱን የጳጉሜን ቀናት የነፃ ምርመራ ዘመቻን ጨምሮ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትን ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ ገብቷል። በዚህ ዘመቻም ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ ዜጎች የሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ፣ አልትራሳውንድ፣ ላብራቶሪና ሌሎች አገልግሎቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኃይሉ እንደሚናገሩት ማዕከሉ የተሟላ የዲያግኖስቲክ ኢሜጂንግ አገልግሎት፣ አድቫንስድ ከላብራቶሪና ፓቶሎጂ አገልግሎት እንዲሁም የጋስትሮኢንትሎጂ፣ ዩሮሎጂና ካርዲዮሎጂ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል። እነዚህን አገልግሎቶችንም ነው ‹‹በጳጉሜን ለጤና›› የምርመራ ዘመቻ ዝቀተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በነፃ የሚያቀርበው። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ሊያገኙ የሚችሉትም በቅድሚያ 9888፣ 0940040404 ወይም 0940050505 ስልክ ቁጥሮች ደውሎ በመመዝገብ ነው።
አገልግሎቱን ፈልገው ለምርመራ የሚመጡ ሰዎች ከመንግሥት መሥሪያ ቤት ቢሆን ዘመቻው ትክክለኛ አላማውን ማሳካት ይችላል። ምክንያቱም የጳጉሜን ለጤና ዘመቻ ዋነኛ አላማ ነፃ ምርመራ ማድረግ ብቻ ሳይሆን አቅም የሌላቸው ነገር ግን የሲቲ ስካን፣ ኤም አር አይ፣ አልትራ ሳውንድና የተለያዩ የላብራቶሪ ምርመራዎች የጂ አይ ኮሎኖስኮፒና ኢንዶስኮፒ ምርመራዎች ለሚያስፈልጋቸው ለማድረስ ነው።
እንደ አቶ ዳዊት ማብራሪያ የጳጉሜን ለጤና የምርመራ ዘመቻ የተጀመረው ማዕከሉ ገና እንደተመሰረተ ከዛሬ አስራ አራት ዓመት በፊት ነው። የዘንድሮው ደግሞ አስራ አምስተኛ ዓመት ዘመቻ ነው። በወቅቱ ማዕከሉ ይህን በጎ ተግባር ያኔ የጀመረው ገና በደንብ ሳይቋቋምና በእጁ ላይ በቂ ገንዘብ ሳይኖረው ነው። ዘንድሮ ይህ ዘመቻ ለአስራ አምስተኛ ጊዜ ሲደረግ ሌሎች በጎ ተግባራቶችም ተካተው ነው። ከጳጉሜን አንድ እስከ አምስት ድረስ ማዕከሉ የሚሰጣቸውን ምርመራ አገልግሎቶች ሁሉ በነፃ ይሰጣል።
ከዚህ ውጭ ግን ማዕከሉ ሌሎች የበጎ ሥራዎችን ያከናውናል። ለምሳሌ በዘንድሮው ዓመት ለተቸገሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ብርድ ልብስ ያበረክታል። የዓይን ምርመራና ሕክምና የሚያደርግበትና መነጽርና መድኃኒት የሚሰጥበት መርሃ ግብርም አለው። በካንሰር ከተጠቁ ወገኖች ጋር ማሳለፍ ፕሮግራምም ይዟል። ሌሎች በጎ ሥራዎችንም ያከናውናል። ማዕከሉ ከሚሰጠው ነፃ የምርመራ አገልግሎት በተጨማሪ በሌሎች የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ የተሰማራው ጳጉሜን ለጤና የሚለውን መርህን ይበልጥ አስፍቶ ለማስቀጠል ነው።
የጳጉሜን ወር በጎ በጎ ነገሮች የሚሸተቱበት፣ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ዓመት ሽግግር የሚደረግበት፣ አዲስ እቅድ የሚያዝበት፣ ከመጥፎ ሱስ እውጣለሁ ብለው ቃል የሚገቡበት፣ አገባለሁ፤ እወልዳለሁ የሚሉበት፣ እማራለሁ የሚሉበት ነው። ከዚህ አንፃር ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል በየዓመቱ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ ምርመራ እንዲያገኙ በማድረግ በጎ ተግባር ይፈፅማል። ይህ በጎ ተግባር ሌሎችም በየራሳቸው እንዲፈፅሙ የሚያነሳሳም ነው።
ከጳጉሜን 1 እስከ 5/2016 ዓ.ም በሚካሄደው የጳጉሜን ለጤና የምርመራ ዘመቻ ከዚህ በፊት ከነበረው ልምድ በመነሳት አምና የተመረመረውን 1 ሺ 500 ሰው ዘንድሮም ከዚህም በላይ ቁጥሩን በማሳደግ እስከ 2 ሺ ሰው ለመመርመር ዕቅድ ተይዟል። ነገር ግን ሰዎች ምዝገባውን አካሂደው እንደ ኬዛቸው አስቸኳይነት ለምርመራ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ይደረጋል። ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን ደግሞ ከጳጉሜም አልፎ እስከ ታኅሣሥ ድረስ ምርመራቸው ሊካሄድ ይችላል። ስለዚህ ሰዎቹ ተመዝገበው በየወረፋቸው ነፃ የምርመራ አገልግሎቱን ያገኛሉ። አገልግሎቱም በአዲስ አበባ በማዕከሉ በሚገኙ ሰባት ቅርንጫፎች ላይ ይሰጣል። በዋናነት ግን አገልግሎቱ በወዳጅነት ፓርክ ጀርባ በሚገኙ የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ይሰጣል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ማዕከሉ በዚህ ዓመት ሰዎች አስቀድመው ጤንነታቸውን እንዲያውቁ ሶስት ዋና ዋና የጤና ጥቅሎችን አዘጋጅቷል። እነዚህ የጤና ጥቅሎች አንደኛው ለጤናዎ ይነሳሱ/be motivated/፣ ሁለተኛው ጤናዎን ያረጋግጡ/be reassured/ እና ሶስተኛው ለጤናዎ ይቅደሙ/be ahead/ የሚሉ ናቸው። እነዚህ የጤና ጥቅሎች አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ጤነኛ እያለ በራሱ ተነሳሽነት ጤናውን በየጊዜው እንዲያረጋግጥ የሚያስችሉ፣ ምንም ነገር ከመጀመሩ በፊት በቤተሰብ ውስጥ የነበሩ የጤና ችግሮች ካወቁ በኋላ እነዚህን በሽታዎች ለመመርመር የሚረዱና በመጨረሻ የጤና እክሎች ከመከሰታቸው በፊት ትንንሽ ችግሮችን በማየት እነዛን ችግሮች ቀድሞ በመንቃት ምርመራዎችን ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።
የራዲዮሎጂ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ተስፋዬ ከበደ በበኩላቸው እንደሚሉት ማዕከሉ ይህን ነፃ የምርመራ እድል ሲያመቻች በምርመራ ወቅት ጨረር የሚያመነጩ መሳሪያዎች ስለሚኖሩና ሁልጊዜ ደግሞ ምርመራ የራሱ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ያለው በመሆኑ ይህን ከግምት ውስጥ አስገብተው ወደ ምርመራ ቦታ መምጣት ይጠበቅባቸዋል። ለአብነት ሲቲ ስካንና ኤክስሬ ጨረር የሚያመነጩ መሳሪያዎች ናቸው። ሐኪም ምርመራው ያስፈልጋል ብሎ ፅፎ ካላዘዘ በስተቀር ሰዎች መጥተው ጤንነታችንን ማወቅ እንፈለጋለን ብለው ሊመረመሩ አይገባም።
ስለዚህ የሲ ቲ እስካንና የኤክስሬ ምርመራ ለማድረግ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ሰዎች ከሐኪም የታዘዘ ወረቀት ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል። አልትራሳውንድ፣ ኤም አር አይ፣ ኮሎኖስኮፒ፣ ላብራቶሪ ምርመራ ፈልገው ሰዎች ወደ ማዕከሉ ቢመጡ ሊሰራላቸው ይችላል። አቅም ሳይኖራቸው በሐኪም የታዘዘ ወረቀት ይዘው ወደ ማዕከሉ መጥተው ግን ሲቲ ስካን ወይም ኤክስሬይ መነሳት ለአደጋ ሊያጋልጣቸው ስለሚችል ለመመርመር የሚመጡ ሰዎች ይህን መገንዘብ ይኖርባቸዋል።
በተለይ ሕፃናትና ነብሰ ጡሮች በጣም አስፈላጊ ካልሆነና በሐኪም ካልታዘዘ በስተቀር ጨረር ከሚያመነጩ መሳሪያዎች መራቅ ወይም ባይጠቀሙ ይመረጣል። ህብረተሰቡ ቢችል ከሐኪም የታዘዘ ወረቀት ይዞ መምጣት የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ምርመራ ቦታ ላይ ያለውን የህክምና ባለሞያ ማማከርም ያስፈልጋል። አንዳንድ ሴቶች ነብሰ ጡር መሆናቸውን የሚጠራጠሩ ከሆነ ለሐኪም መንገር ተገቢ ነው። የኤም አር አይ ምርመራዎች ማግኔት ያላቸውና ብረት ነገሮችን የሚስቡ በመሆናቸው በሰውነት ውስጥ በሕክምናም ይሁን ለሌላ ነገር ብረት ነክ ነገሮች የተቀበሩላቸው ሰዎች ለሐኪሞች ቀርበው መናገር አለባቸው። የጭንቅላት፣ የልብ ሕክምና ተደርጎልኛል። ውስጥ የተቀመጠ ነገር አለ ማለት አለባቸው።
በነፃ ለሚደረጉ ምርመራዎች አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በገቢ ዝቅተኛ እንደመሆኑ መጨናነቆች ይፈጠራሉ። ስለዚህ ሰዎች ምርመራውን ካገኙ በኋላ በተለያዩ መንገዶች ባሉበት ቦታ ውጤት እንዲደርሳቸው ማዕከሉ ይህንን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት። አብዛኛው ሰው የሶሻል ሚዲያ ተጠቃሚ እንደመሆኑ ውጤታቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲደርስና ተመልሰው እንዳይመጡ ይህን የሶሻል ሚዲያ ፕላትፎርም መጠቀም ይገባል።
በጤና ሚኒስቴር የሚንስትሯ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር አስቻለው ወርቁ እንደሚሉት አንድ ሰው ጤናማ ሆኖ ለመኖር ሲያስብ ቅድመ ጤና ምርመራ ሊያደርግ ይችላል። አመጋገቡን ሊያስተካክል ይችላል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ያደርጋል። በውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል እየተከናወነ ያለው የጳጉሜን ለጤና ነፃ የምርመራ ዘመቻ ይህን ያጠናክራል፤ በጎ ተግባርም ነው።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት በተጠናከረ መልኩ መሰጠት ከጀመረ ስድስት ዓመታትን አስቆጥሯል። የበጎ ፍቃድ ሥራ ከሚከናወንባቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ ደግሞ ጤና ነው። በጤናው ዘርፍ በየዓመቱ በሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች በወጣቶችና፣ ባለሀብቶችና በሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ይከናወናሉ። ባለፉት ስድስት ዓመታትም ሆስፒታሎችን የማደስ፣ ታካሚዎችን የማገዝ፣ ሐኪሞችን የመደገፍ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከልም መንግሥት በሚጠራቸው የተለያዩ የጤና የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ላይ በንቃት ሲሳተፍ ቆይቷል።
ጤና ሚኒስቴርም ይህንኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ በስፋት እያከናወነ ይገኛል። በተለይ በክረምት ወቅት በየዓመቱ የልየታ ሥራ ይሰራል። የታመሙትን ያክማል። ትምህርት ይሰጣል። ችግኝ ተከላ ያካሂዳል። በዚህ ዓመት ደግሞ ሁለት ባለሞያዎችን ለሙከራ ከውጭ ሀገር በማስመጣት ጳውሎስ፣ አለርትና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች ውስጥ ውድ የሆኑና በሀገር ውስጥ በቀላሉ ሊሰጡ የማይችሉ ሕክምናዎችን በበጎ ፍቃደኞች የሕክምና መሳሪያውንም ሆነ ክህሎቱን ይዞ በመምጣት ሥልጠናና የሕክምና አገልግሎት ሰጥተው ተመልሰዋል።
አሁን ደግሞ 16 አባላት ያሉት የልብ ቀዶ ሕክምና ባለሞያዎች መጥተው 90 ለሚደረሱ የልብ ህመም ላለባቸው ታካሚዎች ነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሰጥተዋል። ስለዚህ የጤና በጎ ፍቃድ አገልግሎቱ እየሰፋ መጥቷል። ጤና ሚኒስቴርም ይህን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በይበልጥ አጠናክሮ አስቀጥሏል። በሌላ በኩል ደግሞ የተበላሹ የሕክምና እቃዎችን ሜዲካል ኢንጂነሮችን ከህንድ ሀገር በማስመጣት የማስጠገን ሥራዎች ተከናውነዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም