የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያደረገው የቻይና- አፍሪካ ፎረም

ዜና ትንታኔ

የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) በቻይናና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ውይይት፣ ትብብርና የኢኮኖሚ አጋርነት እንዲያድግ የሚያስችል ቁልፍ መድረክ ነው።

ቻይና የአፍሪካ ትልቁ የንግድ አጋር ስትሆን፣ በየዓመቱ ከአፍሪካ ጋር የምታካሂደው የንግድ ልውውጥ ከ200 ቢሊዮን ዶላር ማለፉ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ፎረሙ የንግድ ሚዛንን ማስጠበቅ፣ በኢንዱስትሪ መስፋፋትና ለአፍሪካ ምርቶች የገበያ መዳረሻዎችን ማመቻቸት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ይነገራል፡፡

የትብብር ትስስሩ የበይ ተመልካች የሌለበት ስለመሆኑም በተለያዩ ጊዜያት አስተያየታቸውን የሚሰጡ ባለድርሻዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ያረጋግጣሉ፡፡ የባቡር ሐዲዶች፣ ወደቦች እንዲሁም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የተሠሩት ሥራዎች የአፍሪካን መገናኛ አው ታሮች እና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን የቻይና -አፍሪካ የትብብር ፎረም ፍሬዎች ስለመሆናቸውም አጠራጣሪ አይሆንም፡፡

የትብብር ፎረሙ የጋራ ተጠቃሚነትን መርሁ አድርጎ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች የተለያዩ ሥራዎች መሥራት ከተጀመሩ ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ ከሁለት ቀናት በፊትም የቻይና የአፍሪካ ሀገራትን የትብብር መስክ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ ዘጠነኛው የቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረም በቻይናዋ መዲና ቤጂንግ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ጊዜ ታዲያ ቻይና ከአጋሮቿ ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ ማሳደግ የሚያስችላት አስር ዘርፎችን ይፋ አድርጋለች። ከነዚህም ንግድ፣ ኢንዱስትሪ ፣ ጤና፣ ግብርና፣ መገናኛ አውታሮች ልማት፣ አረንጓዴ ልማትና ደህንነት ይገኙበታል። በዚሁ ጊዜም ነው ቻይና ለአንድ ሚሊዮን አፍሪካውያን የሥራ እድል እንደምትፈጥር ለአጋሮቿ ቃል የገባችው፡፡

በቢጂንግ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ላይ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢን ፒንግ 50 ቢሊዮን ዶላር በመመደብ በብድር እና በድጋፍ መልኩ የሥራ እድልን እንደሚፈጥሩ አስታውቀዋል፡፡ ከአሕጉሪቱ ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከርም 30 የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ትስስሯን እንደምታጠናክርም ገልጸዋል፡፡

እነዚህ የትብብር መስኮችም ኢትዮጵያን ከትብብር ማእቀፉ እንድትጠቀም የሚያስችሉ ስለመሆናቸውም በጉባዔው ላይ የጠሳተፉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ከቤጂንጉ የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ጎን ለጎን ከቻይናው አቻቸው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያና ቻይና በ17 ዘርፎች በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያና ቻይና ላለው በሁሉም ሁኔታ ለማይለዋወጠው ስትራቴጂያዊ ትብብር ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም ምርታማነትን ለማሳካት ሥራዎች በሚዘምኑበት የግብርና ትብብር መንገድ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ልማትና በዲጂታላይዜሽን ሥራዎቻችን ላይ ድጋፍ ስለሚገኝበት ሁኔታ የጋራ ውይይት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ትብብሩ በኢንቨስትመንት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እድገትና አዲስ የኃይል ምንጭ ልማት ላይ ለማጠናከር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት የትብብር ግንኙነት ሰፊና ጠንካራ መሠረት ያለው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በወንድማማችነትና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ የተመሠረተ ዘላቂ የትብብር ግንኙነት እንዲኖር የሁልጊዜም ፍላጎቷ እንደሆነ ገልጻለች ያሉት አምባሳደር ታዬ፣ ሁለቱ ሀገራት በጥንት ሥልጣኔ ሰፊ ተሞክሮ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት በመሆናቸው ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ሰፊ ምክክር መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከልማት ተነሳሽነት መርህ አንጻርም ከቻይና በርካታ ተሞክሮና የልማት ትብብሮች ለማሳደግም ፍሬያማ ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም መሪዎቹ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በተፈጥሮ ሀብት ልማት በጋራ መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ለእድገቷ እና ለደህንነቷ የባህር በር እንደሚያስፈልጋትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይታቸው ማንሳታቸውን አምባሳደር ታዬ ጠቅሰዋል፡፡

ከቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ጎን ለጎን የቻይናና የኢትዮጵያ መሪዎች ባደረጉት ውይይት፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ተሰሚነት፣ በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ የምታደርገው አስተዋጽኦ እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍ ካላት ከፍተኛ አቅም አኳያ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማድረግ ፍላጎት እንዳለት የተገለጸበት ነው ያሉት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተከትሎ የቻይና ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ግፊት እንደሚያደርጉ የቻይናው ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል ያሉት አቶ አህመድ፤ የእዳ ሽግሽግ እንዲደረግ ቻይና የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታበረክት ከስምምነት መደረሱን ያብራራሉ፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት በተለይ የኢኮኖሚ ትብብር የበለጠ ትኩረት እንዲኖረው፣ በብርና በዩዋን መለዋወጥ እንዲቻል፣ የቻይና የፋይናንስ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሠሩ እንዲሁም ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና ተጨማሪ ድጋፍ የሚገኝበት ነው፡፡ በተጨማሪም ቻይና ለኢትዮጵያ ከአራት መቶ ሚሊዮን ዩዋን በላይ ድጋፍ እንደምታደርግ ያረጋገጠችበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የፖሊሲ ነጻነቷን ተጠቅማ የኢኮኖሚ ማሻሻያዋን ተግባራዊ በማድረግ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቷ እንዲሁም ከዚያ በፊት በተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባቷ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የኢኮኖሚ ትብብሯን እንድታሳድግ ማድረጉንም ያክላሉ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራሉ፡፡

ፎረሙ ቴክኖሎጂ ሊሰጥ የሚችለውን ጠቀሜታ ለማግኘትና የሀገሪቱን አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ትልቅ እድል ይዞ የሚመጣ ነው የሚሉት ዶክተር በለጠ፤ ከአስሩ የትብብር መስኮች የቴክኖሎጂ ዘርፍ አንዱ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ቻይና ሆስፒታሎችን መገንባት፣ የሕክምና ባለሙያዎችን እና የሕክምና መሣሪያዎችን ማቅረብን ጨምሮ በተለያዩ የጤና ዘርፍ ማሻሻያዎች ላይ በትብብር ለመሥራት ስምምነት ተደርጓል ይላሉ፡፡

እንደ ዶክተር መቅደስ ገለጻ፤ በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ከተደረጉ አስር ስምምነቶች አንዱ ጤና ዘርፍ ነው ያሉ ሲሆን ለኢትዮጵያም ለወባ በሽታ የሚሆኑ ድጋፎችን ከቻይና እንዲሰጡ ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል፡፡ ስምምነቱ በተለይ የጤና ኢንዱስትሪውን ለማሳደግና የተለያዩ የህክምና ግብዓቶች ለማግኘት የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ልጃለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 /2016 ዓ.ም

Recommended For You