የፍትህ ዘርፉ ጠንካራ ሆኖ የሀገር ገጽታን መገንባት፣ አስተማማኝ፣ ነጻ እና ገለልተኛ ዳኝነት አለ ወደሚያስብል ደረጃ መድረስ ይገባዋል፡፡ ለአንድ ሀገር ሕልውና በፍትህ ሥርዓትና በተቋማቱ ላይ ጠንካራ አመኔታ ያስፈልጋል፡፡
በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ፣ ኢኮኖሚውም እያደገ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ሂደቱን የሚያግዝ የፍትህ ሥርዓት መገንባት እንደሚገባ፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ለአንድ ሀገር ትልቁ መለኪያ የፍትህ ሥርዓቱ ጥንካሬ መሆኑንም የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ወጪ ቆጣቢ የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በለውጡ ማግስት የተጀመሩ ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው፡፡ በተለይ አፋኝ የነበሩ የሕግ ጉዳዮችን በማሻሻል የተሰሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካርያስ ኤርኮላ፤ በፍትህ ዘርፉ በተለይም የሕጎች ማሻሻያ መደረጉ፣ ዳኞች በነጻነት የሚሠሩበት ሁኔታ መፍጠሩን በበጎነት ያነሳሉ፡፡
የፍትህ ዘርፉን አስረው ይዘዋል፣ አስቸጋሪ ናቸው፣ ሠብዓዊ መብት ይጥሳሉ የተባሉ ሕጎች በስፋት መሻሻላቸው ለዘርፉ ትልቁ ለውጥ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡ ሌሎችም በ1960ዎቹ የወጡ እንደ ንግድ ሕግ ያሉትም እንደገና ተሻሽለዋል ብለዋል፡፡
አቶ ዘካርያስ፤ የዳኝነት አካሉ ከየትኛውም አካል ነጻ ሆኖ በነጻነት መሥራት እንዲችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የዳኝነት ነጻነት፣ ተጠያቂነት እና ገለልተኛነት እንዲጠበቅ ተደርጓል ሲሉም ይጠቁማሉ።
በፍርድ ቤቶችም ሆነ በሌሎቹ የፍትህ አካላት የአሠራር ሥርዓቶችን የማሻሻል፣ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ሁኔታዎች በይበልጥ እየተሠራባቸው ይገኛሉም ይላሉ፡፡
“ነጻ እና ገለልተኛ ዳኝነት መኖር ወሳኝ ነው፤ ዐቃቤ ሕግ፣ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤቶች በተለይ ለሕግ በዘርፉ የማጥራት ሥራ መሠራቱ በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተመሩ የሚሠሩ ንጹህ ዳኞች ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በጣም በርካታ ችግሮች ውስጥ እየገቡ የሚሠሩ ሊኖሩ ይችላሉና መጥራት አለባቸው፡፡ ተግባሩ በሂደት መሠራት ያለበት፣ የሕግ ማዕቀፍም የሚፈልግ ነው ባይ ናቸው፡፡
“የማስቻያ ቦታዎችን ጨምሮ በዘርፉ አስፈላጊ ግብዓቶችና መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በጀትም መድቦ እየሠራ ይገኛል፡፡ በስፋትም መሠራት፤ አለበት ለምሳሌ አንዳንድ ቦታ የማስቻያ ሥፍራዎች በኪራይ የሚጠቀሙበት ሁኔታ አለ” ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች የራሳቸው የሆነ መሠረተ ልማት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ህንጻ መገንባት አለባቸው፡፡ የተሻለ የሥራ አካባቢም መኖር አለበት፡፡ እነዚህ ችግሮች ወደ ክልል ሲኬድ በጣም የሰፉ ናቸው፡፡ በመሆኑም እንደሁኔታው ቅድሚያ እየሰጡ፣ ያለውን ሀብት ባግባቡ እየተጠቀሙ መፍታት ይገባል፡፡
ቴክኖሎጂን በመጠቀም ረገድ በፌዴራል ደረጃ የተሻለ እንቅስቃሴ አለ፡፡ በክልሎችም ሊተገበር ይገባል፡፡ የፍትህ ዘርፉ ጠንካራ ሲሆን ነው የሀገር ውስጥ፣ የውጭ ኢንቨስትመንቱም የሚንቀሳቀሰው፡፡ እውቀቱም ሀብቱም ሥራ ላይ መዋል የሚችለው ሰላም ሲሰፍንና ጸጥታ ሲኖር፣ ደህንነት ሲሰማ ነው ብለዋል፡፡
ይህ ሊረጋገጥ የሚችለው የፍትህ ዘርፉ ላይ ትኩረት ተሠጥቶት ሲሠራ ነው፡፡ ለሕግ መቅረብ ያለባቸው ወንጀል የሚሠሩ፣ ለልማትም ለሥራም እንቅፋት የሚሆኑ ሰዎች ለሕግ ሲቀርቡ፣ ሲቀጡ፣ የሕግ የበላይነት ሲኖር ነው ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ መግባት የሚቻለው፡፡ ካለዚያ ስጋት ውስጥ ይከታል ሲሉም አክለዋል፡፡
ሀገራዊ ሪፎርሙ ከመንግሥት ፖሊሲ አንጻር በመሠረታዊነት የዜጎችን የፍትህ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ መንግሥት በሀገር ደረጃ ሰላም እንዲሰፍን፣ ብልጽግና እንዲመጣ ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም የፍትህ ዘርፉ ተግባር ሰው የበለጠ ወደ ሥራ የሚገባበት፣ በነጻነት መሥራት የሚችልበት ምቹ የሥራ ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 /2016 ዓ.ም