“እዮሀ አበባዬ መስከረም ጠባዬ ፤ መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ” ብለን ጆሮ ገብ በሆነው የልጆች ዝማሬ ነው አሮጌውን ዓመት ሸኝተን አዲሱን ዓመት የምንቀበለው። አዲሱ ዓመት አዲስ የሚሆነው በለመድነው እሳቤ በለመድነው መልኩ ስንቀበለው አይደለም። እንደመስከረም አበባ ሁሉ ዘመኑ የፈካና ያማረ፣ የሚያስደስት፣ የብዙዎችን ዓይን የሚስብ፤ መልካም ዜና የምንሰማበትና የምናወራበት ሆኖ እንዲያልፍ በመመኘት ፤ ምኞታችንን ለማሳካት አዳዲስ እቅዶችን በማቀድና ለመፈጸም ቃል በመግባት ነው።
መስከረም ሲጠባ እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዕዳ የሚባለው ዘመን ሲለወጥ የአስተሳሰብ ለውጥ አድርገን ሁሉንም እኩል የምናይበት ፣ የምንጠያየቅበት፣ ቂምና ቁርሾ ትተን በአንድነት ለአንድነት የምንተጋበት እንዲሆን የምንመኝበት ጊዜ እንዲሆንልን በመመኘት ጭምር ነው። ጎጂ ትርክቶችን ጥለን የሚጠቅሙንን የምናሻግርበት ዘመን እንዲሆን በማሰብ ጭምር ነው።
አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት፤ አዲስ ዕቅድ የሚተለምበት፤ እቅዱን ለማሳካት ቃል የሚገባበት እንደ በጎ ጅማሮ እና አዲስ ምዕራፍ የሚወሰድበት እንደመሆኑ መጠን መንግሥትም ሆነ ሕዝብ አዲሱን ዓመት ለመቀበል የሚዘጋጁት አዲስ ተስፋን በመሰነቅ፤ በሁሉም መስክ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት በመዘጋጀት ነው። የተቸገሩትን የምንረዳበት፣ የተጎዱትን የምንክስበት፣ መልካም የሆኑ እሳቤዎችን ሁሉ የምናሻግርበት ነው።
እንደ ግለሰብ ያለፉ መጥፎ ባህሪያትን፣ አስቸጋሪ የሚባሉ የሕይወት ውጣውረዶችን ለማቆም የሚወሰንበት አዳዲስ የሕይወት ምዕራፍ የሚጀመርበት በመሆኑ በአዲስ ዓመት ልዩ ልዩ ስንቆችን ሰንቆ መልካም የሆኑትን እርሾዎች ይዞ ወደፊት ለመራመድ መሠረት የሚጣለው በወርሀ መስከረም ነው።
እንደ ሀገርና መንግሥትም ባለፈው ዓመት የነበሩ ጠንካራ ጎኖች ሰፍተውና ለምልመው የሚቀጥሉበት መጥፎ፣ አስቸጋሪና ፈታኝ የነበሩትን አራግፎ ድክመቶችን አርሞ መልካም እድሎችን አስፋፍቶና አጠናክሮ አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት ዘመን እንዲሆን በመመኘት ብቻ ሳይሆን አቅዶ በመሥራትና በማሰራት ነው። ጳጉሜም አሻጋሪ ድልድይ ናት ያለፈውን ዓመት ደህና ሰንብት ብላ ትሸኛለች አዲሱን ዓመት ደግሞ እንኳን በሰላም መጣህ ብላ ትቀበላለች። ጳጉሜን አንድ ቀንም በመንግሥት የመሻገር ቀን ተብሎ ሲሰይም መልካም የሆኑ አስተሳሰቦችን ማሸጋገርን ታሳቢ በማድረግ ነው።
ያሳለፍናቸው ስድስት የለውጥ ዓመታት በየዘርፉ አኩሪና ዕምርታዊ ድሎች በማስመዝገብ ሀገር ማስቀጠል የተቻለበት ጊዜ ነበር። በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በኢነርጂ፣ በቱሪዝም፣ በሸገር ፕሮጀክት፣ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት፣ የአቅመ ደካሞችን የመኖሪያ ቤት በመገንባት፣ በተማሪዎች ምገባ፣ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የእርማት ሥራ፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፣ በልማት ኮሪደር፣… አቅዶ በመፈጸም፣ ፈጽሞ ሪቫን በመቁረጥ ብዙ ሊነገርለት የሚገባ፤ ትምህርት የሚቀሰምበት እና ለቀጣይ ሀገራዊ ድሎች እንደወረት ሊወሰድ የሚችል በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ እጅን አፍ ላይ የሚያስጭኑ አስደማሚ ውጤቶች ተገኝተዋል። ይሄንን መልካም ስኬት በቀጣዩ ዓመት አሻግረን የምናስቀጥለው ከሀገር አልፈን ዓለምን በማስደነቅ ጭምር ሊሆን ይገባል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የማንሻገራቸው ይመስሉን የነበሩ ነገር ግን በተደረገው ሀገራዊ ርብርብ ትልቅ ድል የተቀናጀንባቸውን የግብርና ሥራዎቻችንን በዛሬ የመሻገር ቀን አንዱን ማሳያ ማስታወስ የግድ ይላል። ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ድል ከምንታወቅበት በተጨማሪ መገለጫችን የስንዴ ልመና እንደነበር የምንዘነጋው ታሪክ አይደለም። ዛሬም ከአእምሯችን የፋቅነው ሳይሆን ታሪካችንን ለመቀየር መሠረት መጣል የጀመርንበት ወቅት ላይ እንገኛለን። በግብርና ዘርፍ ከስንዴ ልመና ወጥተን የውስጥ ፍጆታችንን በመቻል ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴ ለውጭ ገበያ ወደ ማቅረብ የተሸጋገርንበትን የመጀመሪያው የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ኢትዮጵያ ካሏት ዜጎች ከ80 ሚሊየን በላይ አርሶ አደር ቢሆንም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን ስንዴን ጨምሮ የምግብ ሰብሎችን በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ከውጭ ሀገር ታስመጣ ነበር። የምግብ ፍጆታ ምርቶችን ከውጪ ማስገባት ሀጢያት ባይሆንም ሀገሪቱ ካላት የውጪ ምንዛሬ አቅም አንጻር በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ ከስንዴ ጋር ተያይዞ የነበረው ፖለቲካዊ ትርጉም የዜጎችን አንገት ቀና የሚያስደርግ ሳይሆን አንገት የሚያስደፋና እጅ የሚያስጠመዝዝ እንደነበር የምናስታውሰው ነው።
ይሁን እንጂ በቁጭትና በጥንካሬ ይሄንን ታሪክ ለመቀየር በ2011 ዓ.ም በ3ሺ 500 ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው የስንዴ የመኸር እርሻ አሁን በጋና መኸሩን ጨምሮ በተሰራው የግብርና ሪፎርም ፣ በኩታ ገጠም እርሻ ዛሬ ከሀገር ውስጥ የምግብ ፍላጎት አልፎ ለውጭ ገበያ እስከ ማቅረብ ተደርሷል። ይሄ ከምንም የተገኘ ሳይሆን በበሳል እስትራቴጂ ዕቅድ፣ በራሳችን መሬት፣ በራሳችን አርሶ አደርና ባለሀብት በቆራጥነት በተሰራ ሥራ በበሳል አዕምሮ በተመራ የአመራር ብቃት የተገኘ ውጤት ነው።
ዛሬ ከነበርንበት የስንዴ ገበያ እና የስንዴ ርዳታ ወጥተን ስንዴን ለውጭ ገበያ አቅራቢነት የተሸጋገርንበት በኩራት የምንናገረው ዓለም ጭምር የመሰከረው ነው። አሁንም በዚሁ እንቆማለን፣ በዚሁ ረክተናል ለማለት አይደለም ቀጣዩ ዓመት ከዚህ ባለፈ ቴክኖሎጂዎችን፣ አዳዲስ ስትራቴጂዎችን ተጠቅመን፣ በአንድነትና በጥንካሬ ለተሻለ ለውጥ የምንሰራበት ለዚህም ቃል የምንገባበት ወቅት ላይ ነን።
በኢንዱስትሪው መስክ ኮቪድ 19 ያሳደረውን መጥፎ ተጽዕኖ የሀገሪቱ አጠቃላይ የማምረት አቅምን የተፈታተነ እንደነበር የምናስታውሰው ነው። ያኔ የበርካታ ኢንዱስትሪዎች ሥራቸው የተቀዛቀዘበት፣ ገበያ ያልነበረበት፣ በርካታ ችግሮች የተስተናገዱበት ነበር። ይሄንን የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን በተሰራው ሥራ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ከቆሙበት ወደ ተሟላ ማምረት እና የተኪ ምርት ትግበራ ተሸጋግረዋል። ኢንዱስትሪዎቹ በተሻለ መልኩ በማገገማቸው ዛሬ ሠራተኞችን በመቅጠር ለብዙዎች የሥራ ዕድል ከፍተዋል። ዜጋው የሀገር ምርቶችን እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል። በቀላሉ በሀገሪቱ የሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ለዚህ አንዱና ትንሹ ማሳያ ነው።
በ2003 ዓ.ም በወርሃ መጋቢት 24 የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ፣ ጉልበትና እውቀት የተጀመረው የኢትዮጵያውያን ኩራትና መለያ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በታየበት ብልሹ አሰራርና የፕሮጀክቶች የመምራት አቅም ውስንነት ተንገራግጮ በመቆሙ ብዙዎች አዝነውና ተስፋ ቆርጠው ነበር። ይሁን እንጂ የብልጽግናው መንግሥት” እንደጀመርን እንጨርሰዋለን” የሚለውን መርህ ወደፊት በማምጣት ባደረገው ጥልቅና ሰፊ ግምገማ የችግሮችን ምንጭ ተረድቶና በፕሮጀክቱ ላይ የነበሩ ስህተቶች ታርመውና ተስተካክለው እንዲቀጥሉ በሰጠው ቆራጥ አመራር ለሊት ከቀን በተደረገ ክትትል ዛሬ የተደረሰበት ደረጃ ላይ መድረስ ተችሏል።
የመላው ኢትዮጵያውያን ዐሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን እድገት የማይመኙ የውጭ ሀገራት ሥራውን ለማደናቀፍ በተደጋጋሚ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል። አብሮ የመልማትና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያነገበው መንግሥት ግን አንድም ጊዜ ከዓላማው ሸብረክ ሳይል የልማት አደናቃፊ የሆኑ ክሶችን በበሳል ባለሙያዎችና አመራሮች ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማክሸፍ በመቻሉና ሥራውም ጥራቱን ጠብቆ በመሰራቱ አሁን አራት ተርባይኖች ተጠናቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ትልቁ ስኬት ነው። ቀሪው ሥራም ሀገርን የሚፈትን ሳይሆን በአንድ ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሆኖ ዕቅድ ተይዞለታል። ጊዜ ተቆርጦለታል። ይሄ የሀገር ኩራት ለጠላት የውስጥ እግር እሳት ሆኖ ቀጥሏል። እያንዳንዱ ዕቅድ እያንዳንዱ ፕሮጀክት ሲሰራ በርካታ ተግዳሮቶች የማይታለፉ የሚመስሉ ግን የታለፉ ችግሮች አጋጥመዋል። በየአካባቢው የሚታዩ የሰላም መደፍረሶች በሥራው ላይ የፈጠሩት መሰናክል ሕይወትን ጭምር ያስገበሩ የሚያስገብሩ እንደነበሩ ማስታወስ የግድ ይላል።
በቱሪዝም ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላት አቅምና ሀብት፣ ሰው ሠራሽና ተፈጥራዊ ጸጋዎች ዓለምን የሚያስደምም ዕድል ቢሆንም በልኩ ሳትጠቀምበት ቆይታለች። የጎረቤት ሀገራትን የቱሪዝም ሀብት እያዩ ከማድነቅ ይልቅ ተስፋ ያለው ሥራ አልተሰራም። አሁን ግን ይሄንን ታሪክ የሚቀይር ከመሀል አዲስ አበባ እስከ ክልሎች የሚደነቅ ለዓይነ ሳቢና አስደማሚ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መገንባት ተችሏል። የአፍሪካዊያን መኩሪያ የሆነች የቱሪዝም መናኸሪያነት የተሸጋገርንበትን ዘመን ላይ ደርሰናል።
የአንድነት ፓርክ ፣ የወዳጅነት ፓርክ ፤ የእንጦጦ ፓርክ፣ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የወንጪ ዳንዲ፣ የጎርጎራ፣ የጨበራ ጩርጩራ፣ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም… የቱሪስትን ዓይን የሚስቡ ታይተው የማይጠገቡ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ናቸው። በሰው ሠራሽ ሐይቆች የተከበበው የሀገራችን ቅንጡ ሪዞልቶች እነ ሃላላኬላ ተመርቀው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን አስተናግደዋል። የገቢ ምንጭ መሆን ጀምረዋል። ይሄ ቁጭ ብሎ መናን ከሰማይ በመጠበቅ የተገኘ ውጤት አይደለም። ይሄ መሥራት እንደሚቻል ተሰርቶም ውጤቱ በተጨባጭ የታየበት የአመራር በተለይም የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የማቀድ፣ የመምራትና የመፈጸም አቅምን ልክ ያሳየ ነው።
ሁልጊዜም “ማቀድ ብቻ ሳይሆን ጨርሰን ሪቫን እንቆርጣለን” የሚሉበትን አንደበታቸውን በተጨባጭ ያስመሰከሩበት ሥራዎችና ፕሮጀክቶች ናቸው። ይሄ ትምህርት የቀሰምንበት፣ የእውቀት ሽግግር የተደረገበት፣ መሥራት መለወጥ እንደሚቻል የታየበት ነው። በቀጣይም ለተሻለ እቅድና ሥራ ለመሥራት መንግሥትና ሕዝብ የሚነሳሱበት አንዱና ትልቁ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ይሆናል።
ከዚሁ አመርቂ ስኬት ጎን ለጎንም በርካታና ውስብስብ ፈተናዎችን ባለፉት ዓመታት አጋጥመዋል። በተለይ ከሰላምና ጸጥታ ጋር ተያይዞ፣ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ሁሉ ዓይናቸውን አፍጥጠው ጥርሳቸውን አግጥጠው መጥተው አልፈዋል። ለነገ የቤት ሥራ ሊሆኑ የሚገቡ ትምህርት የሚወሰድባቸውና የተወሰደባቸውም ነበሩ። ይሁን እንጂ ከሞላ ጎደል ሁሉንም መሻገር ተችሏል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
መጪው አዲስ ዓመት ደግሞ የነበሩ ድሎቻችንና ስኬቶችን ይበልጥ የምናሰፋበት፣ ተግዳሮቶቻችንን የምንቀንስበት ዓመት ሊሆን ይገባል። የተመኘነው ስኬትም በውጤታማነት ለማስቀጠል የትናንቱን መለስ ብለን መቃኘት ያስፈልጋል። ስህተቶቻችንን ማረም፣ ችግሮቻችንን በምክክር በመግባባት መፍታት፤ የሚጠቅሙንን ትርክቶቻችንን ወደፊት አስቀድመን የማይጠቅሙንን ጥለን የወደፊቷን ኢትዮጵያ ማየትና ማለም ይገባል። ልዩነታችንን ማጥበብ በፖለቲካው ዘርፍ ልንሰራቸው የሚገቡን የቤት ሥራዎች ናቸው።
ኢትዮጵያውያን ታሪካችንን የምናስቀጥለው በጦርነት ብቻ ያገኘናቸውን ድሎችን በማንሳትና በማወደስ ብቻ መሆን የለበትም። በየዘመኑ የተሰሩና የሚሰሩ የልማት አርበኛ ያደረጉንን ታሪኮቻችንን ጭምር ወደፊት በማምጣት ፤ እዛ ላይ ቆመን የነገዋን ሀገር በተሻለ መንገድ በማሰብና ለዛም አቅደን በማሳካት ነው። ለዚህ ደግሞ የዛሬው ስኬቶችና ድክመቶቻችንን ትምህርት አድርገን ልንወስድ ይገባል። የጎደለውን ሞልተን፣ ያነሰውን አብዝተን፣ የጠበበውን አስፋፍተን ሀገራችንን ወደ በለጸጉት ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ይጠበቅብናል። በዛሬው የመሻገር ቀን መልካም መልካሙን ተሞክሮ እናሻግር መልዕክታችን ነው። ቸር እንሰንብት!
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም