በመሻገር ጥሪት ወደ አዲስ ብርሃን

ወርሃ ነሐሴ ከነነጎድጓዱ እልቀ፣ ወርሃ ጳጉሜ ከተስፋው ጋር ደግሞ ከተፍ አለ። በአስራ ሶስት የወራት ጸጋ ዘመኗን ያሰላችው ሀገራችን ኢትዮጵያ የልዩ የመሆንን ስም ካተረፈችባቸው አጋጣሚዎች መሀል አንዱ ይሄ አጋጣሚ ነው። አሮጌውን ከነግሳንግሱ ሸኝተን በተስፋና በበጎ መሻት አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት በተለይም ደግሞ በብዙ መንገጫገጭ ውስጥ ላለፈችው ሀገራችን በተግባቦት ብርሃንን መውለድ ከምኞቶቿ መሃል ነው።

በየዓመቱ ጳጉሜን ተንተርሰን በአሮጌው ዓመት ማብቂያና በአዲስ ዓመት አፋፍ ላይ ቆመን የምንመኘው ብዙ መልካም ምኞት አለን። ዘንድሮው እንዳለፈው ጊዜ ‹የመሻገር ጥሪቶች፣ የአዲስ ብርሃን ወረቶች› በሚል መነሻ ሃሳብ ወደ አዲሱ ዓመት የሚያንደረድረንን በኩረ መሻት ጀምረናል። በዚህ መነሻ ሃሳብ ስር ‹ጥሪት› ማለት ሀብት፣ ውርስ፣ ትውፊት ማለት ነው። ሁሉም ትርጓሜ ሀገርና ሕዝብ ላይ የሚያርፉ ብዙሃነትን ገላጭ ጽንሰ ሃሳቦች ናቸው። በጋራ ውርስ፣ በጋራ ሃሳብ፣ በጋራ ትውፊት የአዲስ ብርሃን ወረቶችን እንፍጠር የሚል ጠቅለል ያለ ትርጓሜ ያለው ይሆናል።

መሻገር ማለፍ ነው። ወደአዲስ ብርሃን፣ ወደተስፋ፣ ወደጋራ ትርክት መተላለፍ ነው። ከፉክክር ወደምክክር፣ ከችግር ፈጣሪነት ወደመፍትሄ አመንጪነት ሽግግር ነው። የመሻገር ጥሪቶች ሰላምን ማዕከል ያደረጉ፣ በሀገርና ሕዝብ ሉዓላዊነት የማይደራደሩ እሴቶች ናቸው።

እነርሱም እንደእርቅና ተግባቦት፣ እንደአንድነትና ህብረብሄራዊነት ያለ ትርጓሜ ያላቸው ናቸው። አሁን ባለው የፖለቲካ መልክና ሀገራዊ ውዥንብር የመሻገር ጥሪቶች ዋጋቸው በምንም የማይተካ ነው። ጳጉሜን በዚህ ልዕለ ሃሳብ ሰይመን ወደብርሃናማ ነገ የምናደርገው ጉዞ እንዳለፈው ጊዜ በወሬ ብቻ እንዳይቀሩ በማስተዋል ቀኑን ማሰብ ተገቢ ነው።

ባለፉት ዓመታቶች እንዲህ ባሉ የአዲስ ዓመት አፋፎች ላይ ተስፋን ጫሪ ንግግሮችና ጽሁፎችን አሰራጭተናል። ምኞታችን ከሃሳብ አልፎ ወደ ተግባር ካልተንጸባረቀ መሪ ሃሳብ ብቻውን የተሃድሶ መንገድ አይሰጠንም። ተስፋንና ሰላምን ምኞቱ ላደረገ ማህበረሰብ መሻገር ብዙ ትርጓሜ አለው።

በፖለቲካና በሰጣ ገባ ያልተሻገርናቸው በርካታ ችግሮች አሉብን። በጦርነትና በመርዘኛ ትርክት አነካክሰው ሊጥሉን የተጠመዱ የክፋት ወጥመዶች ስር ነን። ስለሆነም ከጋራ እምነት የፈለቀ አግባቢና ለአዲስ ወረት የሚያበቃ የመሻገር ጥሪት ግድ ይለናል።

ጭንጋፍ ሃሳብ ጭንጋፍ ፖለቲካና ሀገር ነው የሚፈጥረው። የጨነገፍንውና እየጨነገፍን ያለነው ለመሻገር የሚያበቃ ከእኔነት ወደብዙሃነት የተላለፈ ኢትዮጵያዊነትን ያገነነ ሃሳብና እምነት ስላላዳበርን ነው። ጽንሶቻችን ሀገር ወልደውና ትውልድ አቅፈው አያውቁም። ሃሳቦቻችን ባልተገባ አስተሳሰብ ተሞርደው እሾህና አሜኬላ እያበቀሉ ብዙ በዋጋ አስከፍለውናል። ‹የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች› የሚለው የአዲስ ዓመት መግቢያ ሀቲት ከዚህ አይነቱ ልምምድ ወጥተን በከበረ እሴትና በጋራ ሥርዓት ተከባብረን የሚከባበር ትውልድ እንድንፈጥር በማሰብ ነው።

የመሻገር ጥሪቶች አዲስ ተስፋን፣ አዲስ ብርሃንን የሚወልዱ ክበድ አስተሳሰቦች ናቸው። በሃሳቦቻችን ሀገራችንን የምንወልድበት፣ ህልሞቻችንን የምንታቀፍበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን። ለትውልድ በሚተርፍ ተሻጋሪና አሻጋሪ ጥሪቶች ተነጋግረን በመግባባት መጪውን ጊዜ የሉዓላዊነታችን እና የእድገታችን ዋስትና ማድረግ እንችላለን።

የመሻገር ጥሪቶችን ሰውነትን የለወሱ አሻጋሪና ተሻጋሪ በሚል እንክፈላቸው እና እንመልከታቸው ..አሻጋሪ ስንል የሸር ትርክቶችን ሽረው ከትናንት ወደ አዲስ ዛሬ የሚመልሱ የኢትዮጵያዊነት ቀለም የፈሰሰባቸው ሲሆኑ ተሻጋሪ ስል ደግሞ እኛ ላይ ሳይቆሙ ወደነገ ተላልፈው ትውልዱን ከክፉ የአስተሳሰብ ደዌ ነጻ የሚያወጡ ብለን እንያቸው። አንድ ትውልድ ላይ ያልቆሙ አቃፊና አስታራቂ ጥሪቶች የወሳኝ ምዕራፍ መታጠፊያዎች ናቸው። ይሄን ወሳኝ መታጠፊያ የሚፈጥሩት ደግሞ ወደ አዲስ የብርሃን ወረቶች የሚያሸጋግሩ የመሻገር ጥሪቶች ናቸው።

አዲሱን ዓመት በተመሳሳይ መንገድ እንዳንቀበለው የሚያደርጉ ሰላምና አንድነትን መሠረት ያደረጉ በርካታ የሕዝብና የትውልድ ጥያቄዎች አሉ። ሰላም እንደዋነኛ ጥያቄ ሆኖ የሚነሳ ጉዳይ መሆኑ ሀቅ ቢሆንም የሰላም አማራጮችን አለመጠቀማችን እንዲሁ አብሮ የሚነሳ እንከናችንም ነው። አሁን ላለንበት ለየትኛውም አጀንዳ ወሳኝ ተዋናዮች እኛ ነን። ከዘመን ጋር በዘመነ ሃሳብና አመለካከት ወደፊት ለማቅናት ካልተሰናዳን በድሮና በነበር አሉባልታ ነጻ መውጣት አንችልም።

በተፈጥሮ ሂደት ዘመን ይመጣል ይሄዳል። አዲስ ዓመት ትርጉም የሚሰጠው በተቀየረ ልብና በተለወጠ አመለካከት ስንቀበለው ነው። የመሻገር ጥሪቶች አዲሱን ዓመት በአዲስ አእምሮና ልብ እንድንቀበለው፣ ስለሀገርና ሕዝብ ተቆርቋሪነት የሚሰማው ማንነት እንዲኖረን መሠረት የሚጥል ነው። ከነባርና ጠባብ ጠብ ወለድ ልምምድ ወጥተን ወደአዲስና ተራማጅ ሥርዓት የምናቀናበት እንዲሁም ከንቅቅፍ ወደትቅቅፍ ፖለቲካ የምናመራበት የአዲስ ዓመት አዲስ ገጸበረከታችን ነው።

በእውነት እና በጸና ልብ መሻገር የምንፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። በአዲስ ዓመት አፋፍ ላይ ስለመሻገር ስናወራ ጳጉሜን በተለያዩ አንቂና አብቂ ሃሳቦች የመቀበል ልምድ ኖሮን ሳይሆን የእውነት መሻገር ስለሚያስፈልገን ነው። እዛም እዚም በተወለዱ መከራዎች መሀል ነን። ጦርነት አላባራም። ሰላም ቅንጦት ሆኖብናል። ለተነጋግሮ መግባባት አሻፈረኝ እያልን ነው እናስ መሻገር አያስፈልገንም?

የአዲስ ብርሃን ክስተቶች በሰማያችን ላይ የለም። ጦርነትና ጸብ እንደአልቦ በላያችን ላይ ፋፍተዋል። ደመና ባረገዘ የሞት ቀለያት እስከመች እንዳምናለን? እያረገዝን ስናስወርድና እየተመኘን ስንከሽፍ ብዙ ዘመናት ጠብተዋል። ተስፋችን ምኞታችንን ካልወለደ፣ ምኞታችን ፍቅርና የእርስ በርስ ትስስርን ካልሰጠን ዋስትናችን በምንም አይረጋገጥም። የመሻገር ጥሪቶች ወደሕይወታችን፣ ወደፖለቲካው፣ ወደትውልዱ፣ ወደማህበረሰቡ ወርደው አዲስ ዘርን እንዲያዘሩ የአዲስ ዓመት ተስፋችን ነው።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን  ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም

Recommended For You