የመሻገር ተስፋችን በእጅ ፤ በደጃችን ነው!

እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ እያስከፈለን ካለው ድህነት እና ኋላቀርነት ወጥተን ሰላም እና ልማት መገለጫዋ የሆነች ሀገር ለመፍጠር በየዘመኑ በብዙ መነቃቃት ተንቀሳቅሰናል። እነዚህን መነቃቃቶች በአግባቡ መረዳት እና ለነሱ የሚሆን ማህበረሰባዊ መሠረት መጣል ባለመቻላችን ትናንቶቻችንን ተሻግረን ብሩህ የሆኑ ነገዎቻችንን መጨበጥ ሳንችል ቀርተናል።

ከትናንት የትልቅነት ትርክታችን የሚመነጨው ፣ሁሌም ነገን በቁጭት ብሩህ አድርጎ የማየት እና ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት የመፍጠር ማህበረሰባዊ መነቃቃታችን፣ በያንዳንዱ ትውልድ ውስጥ “ትልቅ ነበርን፣ ትልቅ እንሆናለን” ከሚል የትናንት የታላቅነት የገዘፈ ታሪክ ምእራፍ ውስጥ የሚቀዳ እና በትውልዶች የማንነት ስሪት ውስጥ ጎልቶ የሚደመጥ ነው።

እንደ ሀገር በዚህ ከትናንት የመሻገር ማህበረሰባዊ መነቃቃት ውስጥ ያላለፈ ትውልድ የለም፤ እያንዳንዱ ትውልድ በዘመኑ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ ሆኖ የተረዳውን፤ እንደየዘመኑ ዘመኑን ይዋጃል ያለውን አስቦ ለተግባራዊነቱ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። የተከፈለውን ያህል ፍሬ ባያፈራም በየዘመኑ የተከፈሉ ዋጋዎች ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ በተሻለ የመሻገር የታሪክ ምእራፍ ላይ እንዲገኝ የተሻለ እድል ፈጥረውለታል።

ይህ ትውልድ በተጨባጭ ከቀደሙት ትውልዶች በተሻለ ከትናንት የመሻገር እድል የተፈጠረለት ነው። ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ እውነታዎችን በአግባቡ ማጤን፤ ህልሞቹን ታሳቢ አድርጎ በበጎ ህሊናና እና በቅንነት መመላለስ ከቻለ የመሻገር ህልሙን እውን ለማድረግ የቀደሙ ትውልዶች በተፈተኑባቸው ፈተናዎች ተፈትኖ የሚወድቅበት ክፍተት ጠባብ ነው።

ትውልዱ አሁናዊ የእውቀት መገለጡን፣ ከአባቶቹ ቅንነትን፣ አርቆ አሳቢነትን፣ አብሮ የመኖር ሆደ ሰፊነትን፤ የሀገር ፍቅርን እና ብሄራዊ ክብርን ተምሮና ደምሮ መራመድ ከቻለ ፤ ብዙ ትውልዶች በብዙ ተመኝተውት ሳይጭብጡት ከሩቅ ሆነው የተሰናበቱትን ማህበረሰባዊ መሻትን እውን አድርጎ አዲስ ሀገራዊ ትርክት ለመፍጠር የተሻለ በሚባል የታሪክ ምእራፍ ላይ ነው።

በለውጡ ዋዜማ እንደ ሀገር የተጀመረው የለውጥ /የመለወጥ መነቃቃት የዚህ እውነታ ማሳያ ነው። በወቅቱ በሕዝባችን ላይ የታየው የለውጥ መነሳሳት በመሠረታዊነት ከትናንቶች የመውጣት እና ብሩህ ነገዎችን እውን የማድረግ እና ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት ነው። ከትናንቶች የሚጠቅመውን ወስዶ ከማይጠቅሙት ጋር የመፋታት መነሳሳት ነው።

ከትናንት መፋታት ከትናንቶች ጋር ለረጅም ዘመናት አብሮ ከመኖር ጋር ከሚፈጠር መልመድ ጋር ተያይዞ በቀላሉ የሚከወን፤ ለራስ ብዙ ጊዜ ሰጥቶ ማሰላሰልን፤ በራስ ፍላጎት ላይ መጨከንን ለዚህ የሚሆን የመረዳት ቅንነትን የሚጠይቅ ነው። ከሁሉም በላይ ከራስ ወጥቶ ለማህበረሰብ የመሻገር ፍላጎት መሞትን የሚጠይቅ ነው።

የቀደሙት የለውጥ ታሪኮቻችን፣ የለውጥ መነሳሳቶቻችንን በተለወጠ ማንነት፤ በጠራ እውቀትና የመዳረሻ መንገድ ባለመገራታቸው ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል። በግለሰቦች እና በቡድኖች መካከል የተፈጠሩ ትርጉም አልባ አተካራዎች፤ የሥልጣን መሻቶች እና እነዚህ የፈጠሯቸው የሴራ መንገዶች የታሰበላቸውን ግብ ሳይመቱ ባክነዋል።

የሕዝባችንን የዘመናት መሻት /ከትናንት የመሻገር ህልም ተጨባጭ ከማድረግ ይልቅ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ያለውን አሳጥተውታል፤ የነበረውን አጥቶ በነበረው ነገር ተስፈኛ እንዲሆን፤ የማንነቱ መገለጫ ከነበሩ እሴቶቹ ወጥቶ፣ ከሚያወግዛቸው፣ ከሚጠየፋቸው እና ከሚረግማቸው ያልተገቡ ተግባራት ጋር እንዲለማመድ አድርገውታል።

ይህ ትውልድ ግን ከዚህ ሁሉ የትናንት ትውልዶች ስህተት ተምሮ፤ትናንቶችን በመድገም ከሚፈጠር የከፋ የታሪክ ስህተት እራሱን መታደግ በሚችልበት ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ውስጥ ነው፤ የሚያስፈልገው ለዚህ የሚሆን ስክነት፤ ከስክነት የሚመነጭ ሃላፊነት እና ከራስ እውነተኛ ማንነት ጋር የመታረቅ ቁርጠኝነት ነው።

ስክነት፤ ከስክነት የሚመነጭ ኃላፊነት እና ከራስ እውነተኛ ማንነት ጋር የመታረቅ ቁርጠኝነት በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች መሻት የሆነውን ትናንትን ተሻግሮ ብሩህ ወደሆኑ ነገዎች የሚደረግ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጅማሬ ነው። ይህን ማድረግ ደግሞ የመሻታችን የፍጻሜ ጅማሬ ነው።

የዛሬው የለውጥ ጉዟችንም የዚህ ታሪካዊ እውነት አካል ነው፤ ከትናንቶች ጋር አብረን ከኖርንባቸው ረጅም ዘመናት አኳያ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የማለፍ አስገዳጅ ሁኔታዎች ቢኖሩም እነዚህ ፈተናዎች ግን በትውልድ ውስጥ ካለ የመሻገር መነቃቃት የሚበልጡ ባለመሆናቸው ፈተናዎቹን የመሻገር ተስፋችን በእጅ በደጃችን ነው።

አዲስ ዘመን  ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም

Recommended For You