‹አረንጓዴ አስተሳሰብ ለአረንጓዴ ምድር› ከኢትዮጵያ አበይት የልማት አቅጣጫዎች አንዱ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል። ትግበራውም ላለፉት አምስት ዓመታት በላቀ ውጤት ያለ ማቋረጥ እንደቀጠለ ነው ፤ ዘንድሮም አዲስ ገድል ሰርተናል። ትውልድ በአስተሳሰብ ነው የሚፈጠረው።
አስተሳሰቡ መልካም የሆነ መሪና ሕዝብ በሃሳቡ በኩል ሀገር ይፈጥራል። ሀገር ከሚፈጠርባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ዛሬ ላይ የማይቆም ነገን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ናቸው። ሃሳብ እንደወጋገን ነው። የዛሬን ጨለማ አንግቶ ወደ ነገ የሚበራ ብርሃን ነው። በሃሳባችን መልካም ዘርን ለመዝራት ካልተነሳን በክፉ ትርክት ተያይዘን ለመውደቅ ማንም የማይደርስብን እንሆናለን።
አረንጓዴ ዐሻራ የመልካም ሃሳብ ዘር ነው። የሃሳቡ ተቋዳሽ በመሆን የምናደርገው የትብብር እንቅስቃሴ ነገን በብርሃን ከመኳል ባለፈ ተመስጋኞች ነው የሚያደርገን። በጎና አዋጪ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት መሳተፍ እንደ ጋራ ትርክት የሚወሰድ አግባቢና አዋሃጅ እሴት ይቆጠራል። በአረንጓዴ አስተሳሰብ አረንጓዴ ትውልድና ምድር ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት አብሮነትን ከማጽናት ጎን ለጎን አፋችንን በኢትዮጵያዊነት እንድንፈታ የሚያደርግም ጭምር ነው። ተፈጥሮ መልኳ አረንጓዴ ነው።
የተፈጥሮ ማህጸን አረንጓዴን ወልዶ እንዲያሳድግ በተፈጥሮ አስገዳጅነት የጸና ነው። እንደ ሰው ልጅ ተፈጥሮን የሻረ፣ ሥርዓትን የተዳፈረ የለም። እየሞትንና እየተጎሳቆልን ያለነው በእንዲህ ዓይነቱ የሥርዓት ሽረት ነው። በገዛ እጃችን ያራቆትነውን ምድር በገዛ እጃችን እስካላለበስን ድረስ በገዛ እጃችን ሞትን መርጠናል ማለት ነው። ሰው ለችግሩ መፍትሔ የሚሆን ሃሳብና መላ ሲፈጥር ነው የሚጀግነው። ልክ እንደዚህ አረንጓዴ አስተሳሰብ የሰውን ልጅ ሁሉ ከጉስቁልና የሚታደግ እሳቤ ነው።
ዓለም እየሞተች ያለችው በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ እንደሆነ አሁን ላይ ነጋሪ የሚያስፈልገን ጉዳይ አይደለም። የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ ከአረንጓዴ እሳቤ ያፈነገጠ ስልጣኔና ዘመናዊነት አብረው የፈጠሩት የራስ ወዳድነት ውጤት ነው። ከትላንት ወደዛሬ የመጣ ወደነገም ሊሄድ የሚያኮበኩብ የሥልጣኔ ልክፍት። የሚታደገን ወደ ተፈጥሮ መመለስ ነው። አረንጓዴነት አስተሳሰብን ማራመድ።
በያዝነው ቁርጠኛ እንቅስቃሴ በርካታ ለውጦችን እያየን ነው። ዘፍጥረት የሕይወት መግቢያ ነው። ዓለም እና የሰው ልጅ፣ ፈጣሪ እና ተፈጣሪ የተዋወቁበት። ፈጣሪ በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረና የሰውን ልጅ ቆይቶ ፈጠረው። የሰው ልጅን ዘግይቶ የፈጠረው አስቀድማ የተፈጠረችውን ምድር ለመኮርኮም ምሳር እንደሚያነሳ አይመስለኝም። እንዲያውም ግዛት ጠብቃትም የሚል ትእዛዝ ሰጥቶታል።
የሰው ልጅ ግን ለምድርና ለተፈጥሮ በጎ የሆነበት ጊዜ አልነበረውም። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ በፈጣሪ የጸናችው ምድር በሰው ልጅ ክፋት የምትጠፋ መሆኑ መነገሩ ነው። ዓለም በፈጣሪ ተጀምራ በሰው ልጅ ማብቃቷ አሳዛኝ ነው። ወደ ተፈጥሮ እስካልተመለስን ድረስ ሞታችንን መግደል ቀጣይ ሥራችን አብረን እንደተከልን አብረን ማጽደቅ ነው አንችልም። ወደ አረንጓዴ አስተሳሰብ እስካልመጣን ድረስ አረንጓዴ ምድር መፍጠር አይቻለንም። ምድር አሁን ላይ የተፈጥሮ ቀሚሷን አውልቃ ርቃኗን ናት። ሁላችንም ሀፍረተ ሥጋዋ ፊት ቆመን የምናላግጥ ነን።
ምድር ወደተፈጥሮዋ እስካልተመለሰች ድረስ መኖራችን ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ ነው። ይሄን ዓይነቱን የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅና ለማስተካከል በኢትዮጵያውያን በኩል ቁርጠኛ አቋም ተወስዶ እየተሰራ ይገኛል። ያለፉት አምስት የክረምት ዓመታት እንደ ዓለም የተጋረጠብንን የህልውና ስጋት ለመመከት ችግኝ በመትከል ኃላፊነታችንን ስንወጣ መቆየታችን ይታወሳል። ዘንድሮም እንደ አምናው ‹የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ› በሚል መነሻ ሃሳብ አካፋና ዶማ ጨብጠን ተጨማሪ ታሪክ መሥራት ችለናል።
ያለፉትን ጊዜያቶች ማስታወስ ብንችል በአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም ከአፍሪካ አልፈን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘንበት ተሳትፎ ነበር። ዘንድሮም በላቀና በበረታ መልኩ ካለፈው ተሽለን በአንድ ጀምበር ከስድስት መቶ ሚሊዮን (600 ሚሊዮን) በላይ ችግኞችን መትከል ችለናል። አፍሪካ የመከራ እቃ ቤት ናት። ይሄን እውነት የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። በዚህም በአየር ንብረት ዋነኛ ተጠያቂ የሆኑት የበለጸጉ ሀገራት ናቸው፤ የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ግን አፍሪካውያን ናቸው።
በእንዲህ ዓይነቱ መንገድ በድህነት ተቆራምዳ ለሰው ሠራሽ ችግሮች ሰለባ ለሆነችው አፍሪካ በአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ስቃያችንን መቀነስ እንችላለን። በተለይም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በድርቅ ሳቢያ ዜጎቻቸውን ለርሀብና ለሞት ሲዳርጉ ዓመታትን አስቆጥረዋል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ከአንዱ በሽታችን ሳናገግም በሌላ በሽታ መጠቃታችን የአፍሪካ መገለጫ ሆኖ ዘመናትን አስቆጥሯል።
ስጋቱን ከፍ ያደረገው ደግሞ በየአስር ዓመቱ ቤታችንን አንኳኩቶ ይመጣ የነበረው ድርቅና ርሀብ በየዓመቱ መምጣቱ ነው። ይሄ መሰሉ ያልተለመደ ለውጥ የአየር ንብረት መዛባት የፈጠረው ነው። በየዓመቱ አይደለም በየአስር ዓመቱ እንኳን ድርቅና ርሀብ ያማል። አባቶች ከርሀብ ጦርነት ይሻላል ይላሉ። ጦርነትም ርሀብም አይሻለንም። ግን ሁለቱን ሚዛን ላይ ብናስቀምጣቸው አንዱ ሻል ብሎ የምናገኘው ይመስላል። ከሁለት መጥፎ አንድ መጥፎ ማለት ነው። እንግዲህ ቀጠናችን የአፍሪካ ቀንድ እንዲህ ባለው ከጦርነት በላይ በከፋ ርሀብ የምትሰቃይ ናት።
ድርቅና ርሀብ መጥቶብን አይደለም ወትሮም በቀን ሶስት ጊዜ ለመብላት የምንገዳገድ ሕዝቦች ነን። የቀጠናው ስጋት ከእንዲህ ዓይነቱ የህልውና ስጋት የሚተርፍበት አንድ የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ በየዓመቱ የሰኔን መግባት ተከትሎ የሚተገበር ብሔራዊ ንቅናቄ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከላይ የዘረዘርኩትን ድርቅና በርሃማነት በመከላከል ረገድ ሚናው የላቀ ነው።
አፍሪካ በተለይም በጦርነትና በሌላም ችግሮች የሚሰቃየው የአፍሪካ ቀንድ በአስር ዓመት አንድ ጊዜ የሚጎበኘው ድርቅና ርሀብ በየዓመቱ መከሰቱ አደጋው ምን ያክል እንደሆነ መገመት አይከብድም። እንዲህ ዓይነቱ አደጋ ዓመት በዓመት እየመነመነና እየሳሳ ከመጣው የአካባቢ ጥበቃ እሳቤ ማነስ መሆኑ የማይታበል ቢሆንም፤ መፍትሔ ተኮር እንቅስቃሴ እንደሚያሻ አመላካች ነው።
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1970 ጀምሮ በአየር መዛባት ሳቢያ ምስራቅ አፍሪካ ህመምተኛ ናት። በአየር ንብረት ለውጥ በሚመጡ ስጋቶች ‹‹እህህ›› ሳትል ቀርታ አታውቅም። ህመሟን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ በግራና በቀኝዋ ታካ የያዘችው የሰሀራ በረሃና ሳይጎበኛት የማያልፈው የድርቅ ወቅት ነው።
እንደ መንግሥት የአረንጓዴ ልማት እሳቤ እንዲህ ዓይነቱን ከአፍሪካ ቀንድ አልፎ አፍሪካን የሚበጅ ከፍ ሲልም ለዓለም የአየር ንብረት ስጋት መልስ የሚሰጥ እንቅስቃሴ መሆኑ ታምኖበት ትግበራ መጀመሩ ‹ቀድሞ መንቃት› ወይም ደግሞ ‹ሳይቃጠል በቅጠል› የሚል አቻ ትርጉም ከመስጠት ባለፈ ይበል የሚያሰኝ ቁርጠኝነት ነው። ይሄን ዓይነቱን ሁለንተናዊ ቀውስ ለማስቀረት በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለው የቁርጠኝነት ግስጋሴ ምሠራቅ አፍሪካን ከስጋት እንደሚታደጋት እሙን ነው።
በቀጣይ የሚተከሉት ችግኞችና የተተከሉት ችግኞች ወደዛፍነት ተቀይረው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ሚዛን ደፍተው የሚፈለገው ውጤት ሲመጣ ውሳኔያችን ምን ያክል ትክክል እንደነበር እንረዳለን። በአረንጓዴ ዐሻራ በኩል የመንግሥት ቁርጠኝነት የት ድረስ እንደሆነ በተወካዮች ምክር ቤት በኩል በተደረገ ጥናት በመንግሥት እየተመራ ያለው የአረንጓዴ ልማት እምርታ ማሳየቱ አንዱ ተጠቃሽ ነው።
በመጀመሪያው የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ከተተከሉት ችግኞች ከ83 ከመቶ በላይ የጸደቁ ሲሆን በቀጣዩ የክረምት ወር ከተተከሉት ውስጥ ደግሞ 80 ከመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን የመንግሥትን ጨምሮ በገለልተኛ አካላት የተደረገ ጥናት አሳውቋል። ይሄ ብቻ አይደለም ችግኞቹ አድገው የሚፈለገውን አገልግሎት በመስጠት የታሰበውን አላማ ማስገኘታቸው በጥናቱ ተጠቅሷል።
ዛሬ ላይ እያደረግን ያለነው አረንጓዴ ልማት የነገ የመኖር ዋስትናችንን ከማረጋገጡም በላይ ከአየር ንብረት ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ችግሮች አስቀድሞ ምላሽ መስጠትም ነው። ከእኛ አርቀን ለሌሎች፣ ከሌሎች ገፍተን ለሚመጣው ትውልድ ስንቅ ማስቀመጥ ማለት እንዲህ ነው። ከዚህ ራቅ ካለ ደግሞ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ሁለት አስርት ዓመታትን ሊደፍን ጥቂት በቀረው አፍሪካ ተኮር የልማት ጥንስስ ወይም ደግሞ የአፍሪካ ህብረት የአረንጓዴ ልማት እሳቤን የሚደግፍ፣ የሚመራ፣ የሚያነቃቃ ሕዝባዊ ተሳትፎም ጭምር እንደሆነ መናገር ይቻላል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ እያደረጉ ያሉት የአረንጓዴ ልማት ትግበራ ከሀገር አልፎ አፍሪካን ከአፍሪካም ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው እንደሆነ በተለያዩ ጊዜ ብዙ የውዳሴና የሙገሳ ድምጾችን ሰምተናል። ለዚህ ምስክር ከሚሆኑን አካላት ውስጥ አንዱ የአፍሪካ ህብረት ነው። የአፍሪካ ህብረት እስከመጪው 2030 ድረስ የሚተገበር የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም አለው። በአፍሪካ ህብረት በኩል የተያዘው ይህ የአረንጓዴ ልማት ትግበራ በሚፈለገው ፍጥነት፣ በተፈለገው ጊዜ አለመከናወኑ እንደ አንድ ጉድለት የሚጠቀስ ሲሆን በተቃራኒው በቁርጠኝነት ከእቅዳችን በላይ በአረንጓዴ ልማት ላይ ዐሻራችንን እያሳረፍን ያለነው እኛ ለአፍሪካ ህብረት የዝግታ ጉዞ ኃይል እንደሚጨምርለት የታመነ ሆኗል።
የመንግሥት የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም ችግኝ በመትከል የሚያበቃ አይደለም። ለብዙዎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ማህበረሰቡ ከጓሮው አልምቶ ከጓሮው የሚበላበትን የከተማ ግብርና የፈጠረም ነው። ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ ከተሜው ባለው ትርፍ ቦታ ላይ የጓሮ አትክልቶችን አብቅሎ በመመገብ ራሱን በምግብ እንዲችል በመሰራቱ አረንጓዴ ዐሻራ እመርታ አምጥቷል። ባለፈው ጊዜ በአጭር ጊዜ ፍሬ የሚሰጡ እንደ አቡካዶና አፕል የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች በሰፊው ተደራሽ የሚሆኑበት አሠራር ቅድሚያ ተሰጥቶት የተሰራበት ሲሆን ውጤቱም አመርቂ ነበር። ከጓራችን እየበላን፣ በአረንጓዴ እሳቤ በአረንጓዴ ምድር ላይ ሳይሞቀንና ሳይበርደን፣ በተስተካከለና ስጋት በሌለው ከባቢ ውስጥ ሕይወትን መምራት ከምንም በላይ ደስ የሚል ነገር ነው።
ሂደቱ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ያለፉትን አራትና አምስት ዓመታት ውጤት እያየን ነው። በቀጣይ ከአፍሪካ ተሻግሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማችንን የሚያስጠራ የአረንጓዴ አስተሳሰብ ርዕዮት እንደምንፈጥር ሳይታለም የተፈታ ነው። “የምትተክል ሀገር የሚያጸድቅ ትውልድ” በሚል አንቂና አብቂ መሪ ሃሳብ የዘንድሮ ንቅናቄያችን በብዙ አዲስ የታሪክ ትርክት ታጅቦ ወደ ፍፃሜው እየተጓዘ ነው። ለአንድ አላማ በአንድ መቆምን የመሰለ የድል ገጽ እንደሌለ በተለያዩ መድረኮች አስመስክረናል። አረንጓዴ ዐሻራም የዛ ውጤት አንዱ ማሳያ ሆኖ እየታየ ነው። አሁን የሚቀረን አብረን እንደተከልን አብረን ማጽደቅ ነው።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም