ኢትዮጵያ የቀጠናውን ሀገራት ከማስተሳሰር ጎን ለጎን በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የበኩሏን ጥረት የምታደርግ ሀገር ነች። በጎረቤት ሀገራት የሚነሱ አለመግባባቶች ቶሎ እንዲፈቱና ሀገራቱ በፍጥነት ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለችው ሚና መተኪያ የሌለው ነው።
በተለይም ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በሰሜን ሱዳን፤ በሱዳንና በሶማሊያ ወደ ግጭት የገቡ ኃይሎችን በመሸምገል ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች። ግጭት ባልቆመባቸው በሱዳን የአብዩ ግዛትና በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ኢትዮጵያ ለአባል ሀገራቱ ጥላና ከለላ መሆን ችላለች። በቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን ወደ ሰላም ለመመለስም በብቸኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመጀመሪያው ትኩረት የጎረቤት ሀገራት በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከየትኛውም ዓለም አቀፋዊም ሆነ አህጉራዊ ጉዳዮች በበለጠ ለጎረቤት ሀገራት የቅድሚያ ትኩረት ትሰጣለች። ይህንኑ መነሻ በማድረግም ግጭት እና ሁከት ውስጥ የሚገኙትን ሶማሊያ፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በመሪዎች መካከል ተደጋጋሚ ውይይት እንዲደረግ ኃላፊነትን በመውሰድና አልፎ ተርፎም የሰላም አስከባሪ በመላክ ሀገራቱ አንጻራዊ ሰላም እንዲኖራቸው አበክራ በመሥራት ላይ ትገኛለች።
ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና ለዘመናት ቆይታለች። ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥረት እኤአ ከ2008 ጀምሮ ሶማሊያ መንግሥት መስርታ አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ቆይታለች። ለሶማሊያ መረጋጋትና የሶማሊያን ሕዝብ ለመታደግ ሲባልም ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆሩ ወታደሮቿን አጥታለች።
በፊት ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ተልዕኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግሥትም ተረጋግቶ መንግሥታዊ ሥራዎችን እንዲያከናውን ስታደርግ ቆይታለች።
በተመሳሳይም ሱዳን ግጭት ውስጥ በገባችበት ወቅት ሁሉ ከሕዝቡ ጎን በመቆም ሱዳን ወደ ተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንድትመጣ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በሱዳን የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረትም ግንባር ቀደም ሚናዋን መወጣቷ የሚታወስ ነው።
ከወራት በፊትም በግጭት አዙሪት ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን ወደ ሰላሟ እንድትመለስ ማንም መሪ ባላደረገው መልኩ ፖርት ሱዳን ድረስ በመሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አል ቡርሃን ጋር ተወያይተው ተመልሰዋል። ውይይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም “የወንድም ሱዳን ሕዝብ ችግር የኛም ችግር፤ ሰላማቸውም ሰላማችን በመሆኑ ለሱዳን ሕዝብ እፎይታ እና የብልፅግና ጉዞ ዛሬም እንደ ትላንቱ ከልብ እንሰራለን።” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳንም እንደ ሀገር እንድትቆም ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚና ከመጫወቷም ባሻገር በሀገሪቱ የነበረው የእርስ በእርስ ግጭት እንዲያባራና አንጻራ ሰላም እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚና ተጫውታለች።
በጎረቤት ሀገራት የሚታየውን ግጭትና ጦርነት እንዲያበቃ ከመሥራት ጎን ለጎንም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በልማት እንዲተሳሰሩ በማድረግ ረገድም የኢትዮጵያ ሚና የጎላ ነው።
ኢትዮጵያ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ በበርካታ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በቀጠናው የሚታየውን ድርቅ በዘላቂነት ለመቋቋም አበክራ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ከዚያም ባሻገር የአካባቢ መራቆት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ዋነኛ ችግር መሆኑን በመረዳት የአረጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ከኢትዮጵያ አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት ዘንድ እንዲተገበር የመሪነት ሚናውን ወስዳ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የቀጠናውን ሀገራት ልማት በማቀራረብ ረገድ እየተጫወተችው ያለችው ሚና በአካባቢ ጥበቃ ብቻ የተገታ አይደለም። በተለይም ከዓባይ ግድብና ከጊቤ ሶስት ግድቦች የሚነጭ ኃይልን ለጎረቤት ሀገራት በተመጣጣኝ ዋጋ በማዳረስ ቀጠናው በኃይል እንዲተሳሰር በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በድርቅና ርሃብ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ዛሬ ስንዴን በማምረት ኤክስፖርት የማድረግ ደረጃ ላይ ደርሳለች። ይህ የአካባቢውን ሀገራት ከማነቃቃቱም ባሻገር አባል ሀገራቱ በቅርበት ስንዴን እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
ሆኖም አንዳንድ የጎረቤት ሀገራት ዛሬም ኢትዮጵያን በጠላትነት በመፈረጅ ለእድገቷ እንቅፋት ለመሆን ሲሞክሩ ይታያሉ። በተለይም ከዓባይ ግድብ መገንባት እና ከባህር በር ጥያቄ ጋር ያላትን መብት ወደ ኋላ ለመመለስ የሚታትሩ ሀገራት ተከስተዋል።
በተለይም የኢትዮጵያን የወደብ ጥያቄ በማጣጣልና ጎረቤት ሀገራትም በበጎ እንዳይመለከቱት ለማድረግ በማያገባቸው እየገቡ ቀጠናውን ለማወክ የሚሞክሩ ሀገራትም ብቅ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ላይ ይዞታ የነበራትና ቀይ ባህርንም ስታዝበት የኖረች ሀገር ነች። 1ሺ800 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የቀይ ባህር ይዞታ በቁጥጥሯ ሥራ ያኖረችና ለወጪና ገቢ እቃዎች ሁለት ወደቦች የምታስተዳደር ሀገር ነበረች። ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ውጪ ቀይ ባህርንም ከኢትዮጵያ ውጭ ማሰብ አይቻልም ነበር።
ሆኖም የኢትዮጵያን ማደግ በማይፈልጉ ኃይላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትወገድ ተደርጓል። ለዘመናትም ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ምንም ድርሻ እንዳልነበራት ሆን ተብሎ በተሰራጨው ትርክት ኢትዮጵያና ቀይ ባህር ተቆራርጠው ኖረዋል። ከሕዝቡ ልብ ውስጥ ቀይ ባህርን ማውጣት ባይቻልም ስለቀይ ባህር ማሰብና ማውራት እንደ ሀጢያት ሲቆጠር ቆይቷል። ባለፉት 30 ዓመታት ስለወደብና ባህር በር ማውራትም ሆነ የኢትዮጵያን የባለቤትነት መብት መጠይቅ እንደነውር ከማስቆጠሩም በላይ ጸብ አጫሪ አስብሎም በነገረኛነት ያስፈርጅ ነበር።
የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆንም ከሥነ ልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሕዝቡ እንዲጋለጥ አድርጎታል። የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል። ለበርካታ መሠረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶችን ይውል የነበረውን ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለኪራይና ለመጓጓዣ ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።
በዲፕሎማሲ እና በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ረገድ የኢትዮጵያ ሚና አሽቆልቁሏል። ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ በዓለም እጅግ ተፈላጊ ከሆኑትና የኃያላን ሀገራትንም ቀልብ የሚስብ በመሆኑ እድገቷን የማይፈልጉ አካላት በተቀነባበረ ሴራ ከቀይ ባህር እስኪያርቋት ድረስ ገናና እና በሁሉም ዘንድ ተፈላጊ ሆና ቆይታለች። ሆኖም ሀገሪቱ ወደብ አልባ ከሆነች ጀምሮ ተፈላጊነቷ አሽቆልቁሏል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት 16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ 126 ሚሊዮን ደርሷል። በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ የባህር በር የሌላቸውን ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን ይሸፍናል።
ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ የባህር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር የለም። ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ በባህር በር የተከበበች ሀገር ነች። ከላይ እንደጠቀስኩት በሴራ እና በተሳሳተ ትርክት ከቀይ ባህር እንድትርቅ ከመደረጓ በስተቀር በአፈጣጠሯ ለቀይ ባህር የቀረበ ነው። በሶስተኛ ደረጃ በታሪክም በቀይ ባህር ላይ ለዘመናት የበላይ ሆና መቆየቷን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ያሏት ሀገር ነች።
ስለዚህም ኢትዮጵያ በግፍ ከይዞታዋ እንድትነቀል ከመደረጓ ውጪ ባለቤትነቷን የሚከለክላት አንዳችም ዓለም አቀፍ ሕግ የለም። ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችበትም ሆነ ከቀይ ባህር እንድትወገድ የተደረገበት አካሄድ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው ነው። ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትወገድና ወደብ አልባ እንድትሆን የተደረገው በ1900፤ 1902 እና 1908 ከቅኝ ገዢዎች በተደረጉ ውሎች አማካኝነት ነው። እነዚህ ውሎች ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት መመስረቻ ቻርተር ሕጋዊነታቸውን አጥተዋል።
ስለዚህም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ታሪካዊም ሕጋዊም ነው። ስለዚህም ይህንን ሀቅ መጋፋት የትም አያደርስም። ኢትዮጵያ ይህንኑ ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብቷን መነሻ በማድረግ ከሶማሊ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟ የሚታወስ ነው። ይህ የመግባቢያ ሰነድ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጠናው ሀገራት ሰላምና መረጋጋት የሚፈጥር ቢሆንም አንዳንድ ሀገራት ድንበር ተሻግረው ሁኔታውን ከልኩ በላይ ለማጦዝ ሲሞክሩ ታይተዋል። ጭራሹኑ በሰላም ማስከበር ስም ጦራቸውን ለማስፈር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ለኢትዮጵያም ሆነ ለቀጠናው ሀገራት ስጋት መሆኑ አይቀሬ ነው።
ሶማሊያ ባለመረጋጋትና በግጭት ውስጥ የምትኖር ሀገር ነች። ከዚያም አልፎ መንግሥት አልባ ሆና ዘመናትን ተሻግራለች። በእነዚህ የመከራ ዓመታት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሶማሊያ ሕዝብ ጎን ተለይቶ አያውቅም።
በፊት ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ተልዕኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግሥትም ተረጋግቶ መንግሥታዊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት 60 በመቶ የሚሆነውን የሶማሊያ ክፍል የሚጠብቀውና ከአልሻባብ ጥቃት የሚከላከለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጠንካራ መንግሥት እንዲፈጠር መስዋዕትነት ስትከፍል ቆይታለች። ሆኖም በሶማሊያ መንግሥት በኩል እየተሰጠ ያለው ምላሽ የኢትዮጵያን መስዋዕትነት የዘነጋ እና በአካባቢውም ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጠር ነው።
ሌላኛው ተጽዕኖ ከዓባይ ግድብ ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ የዓባይን ግድብ መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ከታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በርካታ ጫናዎችን አስተናግዳለች። በዓባይ ግድብ የተነሳ አሜሪካና የተወሰኑ የአረብ ሀገራት፣ የተወሰኑ ሀገራት ከአውሮፓም ከአፍሪካም ከግብጽ ጎን ቆመው ኢትዮጵያን እስከ ማስፈራራት እና ጫና እስከ መፍጠር፣ ብድር እስከ ማስከልከል መንቀሳቀስ እና ርዳታ እስከ መሰረዝ የሄዱበት ሁኔታ ነበር።
ሆኖም ኢትዮጵያ ጫናዎችን ተቋቁማ የግድቡን ግንባታ ወደ ማጠናቀቁ ደርሳለች። አራት ተርባይኖችም ኃይል ማመንጨት ጀምረዋል። ይህም ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የመልማት እድልን ፈጠሯል። ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ እድል በመቀየር ወደ አዲስ ተስፋ በመስፈንጠር ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም አንዱ የእነዚሁ የተፈጥሮ ጠላቶችና የተላላኪዎቻቸው የትኩረት መስክ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፍና ዘመናዊ የአቪየሽን ዘርፍ ነው። በተወዳደረበት መስክ ሁሉ የሚያሸንፍና ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ኩራት የሆነ ተቋም ነው። ሆኖም ከዚህ ግዙፍ አየር መንገድ ጋር ተወዳድረው ማሸነፍ ያልቻሉና አልፎ ተርፎም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መጉዳት የሚፈልጉ ሀገራትና አካላት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአየር መንገዱን ዝና ለማጠልሸት በርካታ ዘመቻዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ጥቂቶቹን ለማስታወስ ሰኞ ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም. ከሱዳን የተነሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን አብራሪዎች “እንቅልፍ ጥሏቸው” መዳረሻቸውን አልፈው እንደነበር የሚያወሳ ዘገባ ተሰራጭቶ ነበር። በተደረገው ማጣራትም ዘገባው ሀሰት መሆኑ ተደርሶበታል።
ሰሞኑን ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምሥል አንዲት ተሳፋሪ በአየር መንገዱ ሠራተኞች ከአውሮፕላኑ እንድትወርድ ስትጠየቅ እና ተሳፋሪዋ አልወርድም እያለች ከሠራተኞቹ ጋር የምታደርገውን የተካረረ ክርክር የሚያሳይ ምሰል ተጋርቶ ነበር። ይህንን ጉዳይ በዋነኝነት ታዋቂው ኬንያዊ የሲንኤንኤን ጋዜጠኛ ላሪ ማዶዎ ጉዳዩን ከልክ በላይ ሲያጦዘው ነበር። ይህ ጋዜጠኛ በዚህ ልክ ጉዳዩን ማጦዙ ከጋዜጠኝነት ሙያው ይልቅ ጉዳዩን መወዳደር የተሳነውን የኬንያን አየር መንገድ በአቋራጭ ለመጥቀም የተደረገ ሴራ መሆኑን ልብ ይሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ የጎረቤት ሀገራት ሰንካላ ምክንያት በመፍጠር አየር መንገዱ ወደ ሀገሬ እንዳይበር የሚሉ ድምጾችም ተሰምተዋል።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን አየር መንገድ ዝና ጥላሸት ለመቀባት የሚደረጉ ጥረቶች በተቀናጀ መልኩ እየተፈበረኩ ነው። ከግለሰቦች አልፎም ሀገራት ጭምር ጥቃቅን ሰበቦችን እየፈለጉ የአየር መንገዱን ዝና የሚያወርዱ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ለመመልከት ችለናል። ሆኖም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመን ተሻጋሪ ልምድ እና እውቀት ያለው ተቋም በመሆኑ በወሬ የሚረታ ቁመና የለውም። ስለሆነም እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አንግቦ በአፍሪካ ሰማይ ላይ ይነግሳል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ፈተና የማያጣት ሀገር ነች። ከቤት እስከ ጎረቤት የምትፈተን፤ ጉዞዋ ሁሉ ከሜዳነት ይልቅ ዳገትና ቁልቁለት የሚበዛበት ነው። ሆኖም ጽኑ በሆኑ ሕዝቦቿና ቆራጥ በሆኑ መሪዎቿ በመታገዝ እሾህና አሜካላውን እያወስወገደች፤ ለጠላቶቿ የነብር አራስ እየሆነች አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን አስከብራ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ነገንም ትሻገራለች። ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛል እንደሚባለው ኢትዮጵያ ችግሮቿን እንደ እድል በመጠቀም ወደ አዲስ ምዕራፍ የልማት ግስጋሴ ውስጥ ገብታለች።
አሊሴሮ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም