አመሠራረቱ፣ በሰብዓዊነት መርህ ተቃኝቶ፤ ለሰው ልጆች ችግር መፍትሔን፣ በመከራዎቻቸውም ወቅት ደርሶ መደገፍና እንባ ማበስን ማዕከል አድርጎ ነው፡፡ ምንም እንኳን በሚጠበቀው ልክ ሰርቷል ባይባልም፣ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት አንድም ዜጎች ለችግር እንዳይዳረጉ ቀድሞ በማስገንዘብ፤ ሁለትም፣ ዜጎች አደጋ በገጠማቸው ጊዜ አፋጣኝ ምላሽና ድጋፍን በማድረስ፤ ሦስትም፣ ዜጎች ከችግሮቻቸው ባሻገር ሆነው እንዲገለጡ የመልሶ ማቋቋምን ተግባር ለመከወን ሲጥር ኖሯል፤ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፡፡
ዛሬም እነዚህን ሦስት ተግባራት ሚዛን አስጠብቆ ለማስኬድ የሚገዳደረው መልከ ብዙ ፈተና ያለበት ቢሆንም፤ በፈተና አዙሪት ውስጥ ሆኖ ችግር ከማውራት ይልቅ፤ የችግሮቹን ምንጭ ለይቶ ለመፍትሔዎቻቸው መሥራትን እንደ አቅጣጫ ይዞ በመንቀሳቀስ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ተረጂነትን ታሪክ እንዲያደርጉ የሚያስችል የትግበራ መንገድ ስለመጀመሩ ይነገራል፡፡ በተለይ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መከወንን ግቡ አድርጎ፤ በኢትዮጵያ ምድር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ዓላማን ይዞ እየሰራ ስለመሆኑም ይገለጻል፡፡
ታዲያ የዚህ መልካም ሕልምና ዓላማ ትልምን ከማሳካት አኳያ፤ እንደ ተቋም፣ እንደ ሀገር፣ እንደ ሕዝብና መንግሥት እሳቤውን ገዝቶ የድርሻን ከመወጣት አንጻር ምን አቅምና እድል አለ፤ ምንስ ፈታኝ ሁኔታዎችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተለይተዋል፤ የሚሉ ጉዳዮችን በማንሳት፣ ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምንድን ነው? በማንስ ይከወናል?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር በሀገር ደረጃ ሲታይ የሰብዓዊ መብትን፣ ማህበራዊ ፍትህን፣ ብሔራዊ ደህንነትንና ዘላቂ ሰላምን የሚያቅፍ ነው፡፡ የአንድ መንግሥት የመንግሥታዊ ቅቡልነትን የሚያመላክትም ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ዜጎች መንግሥት አለኝ ብለው እንዲያስቡ ከሚያደርጋቸው ጉዳይ አንዱ፣ በሚቸገሩበት ወቅት የሚታደጋቸው መኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ የአደጋ ሥራ አመራር አንዱ መገለጫው ለሕዝቦች መድረስ ነው፡፡
ሁለተኛው፣ ሁለንተናዊ እይታን መጠየቁ ሲሆን፤ ይሄም በሚዛናዊነት በቅድመ አደጋ፣ በአደጋው ወቅትና ከአደጋ በኋላ የሚሰሩ ሥራዎችን ማካተቱ ነው፡፡ ሦስተኛው፣ ሥራው ሁሉንም የሚመለከት መሆኑ ሲሆን፤ ማህበረሰቡን፣ የግልም ይሁን የመንግሥት ተቋማትን፣ የአስተዳደር እርከኖችን በሙሉ ማካተቱ ነው፡፡
ስለዚህ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ስንል፣ ሁሉንም የሚመለከት፣ የሁሉም ኃላፊነት ያለበት፣ የሁሉንም ምላሽ የሚጠይቅ ተግባር ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የአደጋ ሥራ አመራር ሀገራዊ ገጽታ አለው፤ የደህንነት ገጽታ አለው፤ መላው ማህበረሰቡም መጫወት ያለበትን ሚናም የሚያካትት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር በሀገራችን ምን ገጽታ አለው?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- በሀገራችን የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ተቋቁሞ መሥራት ከጀመረ 50 ዓመታት እየሆነው ነው፡፡ በ50 ዓመታት የሥራ ታሪክም በጎ ነገሮች እንዳሉ ሆነው፤ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችም ተተክለዋል። ለምሳሌ፣ የሰብዓዊነት ሥራ ዓለም አቀፋዊ እይታና ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ ነው፡፡ ነገር ግን ሰብዓዊነት ከዛ እያለፈ እየሄደ፣ ሰዎች ሲቸገሩ ከመደገፍ ባለፈ፤ ተረጂነትን እንዲለማመዱ፣ የማይመለከታቸውም ጭምር በሰብዓዊነት ማዕቀፍ ውስጥ እንዲታዩ የሆነበት ሁኔታም አለ፡፡
ሥራው 1960ዎቹ ሲጀመር፣ በተለይም የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ፣ በሕይወትና ሞት መካከል ያሉ ሚሊዮኖችን የመታደግ ሥራ ተሰርቷል፡፡ የቅድመ ማስጠንቀቂያው ሥርዓትም ቀላል የሚባል አይደለም። በዚህም በተለያየ መንገድ (ለምሳሌ፣ በሴፍቲኔት እና በድንገተኛ መንገድ) ሰዎች ሲታገዙ መጥተዋል፡፡ በዚህ በኩል ሲታይ፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ሥርዓታችን በሰብዓዊነት ላይ ሰፊ ሥራ ሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡
በተለይም ከቅድመ አደጋ፣ በአደጋ ወቅት እና ከአደጋ በኋላ ተግባራት አኳያ ሲመዘን፤ በአደጋ ወቅት የነበሩ የተለያዩ ችግሮችን በመቅረፍ በኩል የማይናቅ ድርሻ ነበረው። ይሁን እንጂ በሂደት በተለይም በሀገራችን በአጼው ሥርዓት የተፈጠረው ከፍ ያለ የሰብዓዊ ቀውስ ንጉሱ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ምክንያት የሆነበት አጋጣሚም ተፈጥሮ ነበር፡፡ በወቅቱ የሰዎችም፣ የበርካታ እንስሳትም ሕይወት ጠፍቷል። ሌሎች የኑሮ መሠረቶችና መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡
በሂደት ሰብዓዊነት በሁለት ተከፈለ፡፡ አንደኛው፣ ሰዎች የእለት ድጋፍ አግኝተው ሕይወታቸውን መታደግ የሚያስችል አሠራር ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ ከድጋፍ እንዲወጡ የአይበገሬነት ግንባታ ላይ መታገዝ አለበት የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይሄ እሳቤም የሰብዓዊ አያያዝ የዛሬውን ችግር ከመቅረፍ ባሻገር ካሉ ተግባራት አኳያም የራሱን እድገት እያሳየ፤ ሰብዓዊነት ሥራውም ልማትን፣ ሰብዓዊነት እና ዘላቂ ሰላምን ባጣመረ መልኩ እንዲከናወን እያስቻለም መጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ አሠራር ከደጋፊነት ባሻገር የተረጂነት እሳቤነት እያጎለበተ መምጣቱ ይነገራል፡፡ ይሄን የተረጂነት እሳቤና አካሄድ እንደ ሕዝብና ሀገር ተጽዕኖው እንዴት ይገለጻል?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- የሰብዓዊ ድጋፍን ከ1960ዎቹ ጀምረን ስናይ፤ ሰብዓዊነት መልኩን እየቀየረ ሄዷል፡፡ ለምሳሌ፣ የ1965/66ቱ ማህበረሰብን ለመታደግ የተደረገ ሰብዓዊነት ነው፡፡ ይሄ ድጋፍም በሀገር ውስጥ አቅም ሳይሆን፣ በአጋር አካላት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ይህ እየተቀየረ መሄድ ነበረበት፡፡
ሆኖም ርዳታው ሰዎች ባልተቸገሩበት ሁኔታም ሲደረግ ስለነበረ፤ ሰብዓዊነት በሂደት ወደ ተረጂነት ዞረ፡፡ ሊደገፍ የሚገባውና የማይገባው የማይለይበት ሁኔታም ተፈጠረ። ይባስ ብሎ የርዳታ ድጋፍ የሚባለው ለተለያዩ ፍላጎቶች የሚታደል፤ የዘመድ አዝማድ መጠቀሚያ ሆነ፡፡ ለአቋራጭ ባለሀብትነት አቅም፤ የተለያዩ ፍላጎቶችን ማሳኪያ እየሆነ ሄደ። እናም በሂደቱ ሰብዓዊነት ቅርጽ እያጣ በብልሽት ውስጥ ላሉ ሰዎች መጠቀሚያ እየሆነ ብዙ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡
በዚህም፣ የመጀመሪያው ጉዳት፤ ሰው በጥረትና በታታሪነት ሊወጣው የሚችለውን እለታዊ ችግር፣ የዘላቂ ችግር ባለቤት እንዲሆን አደረገው፡፡ በዘላቂነት ከችግር እንዲወጣ የነበረውን አስተሳሰብ በመዋጮ ምክንያት ያለውን ጥሪት እየሸጠ እዛው እንዲሆን በመደረጉ፣ በተረጂነት የመኖር ፍላጎት እየገነገነ ሄደ፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዘን የምናየው ሌላው ጉዳት፣ የሀገረን ሰላምና ልማትን ከማወክ ጀምሮ፤ የራሳችን የመንግሥት መዋቅር የምንላቸውም አካላት በዚህ ውስጥ እየሰመጡ እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ ከዚህ ተነስቶም የተቸገረ የሚኖር ቢሆንም፤ ይሄን የተቸገረ ከማሳወቅ አኳያ ቁጥሮች እጅጉን ተጋንነው የሌለ የተረጂነት ቁጥር ይነገር ጀመረ፡፡
ይሄ ቁጥርን አጋንኖ የማቅረብ ችግር የተቸገረን ሰው ቁጥር በአስር አባዝቶ ማቅረብ ችግር የለውም በሚያስብል ደረጃ የሚገለጽ ነው፤ ምክንያቱም በሺህ ተባዝቶ ሲቀርብ ተስተውሏል፡፡ ለዚህ ምክንያትም የሌለና ያልተፈጠረ ነገር ተፈጥሯል፤ በጣም ብዙ ሰው ተጎድቷል፤ በጣም ብዙ ሰው ተርቧል፤ በጣም ብዙ ሰው ሞቷል ይባላል፡፡ እንደዚህ እየተባለ የሚሄደው ነገር ደግሞ፤ ተመልሶ ለራስ ጥቅምና ለግል ፍላጎት ማስኬጃ ይውላል፡፡ በተለያዩ ትስስሮችም በየእህል ወፍጮ ቤት፣ በየገበያውና ሱቆች ያለማንም ከልካይና ጠያቂ፤ አንዳንዴም ሕጋዊ በሚመስል መንገድ በጠራራ ፀሐይ የሚቸበቸብበት ሁኔታ አለ፡፡
ስለዚህ ጉዳቱ፣ እንደ ማህበረሰብ ታታሪነታችንንና ሥራ ፈጣሪነታችንን በጣም ጎድቷል፡፡ ካጋጠመን የትኛውም ዓይነት ተፈጥሯዊም ይሁን ሰው ሠራሽ ችግር የሚሰራው ድራማም እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ እናም ይሄኛው ገጽታው በጣም የተበላሸ ነው፡፡ ሀገር ክብሯ፣ ነፃነቷና ሉዓላዊነቷ ላይ ትልቅ ደንቃራ ፈጥሯል፡፡ ይሄም በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሚነገር አይደለም፡፡
በዚህ መልኩ በአንድ ሀገር ላይ ዜጎች በራሳቸው መንገድ የራሳቸውን ችግር መቅረፍ እያቃታቸው ሲሄድ፤ በየትኛው መንገድ አግዛለሁ፣ እደግፋለሁ የሚል ሰው በራሱ እና በተለያዩ ምክንያት መምጣቱ አይቀርም፡፡ ያ እየበዛ እየበረከተ ሲሄድ፤ የአንድ ሀገር ግማሽ እና አንድ ሶስተኛ በሚባል ደረጃ እየሰፋ ሲሄድ የሚያመጣው ችግር ። ይሄም ያ ሀገር በራሱ ፖሊሲ፣ በራሱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ በራሱ ሕግና ደንቦች ሊመራ አይችልም፡፡
ምክንያቱም ደገፍኩ የሚለው አካል፣ እኔ በምለው መንገድ መታዘዝ አለብህ፤ እኔ ያልኩህን መተግበር አለብህ፤ የምትወስነው ውሳኔ፣ የምትሄድበት መንገድ እና የምታወጣው ፖሊሲ እኔ በምለው መንገድ ብቻ ነው የሚሆነው በሚል ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ ይሄ ሲሆን ደግሞ ሀገር እንደ ሥርዓተ መንግሥት ሕገ መንግሥት ያላት፤ ሕግ እና ሥርዓት ያላት ልትመስል ትችላለች፡፡ በተግባር ሲታይ ግን ከሁሉም የወጣች ትሆናለች፡፡
በአፍሪካ ሀገሮች የምናየው ይሄንኑ ነው፡፡ በአፍሪካ ሀገሮች መንግሥታቱ አሉ ይባላል፤ የሚመሩት ግን ከሌላኛው ካፒታል ነው፡፡ መንግሥታት ገንዘብ አላቸው ይባላል፤ የገንዘቡ መጠን፣ የገንዘቡ ዓይነትና የገንዘቡ ጥንካሬ የሚለካው ግን በሌላኛው ካፒታል ነው፡፡ ይሄ በተለይም በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ስለዚህ ተረጂነት ስር እየሰደደ ሲሄድ፤ የዜጎችን የመሥራትና የመፍጠር ትልቅ ችሎታና አቅማቸውን እያኮሰሰው ይሄዳል፡፡ ሀገርንም እንደ ሀገር ነፃነትና ክብሯን፤ የዜጎችንም ክብር እና ሉዓላዊነትን እያኮሰሰ የሚሄድ ነው። ስለዚህ ሰብዓዊነት መልኩን ትቶ ወደ ተረጂነት ከተቀየረ የዜጎችንም ይሁን የሀገርን ህልውና ክፉ ነገር ውስጥ በማስገባት፤ ወደ ማይመለስበት አዘቅት እንዲወርድ የማድረግ አቅሙ በጣም ትልቅ ነው፡፡
ይሄ ከውጭ አካል አንጻር ሲታይ፤ ለምሳሌ፣ በ1885/86 ምዕራባዊያኑ አፍሪካን ለመቀራመት ተስማምተውና የፖለቲካ ውሳኔ ወስነው ተንቀሳቀሱ፡፡ ይሄ ሀገራችንን ጨምሮ አፍሪካን የማንበርከክ እቅድ ነበር፡፡ የ1940ዎቹ (1944 አካባቢ) የብሪቴን ዉድ ስምምነትም፣ ዓለም በሙሉ በዶላር ይመራ፤ ገበያውም ቢሆን በዶላር እንዲገዛ ይደረግ የሚል ነበር፡፡
በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ጣፋጭ በሚመስል ሃሳብ፣ ‹‹ሪስፖንሲቢሊቲ ቱ ፕሮቴክት›› የሚል ነገርን አሰፈረ፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ሀገሮች ያላቸው ሉዓላዊነት ኃላፊነት ነው እንጂ መብት አይደለም የሚል ነው። በዚህ ድፍረት በተሞላበት አሠራር፣ በአንድ ሀገር በሆነ መንገድ ሰብዓዊ መብት ቢጣስ እና እነሱ ደግሞ ተጥሷል ብለው መደምደሚያ ላይ ቢደርሱ የሌላ ሀገር ጣልቃ የሚገባበት (ለመከላከያውም ጭምር በጸጥታው ምክር ቤት እያስወሰነ) ሁኔታ አለ፡፡
በመሆኑም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውንም ስናይ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት፣ የምግብም ሉዓላዊነት የሚባል ነገር እንዳይኖር በማድረግ ለማንበርከክ ከመጀመሪያውም የተዘጋጀ ዓለም ላይ ተረጂነት ሲጨመርበት፤ ተጋላጭነ ታችንን በጣም ከፍ ያደርገዋል፡፡
ስለዚህ ተረጂነት መነሻውም መድረሻውም ህልው ናንም ነፃነትንም ሉዓላዊነትንም የሚያሳጣ፤ ዜጎችንም በማይጨበጥ ተስፋ ውስጥ አስገብቶ በዘላቂነት የሚወጡበት ነገር ላይ ሳይሆን፤ በማጥ ውስጥ እንዲሰነብቱ የሚያደርግ አደገኛ ልምምድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ አዲስ ፖሊሲ ቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱ፣ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ከመፍታት እና የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚገባቸው ብቻ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ምን እድልና አቅም ይፈጥርለታል? ምን የማስፈጸሚያ ስትራቴጂስ ተቀምጧል?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- በ2016 ዓ.ም የካቲት አጋማሽ ላይ፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ በአዲስ መንገድ በአዲስ ሁኔታ ተቀርጾ በሚንስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል፡፡ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ለሁሉም ነገር አቅጣጫ የሚሰጥና በር የሚከፍት በመሆኑ በሴክተሩ ለምናካሂደው መሠረታዊ የለውጥ ሥራዎች አንዱና የመጀመሪያው አቅም ነው፡፡
ይህንን የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ተከትሎም፣ የሕግ ማዕቀፎች እና የአደረጃጀት ክለሳዎች ተፈጥረው እየተሰራ ነው፡፡ የዚህ አንዱ ነጥብ፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር
ሥርዓታችን መንግሥት መር መሆን አለበት፤ ሁለተኛው፣ ሕዝቡ በየደረጃው እና በያለበት ቦታ ላይ ድርሻውን የሚወጣ ሊሆን ይገባል፤ ሶስተኛው፣ የላይኛው አካል ድጋፍ በሚያደርግበት ጊዜ የታችኛው አካል የሚገባውንና የሚችለውን እያደረገ መሆኑን በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል፤ ከዚህ ሲያልፍና ሲቸገር ደግሞ የእወጃ ወይም ይፋ የማድረግ ሥርዓትን ተከትሎ የመደጋገፍ ሂደት ይኖራል የሚል ነው፡፡
በዚህ ሂደት ላይ ቅጽበታዊ አደጋዎች ካልሆኑ በስተቀር፣ ዘገምተኛ ለሚባሉ የትኛውም አደጋዎች ምላሽ ሙሉ በሙሉ በየአካባቢው ሊሸፈን ይገባል የሚል ሲሆን፤ ቅጽበታዊ አደጋ ከሆነ ግን (እንደ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና እሳት በሚነሳበት ጊዜ) የፌዴራል መንግሥት በኮሚሽኑ በኩል 30 በመቶውን፣ ቀሪውን 70 በመቶ ደግሞ ክልሎች ይችላሉ የሚል ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ማዕቀፍ ተረጂነት እና ልመናን የማይፈቀድ እንዲሆን፤ በሂደቱ ግን ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖች ስለሚኖሩ ለእነዚህ በራሳችን አቅም ለመደገፍ ዝግጅት እንድናደርግ የሚል አካሄድ ነው፡፡
ለዚህም፣ የመጀመሪያው የሰብዓዊ ድጋፍ ግንባር ተብሎ የሚወሰደው ማህበረሰቡ ራሱ ነው፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ በየቀበሌው ብዙ አቅም አለ፡፡ እናም በሕዝባችን ውስጥ ያለውን አቅም በማደራጀትና በማደጋገፍ፤ የሚቸገረውን በመለየት እና የተለየውን ደግሞ በእለታዊነትም ይሁን በዘላቂነት ከችግር ለማውጣት ዝግጅት ማድረግ አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልልና ፌዴራል መዘጋጀት አለበት የሚል ሃሳብ አለ፡፡
ይህንን ለመሥራት የስትራቴጂክ ምግብ ክምችት (መጠባበቂያ ክምችት የምንለው) መያዝ ያስፈልጋል፤ የመጠባበቂያ ፈንድ ማደራጀት ያስፈልጋል፤ በማህበረሰብ ደረጃ የመተጋገዣ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ አልፎ እነዚህ የሚያዙባቸውን የመጋዘንና ሌሎች የተለያዩ ሥራዎችን ጭምር ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ለአደራሹም፣ መጠባባቂያ ክምችቱም፣ ለዚያ የሚያስፈልጉ የገንዘብና መሰል ሀብትም በየደረጃው ይደራጃል በሚል እየተሄደ ነው፡፡
ከዚያ አልፈን ስንሄድ ግን መሥራት ያለብን ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ ተረጂነት አጥፊ ነው፤ ክፉ ልምምድ ነው፤ አመንምኔ ነው የሚለው ላይ የጋራ አረዳድ መፍጠር ነው፡፡ ከዚያ ሰፈር ካልመጣ እዚህ የሚሰራ ነገር የለም የሚል አስተሳሰብም ትክክል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህች ሀገር ሀብታም ሀገር ናት፡፡
ለምሳሌ፣ ሰፊ የሚታረስ መሬት አለ፡፡ እስከዛሬ አርሰናል ተብሎ የሚባለውም የዚህን ግማሽም አይደርስም። በጣም በርካታ ወጣት ሃይል እና ሰፊ ጉልበት አለ፡፡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ወንዞችም ብዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ መልከዓ ምድሯ የሰጣት ተደማሪ ፀጋ አላት፡፡ አንዱ ጋ ድርቅ ሆነ ብለን ስናስብ፣ ሌላ ቦታ ላይ ልምላሜ፤ አንደኛው ቦታ ላይ የሆነ ነገር ተፈጠረ ብለን ስናስብ፣ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ የተሻለ ነገር አለ፡፡
ስለዚህ በመጀመሪያ፣ እነዚህን ፀጋዎች ይዘን ከተረጂነት መውጣት አስፈላጊ ነው ብለን መግባባት ይገባል፡፡ እናም ተረጂነትን ወደ ምርታማነት በመቀየር፣ ከምግብ ዋስትና እሳቤ ወጥተን፣ የምግብ ሉዓላዊነት ወደሚለው አስተሳሰብ መሄድ አለብን፡፡ ምክንያቱም፣ የምግብ ዋስትና የምንለው በአብዛኛው ሰዎች በየትም መጣ በየት የምግብ ፍላጎታቸው የሚያሟላውን ነገር ማቅረብ ማለት ነው፡፡ ይህ ከውጭም ሊመጣ ይችላል፤ ከውስጥም፣ ከሰፈርም ሊመጣ ይችላል፡፡
የምግብ ሉዓላዊነት ስንል ግን፣ የምንመገበውን ነገር ማምረት ማለት ነው፡፡ የምንመገበው ነገር እንዴት ነው የተመረተው? ማን ነው ያመረተው? የት ነው የተመረተው? የሚለውን ሃሳብ በሙሉ በመያዝ፤ በዘላቂነት የምግብም ይሁን ሌሎች ጉዳዮችን በራሳችን ባለቤትነት ራሳችንን ማዕከል አድርጎ ምርቱንም፣ ግብይቱንም፣ ገበያውንም ራሳችን ተቆጣጥረን መምራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለዚህ ነው ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ “አሁን ጉዟችን ወደ ምግብ ሉዓላዊነት ነው፤” የሚሉት፡፡ ይሄ ደግሞ ከምግብ ዋስትና የሰፋ አቅምም፣ የሰፋ ተልዕኮም ያለው ስለሆነ፣ በዚህ ላይ መግባባት አለብን፡፡
ሁለተኛው ነጥብ፣ ማጥራት የሚል ነው፡፡ ማጥራት ማለት ቅድም እንዳነሳነው፣ ሳይገባቸው እዚህ ውስጥ የሚገኙ፤ በተለያየ ምክንያት ይህንን ሰብዓዊ ድጋፍ ለመጠቀም ያሰፈሰፉ፤ ወይም ጥቅም ላይ ያሉ በተለያየ መንገድ ከዚህ ውስጥ መውጣት አለባቸው፡፡ እዚህ ጋ ልብ ሊባል የሚገባው በተለያየ ምክንያት ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልገው ሰው በየትኛውም ጊዜ ይኖራል፡፡ ይሄ ዓለም አቀፍ ልምድም ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በአካላዊ፣ በአካባቢያዊ፣ ተፈጥሯዊ አልያም በእድሜ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሰዎች ሊፈናቀሉ ወይም በቅጽበታዊ አደጋዎችም ሊጠቁ ይችላሉ፡፡
እንዲህ ሲሆን ሰዎች ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ግን ድጋፍ ነው እንጂ ርዳታ አይደለም፡፡ ርዳታ የሚባለው ሰው ሊደገፍ ሳይገባው ዝም ብለህ ስትሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም ሳይገባቸው በዚያ ውስጥ የተቀላቀሉ አካላት በሙሉ ተለይተው ሊታወቁ፤ በአንጻሩ መደገፍ ሲገባቸው የቀሩ ካሉም ለይቶ የማወቅና የማጥራት ሥራ በማከናወን ችግሮችን ማስተካካል ይገባል፡፡
ሦስተኛው ጉዳይ፣ ራሳችንን ማዘጋጀት ነው፡፡ ምክንያቱም ሌላው ዓለም የድጋፍ እጁን እያጠፈ ሂዷል፡፡ ፍላጎቱም ትኩረቱም ወደሌላኛው እየሄደ፤ ምናልባትም ሰብዓዊነትን ከመደገፍ ይልቅ ጦርነትን ማፋፈም የሚመስል ዝንባሌዎችም አሉ፡፡ ስለዚህ ይሄን እውነት ተገንዝበን ራሳችንን በራሳችን ለመደገፍ ልንዘጋጅ ይገባል፡፡
ለዚህ ደግሞ፣ አንዱ እና ትልቁ ማህበረሰቡ በራሱ የሚያደርገው መደጋገፍ ነው፡፡ ለዚያም መዘጋጀት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ስትራቴጂክ ክምችት በየደረጃው መያዝና መኖር አለበት፤ ገንዘብም መያዝ ይፈለጋል፡፡ ለዚህ መሰሉ ሥራ እንደ ሀገር ወደ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያስፈልገናል ብለን አስልተናል፡፡ ከዚያ ውስጥ ወደ 500 ሺህ መጠባበቂያ፤ ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ የእለት ደራሽ ይሆናል፡፡
ከዚያ ባለፈ፣ የግዥ ሥርዓቱን ለማከናወን የፈንድ ሥርዓት ስለሚያስፈልግ፣ ፈንድ መያዝ አለብን፡፡ ይሄ በፌዴራልም በክልሎችም ሊያዝ የሚችል፤ የሚያስፈልገን ስትራቴጂክም እንበለው የእለት ደራሽም ይሁን፣ ለቅጽበታዊ አደጋዎች የሥራ ማስኬጃ ለመሳሰሉት ለማስቀመጥ እና ለመግዛት ነው፡፡ ለዚህ የሚሆኑ መጋዝኖች፣ ማሽነሪዎችን እና ግብዓቶችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
የድጋፍ ሂደቱም፣ የሚደገፈውን ለይቶ የመደገፍ፣ ሲደገፍም የምግብ፣ የሥነ ምግብ፣ የመጠለያ፣ የቤትና የአልባሳትን በመሳሰሉ ድጋፍ ፈላጊው የቸገረውን ነገር በሙሉ በሚሸፍን መንገድ ተዘጋጅቶ የመሸፈን ነው፡፡ ሆኖም አሁን እኛ እየሄድን ባለንበት አግባብ የሚሸፈነውንም በትክክል አንሸፍንም፤ የማይገባውም እዚያ ውስጥ ገብቶ እየዳከረ የሌላኛውን ድርሻ ይሻማል፡፡
በመሆኑም በማጥራትና በመዘጋጀት ሂደት፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሚታገዘውና የሚደገፈው ሕዝብ እየጨመረ እንዳይሄድ ይህንን በደንብ አድርጎ ማስተዳደር፤ በድጋፍ ውስጥ ያሉ ዜጎችንም ከሌሎች ፕሮግራሞች ጋር እያቀናጁ ራሱን እንዲችል ማድረግና ከድጋፍ ማስወጣት ይፈልጋል። ለምሳሌ፣ ከሌማት ቱርፋት ፕሮግራሞች፣ ከክህሎት መር ሥራ እድል ፈጣሪ ፕሮግራሞች፤ ከኩታ ገጠም የእርሻ ሥርዓቶች ጋር እና ሌሎችም ጋር ማገናኘት ይቻላል፡፡ ሰው የመሥራት አቅም እስካለው ድረስም ሊሳተፍ ከሚችልበት አማራጭ ጋር ማቀናጀት ይቻላል፡፡
በዚህ መልኩ ከሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊነት ራስን መቻል ደረጃ ሲደርስ የማሸጋገር ሥራ ሊሰራ ይችላል፡፡ ማሸጋገር ሲባል፣ ለምሳሌ፣ ሰዎች ተፈናቅለዋል ብንል፤ እነዚህን የተፈናቀሉ ሰዎች በዘላቂ የልማት ፕሮግራሞች አማካኝነት ወይ ወደነበረበት እና ወደተነሳበት አካባቢ ሂዶ ምርቱንም እርሻውንም ደግፎ ወደ ሥራ እንዲገባ የማድረግ፤ ወይም እዚያው ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ ኑሮውን እንዲመራ የማድረግ፤ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ ሕይወት እንዲጀምር የማድረግ ሥራዎችን የመሳሰሉት ሊሰሩ ይችላሉ፡፡
ስለዚህ የማቀናጀት እና የማሸጋገር ሥራዎች የድጋፍ ፈላጊን መጠን በራሱ ጊዜ እየቀነ እንዲሄድ የሚያደርግ ሲሆን፤ ይሄ ምናልባትም እንደ ሀገር ከድጋፍ ፈላጊነት ወደ ድጋፍ ሰጭነት የመሻገር ነገር እየፈጠረ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ከተረጂነት ወጥተን ወደ ምርታማነት፤ ከተረጂነት ወጥተን ወደ ምግብ ሉዓላዊነት እንሻገር ስንል፤ እጃችን ላይ ያለውን በዚህ መንገድ እያጠራን እንሂድ የሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዙሪያ ያለውን ስሜት ለመገንዘብም ሆነ ይሄንን እሳቤ ለመዋቅሩም፣ ለሕዝቡም ከማሳወቅ አኳያ ምን ሰርታችኋል?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- በዚህ ሂደት ላይ በተለያዩ ከተሞች ወደ 32 ሺህ ከሚጠጉ አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ይህ ከአመራሮች ጋር የተደረገ ውይይት በከፍተኛ አመራሮች የተመራ ሲሆን፤ ክልሎችም በየራሳቸው ጊዜ በየደረጃው ወደ አስር ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ አወያይተዋል፡፡ ይህ ድጋፍ ተፈላጊ ነበር ወይስ አልነበረም በሚልም በድጋፍ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ጭምር ውይይት ተደርጓል፡፡ ሕዝቡ በአንድ ድምጽ ያነሳው፣ በየትኛውም መዋቅር እና መድረክ ላይ እኛ ድጋፍ ፈላጊ ነን እርዱን ብሎ የጠየቀበት አግባብ አለመኖሩን ነው፡፡
ይልቁንም ሕዝቡ የተናገረው፣ ከመጀመሪያውም የእናንተ የአመራሮቹ አባዜ ነው፤ ይህንን እኛ ፈልገን አይደለም ያመጣነው፤ ያመጣችሁትንም እናንተው ናችሁ የምትወስዱት የሚል ነው፡፡ እኛ ከእናንተ የምንፈልገው ግብዓት እንድትሰጡን ነው፡፡ ለመደገፋችሁ ርግጠኛ ከሆናችሁ፣ በእንስሳትም ይሁን፣ በእህልም ይሁን፣ በአትክልትም ይሁን፣ እኛ የሚያስፈልገንን እንድትደግፉን ነው፡፡ እናም ምርጥ ዘሩን፣ ማዳበሪያውን ማቅረብ ከቻላችሁ እኛ ሥራችንን መሥራት እንችላለን፡፡ የሚደገፍ እንኳን ቢኖር በራሳችን የመደጋገፍ እና አንዱ ለአንዱ የመድረስ ባሕላችንን ተጠቅምን እንደርሳለን የሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሕዝቡ ሃሳብና አስተያየት ምን ተምራችሁ፤ ምንስ የተለየ ነገር ለመሥራት አቀዳችሁ?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- የሕዝቡ ሃሳብና አስተያየት የፌዴራሉም የክልሎችም የቤት ሥራ ተደርጎ የተሰጠ የሕዝብ መልዕክት ነው፡፡ ይሄን ለማሳካት የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጿል፡፡ አሁን ላይ የሕግ ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው፡፡ ይህንን ዝግጅት በምናደርግበት ሂደትም ወደማምረት ትግበራ ተገብቷል፡፡ ቀደም ብዬ የገለጽኩት ሁለት ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን እህል ለዚሁ ዓላማ የማምረት ውጥን ተይዞ ወደሥራ መገባቱም የዚሁ አንድ አካል ነው፡፡
ክልሎችም እንደ ሀገር ለዘርፉ የሚያስፈልገንን ለማምረት ከ253 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማረስ፤ የሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እህል ፍላጎትን ለመሸፈን መንገዱን ጀምረዋል። ሥራውን ዘግየት ብለን የጀመርን ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜም ወደ አንድ መቶ ሺህ ሄክታር ተለይቶ ወደ እርሻም ተገብቷል። በሚቀጥሉት ወቅቶችም የተባለውን 253 ሺህ ሄክታር የመሸፈን አቅሙ አለ፡፡ የሚቻልም ነገር ነው፡፡
በዚህ ዓይነት መንገድ ስንሄድ ግን መከታተል ያለብን ነገር አለ፡፡ አንደኛው ተጠያቂነትን መፍጠር ሲሆን፤ በየደረጃው ለተሰጠው ኃላፊነት፣ ለተሰጠው ሥልጣን፣ ለሚያስተዳድረው የአስተዳደር እርከን ኃላፊነት እና ተጠያቂነት መኖሩ ማረጋገጥ አለበት፡፡ ምክንያቱም ለምርጫ ሲሆን ምረጡን የምንል፤ ሰዎች ችግር ውስጥ ሲገቡ የለንበትም የምንል፤ የመጣውን ሰብዓዊ ድጋፍ ደግሞ ላልተገባ አላማ የምናውል መሆን የለብንም፡፡ ይህ ክብረ ነክ ነው፡፡ ከዜግነትም በታች ነው፡፡ ሀገርን፣ ዜግነትንና ዜጋንም ጭምር መሆን የሚገባውን ቦታ የሚያሳጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን የማይመጥን ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሰው እንዲሰራ ተጠየቂነት በቦታው ላይ መሆን አለበት፡፡
ይሄ ግን ቀላል ነገር ነው ተብሎ የሚወሰድ አይደለም። ለ50 እና 60 ዓመታት በሰው ሥጋ፣ ደም እና አጥንት ውስጥ የገባ ጉዳይ ነው፡፡ መድረክ ላይ ለመናገር በጣም ቀላል ቢሆንም፣ መሬት ላይ ለመሥራት ግን ምናልባትም ወገብ የሚያጎብጥ፤ የሚገዳደርና መልሶ እዚያው ማጥ ውስጥ የሚከትም ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ላይ ሚዲያዎች ሊያግዙን፤ ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር እንዲሰፍን የሚያስችሉ ዘገባዎችን ማከናወን አለባቸው፡፡ ለዚህም ችግሩን ለማቃለል ማን እንዴት ተንቀሳቀስ፣ ምንስ አደረገ፣ ምንስ አቃተው የሚሉ ግንዛቤን ፈጣሪ እና አቅጣጫ አመላካች አጀንዳዎችን ተከታታይ በሆነ መልኩ ማስረጽ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ስለዚህ ሥራው ማን ምን አደረገልኝ ከሚል ወጥቶ፣ ማን ምን አደረገ በሚል ቅኝት እንዲመራ፤ የተጠያቂነት ሥርዓቱም ከላይ እስከ ታች ተጠናክሮ የሚሄደበትን ሁኔታ መፍጠር ትልቁ ጉዳይ ይሆናል፡፡ በመሆኑም በዚህ መልኩ መሥራት፣ ያሉንን አቅምና ልምዶች መጠቀም ከተቻለ በርግጥም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ከምግብ ዋስትና ወደ ምግብ ሉዓላዊነት መሻገር ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር አማካኝነት ከ25 ዓመታት በላይ ተረጂነት እንዲሰርጽ ከተደረገበት አካሄድ ምን የተለየ ሥራ በመሥራት ተረጂነት እሳቤን ሽሮ የምግብ ሉዓላዊነት አጀንዳ እውን ማድረግ ይቻላል?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- ከሰብዓዊ ድጋፍ፣ ራስን ወደ መቻል የሚለውን ስናነሳ፤ ዋናው ቁም ነገር ማምረት ነው። ምርት የማምረት ሥራ ደግሞ በራሳቸው በድጋፍ ፈላጊዎች ሊሰራ ይችላል፡፡ በአካባቢው መዋቅርም ሊሰራ ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ካሉት የልማት እንቅስቃሴዎች ጋር አስተሳስረን መፈጸም አለብን፡፡ ሰዎች በየጓሯቸውም ይሁን በጋራ፤ በግልም ይሁን በኩታ ገጠም፤ በሌማት ቱርፋትም ይሁን በክህሎት መር የሥራ እድል ፈጠራዎች፣ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሰዎች በዚህ ማዕቀፍ ስር እንዲቀናጁ በማድረግ ወደሌላኛው ከፍታ እንዲሸጋገሩ የማድረግ ሥራ በትኩረት መሰራት አለበት፡፡
በዚህ አግባብ ስንሰራና ዜጎችን ስናሸጋገር ምርታማነትን ስለምናሳድግ፣ የሚቀረው ሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊ ቁጥር በራሳችን አቅም የምንሸፍነው ይሆናል፡፡ ይህ ሲሆን የማንንም ርዳታ እና ድጋፍ አንፈልግም፡፡ አንፈልግም ብንል፣ የዓለም አቀፉ ድጋፍ እያሽቆለቆለ ሂዷል፡፡ ለምሳሌ፣ በረጂዎች ባለፉት ዓመታት ምናልባት 90 እና 80 በመቶ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ይሸፈን ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት ወደ 33 በመቶ ወርዷል፤ አሁን ባለንበት ዓመት እስካሁን ከ18 በመቶ በታች ነው፡፡
ከፍላጎት አኳያ ብናይ፣ ባለፈው ዓመት አራት ቢሊዮን ዶላር ነበር የጠየቅነው፡፡ ያገኘነው ግን ወደ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ እናም የዓለም አቀፍ ድጋፉ እያሽቆለቆለ የሚሄድበት ፍጥነት በራሱ እጅግ በጣም የሚያስደነግጥ ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ሊኖር ከሚችለው ነገር አንጻር እስኪ ራሳችንን እንቻል የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ካናዳ ላይ ስንዴ እየዘነበ ወይም ሌላ ቦታ አንድ ነገር እየተፈጠረ እዚህ ያለውን ይታደግልኛል የሚባል ነገር የለም፡፡ አሁን የሚሆነው ነገር ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ራስን መቻል እና ችግሩን መፍታት ነው፡፡ በተረጂነት እቀጥላለሁ ቢባልም እድሉ የለም፡፡
በጥቅሉ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎትን በትክክለኛው እናስተዳድረው፣ የምግብ ሉዓላዊነትንም እናረጋግጥ ሲባል፤ ሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊውን ገፍተን እናስወጣው ማለት አይደለም፡፡ እንደዚህ የሚል ሃሳብም የለንም፡፡ ሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቱም፤ ፈላጊውም ይኖራል፡፡ ነገር ግን ፈላጊውን ትክክለኛ እናድርገው፤ ፈላጊውን እናቀናጅና ከዛ እናስወጣው፤ እናሸጋግረውና የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊን ቁጥር እንቀንስ፤ በዚህ ውስጥ የተረጂነት አስተሳሰብ ሂደቱን እንዳይጫነው፣ የተረጂነት አስተሳሰብ እንዳያሰናክለው እንከላከል የሚል ነው፡፡ ይሄንን በተጠያቂነት መርህ፣ በምርታማነት መርህ እንሻገረው የሚል ነው፡፡
ከዛ ተርፎ የሚመጣ ካለ በራሳችን አቅም ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት እናድርግ ነው፡፡ ይሄን የምናደርገው ደግሞ ቀደም ሲል ባነሳኋቸው አግባብ ነው፡፡ የማህበረሰቡ የእርስ በእርስ መተጋገዝ ባሕል ተጠቅመን፤ የስትራቴጂክ ክምችትን አሳድገን፤ የእለት ደራሹን ይዘን፤ ፈንድ አደራጅተንና ዝግጁ ሆነን ስንጠብቅ ነው፡፡ ይሄን ስናደርግ የሆነ ነገር ሲመጣ አንዋከብም፤ አንበረግግምም፡፡ ምክንያቱም ተዘጋጅትን ነው ያለነው፤ ምን እንደሚመጣም እናውቃለን፡፡ በመሆኑም አቅጣጫው በዛ መንገድ እንሥራ የሚል ነው፡፡
በዚህ ዓይነት መንገድ ስንሰራ ትልሙን እውን ማድረግ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እንደ መንግሥትም የመቻል ታሪክ አለን፡፡ እንደ ሀገርም እኛ በጣም ታላቅ ሀገር ነን፡፡ በዓድዋ ላይ በጦርነት ማጥ ውስጥ ገብተን አሸንፈን የወጣን ሕዝቦች ነን፡፡ ባልተቆራረጠው ሥርዓተ መንግሥታችንም ብዙ የሉዓላዊነት ተንኳሾችን አሳፍረን እና አንገት አስደፍተን መመለስም የቻልን ሀገርና ሕዝብ ነን፡፡ ዛሬም እንደ ዓባይ ግድብ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በራሳችን አቅም ሰርተን እየተወጣን ነን፡፡
ታዲያ የተረጂነት እሳቤ ለምን እንደዚህ እጅና እግራችንን ጠላልፎ ሊይዘን ቻለ፣ የሚለውን መመርመርና ሚስጢሩን መፍታት ሲቻል፤ ትክክለኛ መልሱን ማግኘትም፤ ከችግሩ ልቆ መውጣትም ይቻላል፡፡ አሁን ያለው የተረጂነት እሳቤና መንገድ ኢትዮጵያንም፣ ኢትዮጵያውያንንም፣ ኢትዮጵያዊነትንም ስለማይመጥን ከዚህ መውጣት አለብን፡፡
ምክንያቱም፣ ለርዳታ እጁን ዘርግቶ ርዳታ የሚወስድ አካል፣ ሞራል ኖሮት ከሌላው ጋር እኩል መቆምና መገዳደር አይችልም፡፡ ይሄ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ሰብዕና ሊሆን የማይገባው፤ ገጽታችንንም የሚያበላሽ፤ ማንነታችንን የሚያኮላሽ ክብረ ነክ ጉዳይ ስለሆነ፤ ከዚህ እሳቤና ችግር በቻልነው ፍጥነት መውጣት አለብን፡፡
በሂደቱም አንደኛው ዜጋ የበለጠ ጉዳዩ ተቆርቋሪ፣ ሌላኛው ደግሞ ከፊል ተቆርቋሪ ሊሆን አይችልም፡፡ ጉዳዩ ሁሉንም የሚመለከት፤ የሁሉም ድርሻ፣ የሁሉንም ተሳትፎና ኃላፊነት የሚሻ ነው፡፡ በዚህ አግባብ ባለን አቅምና ጉልበት ሁሉ በስፋት ከተረባረብን ደግሞ ፈጣሪም ስለሚያግዘን የማናሳካበት ምክንያት ስለማይኖር፤ ሁላችንም በእኩል ቁጭትና ወኔ በርትተን ልንሰራ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በራስ አቅም ምላሽ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ለቅጽበታዊ አደጋዎች ምላሽ ከመስጠትም ሆነ፤ የአጋር አካላትን ድጋፍ ተቀብሎ የዘላቂ ልማት አቅም ከማድረግ አኳያ ያለው አካሄድ ምንድን ነው?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- ከቅጽበታዊ አደጋዎች ጋር በማያያዝ ትልቁ ጉዳይ ቅድመ ዝግጅት እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ አሁን ባለንበት ወቅት ላይ ዝናብ እንደሚበረታ የታወቀው ከስድስት እና ሰባት ወር በፊት ነው፡፡ ዛሬ ስለዘነበ አዲስ ክስተት ነው ማለት አይቻልም፡፡ ለዛ የሚሆን ዝግጅት ቀድሞ ማድረግ፤ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ያሉ ነገሮች ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል፡፡ ሕዝባችንም የመከላከሉም፣ የምላሹም አካል እንዲሆን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ከዛ ባሻገር አቅም በቻለና በፈቀደ መጠን ሌሎች የሚያግዙ ካሉ፣ ለእነሱም በራችን ዝግ አይደለም፡፡
በራስ አቅም ምላሽ መስጠትን ስናስብም፣ የሆነ ሰው አንድ ነገር ይዞ ቢመጣ፣ አይ ይዘህ ሂድ እያልን አይደለም፡፡ ይልቁንም ሰብዓዊ ድጋፍን በሚመለከት ሰዎች አቅም እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ መጠቀም የሚገባ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ይሄ ዓሣን ከምታበላው ዓሣን እንዴት እንደሚይዝ አስተምረው እንደሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ሰውን በየቀኑ እመግብሃለሁ ከማለት፤ ምግቡን ራሱ እንዴት እንደሚያመርት በማሳወቅና በማገዝ ላይ የተመሰረተ መደጋገፍ ነው የሚፈለገው። በዚህ ረገድ አቅም አለኝ የሚል ማንኛውም አካል ካለ አሁንም ሊደግፍ የሚችልበት ሰፊ እድል ስላለ ሊሳተፍ ይችላል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፉም ላይ አለን የሚሉ ካሉ ይዛችሁ እንዳትመጡ አላልንም፡፡ እያልን ያለነው፣ ዓለም አቀፉ ድጋፍ እየነጠፈ ሄዷል፡፡ እናም በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካል ሌላ የማንንም ይሁንታም ይሁን ርዳታና ድጋፍ ሳይጠይቅ፣ ድጋፍን በራሱ ለማድረስ ዝግጁ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ሆኖም በአቅሙ ሰርቶ ሲያበቃ የሚያቅተው ነገር ካለ የሚቀጥለውን አካል በይፋ ይጠይቃል፡፡ የጠየቀው ነገር ትክክለኛ መሆኑ እየተለየም ድጋፎች ይቀጥላሉ፡፡ ምክንያቱም ዜጋን በተመለከተ የመጀመሪያው ተጠያቂ ራሱ መንግሥት (በየደረጃው ያለው የመንግሥት አካል) ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኮሚሽኑ የሥራ ተሞክሮ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ከፍ ላለ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ሰብዓዊ ጉዳት የሚዳርግ፤ የኮሚሽኑም የቀጣይ ጉዞ ፈተና መሆኑን ተገንዝቦ ከመፍታት አኳያ ምን ታስቧል?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- ይሄ ትክክለኛ ችግርም፤ ፈተናም ነው፡፡ ችግርና ፈተናነቱ ከአጋር አካላት ጋር ብቻ ሳይሆን፤ እንደ መንግሥት መዋቅርም ፈተና ነው፡፡ እንደ መንግሥት መዋቅር የቅድመ አደጋ ብለን ስናነሳ እና ወደ ተቋማት ስናመጣው የአደጋ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት በእቅዶቻቸው ውስጥ አስገብተው እና በጀት መድበው፣ እንዲሁም የሰው ኃይል አሰማርተው መተግበርን የሚመለከት ነው፡፡
ለምሳሌ፣ ይሄንን ከግብርና አንጻር ብንመለከተው፤ ድርቅ ሊመጣ ሲሆን ሁሌም ቅድመ ትንበያ አለ፡፡ በዚህ አካባቢ ድርቅ ሊከሰት ነው ሲባል የእንስሳት መኖ ያዘጋጃል፤ የእንስሳትን ቁጥር ይመጥናል፤ በአካባቢው ላይ ሊዘራ የሚገባውን ድርቅን ሊቋቋምና ቶሎ ሊደርስ የሚችል ነገር ካለ በእሱ ላይ ይሰራል። እነዚህን ከሰራ ድርቁ እንኳን ቢከሰት ማስታገሻ ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ ምናልባት በጣም የማይቻል ሁኔታ እንኳን ቢኖር ሰውንም፣ አካባቢውንም፣ እንስሳውንም ወደሚመች አካባቢ የማስጠጋት ነገርን ሁሉ ሊያካትት ይችላል፡፡ ይሄ ማለት የተለያዩ የአዳብቴሽን እና ሚቲጌሽን ወይም ችግሩን የማላመድና ችግሩን የመጋፈጥ ነገሮችን እየፈጠሩ መሄድ ማለት ነው፡፡
በውሃ ዘርፉም በተመሳሳይ ነው፤ ውሃ ሊጠፋ ነው፣ ላይኖር ይችላል ከተባለ፤ መውጫ መንገዶቹንና የመፍትሔ አማራጮቹን በመፈተሽ ይዘጋጃል፡፡ በጤናውም ዘፍር ቢሆን እንደዚሁ የሆነ ችግር ሊፈጠር ነው ከተባለ፤ ስለሚፈጠረው ነገር ቀድሞ መረዳት እና የመፍትሔ መንገድ ማበጀት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ፣ የተለያዩ ወረርሽኖች ሊከሰቱ ከሆነ፤ የጤና ተቋማት ችግር ሊያጋጥማቸው ከሆነ፤ የመድኃኒት ክምችት የሚያስፈልግ ከሆነ፤ የቅድመ ክትባት ሥራ የሚያስፈልግ ከሆነ፤… ጉዳዮቹን ቀድሞ ተረድቶ እንደ የጉዳዩ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መፍጠርን የሚመለከት ነው፡፡
የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም፣ እዚህ አካባቢ የሆነ ነገር ሊፈጠር ነው የሚለውን ሲገነዘብ፤ እንደሚከሰቱት አደጋዎች ባህሪ ቀድሜ የምግብ ክምችት መያዝ አለብኝ፤ ምግብ ነክ ያልሆነ ክምችት መያዝ አለብኝ፤ የያዝኩትንስ የት ነው የማዘጋጀው፤ የሚሉ ሥራዎችን መሥራት ማለት ነው፡፡ አንዱ ፈተናም የሚጀምረው እዚህ ጋ ነው፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ሥራ በጀት በትክክል ተመድቦ አይሰራም፡፡ ይሄ የመዋቅራችንም ችግር ነው፡፡
ይሄ በመደበኛነት የእቅድ አካል ቢሆንም፤ ችግሮች በሚፈጠሩባቸው አካባቢዎች ላይ ቀበሌው፣ ወረዳው፣ ዞኑ እና ክልሉ የአደጋ ስጋት ፕሮፋይል (ምን ዓይነት አደጋ አለ፣ ይሄ አደጋ ማንን ተጋላጭ ያደርጋል፣ ይሄንንስ መቋቋም ይቻላል ወይ የሚሉ ጉዳዮች) ሊኖረው ይገባል፡፡ ምክንያቱም የአደጋ ስጋት የከፋ ውጤት የሚባለው የአደጋው መኖር አለመኖር ብቻ ሳይሆን፣ አደጋውን የመቋቋም አቅሙንም ጭምር ስለሚመለከት ነው፡፡ የእነዚህ ሁለቱ ሚዛን ነው የከፋ ጉዳት የማስከተል እና አለማስከተል ውጤት የሚታየው፡፡ ሂሳቡም ይሄ ነው፡፡
ስለዚህ የቅድመ አደጋ ሥራ ላይ ሀብት መድቦ ቀድሞ በመሄድ መሥራት ላይ ያለውን ክፍተት መሻገር በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አሁን ላይ የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ብለን እየሰራን ያለነው አንዱ ሥራ ይሄንን ክፍተት እንዲሸፍን ነው፡፡ ይሄ በሚያስፈልግበት ጊዜ በተቻለ መጠን የመንግሥት መዋቅሩ መጀመሪያ በሴክተሮች የሚሰራው ሥራ ይኖራል፤ ከዛም ለአደጋ ስጋት ምላሽ ተብሎ ለኮሚሽኑ የሚመደብ አለ፡፡ በእነዚህ ሁለቱ ያልተሸፈነና የተንጠባጠበ ነገር ሲኖር ደግሞ በአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ይመለሳል የሚል ስሌት ይዘን ነው እየሰራን ያለነው፡፡ ይሄው ሥራ በመንግሥት በኩልም ይሁንታ ተገኝቶበት እየተከናወነ ያለ ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የአደጋ ጊዜ ምላሽ ነው፡፡ በአደጋ ወቅት ባለው ምላሽ ላይ ብዙ ጊዜ ሲታይ ይብዛም ይነስ ሀብት ይመደባል፡፡ ለምሳሌ፣ በዚህ ዓመት (በ2016) ከ40 ቢሊዬን ብር በላይ በመመደብ መንግሥት በክልልም፣ በፌዴራልም ያወጣው ወጪ አለ፡፡ በዚህ መልኩ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ላይ ያሳረፍነው ሀብት በየደረጃው በቅድመ አደጋ ላይ አውለነውና ተሰርቶበት ቢሆን ኖሮ ብዙ ነገር መታደግ ይቻል ነበር፡፡ ምክንያቱም የቅድመ አደጋ ሥራ ከአደጋ ጊዜ ሥራ በብዙ እጥፍ ያነሰ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡
ይሄንን በገንዘብ ስሌት ለማየት ብንሞክር፤ ለአደጋ ጊዜ ምላሽ ወይም ለቀውስ አስተዳደር የምናወጣው ሃያ ዶላር ቢሆን፤ በቅድመ አደጋ ላይ ሰርተን ቢሆን ኖሮ በአንድ ዶላር ሊሰራ ይችል ነበር፡፡ እናም አንድ ዶላር ኢንቨስት ማድረግ ተቸግረን፣ ሃያ ዶላር ነው ወጪ እያወጣን ያለነው፡፡ ስለዚህ የቅድመ አደጋ ሥራ እጅግ ተፈላጊም፤ የሚደገፍም፤ ከወጪም አኳያ ተመራጭ ነው፡፡ ሆኖም የአደጋ ስጋት ሥራ አመራራችን ውድ በሆነው መንገድ እየተጓዘ የቆየ ነው፡፡
ሦስተኛው ጉዳይ፣ የድህረ አደጋ ምላሽ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በቅድመ አደጋ የሚሰራው ሥራ አደጋ እንዳይከሰት ሲሆን፤ በድህረ አደጋ የሚሰራው ደግሞ በተሻለ ሁኔታ ለማቋቋም እና ሰው ተመልሶ ወደ አደጋው እንዳይመጣ ለመከላከል ነው። ሆኖም እንደ ቅድመ አደጋ መከላከሉ ሁሉ፣ በድህረ አደጋ ምላሽ ላይም ሀብት አይመደብም፡፡ አጋር አካላትም ቢሆኑ ሀብት አይመድቡም፡፡ ሁሉም የሚያተኩረው ቀውሷ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ቀውሱ ፊት ለፊት የሚታይ እና የሚንቀሳቀስ ነገር ስላለው፣ ሁሉም እሷው ላይ ለመረባረብ ይሞክራል፡፡ ከዛ በኋላ ግን ማንም ሰው የለም፡፡
ነገር ግን በድህረ አደጋ ላይም የሚሰራው ሥራ በተሟላ መልኩ ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ፤ ወይም ሰብዓዊነትን፣ ሰላም ግንባታን እና ልማትን ባማከለ መልኩ አቀናጅቶ መሥራት ቢቻል ኖሮ፤ አሉ የምንላቸውን ችግሮች በሙሉ መድረስ ይቻል ነበር፡፡
በመሆኑም እነዚህን ሦስት ጉዳዮች ወይም የቅድመ አደጋ፣ የአደጋ ወቅት እና የድህረ አደጋ ሥራን ሚዛን አስጠብቆ መጓዝ ፈተና ነው፡፡ ይሄ እንደ አጋር አካላትም ሲታይ ፈተና ነው፤ በራሳችን ከታች ጀምሮ ባለው የመንግሥት መዋቅርም ፈተና ነው፡፡ ስለዚህ መግባባት አለብን ከምንላቸው ጉዳዮች አንዱ ይሄ ነው፡፡ በዚህ ላይ ተግባብተን እና ሀብትን በሚዛናዊነት መድበን፤ አንደኛው ላይ የምንመድበው በሌላኛው ላይ ያለውን ወጪ የሚቆጥብ/የሚቀንስ ነው የሚለውን ይዘን መሥራት ብንችል ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ሳይሆን ቀርቶ፣ በከፋ መንገድም ቢሆን ሚዛን ጠብቆ የመሥራትን አስፈላጊነት እየተማርን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በከፋ መልኩም ቢሆን የተገኘውን ትምህርት ይዞ በቀጣይ የተሻለ ሥራን ከማከናወን አንጻር የኮሚሽኑ አቋም እና መልዕክት ምንድን ነው?
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- በከፋ መንገድ መማር ማለት፤ ቅድመ አደጋ ላይ በደንብ ባለመሥራታችን፤ በድህረ አደጋም በትክክል ባለመሥራታችን ምክንያት፤ በአደጋ ወቅት ሥራ ላይ ብቻ አተኩረን እዛው እየሰመጥን ምን እያስከተለ እንደሆነ በተግባር መመልከትና ትምህርት መውሰድ ማለት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ባይሆንና ይሄንን ማድረግ እንደሚገባን በመልካም መንገድ ብንማረው ጥሩ ነበር፡፡ ግን ሆነ፡፡ በመሆኑም በችግርም ቢሆን የተገኘውን ትምህርት በመውሰድ ነገን የተሻለ ነገር ለመፈጸም ነው እየሄድን ያለነው፡፡
ሆኖም አሁንም፣ በዚህ ረገድ በኮሚሽናችን በኩል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ በዚህ ጥልቀት እንዲያዝ መረዳት እንዲኖር፤ ይሄን መረዳትም ወደ ተግባር እንዲቀየር በማድረግ ሰፊ ሥራ ይጠይቀናል፡፡ ሚዲያዎቻችንንም በዚህ ረገድ በስፋት ማሰማራት ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም፣ ስለ ጉዳዩ አንድ ቀን ተናግሮ ሰው ተገንዝቧል ለማለት አይቻልም፡፡
የምንፈልገው ውጤት እስከሚገኝ ድረስ ደጋግሞ መናገር፤ ደጋግሞ መወያየት፤ ደጋግሞ መፍትሔ መፈለግ፤ መፍትሔውም እንደየአካባቢው እና እንደየነባራዊ ሁኔታው እንዲተገበር ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ፈጠራዎችን፣ በማከል ጭምር መሥራትን የሚፈልግ ነው፡፡ እናም ከተባበርን እናሳካዋለን፤ የምግብ ሉዓላዊነትን ማሳካትም ከእኛ ሩቅ አይደለም፡፡
ለምሳሌ፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቀደም ሲል በቢሊዬኖች በሚቆጠር ገንዘብ ነው ስንዴ ከውጭ ይገዛ የነበረው፡፡ አሁን እኔ እስከማውቀው ድረስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከእኛ ዶላር አውጥተን ስንዴ አስገብተን አናውቅም። የምንገዛውንም ከራሳችን ከሀገራችን ገበያ ነው፡፡ ከዛም አልፈን ባለፉት ሁለት ዓመታት በመጣንበት ሂደት የተረጂ ቁጥር እየቀነሰ ሄዷል፡፡
ለአብነት፣ ከዛሬ ሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት ወደ ሃያ ነጥብ አንድ ሚሊዬን ነበረ፡፡ ይሄ አሃዝ የእለት ደራሽ ድጋፍ ፈላጊ ብቻ ነው፡፡ በመካከል ወደ 15 ነጥብ አራት ሚሊዬን ደርሶ ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ወደ አስር ነጥብ አራት ሚሊዬን ነው የነበረው፡፡ በዚህ ሲዝን ላይ ደግሞ ወደ ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዬን ነው እያስተናገድን ያለው፡፡ ስለዚህ የተረጂነት አስተሳሰብ እየቀነሰ ሄዷል፡፡ በዚህ ሂደት ግን የአየር ንብረት ለውጡ መልካም ነበር፡፡ ይሄ መልካም የአየር ንብረት ባለፈው በልግም፣ እያለፈ ባለው ክረምትም የታየ ነው፡፡
አሁን ላይ እየተሻሻለ የሄደው የተረጂነት አስተሳሰብም በመልካም ጅማሮነት የሚያዝ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ አመራሮቻችን ተረጂነት ክፉ ልምምድ ነው በሚለው አጀንዳ ላይ እየተነጋገሩበት ነው፡፡ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጀምሮ በየደረጃው፣ በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጭ አምርቶ ራሱን የማይመግብ ማህበረሰብ ነፃነቱ የተሟላ አይደለም፤ ልመና ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን የሚመጥን አይደለም የሚል ጠንካራ አቋም አለ፡፡
ይሄ ደግሞ የመንግሥት አቋም እንጂ፣ የሆነ ኮሚሽነር ተነስቶ የሚያቀርበው ንግግር ወይም የዜና ፍጆታ ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥትም፣ እንደ ፓርቲም ጭምር አቋም የወሰደበት ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን፣ ከተረጂነት የመላቀቅ እድል የሉዓላዊነት እና የማንነት ልኬት ማሳያ እንደመሆኑ፤ ለተፈጻሚነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላይ ያሳሰቡበትን ሁነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመንግሥት መድረኮችም ይሄው አቋም ነው ያለው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት እና በየደረጃው በነበረን የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት መድረክም፣ ይሄው ጉዳይ እንደ አቋም ተወስዷል፡፡ በዚህ ረገድ የፌዴራልም ሆነ የክልል ሥራም ተለይቶ ተቀምጧል፡፡ በየጊዜው በምናደርገው ክትትልም የብልጽግና ፓርቲ የበላይ አመራሮችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች በቅርበት ክትትል የሚደረግበት ርዕስ ነው፡፡
እናም አጀንዳው በመንግሥት ተይዟል፤ በገዢው ፓርቲ ተይዟል፤ ሕዝቡም በአስተሳሰብ ደረጃ ከዚህ የተለየ ሃሳብ የለውም፡፡ ስለዚህ መሃል ላይ ሊያጋጥም የሚችል ችግር ካለ ወይ ስንፍና ነው፤ ወይም ብልሽት ነው፡፡ ስንፍናን እና ብልሽትን ደግሞ በመዋቅራችን ውስጥ በመታገል በትኩረት ይሰራል፡፡ በዚህ ረገድ ተጠያቂነትም እንደሚኖር የተረጋገጠ ነው፡፡
በአጋር አካላትና በመሳሰሉት በኩልም ውዥንብር ሊኖር ይችላል፡፡ ውዥንብሩ እኛ አልተፈለግንም የመሳሰለ ነገር ከሆነ፤ እኛ ማንም አንፈልግም አላልንም፡፡ እያልን ያለነው እኛን በሚያሳክከን ቦታ ላይ አግዙን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከተረጂነት ለመውጣት ሰው የራሱን አቅም አውጥቶ እንዲጠቀም እንዴት እናግዝ፤ እንዴት እንደግፈው የሚል እሳቤን ከመያዝ አኳያ የሚገለጽ ነው፡፡
በመሆኑም በዚህ መልኩ የሚመጣን ነገር በሰብዓዊነት ቋት ውስጥ እንከትታለን፡፡ ምክንያቱም በድጋፍ ስም እጃችንን አስገብተን እንበጠብጣለን የሚል እስከ ሌለ ድረስ ድጋፉ መልካም ነው፡፡ ችግር የሚሆነው ትንሽ ነገር ከትተናልና፣ እኛ ነን የምንወስንላችሁ ሲባል ነው፡፡ ይሄ ከተባለ ዞሮ ዞሮ ሁነቱ ክብረ ነክ ነው፤ ክብረ ነክነቱም ለሀገርም ለዜጋውም ነው፤ ነፃነትንም፣ ሉዓላዊነትንም የሚጎዳ ነው፤ ያልነው ነገር ነው ተመልሶ የሚመጣው፡፡ ይሄ ደግሞ መፈቀድ የሌለበት ነገር ነው፤ አንፈቅድምም፡፡
ነገር ግን ልንደጋገፍ ነው የሚል አካል ከመጣ፤ አይ የእናንተን ድጋፍ አንፈልግም አንልም፡፡ እንደዛም እያልን አይደለም፤ አልተባለምም፡፡ እያልን ያለነው የራስን ሰብዓዊ ፍላጎት በራስ አቅም ማሟላት ይቻላል፡፡ ይሄ ደግሞ የምግብ ሉዓላዊነት ጥያቄ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ማድረግ ትችላለች፡፡ ለዚህ የሚያስፈልገው ሁለት ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን ያክል እህል መሰብሰብ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ዓመቱን ሙሉ የሚታረሰውን ወቅትና የመስኖ ተግባራትን ሳይጨምር፣ ከዚህችኛዋ ክረምት ብቻ የሚሰበሰበው ከአምስት ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን በላይ ነው።
ስለዚህ እያነሳን ያለነው የሚቻለውን ነገር ስለሆነ ሁሉም ሰው ከተረባረበ፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ክንውንን ሚዛኑን ጠብቀን ከተጓዝን፣ እና የተረጂነት እሳቤን ጨከን ብለን ከውስጣችን ብናወጣው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊት በዓድዋ ላይ ለአፍሪካውያን ነፃነት ፋና ወጊ እንደሆንን ሁሉ፤ አሁንም በምግብ ሉዓላዊነት ፋና ወጊ መሆን እንችላለን፡፡ ለዚህ ደግሞ አፍሪካ ዓለምን ይመግባል ብቻ ሳይሆን፤ አፍሪካ ዓለምን የሚያጥለቀልቅ ሀብት አላት፡፡
ነገር ግን አፍሪካ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ንቅት ብሎ፤ ራስን በራስ መርቶ፤ የራስን ደረጃ አውቆ መንቀሳቀስ ላይ ድክመቶች አሉ፡፡ በመሆኑም መልዕክቴ፣ ቀድሞ የፖለቲካ ቅኝ ግዛት ስንል የነበረውን ሥርዓት በድል እና ነፃነት እንደተካነው ሁሉ፤ አሁንም በኢኮኖሚ ቅኝ ግዛት ውስጥ ከመሆን ወጥተን ራሳችንን እንችላለን፤ ትልቅ ቦታም እንደርሳለን፡፡ በዚህም ሕዝባችንንም፣ ራሳችንንም ነፃ እናወጣለን፤ የሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ሆነው፣ ለሰጡን ሃሳብና ማብራሪያ አመሰግናለሁ!
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው፡- እኔም ሃሳቤን እንድገልጽ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ!
ወንድወሰን ሽመልስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም