ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች ወዲህ የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን በሚጎዳ ተግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ ይህን ተግባር ወደ ጠላትነት ከፍ አድርገውም በቅርቡ የግብፅን ጦር በራቸውን ከፍተው ተቀብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ልዩነት ማስፋትም የዘወትር ሥራቸው አድርገውታል፡፡ ብዙ ዋጋ እየከፈለች ከለላ ስታደርግላቸው የኖረችውን ኢትዮጵያን በመካድ ሩጫም ተጠምደዋል፡፡ የዚያድ ባሬን ስህተት ለመድገምም እየተጣደፉ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል ከሶማሊያ እንዲወጣ ከባድ ሴራ መጠንሰስ ከጀመረ ከራርሟል፡፡ ፕሬዚዳንት ሼህ ሐሰን ሞሐመድ በተደጋጋሚ ከካይሮ እስከ አሥመራ ብሎም እስከ ሪያድ ምልልስ ማብዛታቸው የማታ የማታ እውነቱን አደባባይ ይዞት ወጥቷል፡፡ መንግሥታቸው ለዓመታት ለሠላሙ መከበር ዋጋ ሲከፍል የኖረውን የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደ ወራሪ ኃይል ለመክሰስ አቅም ሆኗቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ2006 ጀምሮ በሶማሊያ ያሰማራችው ሠላም አስከባሪ ኃይል ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ሞቃዲሾን አስለቅቆ ጊዜያዊ መንግሥቱ በእግሩ እንዲቆም አስችሏል፡፡ እስከ ደቡባዊቷ ባይደዋ ከተማ ድረስ ዘልቆም የአሸባሪውን ቡድን አባላት በመደምሰስ ለሶማሊያ መንግሥትና ሕዝብ እፎይታን ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ስትከውን ዓለም እጁን አጣጥፎ ዳር ቆሞ ነበር ሲመለከት የቆየው፡፡
ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሠላምና መረጋጋት በርካታ ጦር፣ ገንዘብና ቁስ ብትሰዋም በተቃራኒው ወራሪ አድርገው ጥላሸት ለመቀባት ሌትተቀን ሲለፉ ማየት አሳፋሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በብዙ ግፊትና ጫና 2008 ላይ ሶማሊያን ለቆ ወጣ፣ በ2007 የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ አሚሶም የተባለ የሠላም አስከባሪ ኃይል አሰማርቶ ነበር፡፡ ሆኖም የአሚሶም አቅም ውስን ስለነበር አልሸባብን እንዳይጠናከር ማድረግ አልተቻለውም፡፡
በኢትዮጵያ ጦር መስዋዕትነት ተዳክሞ የቆየው አልሸባብ ዳግም ማንሰራራት የጀመረው ያኔ ነበር፡፡ በሶማሊያ የተመሠረተው ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር ጨርሶ ሳይጠፋ ማቆየት ቢቻልም የአልሸባብን ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት መግታት ከባድ ሆኖበት ነበር፡፡ ከጅቡቲ፣ ቡሩንዲ፣ ሴራሊዮን፣ ኬንያና ከዑጋንዳ የተውጣጣ ሃያ ሁለት ሺ የአፍሪካ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ጦር በተሠማራባቸው ከ2010 ጀምሮ በዘለቁት ዓመታት የአልሸባብ ጥቃት አይሎ ታይቷል፡፡ በዚህ የተነሳ እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት ይሁንታና በራሱ በሶማሊያ መንግሥት ፍላጎት ኢትዮጵያ ከ2013 ጀምሮ የሠላም አስከባሪ ኃይሏን ዳግም አዝምታለች ፡፡
የኢትዮጵያ ጦር በተናጠል ወደ ሶማሊያ መሠማራቱ በፍጥነት የሀገሪቱ ፀጥታ ላይ መሻሻል እንዲታይ አድርጓል። በ2014 መጀመሪያ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ውስጥ ያዘመተችው ሠራዊት በአሚሶም ተልዕኮ ስር እንዲካተት ፈቀደች፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በተናጠል ባካሄደችው ስምምነት ተጨማሪ ሠራዊት አዝምታለች፡፡
በ2022 ተልዕኮው በተጠናቀቀው አሚሶም ስርም ሆነ በተናጠልና በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ሠላም አስከባሪ ተልዕኮ (አትሚስ) ስር ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሠላም የማስፈኑን ሥራ ቀጥላበታለች፡፡ የአትሚስ ተልዕኮ በ2024 መጨረሻ ሲጠናቀቅ በሌላ ሠላም አስከባሪ ኃይል እንደሚተካ ይጠበቃል፡፡
ይህ ሊሆን በተቃረበበት በዚህ ወቅት ግን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼህ ሞሐመድ ከግብፅ ጋር በኢትዮጵያ ላይ ሴራ ሸረቡ። ሰውየው የበትረ መንግሥታቸውንና ቤተመንግሥታቸው (ቪላ ሶማሊያ) ዘብ የሆነውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ወራሪ ኃይል አድርገው በመሳል በፖለቲካ ሴራ መጠመዳቸውን በመጀመሪያው ዙር የሥልጣን ዘመናቸው ደጋግመው አሳይተዋል፡፡ 2017 ላይ ግን በመሐመድ አብዱላሂ መሐመድ (ፋርማጆ) ተተኩ፡፡
ፋርማጆ የሶማሊያም ሆነ የአፍሪካ ቀንድ ቀንደኛ ጠላት እንደ አልሸባብ አይነት የሽብር ቡድን መሆኑ ቀድሞ ገብቷቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ከአጋር አካላት ጋር ተባብረው አልሸባብ ላይ ጠንካራ ዘመቻ የከፈቱት፡፡ አልሸባብ በፋርማጆ የሥልጣን ዘመን በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሞ ታይቷል፡፡ አልፎ አልፎ ጥቃት ቢፈፅምም የያዘው አካባቢ ተመናምኖ ውስን ቦታ ላይ ተገድቦ ነበር፡፡ በፋርማጆ ዘመን ፀረ አልሸባብ ዘመቻው የተሳካ ቢሆንም ሼህ ሐሰን ዳግም ወደ ሥልጣን መጥተዋል፡፡
ሼህ ሐሰን ከጎረቤት ሀገሮች እስከ ሩቅ ምስራቅ ጉብኝት ሲያደርጉ ግን ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ስድስት ወራት እንደፈጀባቸው መረሳት የለበትም፡፡ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ከማበር በተጨማሪ የዚያድ ባሬ የታላቋ ሶማሊያ ሕልም አቀንቃኝነታቸውም ኢትዮጵያን በበጎ ዓይን እንዳይመለከቷት ያደረገ ምክንያት መሆኑን መጠርጠር አይከፋም፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ዓመት ለሶማሊያ ዋጋ ስትከፍል የት እንደነበሩ የማይታወቁ ኃይሎች ዛሬ ድንገት መጥተው ‹‹ሞታችንን ከሶማሊያ ጋር ያድርገው›› ማለታቸው ሌላ መዘዝ ይዞ እንደሚመጣ የተረዱት አይመስልም። ኢትዮጵያ ያን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለችው ለሶማሊያ ሕዝብና ለቀጣናው መረጋጋት ነው፡፡
ሶማሊያ እንድትረጋጋና ጠንካራ መንግሥት እንዲኖራት ኢትዮጵያ ብዙ ለፍታለች፡፡ ከአልሸባብ ጋር ከመዋጋት አንስቶ የሶማሊያን ወታደሮች እስከ ማሠልጠንና ማስታጠቅ ጥረት አድርጋለች፡፡ ዛሬ ላይ ግን ኢትዮጵያን ከአልሸባብ በባሰ ጠላት አድርገው ፈርጀዋታል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ‹‹የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠንካራና ጀግና ተዋጊ ነው›› ሲሉ የሠላም አስከባሪ ኃይሉ በሶማሊያ ያሳየውን ስኬታማ ሥራ ለዓለም መስክረዋል፡፡
ይህን ታሪክ ዛሬ ገልብጠው ለመፃፍ የተነሱት የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን የወረራ ስጋት ቀለበት ውስጥ ለመክተት እየተጣደፉ ነው፡፡ በጎረቤት፣ ወዳጅና የክፉ ቀን ደራሽ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ይህን አይነት ቁማር መሥራት የትም እንደማያደርስ ግን ከታሪክ አልተማሩም፡፡
ኢትዮጵያ ለሶማሊያ የከፈለችውን ውለታ ወደ ጎን በመተው የሠላም አስከባሪ ኃይሏና መከላከያ ሠራዊቷን ስምና ዝና የማጠልሸት ሰፊ ዘመቻ ተከፍቷል፡፡ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በዲፕሎማሲ ጥረት በቱርኪዬ አማካኝነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑ እየታወቀ ከቀጣናው ውጪ የሆኑ አካላትን ወደ አካባቢው ጦር እንዲያስገባ መጋበዝ ጠብአጫሪነት ነው፡፡
ይህን ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ የመክተት ዘመቻ ኢትዮጵያ በዝምታ እንደማትመለከተው በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል ከሳምንት በፊት የወጣው ጠንካራ መግለጫ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ይህን ሴራ ተረድተው በአንድነት ሊቆሙና ሊሰባሰቡ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለሶማሊያ ሠላምና አንድነት ሞተናል። ኢትዮጵያውያን ለሶማሊያ ያላቸውን ክብር ከማንም በላይ አሳይተዋል፡፡ በሶማሊያ የግዛት አንድነት ላይም የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ጥያቄ አንድና አንድ ነው፡፡ የባሕር በር ጥያቄ፡፡ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር የራሷ ወደብ እንዲኖራት ጥረት ማድረጓ ታሪክም ሆነ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚደግፈው ነው፡፡ ይህም ተገቢነት ያለው ጥያቄ በሠላማዊ መንገድና በንግግር የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መንገድ መፍታት ከዘመኑ ጋር መራመድ ነው ፡፡
ልዑል አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም