ኢትዮጵያውያን ረጅም ዘመን በሚቆጠረው የሀገረ መንግሥት ምሥረታ ታሪካቸው የማንንም ሀገር ብሔራዊ ጥቅም የሚገዳደር ተግባር ፈጽመው አያውቁም። በነዚህ ጊዜያት ውስጥ በማንም ሀገር ላይ ጦር ሰብቀው የተንቀሳቀሱበት ጊዜ የለም። ይህ ከትልቁ ታሪካቸው ሰፊውን ምዕራፍ የሚሸፍን፤ ከማኅበረሰባዊ ማንነታቸው የሚቀዳ እውነታቸው ነው።
ስለ ሀገር ነፃነት፣ ፍትሐዊነት ያላቸው ቀናዒነት መሠረታዊ መገለጫቸው ነው፤ እንግዳን ተቀብሎ እግር አጥቦ እና አልጋ ለቆ ማስተናገድ በዘመናት መካከል የነበረ የማንነታቸው አንድ አካል ነው። ለጎረቤት ትልቅ ክብር መስጠት፤ ደስታን ሆነ ኃዘንን ተጋርቶ አብሮ ማሳለፍ ዛሬም ዋነኛ ማኅበረሰባዊ እሴታቸው ነው።
በዘመናት መካከል ብዙ ዋጋ በመክፈል ነፃነታቸውን አስጠብቀው ዘመናትን ያስቆጠሩ ሕዝቦች ናቸው። የነፃነት ተጋድሏቸው በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ለነበሩ የአፍሪካ እና የላቲን አሜሪካ ሕዝቦች የአልገዛም ባይነትንና የነፃነት መነቃቃት መፍጠር የቻለ፤ እስከዛሬም የነፃነት ሰንደቅ ሆኖ ከፍ ብሎ የሚውለበለብ ነው፡፡
ከራሳቸው አልፈው ለፍትሕ እና ለነፃነት ለሚደረጉ ትግሎች አቅም በመሆን በግዞት ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦች አሁናዊ ነፃነት ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው፤ ዛሬም ለነፃነት እና ለፍትሕ ካላቸው ቀናዒነት አኳያ ተመሳሳይ ዋጋ ለመክፈል ወደኋላ የሚሉ አይደሉም፤ በዚህም ዓለም አቀፋዊ አንቱታን ያተረፉ ናቸው።
ይህ ማኅበረሰባዊ ማንነታቸው በዚህም ትውልድ ማኅበረሰባዊ ስሪት ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ አለው፤ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ያለን ሀገራዊ ተሳትፎ፤ ከዛም ባለፈ፤ በጎረቤት ሀገሮች የሚፈጠሩ የሠላም እጦቶችን፤ ለመከላከል እየከፈሉ ያሉት የሕይወት መስዋዕትነት የዚህ ማኅበረሰባዊ ማንነታቸው ሌላው መገለጫ ነው።
ከሁሉም በላይ ስለሀገራቸው ካላቸው ቀናዒነት አኳያ፤ የሀገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ሲፈጠር ልዩነታቸውን ጥለው አንድ ሆነው የነፃነታቸው ምልክት ስለሆነው ሰንደቅ ዓላማቸው መስዋዕት ለመሆን ያላቸው መነቃቃት በየዘመኑ የታየና አሁንም ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ውስጣዊ ማንነት ጋር በማይበጠስ ገመድ የተገመደ ነው።
ለኢትዮጵውያን የሀገር ጉዳይ የብዙ ትውልዶች የተሰናሰለ የመስዋዕትነት የታሪክ ትርክት ነው፤ በዛሬ ላይ ብቻ የሚሰላ ሳይሆን በብዙ ትናንቶች የተከፈሉ የሕይወት መስዋዕትነት እና ከመስዋዕትነቱ በስተጀርባ ያሉ የነፃነት እና የፍትሕ ማኅበረሰባዊ መሻቶች ድምር ውጤት ነው።
ይህም ሆኖ ግን ጠላቶቻችን እንደ ሀገር በውስጣዊ ችግሮቻችን የተከፋፈልን፤ ይህም ለብሔራዊ ሽንፈት እና መንበርከክ ክፍተት ይሆናል ብለው ባሰቡ ቁጥር፤ እንደ ሀገር ክብራችንን ሊያረክሱ፤ የነፃነት ትርክታችንን ለማጠልሸት ሲንቀሳቀሱ ማየት የተለመደ ነው። በዚህ ከታሪካችን ያለመማር የተዛባ ስሌት ለውርደትና ለከፋ ጥፋት የተዳረጉ ጠላቶቻችን ጥቂት አይደሉም።
ዛሬም ከዚህ ህያው ከሆነው ታሪካችን እና ብሔራዊ ማንነታችን መማር ያልቻሉ፤ በየዘመኑ እጆቻቸውን ከጥፋት መመለስ ያልቻሉ ጠላቶቻችን ዛሬም እንደሀገር ብሔራዊ ጥቅማችንን በሚነካ፤ ከዛም ባለፈ እንደሀገር በብዙ የሕይወት መስዋዕትነት የደመቀውን የትናንት የነፃነት ታሪካችንን ለማቆሸሽ መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
እነዚህ ኃይሎች አንድም ከትናንት የሽንፈት ታሪካቸው መማር ባለመቻላቸው ተመሳሳይ ስህተት ለመፈጸም መነሳሳታቸው ፤ ከዛም ባለፈ አሁናዊውን ዓለም እና የሚገዛበትን ማኅበራዊ፤ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ ማስተዋል አለመቻላቸው በራሳቸው ላይ የሚፈጥሩት ችግር ከትናንት የከበደ እንደሚሆን ይታመናል።
ዘመኑ የሚገዛበት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስተሳሰብ ፍትሐዊነት እና ከዚህ የሚመነጭ ሰጥቶ የመቀበል የጋራ ተጠቃሚነት ነው። በዘመነ ግሎባላይዜሽን/ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየተለወጠች ባለችበት አሁናዊ እውነታ/ከዚህ ውጪ መሆን በራስ ላይ አደጋ ከመጋበዝ ባለፈ ቆሞ ቀር የሚያደርግ ነው። ይህ ደግሞ ኪሳራው ምን ያህል እንደሚሆን መገመት አይከብድም።
በተለይም በዚህ ወቅት እንደ መንደር ጎረምሳ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ፉከራ እና ቀረርቶ ማብዛት፤ ከዚያም ባለፈ አካባቢያዊ ሠላምና መረጋጋትን ወደ ሁከትና ብጥብጥ ለመለወጥ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት፣ የገዛ ሀገርንና ሕዝብን ላልተገባ ብሔራዊ ውርደት እና ውርደቱ ለሚፈጥረው አንገት መድፋት መዳረግ ነው።
ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ፤ በብዙ መስዋዕትነት ዛሬ ላይ ያደረሷትን ሀገራቸውን ሆነ ቀና ብሎ የሚያስኬዳቸውን ነፃነታቸውን እና ብሔራዊ ክብራቸውን ለማስጠበቅ ያላቸው የሁሌ ዝግጁነት ጠላቶቻችን እንደሚያስቡት አይደለም። ይህ አይነቱ ስሌት ለብዙዎች የውርደት፤ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ የተጨማሪ ክብር ምንጭ ሆኗል።
የብዙ ባንዳዎች ዲስኩር እና የባንዳነት ተግባር ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው እና ስለነፃነታቸው ያላቸውን ቀናዒነት የሚሸረሽረው አይደለም፤ በቀደሙት ዘመናት የነፃነት ተጋድሏቸው ወቅትም የብዙ ባንዳዎች ዲስኩር ፈትኗቸው እንደነበር አይካድም፤ ችግሩ ሁሌም የሚከተላቸው የጠላቶቻቸው ከንቱ የተስፋ ስንቅ ነው።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም