የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሳምንት “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ሃሳብ ልዩ የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛር ማዘጋጀቱ ይታወሳል።በንግድ ሳምንቱም የተለያዩ ሁነቶች የተከናወኑ ሲሆን፤ በተለይም በመንግሥትና በግሉ ሴክተር ተሳትፎ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነባው የውጭ ምርቶች ማሳያ ቋሚ የኢግዚቢሽን ማዕከል በይፋ ተከፍቷል፡፡ በልዩ የንግድ ሳምንቱ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የጋራ ምክክርና ውይይትም ተደርጓል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ መቅረብ የቻለበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
በንግድና ቀጠናዊ ትስስር መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር አምራቾችና ጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች የተለያዩ የምግብ ሸቀጦችን ይዘው ቀርበዋል፡፡ በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከቀረቡ ምርቶች መካከል የግብርና ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋብሪካ ውጤት የሆኑ ምርቶች ለአብነትም ዘይት፣ ሩዝ፣ የሕፃናት ወተት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ዱቄትና ሌሎች ምርቶችም ቀርበዋል። በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ምርቶቻቸውን ይዘው ከቀረቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል የግብርና ምርት የሆኑ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ጨምሮ ቦይዝ ፓስታና ማካሮኒ፣ ዲኤች ገዳ ዱቄት ፋብሪካ፣ ቱሬ ጤፍና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ በመገኘት ምርቶቻቸውን ይዘው ከቀረቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል ጥቂቶቹን አነጋግሯል። በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ ተሳታፊ መሆናቸው ምን ጠቀሜታ አለው ሲል ላነሳላቸው ጥያቄም የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የፋብሪካ ውጤት የሆነውን የጤፍ ዱቄት ይዞ የቀረበው ቱሬ ወይም ሶርስ ጤፍ አንዱ ነው፡፡ አቶ ከሊፋ አብዱልቃድር የቱሬ ጤፍ ወይም ሶርስ ጤፍ ፋብሪካ ማናጀር ናቸው፡፡
እሳቸው እንዳሉት በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ በዓይነቱ ለየት ያለና መቶ በመቶ ጥራት ያለው ንጹህ የጤፍ ዱቄት ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ይዘው ቀርበዋል፡፡ የጤፍ ዱቄት በፋብሪካ ደረጃ አዘጋጅቶ ለገበያ ማቅረብ ሀገር ውስጥ ብዙም አልተለመደም። ነገር ግን ጤፍ በፋብሪካ ደረጃ በጥራት ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ድርጅቱ ጤፍን በጥራት እያዘጋጀ በማቅረብ ቀዳሚ ሲሆን፤ ለዚህም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው አይኤስኦ 9001 እና ኤፍኤስሲ 22000 ድርጅቶ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ ቱሬ ወይም ሶርስ ጤፍ በሀገር ውስጥና በውጭ ተቆጣጣሪ ድርጅቶች ደንብ የሚተዳደር ፋብሪካ ነው፡፡
ቱሬ ወይም ሶርስ ጤፍ በ2009 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ በአሁን ወቅት ገበያ ውስጥ በስፋት ገብቷል። ባለፉት ጊዜያት ማህበረሰቡ ጤፍን በዚህ መልክ በፋብሪካ ደረጃ አዘጋጅቶ የሚያቀርብ አልነበረም ሂደቱም ቢሆን በአብዛኛው ሰው የተለመደ አልነበረም። ይሁንና አሁን ላይ ግን ማህበረሰቡ እየለመደው በመምጣቱ ሰፊ የገበያ ፍላጎት መኖሩን መገንዘብ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በተለይም አብዛኛው ሰው ጠዋት ወጥቶ ማታ የሚገባና መኖሪያ ቤቱና ሥራ ቦታው የተራራቀ በመሆኑ ጊዜና ጉልበትን መቆጠብ ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጥራት ተጠቃሚ ሆኗል። ምክንያቱም ቱሬ ወይም ሶርስ ጤፍ መቶ በመቶ የጤፍ የሆነ ዱቄት በጥራት አዘጋጅቶ ያቀርባል። በመሆኑም ተቀባይነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል›› የሚሉት አቶ ከሊፋ፤ ምንም ዓይነት ባዕድ ነገሮች የማይቀላቀልበት እንደሆነ ሲያስረዱም ‹‹ፋብሪካ ውስጥ ጤፍ ብቻ ገብቶ ጤፍ ብቻ ይወጣል›› በማለት ነው፡፡
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይም ተሳታፊ መሆናችን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም የሀገር ውስጥ ምርትን ለሀገር ውስጥ ዜጋ ወይም ለመላው ማህበረሰብ በጥራት እያቀረቡ እንደሆነ ማስተዋወቅ ነው ይላሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በኤግዚብሽንና ባዛሩ ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው ቱሬ ጤፍን የማያውቁ የማህበረሰብ አካላትን እንዲያውቁት ሆኗል፡፡ የገበያ ትስስር መፍጠር ተችሏል፡፡ ቱሬ ወይም ሶርስ ጤፍ ምርቱን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ ገበያ የማቅረብ ዕቅድ ያለው በመሆኑ እንዲህ ዓይነት መድረኮች የገበያ ትስስር ለመፍጠር አጋዥ ናቸው፡፡
ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረው ቱሬ ወይም ሶርስ ጤፍ አሁን ላይ አቅርቦቱና ተደራሽነቱ ካለው ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደለም ያሉት አቶ ከሊፋ፤ ድርጅቱ በቀጣዮቹ ዓመታት ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ተደራሽነቱን ለማስፋት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ለዚህም ድርጅቱ የግብርና ሥራውን ጭምር በመሥራት የጤፍ ምርት በማምረት ጭምር የምርት አቅርቦቱን እንዲሁም ተደራሽነቱን ለማስፋት በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ተናረዋል፡፡
በአሁን ወቅት ቱሬ ወይም ሶርስ ጤፍ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉት ሰባት ቅርንጫፎች አማካኝነት በከተማ ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ አካላት ማለትም ግለሰቦችን ጨምሮ ሆቴሎች፣ ተቋማትና የተለያዩ ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡ በቀጣይም ከከተማ ውጭ ለሚገኙ የማህበረሰብ አካላትም ተደራሽ የመሆን ዕቅድ ያለው ሲሆን፤ በቅርቡ ምርቶቹን ለክልል ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቅቋል።
ቱሬ ወይም ሶርስ ጤፍ አሁን ላይ በተለያየ ዓይነትና መጠን ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ያነሱት አቶ ከሊፋ፤ በዓይነት ነጭና ቀይ ጤፍ መሆኑን ጠቅሰው በመጠን ደግሞ በ10 እና በ25 ኪሎ ግራም ነው ብለዋል፡፡ ይህም ማለት ቀይ ጤፍ ባለ 10 እና ባለ 25 ኪሎ ግራም እና ነጭ ጤፍ ባለ 10 እና ባለ 25 ኪሎ ግራም መጠን ያላቸው ናቸው፡፡
‹‹የጤፍ ዱቄት በተለምዶ ወፍጮ ቤት ሄዶ ይፈጫል›› ያሉት አቶ ከሊፋ የቱሬ ወይም የሶርስ ጤፍ ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ የጤፍ ዱቄት ማዘጋጀትን ዋና ዓላማ አድርጎ ነው የተነሳው፡፡ በመሆኑም በተለምዶ ወፍጮ ቤት የሚፈጨውን ጤፍ ዘመናዊ በሆነ መንገድ በፋብሪካ ተዘጋጅቶ በጥራት ማቅረብ ለሁሉም ጠቃሚ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት በአዲስ ግኝት ልዩ በሆነ ሁኔታ ጤፍ ብቻ የሚፈጭ ማሽን ዲዛይን በማስደረግ ከቻይና አስመጥተዋል፡፡ በመሆኑም ማሽኑ አገልግሎት የሚሰጠው ለጤፍ ብቻ ሲሆን፤ ይህም ለጥራትና ደህንነት ትልቅ ግምት መሰጠቱን ያሳያል፡፡
የጤፍ ዱቄት በምን ያህል መጠን መድቀቅ እንዳለበት ጭምር በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ሲሆን፤ የተለያዩ ጥናቶች ተሰርተውለት ከባዕድ ነገሮች ነፃ መሆኑም ተረጋግጧል፡፡ አቶ ከሊፋ፤ የፍጭት ቦታውም ጥራቱን በጠበቀ መንገድ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ሲያስረዱ የጤፍ ዱቄቱ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ የሚዘጋጅ እንደሆነና ገበያ ውስጥም በስፋት እየገቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዋጋውን አስመልክቶም ቱሬ ወይም ሶርስ የጤፍ ዱቄቱ ለሸማቹ እየቀረበ ያለው ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ነው፡፡›› ያሉት አቶ ከሊፋ፤ ይህን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደንበኛ አንዱ ሲሆን፤ ሌላው በምግብ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጥራት ያለውና ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት ማቅረብ በራሱ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደ ማቅረብ ነው ብለዋል፡፡
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከምግብ ሸቀጦች ውጭ የሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችም ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዴ ማማ የተባለ የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን ከወዳደቁ ቁሶች የሚሰራ አምራች ድርጅት አንዱ ነው፡፡ ሃና ግርማ የአንዴ ማማ ማርኬተር ናት፡፡ እሷ እንዳለችው አንዴ ማማ የወዳደቁ ቁሳቁሶችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን ዓላማ አድርጎ የተመሰረተው ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ወደ ሥራው ከገባ ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል። የሚያመርታቸው ምርቶች በዋናነት የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችና ለመሥሪያ ቤት መገልገያ የሚውሉ ናቸው፡፡
አንዴ ማማ እነዚህን ቁሳቁሶች ለማምረት አነስተኛ ገቢ ያላቸውንና አቅመ ደካማ የሆኑ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ በጽዳት ሥራ ላይ የተሰማሩ እናቶችን ምርጫው ያደረገ ሲሆን፤ ከሴቶችና ሕፃናት፣ ከክፍለ ከተማና ከወረዳ ጋር በጋራ በመሆን ይሰራል። ለእነዚህ እናቶችም ድርጅቱ በቅድሚያ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት ወደሥራ እንዲገቡ ያደርጋል። ሥልጠናውን በነፃ በመስጠት እናቶቹ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ማምረት የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
ሥልጠናውን ያገኙት እናቶችም የቤት ውስጥ መገልገያ የሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እና ጌጣጌጦችን ያመርታሉ፡፡ ከቤት ውስጥ ቁሳቁሶች በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ለእነዚህ ምርቶች ታዲያ በዋናነት የሚጠቀሙት ጥሬ ዕቃ ጋዜጣና መጽሔትን ጨምሮ አገልግሎታቸው ያበቃና የተጣሉ ወረቀቶችን ነው፡፡ እነዚህን ወረቀቶች ለማግኘትም ባንኮችን ጨምሮ 500 ከሚደርሱ ተቋማት ጋር በጋራ ይሰራል። ጋዜጦቹን ሊያበላሽ የሚችለው ውሃ ብቻ እንደመሆኑ ወረቀቱ እንዳይበላሽ ወተር ፕሩፍ ይቀባል፡፡
በውሃ እንዳይበላሹ ወተር ፕሩፍ የተቀቡትና በቀጫጭኑ በቲዩብ የተጠቀለሉት ጋዜጦችም ስልጠና የወሰዱ እናቶች እጅ ሲደርሱ የተለያየ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁስ መሆን ይችላሉ፡፡ እናቶቹ በቤታቸው ሆነው ለሚሰሩት ሥራ ከወረቀቶቹ በተጨማሪ ኮላ ይጠቀማሉ፡፡ በአሁን ወቅትም በሰሩት መጠን የሚከፍላቸው 700 እናቶች ስለመኖራቸው ያነሳችው ወጣት ሃና ከወዳደቁ ወረቀቶች የሚመረቱ ቁሳቁሶች ለገበያ እየቀረቡ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ እናቶቹ ከሚሰሯቸው የእጅ ሥራዎች መካከልም ቅርጫት፣ ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉ የተለያዩ ጌጣጌጦች፣ ቢዝነስ ካርዶች፣ መመገቢያ ሳህን፣ የግድግዳ ሰዓት ይጠቀሳሉ፡፡
ምርቶቹ በአብዛኛው በትዕዛዝ የሚሰሩ ሲሆን፤ እንዲህ ዓይነት ኤግዚብሽንና ባዛሮች ላይ እንደሚሸጡ የገለጸችው ወጣት ሃና፤ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር መሳተፍ መቻላቸው የጎላ አበርክቶው ያለው መሆኑን ነው ያስረዳችው፡፡ በተለይም ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር ፊት ለፊት የመገናኘትና የመተዋወቅ ዕድል ይፈጠራል። ከሚፈጠረው የገበያ ትስስር በባለፈም ሰዎች የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በቀላሉ መሥራት እንደሚችሉ ግንዛቤ ለመፍጠር ያግዛል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያውያን እናቶች የሚሰሩትን የእጅ ሥራዎች ማህበረሰቡ ገዝቶ በመጠቀም እናቶችን ይደግፍ ያበረታታ በሀገሩ ምርት ይኩራ በማለት መልዕክት አስተላልፋለች፡፡
‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› በሚል መሪ ሃሳብ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ልዩ የንግድ ሳምንት በርካታ የምግብ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበው ሸማቹ ሲሸምት ሰነባብቷል፡፡ ከመደበኛው ገበያ በተሻለ ዋጋ በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ ከቀረቡ ምርቶች መካከል ለአብነት ዘይት ተጠቃሽ ነው፡፡ በመደበኛው ገበያ ከአንድ ሺ አንድ ብር እስከ አንድ ሺ ሰባ ብር ድረስ የሚሸጠው ባለ አምስት ሊትር ዘይት በአንድ ሺ ብር ተሸጧል፡፡ እንዲሁም በመደበኛው ገበያ ከ80 ብር በላይ የሚሸጠው ፓስታ በ70 ብር ከሃምሳ ሳንቲም፣ ሲሸጥ ቆይቷል፡፡ ለንጽህና አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ደረቅ እና ዲተርጀንት ሳሙናዎች እንዲሁም ሌሎች ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ሲሸጥ እንደነበር መመልከት ችለናል፡፡
በንግድ ሳምንቱ ማጠቃለያ የተገኙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የንግድ ሳምንት ዋናው ዓላማ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ የሀገር ውስጥ የእጅ ባለሙያዎችን፣ ሥራ ፈጣሪዎችንና ነጋዴዎችን ማበረታታት ለነገዋ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ምርትና አገልግሎት በመግዛትና በመጠቀም ለነገዋ ኢትዮጵያ ኢንቨስት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ መንግሥትም በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ተጨማሪ የንግድ ዕድሎችን የማመቻቸት፣ የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን የሚረዱ የፖሊሲ እና የሕግ ማሻሻያዎችን በማድረግ እንዲሁም የንግዱን ዘርፍ ተዋንያኖች አቅም የማሳደግ ሥራ ይሰራል፡፡
መንግሥት ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓትን ለመገንባት፣ የገቢና የወጪ ንግዱን ለማሳለጥ በርካታ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎችን አድርጓል፡፡ መንግሥት ካደረጋቸው ማሻሻያዎች ውስጥ በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ይህም የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት ለማዘመን ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥትና የግሉ ዘርፍ መናበብ፣ መቀናጀትና መወያየት ከቻሉ የምናስባትን ታላቅ ሀገር በአጭር ጊዜ እውን ማድረግ ይቻላል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም