የማእድን ልማት አበረታች አፈጻጸም- በሲዳማ ክልል

በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር አመት መሪ እቅድ የኢኮኖሚው ምሰሶ ተደርገው ከተያዙት አምስት ዘርፎች መካከል የማእድን ዘርፉ ይጠቀሳል። እንደ ሀገር ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ የገቢ ምርትን ለመተካት፣ ለስራ እድል በአጠቃላይ ለሀገር ምጣኔ ሀብት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ታሳቢ በማድረግም ይህን እምቅ አቅም ለመጠቀም በስፋት እየተሰራ ይገኛል።

ክልሎችም ያላቸውን እምቅ የማእድን ሀብት ለልማት በማዋል ከዘርፉ እነሱም ሀገሪቱም ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተውታል። በዘርፉ በተከናወነው ተግባርም በተለይ ከወርቅ ልማትና ግብይት አኳያ ከህገወጥነት ጋር ተያይዞ ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም በኢንዱስትሪ፣ ኮንስትራክሽን፣ እንዲሁም በጌጣጌጥ ማእድናት ልማት በኩል ለውጦች እየታዩ ናቸው።

ይህ ለውጥ እየታየባቸው ከሚገኙ ክልሎች መካከል የሲዳማ ብሄራዊ ክልል ይጠቀሳል። ክልሉ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት አመት በተለያዩ የማእድን አይነቶች ልማትና ግብይት በኩል ለውጦችን እያስመዘገበ ስለመሆኑ የክልሉ የማእድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ መስፍን መጩካ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ ኤጀንሲው በ2016 በጀት አመት ለማከናወን ትኩረት ያደረገባቸውንና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ በበጀት አመቱ በማእድናት ልማትና ጥናት በኩል ከተከናወኑ ተግባሮች አፈጻጸም መረዳት የሚቻለው በማእድን ልማትና ጥናት በኩል በክልሉ ጥሩ እየተሰራ መሆኑን ነው።

በበጀት አመቱ 330 ሜትር ስኩዌር ቦታ ላይ የማእድን ጥናት ለማድረግ ታቅዶ 378 ሜትር ስኬየር የሆነ ቦታን በጥናቱ ለመሸፈን ተችሏል ሲሉ ጠቅሰው፤ ጥናቱም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን መካሄዱን አስታውቀዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የወርቅ ማእድን ይገኛል። በእነዚህም አካባቢዎች በተለይ በባህላዊ መንገድ የወርቅ ልማት በማካሄድ የወርቅ ምርቱ ለብሄራዊ ባንክ እንዲቀርብ እየተደረገ ነው። በተጠናቀቀው 2016 በጀት አመትም ይህን ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ ፋይዳ ያለውን የወርቅ ማእድን በማምረት ላይ ተሰርቷል ።

በበጀት አመቱ 15 ኪሎ ግራም ወርቅ በባህላዊ መንገድ በማምረት ለብሄራዊ ባንክ ለማስገባት ታቀዶ እንደነበር ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ 13 ነጥብ 7 ኪሎ ግራም ወርቅ በማምረት ለባንኩ ማስገባት መቻሉን አመልክተዋል። አፈጻጸሙም የእቅዱን 91 ነጥብ 7 በመቶ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

እንደ ሀገር የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካትና ምርቶችን ከውጭ ለማስመጣት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት እየተከናወነ ያለው ተግባር በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥትም በስፋት እየተሰራበት ይገኛል። በዚህም በኩል ክልሉ በተጠናቀቀው በጀት አመት 2500 ቶን ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ ማእድናት ለፋብሪካዎች ለማቅረብ አቅዶ እንደነበር አቶ መስፍን ጠቅሰው፣ በእዚህም ከእቅድ በላይ 3100 ቶን ማእድናትን ለፋብሪካዎች ማቅረብ መቻሉን ነው ያመለከቱት።

አቶ መስፍን እንዳስታወቁት፤ ኤጀንሲው በግንባታ ግብአት ማእድናት አቅርቦት ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል። በበጀት አመቱ አራት ሚሊዮን ሜትር ኩብ የግንባታ ማእድናትን ለገበያ ለማቅረብ አቅዶ 4ሚሊዮን 280 ሺ 500 ሜትር ኪዩብ አቅርቧል።

ክልሉ በማእድን ልማት ከሚያከናውናቸው ተግባሮች መካከል የጌጣ ጌጥ ማእድናት ማምረት ሥራ አንዱ ነው። እነዚህን በሀገር ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃም በስፋት የሚፈለጉትን የጌጣጌጥ ማእድናት ለማምረቱ ሥራ ትኩረት ሰጥቷል። በ2016 በጀት አመቱም 40 ቶን የጌጣ ጌጥ ማእድናትን ለማምረት ታቅዶ 73 ቶን ማም ረት ተችሏል።

የማእድን ልማት ሥራዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ማእድናትን በማምረት ለገበያ ከማቅረብ በተጓዳኝ፣ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን በመሳብ እንዲሁም ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠርም ይታወቃሉ።

በሲዳማ ክልል በበጀት አመቱ በማእድን ልማት በተከናወነው ተግባር ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የተቻለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል። በክልሉ በበጀት አመቱ ለ6000 ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ5860 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደተቻለ አቶ መስፍን ጠቅሰው፤ አፈጻጸሙም የእቅዱን 97 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን አመልክተዋል።

እነዚህን አፈጻጸሞች ለማስመዘገብ የተከናወኑ ተግባሮችን እንዲሁም በቀጣይ ሊከናወኑ የተያዙ ሥራዎችንም አቶ መስፍን አያይዘው ገልጸዋል። በበጀት አመቱ ጥናቶች የተደረጉባቸው አካባቢዎች የአሮሬሳና ኦኮ ወረዳዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በእነዚህ አካባቢዎች በጥናት የተለዩት ማእድናትም የኮንስትራክሽን ማጠናቀቂያ ግብአቶች የሚባሉት መሆናቸውን ገልጸዋል። በጥናቶቹም ግራናይትና እምነበረድ መገኘታቸውን በላቦራቶሪ ውጤት ጭምር ማረጋገጥ መቻሉን አስታውቀዋል። በቀጣይም ተመሳሳይ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

እንደ ሀገርም ካለው የማእድን ሀብት አኳያ ሲታይ በጥናት የተለየው በጣም ውስን ነው ይላሉ። ይህን ማእድን ለማጥናትም እየተሠራ ነው ሲሉ ጠቁመው፤ በኛም ክልል በጆኦሎጂካል ሰርቬይ ኢንስቲትዩት በኩል የወርቅ ጥናት ተካሂዷል ሲሉ ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በጂምስቶን ላይ ያጠናልናል፤ እኛም በራስ ሀይል ጥናት እያደረግን ነው ሲሉ ተናግረው፣ የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን ግብአት በሚሆኑ ማእድናት ላይም እንዲሁ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ለማጥናት መታቀዱንም አመልክተዋል።

በባህላዊ መንገድ በስፋት እየተካሄደ ያለውን የወርቅ ልማት ለማዘመንና ልማቱ በኩባንያ ደረጃም እንዲካሄድ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ማህበራት እና ባለሀብቶች አብረው እንዲሰሩ እንዲሁም ኩባንያዎች በራሳቸው ልማቱን እንዲያካሂዱ ለማደረግ እየተሰራ ነው። ባለሀብቶችም የወርቅ ማጠቢያ ማሽንና ኤክስካቫተር ይዘው ገብተው መሥራት ጀምረዋል። ሌሎች በፌዴራል ደረጃ ፈቃድ የተሰጣቸው ሁለት ኩባንያዎች ወርቅ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ጽንስ ወርቅ ላይ ጥናት እያደረጉ ናቸው።

ከወርቅ ልማትና ግብይት አኳያ በተለያዩ ወርቅ አምራች ክልሎች ህገወጥነት መንሰራፋቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግሥት ይህን ህገወጥነት ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑም ይታወቃል። ይህን ተከትሎም በርካታ የውጭ ዜጎች ጭምር በእዚህ ህገወጥ ተግባር ተሰማርተው በመገኘታቸው እርምጃ እንደተወሰደባቸው ይታወሳል። ለእዚህ ህገወጥነት መንሰራፋት አንዱ ምክንያት ማእድኑ በሚለማበት አካባቢ ያለው የጸጥታ ችግር መሆኑ ይጠቀሳል።

በሲዳማ ክልል የጸጥታ ችግር ካለመኖሩ ጋር በተያያዘ ህገወጥነቱ ያን ያህል የሰፋ እንዳልሆነ አቶ መስፍን ገልጸዋል። በተወሰነ መጠን የመቀነስ ሁኔታ እንደሚኖር ይገመታል። ያንን ለማጥፋት አልሚዎቹ የየእለቱን ምርታቸውን እንዲመዘገቡ ይደረጋል። ለእዚህም በየሳይቱ መዝገብ ተዘጋጅቷል ሲሉም ገልጸዋል።

መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ግብይቱን ከጥቁር ገበያው ጋር ስላቀራረበው ህገወጥነቱ በራሱ ጊዜ እየቀነሰ ይሄዳል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ እኛም ከጸጥታ ኃይሎችና ከወረዳ ማእድን ግብረ ኃይሎች ጋር ተባብረን የየእለቱ ምርት እንዲመዘገብ የቁጥጥር ስራ እናካሂዳለን። ይህንንም ህገወጥነት መከላከል የሚያስችል ንቅናቄ በማድረግ አጠናክረን እንቀጥላለን። በእዚህም ማህበረሰቡ ራሱ እንዲሳተፍ እናደርጋለን ብለዋል።

የገቢ ምርቶች መተካት ላይ ክልሉ በተጠናቀቀው በጀት አመት ጥሩ አፈጻጸም አሳይቷል። ለአፈጸጸሙ ውጤታማ መሆን ገበያ ላይ የተሠራው ሥራ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተገልጿል።

በክልሉ በኢንዱስትሪ ግብአት ምርትነት በዋናነት እየተሰራበት ያለው የሴራሚክ ግብአት በሆነው ታልክ ላይ ነው ሲሉ አቶ መስፍን አስታውቀዋል። ይህ ግብአት በሀዋሳ ሴራሚክ ፋብሪካ እንዲሁም ዱከም አካባቢ በተቋቋሙ የሴራሚክ ፋብሪካዎች በብዛት ይፈለጋል ሲሉም ገልጸው፤ እንደ ኳርትዝ እና ፊልድስፓር ያሉ የኢንዱስትሪ ግብአት ማእድናትም በክልሉ እንደሚመረቱ ተናግረዋል።

ዘንድሮ ለፋብሪካዎች በብዛት የቀረበው ታልክ የተሰኘው ማእድን መሆኑን አመልክተው፣ ይህ ማእድን በአሁኑ ወቅት ፋብሪካዎች በስፋት እንደሚፈልግና ማእድኑም በስፋት እንደሚገኝ ገልጸዋል። በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ የታልክ ማእድን እንዳለም ነው የተናገሩት፡

አቶ መስፍን እንዳስታወቁት፤ በዚህ የሴራሚክ ግብአት አምራችነት ከሰባት እስከ ስምንት የሚደርሱ ማህበራት ተሰማርተዋል፤ የማህበራቱ ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ ነው። ፊት ኢንዱስትሪዎች ካለመስፋፋታቸው ጋር በተያያዘ የገበያ ችግር ይታይ ነበር። አሁን ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ መምጣቸውን ተከትሎ ማእድኑን የሚያመርቱ ማህበራት ቁጥርም እየጨመረ ነው። ወጣቶችም በማህበር በመደራጀት ማእድኑን እያወጡ ለገበያ በማቅረብ ሥራ ላይ በስፋት እየተሰማሩ ናቸው።

በኢንዱስትሪ ማእድናት ላይ የሚካሄደው ልማት ይቀጥላል። የመንግሥት አንዱ የልማት አቅጣጫ ኢንዱስትሪ ማስፋፋት ላይ ያተኮረ እንደመሆኑ፤ በተለይ የገቢ ምርትን በመተካት ላይ በተጠናከረ መልኩ ይሰራል። ክልሉም በእዚሁ ልክ በእነዚህ የኢንዱስትሪ ግብአት ማእድናት ልማት ላይ መሥራቱን ይቀጥላል። የማእድን ልማቱ ለወጣቶች የሥራ እድል በመክፈት በኩል ባለው ፋይዳም ትኩረት ተሰጥቶታል።

እሳቸው እንዳሉት፤በግንባታ ግብአት እንደ ግራናይት ባሉት ማእድናት ላይ ያተኩራል። በክልሉ አራት ባለሀብቶች በግራናይት ማእድን ልማት ለመሰማራት እየተንቀሳቀሱ ናቸው። ባለሀብቶቹ የድንጋይ መቁረጫ ማሽን ለመግዛት አዘዋል። ማሽኑ ከመጣና ወደ ስራ ከገባ ግራናይትም ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እንዲሚታሰብ አቶ መስፍን አመልክተዋል።

ሌላው በክልሉ ጥሩ አፈጻጸም የታየው በጌጣጌጥ ማእድናት ልማት ላይ እንደመሆኑ ልማቱ በቀጣይም የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል። በክልሉ እየለማ ያለው ሩታይል የሚባል የጌጣጌጥ ማእድን ሲሆን። በእዚህ ልማት ላይም ወደ አራት የሚሆኑ የወጣቶች ማህበራት ተሰማርተዋል። ማእድኑ እሴት ሳይጨመርበት ወደ ቻይና እየተላከ ይገኛል። ማእድኑ በክልሉ ኦኮ ወረዳ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የሚመረተውም በባህላዊ መንገድ ነው፤ አምራቾቹ ኤክስካቫተር ተከራይተው የሚያመርቱበት ሁኔታም አለ።

ይህ የጌጣጌጥ ማእድን እንደ ኦፓል የከበረ የሚባል አይደለም ያሉት አቶ መስፍን፣ ከፊል የከበረ ጌጣጌጥ የሚባል ነው ይላሉ። በእዚህም ላይ ከሌሎች ክልሎች ልምድ በመውሰድ እሴት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ለማእድን ምርቶች ገበያ በማፈላለግ በኩል ምን ያህል እየተሰራ ነው የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መስፍን፤ ‹‹ቀደም ሲል የኢንዱስትሪ ግብአት ማእድናት ምርት ገበያ ለማግኘት ችግር ነበር፤ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያከናወናቸውን የማስተዋወቅ ስራዎች እየተመለከቱ አምራቾች አሁን ምርቱን ፍለጋ እየመጡ ናቸው፤ ገበያውም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

መንግሥት የመዋቅር ለውጥ ጭምር በማድረግ ለማእድን ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። የዘርፉን እምቅ አቅም ማሳየት ያስቻሉ፣ አምራቾችንና ኢንዱስትሪዎችን ያስተሳሰሩ ዓለም አቀፍ ኢግዚቢሽኖችም ባለፉት አመታት ተካሂደዋል።

ክልሎችም በዘርፉ ያላቸውን እምቅ አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዋቅሮችን ፈጥረው በልማትና ግብይቱ ላይ መስራታቸውን ተያይዘውታል። ይህን ተከትሎም በክልሎች ብዙ ለውጦች እየታዩ ናቸው። በተለይ በድንጋይ ከሰል፣ በሴራሚክ ግብአት ማእድናት ምርት በኩል ለውጦች መመዝገብ ጀምረዋል።

በሲዳማ ክልልም በማእድን ልማት በኩል እየታየ ያለው ለውጥም ከዚሁ አኳያ ሊታይ ይችላል። አቶ መስፍንም ይህንኑ ነው ያሉት። በተጠናቀቀው በጀት አመት በአብዛኞቹ ማእድናት ልማት ስራዎች ላይ ከእቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡም ለውጡ እየጨመረ መምጣት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አመልክተዋል። የማእድን ጥናት ረጅም ጊዜን የሚወስድ ሆኖ እንጂ በጥናት በኩል እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ሲጠናቀቁ በክልሉ በቀጣይም በዘርፉ ለውጦች እንደሚመዘገቡ ይጠበቃል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፤ በቀጣይም ከእስከ አሁኑም የሰፋ አቅድ በመያዝ በማእድን ዘርፉ ላይ ይሰራል። በክልሉ በጸጥታው በኩል ያለውን አስተማማኝ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በዘርፉ ላይ በስፋት የሚሰራ ይሆናል።

በክልሉ በተካሄደ ጥናት በመዳብ/ኮፐር/፣ በታንታለምና በመሳሰሉት ማእድናት ላይ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል ሲሉም ጠቁመው፣ በርካታ ባለሀብቶችም በክልሉ በጸጥታው በኩል ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ክልሉ መጥተው በማእድናት ላይ ጥናቶችን እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። እነዚህ ጥናቶች ቢጠናቀቁ እንደ ክልል ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገርም አፈጻጸሙ ከፍ ይላል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ መስፍን አስታውቀዋል።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You