በኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባሕላችንን ልናጎለብት ይገባል

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ዘወትር መሥራት ይገባል ሲሉ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ምሑሩ አቶ ጥላሁን ሊበን ገለጹ፡፡

አቶ ጥላሁን ሊበን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ችግሮችን በውይይትና በንግግር መፍታት አንዱ የሥልጣኔ መገለጫ መሆኑን በመገንዘብ ችግሮቻንን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት መሥራት ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ በውይይትና በመደማመጥ ችግሮችን የመፍታት ጠንካራ እሴት ያላት ሀገር ናት ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በሰከነ መንፈስ የሚደረጉ ውይይቶችን በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ የሚበጅ ሥራ ከወዲሁ ማከናወን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተሰሙ ያሉ ድርጊቶች ከኢትዮጵያውያን እሴት ያፈነገጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለዚህ ችግር ዋንኛ ምንጩ ደግሞ ጤናማ ያልሆነ የፖለቲካ አሰላለፍ ነው ብለዋል። የመንግሥት ኃላፊዎችም ሆኑ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ንግግራቸው ሕዝቦችን የሚያቀራርብ እንጂ የማይለያይና ለግጭት የማይዳርግ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አመላክተዋል።

በቀደመው ዘመን በትብብርና በአንድነት የነጭን የበላይነት ታግለው ያሸነፉ የዓድዋ ልጆች መሆናችንን መዘንጋት አይገባም ያሉት አቶ ጥላሁን፤ አሁን ላይ ግን ከሚያቀራርቡ ጉዳዮች ይልቅ ልዩነት ላይ በማተኮራችን ላለንበት ውስብስብ ችግር ልንዳረግ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀድሞ የነበረውን የሰሜን ጦርነት ጨምሮ አሁን ላይ በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል የሚስተዋለው ችግርም ውይይትን ቀዳሚ መፍትሔ አድርጎ ያለመሥራት ያመጣው ችግር መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ደግሞ በዋናነት ዋጋ እየከፈለ ያለው የሀገሪቱ የነገ ተስፋ የሆነው ወጣቱ ትውልድ መሆኑን አስረድተዋል።

ችግሮችን ለመከላከል መሥራት እንደሚያስፈልግ አንስተው፤ ለሠላም የሚረፍድ ጊዜ የለምና መንግሥትና ሌሎችም የፖለቲካ ተዋናዮች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የውስጥ ችግራችን ለውጫዊ ጫናዎችም በር የሚከፍት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ ከፖለቲካ ተዋናዮች ባለፈ ምሑራን፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገሩ ሠላም የሚያሳስበው ሁሉ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠላም ፈላጊ በመሆኑ ችግር እንኳን ሲያጋጥመውም መፍትሔ እንዲያገኝ ደጋግሞ ይወተውታል እንጂ ግጭትን አያበረታታም ያሉት አቶ ጥላሁን፤ ዛሬም በየአቅጣጫው ያለው ሕዝብ ሠላም ስጡኝ የሚል ተማፅኖ እያቀረበ በመሆኑ ማንኛውም ዜጋ ለሠላም ያለውን ፍላጎት በተግባር ማሳየት ይኖርበታል ብለዋል።

የትኛውም ችግር ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኘው በውይይት መሆኑን ተገንዝቦ የሌሎችን እውነት ለማዳመጥና ለመነጋገር ዝግጁ መሆን እንዳለበትም አመላክተዋል።

አሁን ላይ እንደሀገር የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ሠላምን ለማምጣት ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸው፤ ምክክሩ የምንጠብቀውን ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም ባለድርሻዎች በንቃት መሳተፍና እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን  ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You