የወጪ ንግዱ ስኬትና ተግዳሮት

ኢትዮጵያ በዋነኝነት ወደውጭ ሀገር የምትልካቸው ምርቶች የግብርና ውጤቶች ስለመሆናቸው ይታወቃል። ከእነዚህም ውስጥ ቡና ትልቁን ድርሻ ሲይዝ፣ የቅባት እህል፣ የአበባ ምርት እንዲሁም ሥጋና የሥጋ ውጤት ተጠቃሽ ነው። እነዚህና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ለማምረት የሚያስችል ተስማሚ የአየር ንብረት፣ በቂ የሆነ መሬትና ውሀ ቢኖርም በሚፈለገው መጠንና ጥራት እየተመረተ ለውጭ ገበያ ሲቀርብ አይስተዋልም።

ከሳምንት በፊት “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መርህ በተዘጋጀው የንግድ ሳምንት ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በ2016 በጀት ዓመት ከአጠቃላይ ወጪ ንግድ ሶስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደተገኘ መግለጻቸው ይታወቃል። መንግሥት የንግድ ዘርፉ ፍትሃዊ፣ ተደራሽና በውድድር ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ይገኛልም ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንዳለና የሀገሪቱንም ኢኮኖሚ መሪና አንቀሳቃሽ ለማድረግ የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በመተግበር ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስሰር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “ያለ ምርት ጥራት የገበያ ውድድር አይታሰብም፤ ጥራት ትልቅ ጉዳይ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ንግድ በማስተሳሰር አይተኬ ሚና ያለው መሆኑንም በወቅቱ አስረድተዋል፡፡

የወጪ ምርትን በመጠንም በጥራትም ማምረት የሚቻለው እንዴት ነው? በዘርፉ ላለው ተግዳሮትስ መፍትሔው ከወዴት ነው? በሚል ጥያቄዎች ተነስተው በዘርፉ ባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። ማብራሪያ ከሰጡ ባለሙያዎች መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክ ትምህርት ክፍል ውስጥ በረዳት ፕሮፌሰርነት እያገለገሉ የሚገኙት አንዱዓለም ጎሹ (ዶ/ር) ናቸው። የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አንዱዓለም (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ የወጪ ንግድን በመመጠንና በዓይነት ለማስፋት ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑት በሚመረተው ምርት ጥንቃቄ ላይና የተመረተውን ምርት በአግባቡ ወደ ገበያ በማድረስ በኩል ያለውን ክፍተት በአግባቡ ማጤንን ነው። ይህ አካሔድ ምን ይመስላል የሚለውን በመጀመሪያ ማስተዋሉ መልካም ነው።

የኢትዮጵያን ምርታማነት ወይም ደግሞ አጠቃላይ ምርቱን ስናጤን የዛሬ ሃያ ዓመት ከነበርንበት ሁኔታ አንጻር ከፍተኛ የሆነ እምርታ አለ። ይህም እምርታ የመጣው የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ብለን ከምንጠራው ግብርና ነው። በወጪ ንግድም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ይኸው የግብርና ምርት ነው፡ ከዚህ አንጻር የዛሬ ሃያ ዓመት ስናመርት የነበረው አምስት ቢሊዮን ዩ.ኤስ ዶላር ነበር። አሁን በቅርብ ዓመታት ውስጥ ማለትም እኤአ በ2018 እና 2019 አካባቢ ሃያ ቢሊዮን ዶላር ዘልለናል፤ በዚህ መልኩ ሲታይ በከፍተኛ ሁኔታ ያደገበት ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ገለጻ፤ በአቅም ደረጃ ሲታይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በሶስተኛ እና በአራተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች። ይህ የሚያመላክተው ለወጪ ንግድ የሚያስችል እምቅ አቅም መኖሩን ነው። ለአብነት ያህል ወደ 60 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ መሬት መታረስ የሚችል ነው። ወደ ምርታማነት ሲመጣ ግን እስካሁን ከፍተኛ የሆነ ክፍተት መኖሩን ያሳያል። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት የሚታረስ መሬት ከ14 በመቶ የሚዘል አይደለም። ስለዚህ ምርታማነት ላይ ብዙ መሰራት የሚጠበቅ ይሆናል።

ለምሳሌ ከምርታማነት አንጻር ብንመለከት ናምቢያ ያላት የሚታረስ መሬት ዜሮ ነጥብ 97 በመቶ ነው። በምርታማነት ደረጃ ስናየው በአንድ ኪሎ ሜትር ስኩዌር (ፐር ኪሎ ሜትር ስኩዌር) ላይ እኛ የምናመርተው ወደ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዩ.ኤስ.ኤ ዶላር ነው። ናምቢያዎች ደግሞ ወደ 67 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዩ.ኤስ.ኤ ዶላር ነው። ይህ ማለት ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን አመላካች ነው ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህል ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ኤዳኦ አብዲ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የወጪ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችላት ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ናት ሲሉ የአንዱአለምን (ዶ/ር) ሃሳብ ያጠናክራሉ። የመልከዓምድሯ አቀማመጥ ለዚህ ምቹ ከመሆኑም በተጨማሪ የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የሚፈልጋቸው ምርቶች አብዛኞቹ የሚመረቱባት ሀገር እንደሆነችም ያስረዳሉ። በዓለም ላይ ያሉ ምርቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረታሉ። ይህ ተፈጥሮ የለገሰችን ቸርነት ነው። እኛ የምንልከው የወጪ ምርት ከብዝሀነት አኳያ ሲታይ ብዙ ነው። ይሁንና በሚፈለገው መጠንና ጥራት እየተመረተ ነው ከተባለ ግን ያንን አላየሁም ይላሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ይሁንና የወጪ ንግዳችንን ልናሳድግበት የምንችልበት ምቹ የሆኑ መደላድሎች አሉ። ዓለም የሚፈልጋቸውን ምርቶችም በሰፊው ማምረት የሚያስችለን እድል አለ። የአግሮኢኮሎጂው በጣም ምቹና ተመራጭ ነው። ነገር ግን ምርታማነት የሚጨምረው ምቹ የሆነ መልከዓምድርና የአየር ንብረት ስላለ ብቻ አይደለም።

ምክንያቱም አብዛኛው ምርት አርሶ አደሩ በራሱ መንገድ የሚያመርተው ነው፤ በአርሶ አደሩ ብቻ የተመረተ ምርት ወደላኪዎች ይመጣል። በዚህ ሂደት ውስጥ ጥራት ውጤታማ መሆን አይችልም። ስለዚህ ከእርሻው ጀምሮ እስከ ላኪ አሊያም ውጭ ሀገር እስከሚደርስ ያለው ሂደት ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን የግድ ነው። ጥራትን ማስጠበቅ የሚቻለው በዚህ መልክ ነውና። በተለይ የምርጥ ዘር አጠቃቀማችን ላይ የምርመምር ማዕከሎቻችንን ጨምሮ በደንብ ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። አምራቾቻችን ገበያው የሚፈልገውን ወደማምረት መምጣት መቻል አለባቸው። የምርምር ማዕከላቱ ከላኪዎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሚገባ ትስስር መፍጠር እንዳለባቸውም ያመለክታሉ።

ሌላውና በጣም ወሳኙ ነገር የግብርናው ሴክተር በፋይናንስ የበረታ መሆን መቻል አለበት። ግብርናው ከሀገሪቱ ጂዲፒ ምን ያህል እንደሚይዝ ይታወቃል። ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የውጭ ምንዛሬ ከምናገኝባቸው ዘርፎች ከ70 በመቶ በላይ የሚይዘው ግብርና ነው። ስለዚሀ ይህ የግብርና ዘርፍ በሰለጠነና በተማረ የሰው ኃይል እንዲሁም ግብዓቱን ጨምሮ አሁን ካለው ይልቅ ወደሜካናዜሽን እንዴት ማሳደግ አለብን በሚል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

አቶ ኤዳኦ እንደሚናገሩት፤ ሌላው ነገር ዓለም የሚፈልገው የምርት ዓይነት የቱ ነው የሚለው መለየት አለበት። ኢትዮጵያ ለዓለም የምታቀርባቸው ለምሳሌ እርሳቸው ያሉበት ዘርፍ የቅባት እህልና የጥራጥሬ ሴክተር ነው። በአሁኑ ወቅት የዓለም ሁኔታ ሲታይ በአመጋገብ ሥርዓት እየተቀየረ ነው። ከእንስሳት ወደ እጽዋት እየሄደ ነው። እሱ ደግሞ የሚፈልገው የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ነው። ዓለም ጤነኛ የሆነ አመጋገብ ይፈልጋል፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ ፍላጎት ተንተርሳ እንዴት አድርገን ነው ማቅረብ ያለብን በሚለው ላይ መሥራት የግድ የሚላት ወቅት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በየዘርፉ እየተካሔዱ ያሉ ማበረታቻዎች የሚያነቃቁ ናቸው የሚሉት አቶ ኤዳኦ፣ ነገር ግን ወጥነት ባለው መልኩ መሔድ መቻል አለባቸው ይላሉ። ለሀገሪቱ ትርጉም ያለው አበርክቶ እንዲኖራቸው አድርጎ መሥራት ወሳኝ ነው። ሌላው ኢትዮጵያ የተቀመጠችበት ሁኔታ በተለይ መካከለኛው ምስራቅ፣ ኢስያ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ሀገሮች ሲሆኑ፣ ለእኛ ቅርብ ናቸው። ይህ ማለት በጣም ብዙ ምርት ማቅረብ ያስችለናል ማለት ነው። እነዚህን ገዥ ሀገራት እንዴት አድርገን ወደ እኛ ምርት እንዲሳቡ ማድረግ አለብን በሚለው ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ምክንያቱም የእኛን ዓይነት ምርት የሚያመርቱ ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት አሉ። እነርሱ ግን ከኢስያ በጣም ይርቃሉ። ስለዚህ የጂኦግራፊ አቀማመጥ እድላችንን መጠቀም አለብን ይላሉ፡፡

አንዱአለም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አጠቃላይ 90 በመቶ የሚሆነው ወደ ውጭ የምንልከው አስር ፕሮፐርቲ ላይ አተኩረን ነው ይላሉ። አብዛኛው ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ አበባ እና የመሳሰሉት ናቸው። መዳረሻዎቹን ስንመለክት 50 በመቶው የሚሆነው ወደአምስት ሀገራት ላይ ሲሆን፣ የቀረውን ጨምሮ 90 በመቶውን ኤክስፖርት የምናደርገው ወደ 30 ሀገራት ላይ ነው። መዳረሻ ከማስፋት አንጻር ገና ብዙ ርቀት መሄድ እንዳለብን ይሰማኛል። ልክ እንደ አቶ ኤዳኦ ሁሉ ብዙ አቅም አለን ሲሉ ያስረዳሉ። እርሳቸው፤ ገቢ ምርቱን ብንመለከት ከ70 በመቶው በላይ የምናሰገባው ከቻይና እንደሆነም ያመለክታሉ።

እንደ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ገለጻ፤ ለወጪ ንግዱ መልካም አጋጣሚ ተብለው የሚወሰዱ አሉ። ይኸውም የዓለም የንግድ ድርጅት ስምምነት በቅርቡ ወደ ትግበራ እየገባ መሆኑ ትልቅ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው። ያንን አቅም ደግሞ አሟጥጦ ለመጠቀም ስምምነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ሁለተኛው የድህነት መጠን በዓለም ደረጃ እየቀነሰ በመምጣቱ በኩል ምናልባት የአፍሪካን ለመጥቀስ ያህል በ1990 ወደ 53 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች የነበረ ነው። በአሁኑ ሰዓት ግን ዝቅ ብሎ ወደ 31 በመቶ ሆኗል። አብዛኛው ሰው ከድህነት ውስጥ ወጣ ማለት የመግዛት አቅሙ በዚያው መልኩ ስለሚጨመር የኢትዮጵያን የኤክስፖርት አቅም ይጨምረዋል። ሀገራቱ የኢትዮጵያን ምርት በዚያው ልክ እየተጠቀሙ ይሄዳሉ። የአፍሪካ የመግዛት አቅም ጨመረ ማለት የወጪ ንግዱም አደገ እንደማለት ነው። የአፍሪካ የሕዝብ ቁጥር ወደ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ያህል ሕዝብ ነው። ስለሆነም ከዚህ አንጻር ትልቅ አጋጣሚ ይኖራል።

ሌላው የወጪ ንግዳችንን በመጠን ብናሳድግ የተቀባይ ሀገራት ስጋት አይኖርም። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት የመጣው እየተሻሻለ ነው፤ ለምሳሌ ከአይ.ኤም.ኤፍም ሆነ ከዓለም ባንክ ጋር በጣም ጥሩ የሆነ ግንኙነት መፍጠር መቻላችን እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችንም መልካም በመሆኑ ለወጪ ንግዳችን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው ይላሉ። ሀገራችን በቅርቡ የወሰደቻቸው ማሻሻያዎች አሉ። አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ብዙ ለውጦችን ይዞ ይመጣል ብዬ አስባለሁ። ምናልባት አንደኛው ለውጥ ውጭ ምንዛሬ በገበያ መር እንዲወሰን መደረጉ የወጪ ንግድ ዘርፉን ያነቃቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡

አንዱአለም (ዶ/ር)፣ ከወጪ ንግዱ አንጻር ተግዳሮት ነው የሚባለው ነገር አንደኛ የጂኦፖለቲክሱ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ መኖሩ ነው ሲሉ ያመለክታሉ። የዩክሬን ፈተና አለ፤ በእስራኤና በጋዛ መካከል የተፈጠረው ችግርም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው። ይህ ዓይነቱ ችግር ወደድንም ጠላንም ሀገራችንን ይነካዋል በማለት ያብራራሉ። ሌላው የባህር በር አለመገኘት በራሱ ተግዳሮት ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ መንግሥት እየወሰደ ባለው እንቅስቃሴ ችግሩ የሚፈታ ከሆነ ተጽዕኖውን መቀነስ ይቻል ይሆናል ይላሉ።

የላኪዎች የፋይናንስ ፈተና እንደ ተግዳሮት የሚጠቀስ ነው የሚሉት አንዱአለም (ዶ/ር)፣ የኢ-ኮሜርስ አለመስፋፋትም እንደተግዳሮት የሚወሰድ ነው ይላሉ። በተለይ የተማረና በቂ የሰው ኃይል አለመኖሩም አንደኛው ተግዳሮት እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡

አንዱአለም (ዶ/ር) እንዳሉት ሁሉ አቶ ኤዳኦም፣ ተግዳሮቱ አንደኛው ውጪያዊ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ውስጣዊ ነው ይላሉ። (ዶ/ር) አንዱአለም የጠቀሷቸው ውጪያዊ ተግዳሮቶች ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ናቸው ይላሉ። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ተግዳሮቱ ዓለም አቀፋዊ መሆናቸው ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ እነርሱ በመንግሥት በኩል በየጊዜው እየታዩ የሚሄዱ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

እኔ ውስጣዊ በሆኑ ችግሮች ላይ ማተኮር እፈልጋለሁ የሚሉት አቶ ኤዳኦ፣ አሁን ያለን የወጪ ንግድ መጠን ሲታይ ለምሳሌ 200 ሺ ሜትሪክ ቶን እናመርትና በዓመት የምንሸጠው መቶ ሺ ነው። ለምንድን ነው 200 ሺውን በስድሰት ወር ውስጥ ወይም በዘጠኝ ወር ሸጠን የማንጨርሰው? ተግዳሮት የሆነብን ነገር ምንድን ነው? እንዴትስ ችግሩን ቀርፈን ዓላማችንን ማሳካት እንችላለን? ሲሉ ይጠይቁና፣ አንዱ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን የማፈላለግ እንቅስቃሴያችን ብዙን ጊዜ ውስን ነው ሲሉ ይመልሳሉ። አስተውለን ከሆነ የምርቶቻችን መዳረሻ ሀገራት በጣም ውስን ናቸው። ላለፉት አምስት ዓመታት ብናስተውል ከአስር ሀገር የዘለለ አይደለም ይላሉ።

ይህንን በምሳሌ ሲያስረዱ እንደገለጹት፤ መካከለኛው ምስራቅ ላይ ብንወስድ በብዛት ወደሳዑዲ አረቢያ ቡና ይላካል። ነገር ግን ኦማን ከፍተኛ ገንዘብ ያላት ሀገር ነች። ኳታርም እንዲሁ ናት። ምን ያህል ነው ላለፉት አስር ዓመታት ቡና፣ ሰሊጥ ወደእዛ የላክነው የሚለውን ብናይ በጣም ትንሽ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ሀገራት የመግዛት አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡። በተጨማሪም ደግሞ ቡና በጣም የሚፈልጉ ሀገራት ናቸው። ሰሊጥም ጥራጥሬም ይፈልጋሉ። ይሁንና የሚገዙት ከየት ነው ቢባል፣ ከእኛ ገዝተው እሴት ጨምረውና ሪብራንድ አድርገው ከሚሸጡላቸው ሀገራት ነው። ስለዚህ የእኛን ስትራቴጂ መከለስ ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

ይህንን ልናሳካ የምንችለው አንዱ በኤምባሲዎቻችን አማካነት ነው፤ የኤምባሲዎቻችን ሚና የሚታወቅ ነው፤ እስከ ዛሬ ድረስ ከሚሰጣቸው ተልዕኮ ውስጥ አንዱ የንግዱ ጉዳይ ነው እንጂ የሀገራቸውን ጉዳይ ማስተዋወቅ ብቻ አይደለም። ለገዥ ሀገራት ምርቶቻችን በኤምባሲዎቻችን አማካይነት ማስተዋወቅ ይጠበቅብናል። ከዚያም አልፎ ተርፎ ገዥዎች ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው ምርቶቻችንን እንዲያዩ ማድረግም ተገቢ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ የነበረው ሂደት ከዚህ አንጻር ሲታይ በጣም አነስተኛ ነው። ለምሳሌ ቻይና እና አርጀንቲና ቀይ ቦለቄ ይመረታል፤ እነርሱ አንድ ሺ ዶላር ሲሸጡ እኛ የምንሸጠው 700 ዶላር ነው። እኛ 900 ዶላር ማድረግ ያቃተን ለምንድን ነው? አንድ የግሉ ሴክተር በራሱ ኤክስፖርቱን እንደ ቢዝነስ የመያዝ ችግር በመኖሩም ጭምር ነው፡። በመሠረተ ልማቱ ላይም ኢንቨስት አናደርግም። ለጥራት ውድድር ራሳችንን እያዘጋጀን አይደለም። ስለዚህ እኛም ለጥራት ወድድር ራሳችን አዘጋጅተን ሌላውን ለማሸነፍ መሥራት አለብን ይላሉ።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ የወጪ ንግዱ በጥራትም በብዛትም እንዳይሳለጥ እንቅፋት የሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የግድ ነው። ምቹ የሆነውን ተፈጥሮ በአግባቡ መጠቀምም ብልህነት ነው። የሎጂስቲክ አቅርቦቱ በአግባቡ የተቀናጀ እንዲሆን ማድረግም አዋጭ ነው። ላለፉት አስር ዓመታት በወጪ ንግዱ ላይ ሲሰራ የነበረው በፈተና ውስጥ በመሆን ነበር። አሁን ተግባራዊ የተደረገው ማሻሻያ ትልቅ ጥቅም ያለው በመሆኑ በራስ መቆም የሚያስችል ነው። ለወጪ ንግድ የሚሆን እድልም ምቹ ሁኔታም ያለን ሀገር እንደመሆናችን ጥሩ ምልክት ያየንባቸውን እንደ የቅባት እህል፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ ሆርቲካልቸር ያሉትን ዘርፎች አቅም በማሳደግ ማስፋት ያስፈልጋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You