ለሁለንተናዊ እድገታችን ስኬት ለሰላማችን አብዝተን መሥራት ይጠበቅብናል

በነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆነው የዓለም ኢኮኖሚ ለበርካታ ጊዜያት መንገጫገጭ ታይቶበት ነበር። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1930 ከታላቁ ድብታ (greatest depression) ጀምሮ ዓለማችን ታላላቅ የኢኮኖሚ ቀውሶችን አስተናግዳለች። ከእነዚህ መካከል ‹‹Great Recession›› እየተባለ የሚጠራው የ2007ቱን እና የ2008ቱን የኢኮኖሚ መንኮታኮት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ከአምስት ዓመታት በፊት የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የናጠው የዓለም ኢኮኖሚም ገና አላገገመም። ወረርሽኙ በርካታ ጥፋቶችን አስከትሎ ጠባሳውን ጥሎ ነው ያለፈው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የዩክሬኑና የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ጠንካራ ክንዱን በኢኮኖሚው ላይ እያሳረፈ ይገኛል። የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስም የቀይ ባህርን የንግድ መስመር በማወክ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከእዚህ ችግር የራቀች አይደለችም። እንጂ የግብርና ምርቶችን በመላክ (export) ከቱሪዝም በምታገኘውን ገቢ እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች በሚልኩት ገንዘብ (Remittance) አማካኝነት ነዳጅ፣ መድኃኒት፣ ማሽነሪዎችን በማስገባት (import) የምትተዳደር ሀገር ነች። ለዚህ ነው የዓለምን ኢኮኖሚ የሚያነቃንቁ ክስተቶች በቀላሉ ኢኮኖሚያቸው ላይ አለመረጋጋት ከሚፈጥርባቸው ሀገራት ተርታ እንድትመደብ ያደረጋት።

ኢትዮጵያ የ120 ሚሊዮን ሕዝቦች መኖሪያ ነች። ከዚያ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ኃይል ወጣት ነው። ይህ ኃይል ወደ ሥራ ቢሰማራና አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ክህሎት ቢያዳብር ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም ነው። ይሁንና አብዛኛው ከመንግሥት እጅ ሥራ የሚጠብቅ ነው። ለአራትና አምስት ሚሊዮን ሕዝብ በየዓመቱ የሥራ እድል መፍጠር ቢቻልም አሁን ላለው ኃይል በሙሉ ግን ይህንን ማድረግ በፍፁም የማይቻል ነው።

ሀገሪቱ የምትገኝበት የፖለቲካ ሥነ ምህዳር (ቀጠና) እንደ እሳተ ጎሞራ የሚንተከተክ ነው። በቀይ ባህር ዙሪያ አያሌ ሽኩቻዎች አሉ። የኢትዮጵያን የመልማት ጎዞ ለመግታት የሚውተረተሩ (እንደ ግብፅ በዓባይ ጉዳይ)፣ የአፍሪካ መዲናነቷ እንቅልፍ የነሳቸው እንዲሁም የተለያዩ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍላጎት ያላቸው አካላት ይገኙበታል። በዚህ ሁሉ መሀል ሆና የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለማቻቻል እየተጋች ትገኛለች። በርግጥ ጉዞው ሸለቆና ወጣ ገባ የበዛበት ከባድ ቢሆንም ይህንን ሁሉ ተሻግሮ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችንና ፍላጎቶችን ማሸነፍ የሚችል ህብረ ብሔራዊ አወቃቀር የያዘች ነች።

በልማት አጀንዳዎች ውስጥ ተይዘው የኢትዮጵያን መፃኢ ተስፋ ያለመለሙ የኢኮኖሚ በረከቶች መኖራቸውን እሙን ነው። ሆኖም ከላይ ባነሳናቸው ልዩ ልዩ ምክንያቶች ተፅዕኖ ውስጥ ቆይታለች፤ ዜጎቿን ለግጭት ሲዳረጉ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ኢትዮጵያ ሰላሟ ደፍርሶ ሁሌም እጆቿ ተመፅዋች እንዲሆኑ ጠላቶቿ ይታትራሉ። በውስጥ ጉዳዮቿ ጭምር እጃቸውን እያስገቡ ህልውናዋ እንዳይቀጥል፣ ሰላሟ እንዳይሰፍን፣ ኢኮኖሚዋ እንዳያድግ የተቻላቸውን ያደርጋሉ፤ አሁንም እያደረጉ ናቸው። በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ኢኮኖሚውን ለማሳደግና በቀጣናው ላይ ትልቅ ኃይል ሆኖ ለመውጣት የሚደረገው ጥረት ግን የተቋረጠ አይደለም።

ከውጭ ጠላቶቻችን ባሻገር ኢኮኖሚያችንን የሚፈትኑ፤ የልማት ጉዞው ላይ ጋሬጣ የሆኑ የውስጥ ባንዳዎችም አልጠፉም። ከትላንታችን ምስቅልቅል ተምሮ ለሀገር ከመሥራት ይልቅ በታመሰ የሀገር ገፅታ፣ በደፈረሰ ሰላም ውስጥ እስትንፋሳቸውን ማስቀጠል የመረጡ ቡድኖች እዚህም እዚያም ተበራክተዋል። ይህም ዜጎች በነፃነት ከአንዱ ወደ አንዱ አካባቢ እንዳይንቀሳቀሱ፣ እንደ ሃሳባቸው ውለው እንዳይገቡ፣ለሀገር እድገት አስተዋፅኦ በሚያበረክቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዳያደርጉ ምክንያት እየሆኑ ናቸው።

የሰላም መስፈን ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት መሆኑ ግልፅ ነው። ያለ ሰላም ጠንካራና ዘላቂ ኢኮኖሚን መገንባት ዘበት ነው። በኢትዮጵያ ረዘም ላሉ ዘመናት የቆየው የተዛባ የፖለቲካ ትርክት እንዲሁም ከለውጡ ዋዜማ አንስቶ በሀገሪቱ የነበረው ጦርነትና ግጭቶች፣ መፈናቀሎች ምን ያህል ኢኮኖሚያችን ላይ ጫና እንዳሳደሩ መገመት አያዳግትም። ለልማት ይውል የነበረ ሀብት በጦርነት መውደሙ ልብን የሚሰብር እውነታ ነው። በሰላም እጦት ምክንያት ተዘዋውሮ አለመሥራት በንግድ ሥርዓቱ ላይ እየፈጠረ ያለው እንቅፋትም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው።

በርግጥ እንዲህ ላሉ ውስጣዊ አለመግባባቶች መንግሥት ‹‹ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በንግግር እንፍታቸው›› ከማለት አልቦዘነም። ለዚህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቃል አስረጂ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተግባር ስኬታማ እንዲሆን መንግሥት በሰላምና መረጋጋት ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ተደጋጋሚ ጥሪዎችም የፖለቲካ ልዩነት ላላቸው ወገኖች በመገናኛ ብዙሃን ሲደረጉ ሰምተናል።

እንደሚታወቀው በተግባርም መንግሥት በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ሆነ ከሸኔ ጋር ንግግር ከጀመረ ውሎ ማደሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል። በተቃርኖ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችና ከመንግሥት ጋር ንግግር የጀመሩ ቡድኖች ቀጣይነት ባለው መልኩ ወደ ውይይት ከገቡ ሰላም ይሰፍናል፣ ሀገሪቱ የምታስበውን ብልፅግና ታረጋግጣለች።

ከዚህ በተቃራኒ እንደ ሀገር በጭንጫም፣ በጭቃም ላይ ፍቅር መዝራት ቸግሮን የጦርነትና የሞት አዝመራ የሰበሰብንባቸው ጊዜያት በብዙ አስከፍለውናል። በእነዚህ ግጭቶችና ጦርነቶች ከሚያልፈው ክብሩ የሰው ልጅ ሕይወት ባሻገር ታዲያ የሚወድመው የሀገር ኢኮኖሚ ቸል የሚባል አይደለም።

ሰላምና ኢኮኖሚ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። የሀገራችን ሰላምና ኢኮኖሚ መነጣጠል የማይችሉ ሁለት ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። ያለ ሰላም ምንም ማድረግ ስለማይቻል ኢኮኖሚው ጉዳት ይደርስበታል። ሰላም ሳይኖር ኢኮኖሚው ቢቀጥልም የታሰበውንና የሚጠበቀውን ያህል ግቡን ሊመታ አይችልም፡፡

ሰላም አንድን ሀገር ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ ከሚያደርጉ አበይት ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋንኛው ነው። ኢትዮጵያ የጀመረችው አዲሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥርዓት የሀገሪቱን የውጭ ገበያ የማሳደግ እና ለሀገሪቱ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የመሳብ እምቅ አቅም አለው።

በተመሳሳይ የሀገርን የውጭ ገበያ ለማሳደግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የግድ ይላል። ለዚህም የሰላም ሚናው ቀድሞ ይነሳል። ስለዚህ እንደሀገር የተተገበረው አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤታማ እንዲሆን ሰላም አማራጭ የሌለው ብቸኛ መንገድ ነው።

ኢትዮጵያ በትላንትነት ልታነሳው በማትሻው የቅርብ ጊዜ ትውስታዋ ብዙ ኪሳራዎችን አስተናግዳለች፣ ከዛሬዋ የተቀነሰባት፣ ለነገዋ የምትዳክር ሀገር ናት። ይህ ሊሆን የቻለው ከውጭ የራሳቸውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ በሚጎነጎን ሴራና በውስጥ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት ነው። ይህ መዘዝ ዛሬም እልባት አላገኘም። ለዚህ ነው በበርካታ ምክንያቶች የገጠመው የኢኮኖሚያዊ ስብራት ይጠገን ዘንድ ሀገሪቱ የምትወስዳቸው ርምጃዎች በውጤት ይታጀቡ ዘንድም ሰላም ወሳኝ መሆኑ ግልፅ የሆነው።

ስለዚህ እንደ ሀገር ለገጠመን የሰላም ችግር ሁሉም በጣምራ ሊታትር ይገባል። ለዚህም ሁለት አማራጮች ይኖሩናል። አንድም ግጭት ውስጥ ሆነን ሁሌም ‹‹ድሀ›› እየተባልን መቀጠል አሊያም ሁላችንም /ሕፃን አዋቂ፣ የተማረ ያልተማረ ሳይባል ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን በቁርጠኝነት መሥራት።

ሰላም የሚጠቅመው አንድን ግለሰብ ወይም አንድን ቡድን ብቻ አይደለም። ሰላም ሲሰፍን ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን። ሰላም መስፈኑ ዓለም አቀፍም ሆኑ ኢትዮጵያዊ ኢንቨስተሮች በብዛት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ይህ ሲሆን የሥራ እድል ይፈጠራል፣ የግለሰብም ሆነ የሀገር ገቢ ይጨምራል፡፡

መንግሥት የሰላምና የልማት እቅዶቹ እንዲሳኩና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጥ እንዲያመጣ ሰላምና መረጋጋት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቋል። የሰላም ጥሪው ግን እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ውጤት እንዳይርቃቸው በሆደ ሰፊነት መሥራት ይገባዋል። የሕዝብ ጥያቄ አለን ብለው መሳሪያን ያነገቡ አካላት ለሰላም ጆሮ ሊሰጡ ይገባል። ችግሮች ሁሉ በጦርነት እንደማይፈቱ ማመን አለባቸው። በጦርነት የሚመጣ ሰላምም ሆነ በጦርነት የሚፈታ ችግር እንደሌለ ተገንዝበው ለውይይት ቦታ መስጠት አለባቸው።

ጦርነት ሀገራችን የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ እንድትገባና እድሜ ልክ የስንዴ ለማኝ ሆና እንድትኖር መፍቀድ መሆኑን ተረድተው መወያየትን ማስቀደም ግድ ይላቸዋል። እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ ሁከቶችን ለማርገብ ከሁሉም ጋር የተቀናጀ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። መሳሪያ አንስተው በጦርነትና በግጭቶች ላይ ተሳታፊ ከሆኑት አካላት ጋር የሚደረገው ውይይትም ዜጎችን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል።

መቼም ሀገራችን አሁን ሰላም ያጣችው በውጭ ወራሪዎች ምክንያት አይደለም። በርግጥ አንዳንድ ኃይሎች የሚያደርጉት ትንኮሳና ጣልቃ ገብነት ችላ ሊባል አይገባም። ይሁን እንጂ ዋናው ችግር ያለው እዚሁ ነው፤ በእርስ በርስ ጦርነት በርካታ ውድመት እየደረሰ ነው። ጦርነቶች ሁሉ ምክንያታዊ መነሻ ይኑራቸው እንጂ ለውጥ ለማምጣት ግን ሁነኛ መፍትሔ አይደሉም። ለውጥ ቢያመጡ እንኳ ያመጡት ለውጥ ወይ በሌላ ጦርነት አሊያም በአመፅ የሚገለበጥ ይሆናል። ታሪክም ይሄንኑ ያስረዳናል።

ሀገራችንን ለዚህ የዳረጋት የተዘራ ክፉ ዘር ነው። ይህንን የመለያየት ዘር ማጥፋት የሚቻለው ደግሞ የመተባበር ዘር በመዝራት ብቻ ነው። የዛሬው ጦርነት ለነገ እሾህን አስቀምጦ የሚያልፍ ነው። መፍትሔው ቁጭ ብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ መመካከር ነው። መነጋገሩ አድካሚ ቢሆንም እሾሁን አንድ በአንድ የሚነቅል ነው፡፡

ከሁሉ በፊት በመነጋገር ውስጥ ‹‹እኔም ዋጋ አለኝ፣ በሀገሬ ጉዳይ ወሳኝ ነኝ›› የሚል ክብርና ኩራት አለ። በመነጋገር ውስጥ ለሀገርና ለትውልድ መልካም አበርክቶን መስጠት አለ። በመነጋገር ውስጥ መተዋወቅ አለ። አንዱ የሌላውን ብሶትና ስጋት፣ ሃሳቡን እንደዚሁ መረዳት አለ። በመነጋገር ውስጥ መቀባበል አለ።

ምክክር በሩቁ እንደዚህ ሊያስብ ይችላል፣ እንደዚህ ልታስብ ትችላለች ብሎ ከመፈራረጅና ከመገማመት አውጥቶ መተዋወቅን ይፈጥራል። ሃሳብ በሃሳብ ይዳብራል፣ ሃሳብ በሃሳብ ይሻራል፣ ሃሳብ በሃሳብ እየተፋጨ ስል ይሆናል። በምክክር የደፈረሰው፣ የዳመነው፣ የጨለመው ይገለጣል፤ ክፉውም ይታረቃል፣ በጎውም ይዳብራል።

ይሄ መንገድ ብዙ ሀገራትን ጠቅሟል። እኛንም ይጠቅማል። ቁጭ ብሎ መነጋገርን ከቅዱሳት መጻሕፍት ጀምሮ ብዙ የፍልስፍናና የፖለቲካ መጻሕፍት ያስተምሩታል። ብዙዎችም በታሪክ ተጠቅመውበታል።

እኛም ነገ በታሪክ እንዘከርበታለን። ብዙዎችም ፈለጋችንን ይከተላሉ። እንደ ኢትዮጵያዊያን በዓድዋ ተራሮች ብቻ ሳይሆን በአዳራሽ ውይይቶችም ድልን እንደምናገኝ የውይይት ወይም የንግግር ጀግኖች መሆናችን ይመሰከርበታል። ይህንን መንገድ የማንከተል ከሆነ የሰላም መደፍረሱ ቀጥሎ ብዙ ነገሮች ባሉበት እንዲቆሙ ምክንያት ይሆናል፤ ወይም ወደ ኋላ ይጎትታቸዋል።

ሰላምና መረጋጋት የእያንዳንዱ አካባቢ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ድምር ውጤት ነው። በመሆኑም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። ይህ ደግሞ የራስን ጥቅም ወደ ጎን በማድረግና የሕዝብን ፍላጎት በማክበር የሚገለፅ ነው። የሰላም ውይይቶች በሂደቱና ውጤት ላይ በማተኮር ተገቢና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መግባባት ላይ መድረስ እንዲችሉ ከፍ ያለ ጥረት ያስፈልጋል። ይህም ለንፁሃን ኢትዮጵያዊያን በማሰብ ጭምር ሊሆን ይገባል።

ከሁሉ በላይ ሰላምን እንደውሀ የተጠማችው ሀገራችን እውነተኛ ሰላምን አግኝታ ወደ ልማቷ ፊቷን ማዞር ይኖርባታል። ምክንያቱም ኢኮኖሚ ያለ ሰላም አይገነባም። በመሆኑም በሀገር ውስጥ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ አለመግባባት ለመፍታት የተጀመረው ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ሁላችንም ታሪክም፣ ሀገርም፣ ትውልድም፣ ፈጣሪም የጣሉብንን ታላቅ አደራና ሸክም በብቃት መወጣት ይጠበቅብናል። ሌላው እዳው ገብስ ነው። የውጭው ኃይል የእኛን አንድነት፣ መስማማት እና ፖለቲካዊ ስክነት ተመልክቶ ማፈግፈጉ አይቀርም። ኢትዮጵያም በቀይ ባህር ላይ የሚኖራት ሚና መግዘፉ እንደዚያው በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል።

በመጨረሻም ኢትዮጵያን ወደ እድገትና ብልፅግና ያሸጋግራል የተባለ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ መሬት ወርዶ ለውጥ እንዲያመጣ፤ ዜጎችም ትኩረታቸው ሥራና ለውጥ ላይ እንዲሆን ሰላማችንን በቅድሚያ ማረጋገጥ ላይ እናተኩር በማለት ርእሰ ጉዳዩን እዚህ ላይ እንቋጭ፡፡

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You