ምስጋና ሊቸረው የሚገባ የከተማዋ የአረንጓዴ ስፍራዎች ልማት !

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማት የሚካሄድባቸውን ስፍራዎች ከሞላ ጎደል ተዟዙሬ ተመልክቼያቸዋለሁ። የተቀሩትን ደግሞ በመገናኛ ብዙሃንና በእግር መንገድ ተመልክቼያቸዋለሁ። በዚህ ልማት ብዙ ሳቢ የሆኑ ሥራዎች እንዳሉም ተረድቼያለሁ።

በልማቱ ኮሪደር እንዲሆን የታሰበውን አካባቢ የማይመጥኑ ግንባታዎችን የማንሳት፣ ዘመኑን የዋጁ የመንገድ፣ የቴሌኮም፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የመጸዳጃ ፍሳሽ ማስወገጃ ፣ የደህንነት መሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ማካሄድ፣ ከተማን ከተማ የሚያሰኙ የመብራት፣ የህንጻ ማሳመርና የመሳሰሉት ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ሁሉም መሠረተ ልማቶች በየራሳቸው ብዙ ሊባልላቸው የሚችሉ ናቸው። እኔ አንዱን የልማት አካል ሳብ አድርጌ ጥቂት ለማለት ወድጃለሁ።

ስለ ከተማ ልማት ሲታሰብ ሕንፃ በሕንፃ የሆነ አካባቢ የሚታሰባቸው ጥቂት አይደሉም፤ ለእነሱ ከተማ ማለት የተገጠገጠ ሕንፃ ወይም የሕንፃ ጫካ፣ ቤት በቤት የተሞላ አካባቢ ያለበት ብቻ ነው። የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡበት፣ በመብራት ያሸበረቀ አርገው የሚያዩም እንዲሁ ጥቂት አይደሉም፤ እንደ ውሃ መብራትና የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት የሚሉም እንዲሁ ጥቂት አይደሉም።

ከተማ ከእዚህ ሁሉ ባሻገር ነው ፤ ኮንክሪት በኮንክሪት መሆን የለበትም፤ ዓይን መስበሪያ በመሆን የሚያገለግሉ እንደ አረንጓዴ ስፍራ ያሉ ሌሎች መሠረተ ልማቶችም ያስፈልጉታል። በተለይ የከተማ ውስጥ የአረንጓዴ ስፍራዎች ትልቅ ስፍራ ይሰጣቸዋል። ለእዚህም ነው የከተማ ልማት ባለሙያዎች ከከተማው ይዞት ውስጥ ለሕንፃና ለመሳሰሉት ግንባታዎች፣ ለአረንጓዴ ስፍራ፣ ለመሠረተ ልማት በሚል በሶስት የሚያከፋፍሉት። እያንዳንዱ መንደር እንዲመሰረት ሲደረግም በዲዛይኑ በተቻለ መጠን ይህን ባካተተ መልኩ እንዲሆን የሚደረግበትም ሁኔታም እንዳለ ይታወቃል። የማህበር ቤት የገነባችሁ ይህን ታውቃላችሁ።

ይሁንና ይህ ዓይነቱ አሰራር በሀገራችን በወረቀት ላይ ብቻ የተቀመጠ ነው። መሬት ተወርዶ ሲታይ በጥቂት ቦታዎች ካልሆነ በቀር የአረንጓዴ ስፍራ ብሎ ነገር የለም። ለእዚህ ታላቅ አላማ የተቀመጠ ስፍራ በሕንፃ በፋብሪካና በመሳሰሉት ተተክቶ ይገኛል። አዲስ አበባ በዚህ ዓይነቱ በሽታ በእጅጉ ተጎድታለች። ለአረንጓዴ ስፍራ የተያዙ ቦታዎች በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ተቸብችበዋል፤ ልጆች ኳስ እየተጫወቱባቸው ያደጉባቸው ቦታዎች ሳይቀሩ ተሸጠዋል፤ በወንዝ ዳርቻዎች ላይ የነበሩ አረንጓዴ ስፍራዎች ጭምር ከታለመላቸው አላማ ውጭ ተደርገዋል።

ከእንጦጦ፣ የካና ጉለሌ የተራራ ሰንሰለት ውጭ ያሉት በከተማዋ ከፍታ ቦታዎች እንዲሁም በመሀል ከተማዋ የሚገኙ በአረንጓዴ ስፍራ የተሸፈኑ ቦታዎቿ በግንባታ ተተክተዋል። ቤት ያላረፈበት ቦታ ሁሉ በኪስ ቦታነት ተለይቶ ለግንባታ እንዲውል ተደርገዋል። ችግሩ በእዚህ አላበቃም፤ አረንጓዴ ስፍራዎችን የማውደሙ የጥፋት ዘመቻ የድፍረቱ ድፍረት በመናፈሻ ቦታነት እያገለገሉ ያሉ በመሀል አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የሚታወቁና የሚወደዱ የመንግሥት የአረንጓዴ ስፍራ /ፓርኮች/ ይዞታዎች ላይ ጭምር ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሟል። በዚህ በኩል አጥፊው መንግሥትና መንግሥት ብቻ ናቸው።

መንግሥት ቦታ የሚያዝ ሆኖ ሳለ ካላጣው ቦታ የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶችን፣ የወጣት ማዕከላትን፣ ጤና ጣቢያዎችን፣ ወዘተ የገነባበት ሁኔታ ጥቂት ተብሎ የሚታይ አይደለም። እነዚህ ግንባታዎች አያስፈልጉም ማለቴ አይደለም፤ በእጅጉ ያስፈልጋሉ። ለምን በእነዚህ ስፍራዎች ውስጥ ተገነቡ ነው ጥያቄዬ። በእዚህ ዓይነቱ ድርጊት መንግሥት ራሱንም የጥፋቱ ዋና ተዋናይ ያደረገበትን ሁኔታ ተመልክተናል። እነዚህ ቦታዎች ሊጠበቁ፣ ሊስፋፋ፣ ሊለሙ ሲገባ በግንባታ እንዲሞሉና እንዲጣበቡ አልፎ ተርፎ ሙሉ ለሙሉ እንዲጠፉ ተደርገዋል።

ከተማዋ ሳምባዋ ተብሎ ከሚጠራውና ቢከፋም ቢለማም በብዙ ግብግብ ተጠብቆ ከቆየው የእንጦጦ የደን ክልል ውጭ ሌሎች ሳምባዎቿ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎችን እንድታጣ በመደረጉ ነዋሪዎቿ እንደ ሠርግ ለመሳሰሉት ተግባሮች ከሕንፃዎች፣ ከደካከሙ ቤቶች፣ ከተጣበቡ መንገዶች ውጭ የሚቆዩባቸው አረንጓዴ ስፍራዎችን ፍለጋ ብዙ ርቀት መጓዝ የግድ ብሏቸዋል። ዓይን መስበሪያ ሊሆን የሚችል አረንጓዴ ስፍራ ማጣት ምን ያህል የከፋ እንደሆነ አሁን ትገነዘቡታላችሁ ብዬ አስባለሁ።

ይህ ሁኔታ እንዲቀየር የከተማ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ወዘተ ባለሙያዎች አጥብቀው ሲጠይቁም ኖረዋል። በከተማዋ የአረንጓዴ ስፍራ እጦት ዋና ችግር ሆኖ መገኘቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ላለችው ኢትዮጵያ ስም አይመጥንም።

ይህ ከተማዋን አረንጓዴ አልባ ሲያደርጋት የቆየ አካሄድ ባለፉት ስድስት ዓመታት ወሳኝ በሆነ መልኩ ተቀይሯል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በገበታ ለሸገር ፕሮግራም በከተማዋ በተካሄዱት የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች እንዲሁም በእንጦጦ ፓርክ ልማት የተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት ሰፋፊ ሥራዎች ለእዚህ ለውጥ ሁነኛ ምስክሮች ናቸው።

መንግሥት እንደ ሀገር ለአረንጓዴ ዐሻራ በሰጠው ትኩረት ሀገሪቱን አረንጓዴ ለማልበስ እያከናወነ ካለው መጠነ ሰፊ ተግባር በተጓዳኝ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ለአረንጓዴ ስፍራዎች ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ ነው። ይህንንም ሰፋፊ ፓርኮች በመገንባት፣ በውስጣቸው ልዩ ልዩ አረንጓዴ ሥራዎችን በመሥራት በሚገባ አሳይቷል፤ እያሳየም ይገኛል።

በከተማዋ ለአረንጓዴ ስፍራዎች የዋለውን መሬት ለጨረታ ቢያቀርበው ብዙ ቢሊየን ብር ሊያገኝበት እንደሚችል እያወቀ፣ ከዚህ በላይ የሚቀድም ተግባር የለም በሚል ተጨማሪ ሀብት ወጪ በማድረግ፣ የልማት አጋሮችን በማስተባበር የዓይን ማረፊያ መሆን የቻሉ አረንጓዴ ስፍራዎችን እየገነባ ነው።

በእነዚህ አረንጓዴ ስፍራዎች ሕፃናት፣ አዋቂዎች፣ ወጣቶች ዘና እያሉባቸው ናቸው። ስፓርተኞች የአካል እንቅስቃሴ እያደረጉባቸው፣ ሙሽሮች እየተሞሸሩባቸው፣ ታዳሚዎቻቸውም እየታደሙባቸው ነው። በቀጥታ ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማይዝናኑም ቢሆን አካባቢዎቹ በእግራቸውና በመኪናም ለሚጓዙ ለቀቅ ያሉና አእምሮ ሊታደስባቸው አረፍ ሊባልባቸው የሚችሉ አረንጓዴ ስፍራዎችን መፍጠር ተችሏል፤ ታላላቅ ሀገራዊና ከተማ አቀፋዊ እንዲሁም የግል ዝግጅቶች ማካሄጃ በመሆን ዝግጅቶችን ለማስተናገድ ይገጥም የነበረውን የምቹ ስፋራ እጦትንም እየቀረፉ ናቸው።

ይህ የመንግሥት ቁርጠኝነት በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማትም ተጠናክሮ ቀጥሏል።ይሄኛው የልማት መንገድ ደግሞ ኪስ ቦታን፣ ኮሪደሪን አይመጥኑም ተብሎ የተነሱ መኖሪያ ቤቶችንና የድርጅቶችን ቦታዎች፣ የወንዝ ዳርቻዎችን ጭምር በአረንጓዴ ስፍራነት ማልማት እያስቻለ እንደመሆኑ ከተማዋ በተለያዩ ምክንያቶች አጥታው የቆየችውን የአረንጓዴ ስፍራ መልሶ ማምጣት እየተቻለ ነው።

በአረንጓዴ ስፍራዎቹ የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች ተተክለዋል፤ እየተተከሉም ናቸው፤ ችግኝ ብቻ ሳይሆን ዛፍ እየተተከለ ነው። የሳርና አበባ ልማቱም በዚያው ልክ እየተካሄደ ይገኛል።

በኮሪደር ልማቱ የተፈጠረው አረንጓዴ ስፍራ ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን ለማስቻል ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። በመብራትና በተለያዩ መንገዶች የማሳመር ሥራ ተሰርቷል። ልማቱን ከመሬት አቀማመጥ ጋር ለማስተሳሰር / ላንድስኬፕ/ እየተከናወነ ያለው ተግባር ሥራውን ይበልጥ ማራኪ እያደረገው ይገኛል። በዚህ በኩል የላንድስኬፕ ባለሙያዎች ጥበብ ጎልቶ ወጥቷል። ይህ ጥበብ የተሞላበት ሥራ ልማቱ ምን ያህል በባለሙያ የተከናወነ ስለመሆኑም ያመለክታል። ይህ ልማት ቄንጠኛ የአረንጓዴ ስፍራ ብንለው ቢያንስ እንጂ አይበዛበትም።

በአረንጓዴ ስፍራ ልማቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓመታት ሥራ የተሰራበት ነው ማለት እወዳለሁ። ከዚህም መረዳት የሚቻለው ለመሥራት ቁርጠኝነቱ ካለ መሰራት የማይቻል ነገር እንደሌለ ነው። ይህ የመንግሥት የከተማና የአረንጓዴ ስፍራዎች ልማት ቁርጠኝነት በእጅጉ ሊመሰገን ይገባዋል። ምስጋናው ሥራው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትልቅ አቅም ሊሆን ስለሚችል ምስጋናው ስለተደረገው ብቻ ሳይሆን ስለሚደረገውም ይሆናል።

በከተማዋ የአረንጓዴ ስፍራ ልማት ተጀመረ እንጂ ብዙ ርቀት አልተጓዘም። ከከተማዋ ቆዳ ስፋት፣ ሊኖራት ከሚገባው የአረንጓዴ ሽፋን፣ የሀገሪቱ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ህብረት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከመሆኗ አኳያ ሲታይ አዲስ አበባ የሚያስፈልጋት አረንጓዴ ስፍራ ገና ብዙ ነው። ለዚህ የመንግሥት ቁርጠኝነት የተሞላበት ርምጃ ስኬታማነት አንዳንድ ባለሀብቶች ፋውንቴኖችን በመገንባትና በመሳሰለው እንዳደረጉት አስተዋጽኦ ሁሉ መላ ኢትዮጵያውያንም በገንዘብ፣ በሃሳብ፣ በቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

አዲስ አበባ ከድህነት መላቀቅ እንደምትችል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ከንቲባና ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናት አካላት በልማቱ ባመጡት ተጨባጭ ለውጥ በሚገባ አሳይተውናል።አሮጌው ቄራ፣ ፖሊስ ጋራዥ፣ ፊት በር፣ ፒያሳ፣ ሠራተኛ ሰፈር፣ አፍንጮ በር ወዘተ በልማቱ ምን ያህል ተአምር እንደተሰራባቸው አይተናል። በፒያሳ፣ በሠራተኛ ሰፈር፣ በአፍንጮ በርና በመሳሰሉት በቀጣይም ድንቅ ሥራዎችን እናያለን ብሎ በርግጠኝነት መናገርም ይቻላል።

ሁላችንም ይህን ታላቅ ልማት እያጣጣምን እንገኛለን፤ በሆነው ሁሉ ደስተኞች ነን ብዬ እገምታለሁ። በተያዘው የአረንጓዴ ልማት መንግሥት ከሕዝብ ብዙም የጠየቀው የለም፤ ልማቱን እንዲጠብቅ፣ እንዲንከባከብ ግን ጥሪውን እያቀረበ ነው። እኛም ልማቱን በሥርዓቱ በመጠቀም ሌሎችም በሥርዓቱ እንዲጠቀሙ በማድረግ በኩል የሚጠበቅብንን ሁሉ በማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣ። አሁንም በድጋሚ አንድ ነገር ማለት እፈልጋለሁ፤ በአረንጓዴ ልማቱ የተሳተፈው ሁሉ ሊመሰገን ይገባዋል! በእጅጉ እናመስግን!

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You