«የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የኮሪደር ልማቱ ውበቱን ጠብቆ እንዲቆይ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል» -ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ

አዲስ አበባ ከተማ አዲስ ገጽታን መላበስ ከጀመረች ወራቶችን አስቆጥራለች። መሽቶ ሲነጋ የሚታዩት አዳዲስ ክስተቶች እንኳን ሰነባብቶ የመጣን እንግዳ ይቅርና በነጋ በጠባ የሚመለከታትን ነዋሪዋን የሚያስደምም ነው። ከተማዋ ባለፉት ስድስት ወራት አካባቢ ያስተናገደቻቸው ለውጦች ፈጣንነት ከመቶ ዓመት በላይ በዘለቀው ታሪኳ አይታው የማታውቀው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በትራፊክ መጨናነቅ ለሰዓታት በተሽከርካሪ ውስጥ ማሳለፍ የዘወትር ሥራ የነበረው የከተማዋ ነዋሪ ቢያንስ የኮሪዶር ልማቱ በተጠናቀቀባቸው መንገዶች በፍጥነትና በምቾት ለመጓዝ በቅቷል።

አፍና አፍንጫን በእጅ ደገፎ አልያም በምናምን ወተፍ ተደርግ የሚታለፍባቸውን መንገዶች ዛሬ የደከመው አረፍ ብሎ ንጹህ አየር የሚምግባቸው ሆነዋል። ከየሽንት ቤቱ የሚወጡ ፍሳሽ እና በቆሻሻ ታጅበው በየቦታው ረግተው የሚታዩት ወንዞች ዛሬ ከተፈጥሯዊ ኡደታቸው ጋር መወዳጀት የጀመሩ ይመስላል።

ይህም ሆኖ ከልማት ትሩፋቶች በተጓዳኝ በበርካቶች የተነሱና እየተነሱ ያሉ ስጋቶችም አሉ። እንደ ሀገር ለጋራ መጠቀሚያዎቻችን የምንሰጠው ትኩረትና እንክብካቤ ጥሩ ታሪክ ያለው አይደለም። የሕዝብ መገልገያ መንገዶችን እንደ ቀልድ እየዘጉ ንግድ ማካሄድ የተለመደ ተግባራችን ነው፡፡ ከግለሰብ እስከ ተቋማት የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችን ሥርዓት አልባ በመሆኑ ብዙ ሲባልበት ቆይቷል። እግረኛም ሆነ አሽከርካሪ ለመንገድ ሥርዓትና ደንቦች ተገዢ ሲሆን የሚታዩት የሕግ አስከባሪ ሲመለከቱ ብቻ ነው። ይህ መልካም ያልሆነ ልምምዳችን ዘመናትን ያሳለፍነበት ቢሆንም አሁን ላይ በቃ ካልተባለ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ላይ አደጋ መጋረጡ አይቀሬ ነው።

ለመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ ደረጃ ትኩረትና ቅድሚያ ሰጥቶ የሰራቸው የልማት ሥራዎች እንዳይባክኑ ብሎም እንዲህ እንዳማረባቸው ለትውልድ እንዲተላለፉ ምን ምን ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ? ስንል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ደንብ ማስከበር ባልሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራን አነጋግረን የሚከተለውን ምላሽ አካፍለውናል።

አዲስ ዘመን፤- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በ2014 ዓ.ም እንደ አዲስ ከተደራጀ በኋላ ምን አዳዲስ ነገሮችን ይዞ መጥቷል ?

ሻለቃ ዘሪሁን፤– ባለሥልጣኑ እንደገና ከተደራጀ በኋላ ያመጣቸውን ለውጦች ለማየት አጀማመሩንና የነበረበትን ደረጃ በጥቂቱ መገንዘብ ያስፈልጋል። ተቋሙ በ2003 ዓ.ም ሲመሰረት በሥራ አስኪያጅ ስር ሆኖ ነበር። በኋላ ግን የተቋሙ መኖር ብቻ ሳይሆን የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የበለጠ መጠናከር እንዳለበት እየታመነ ሲመጣ በ2005 ዓ.ም በዘርፍ ደረጃ ተቋቁሟል። እንዲህ እንዲህ እያለ ከቆየ በኋላም በ2014 ዓ.ም ባለሥልጣን ሆኖ ራሱን ችሎ ለመቋቋም በቅቷል። በአሁኑ ወቅትም አስራ አንድ ዳይሬክተሮችን በመያዝ ከመቶ በላይ ስታፍ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ አደረጃጀቱ ክፍለ ከተማና በወረዳ የሚደርስ የሲቪል ሠራተኛ፤ ሚሊቴሪ እና ፓራ ሚሊተሪ ያካተተ ነው። በእነዚህ መዋቅሮቹም ግንዛቤ በመፍጠር፤ ቁጥጥር የማድረግና ከዚህም አለፍ ሲል እርምጃ ሊወስዱ የሚችሉ ስድስት ሺ በላይ ኦፊሰሮች አሉት። እነዚህም በጥቅሉ የደንብ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የማድረግ፤ ተላልፈው የተገኙ አካላት ሲገኙም ተከታትሎ ተገቢውን እርምጃ የመውሰድ ሥራ የሚያከናውኑ ናቸው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቋቋም ሥራውን የጀመረው በውስን ጉዳዮች ላይ ነበር። በተለይም በከተማዋ የጽዳት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ትኩረቱ በስፋት ይስተዋል የነበረውን ያለ አግባብ የቆሻሻ ማስወገድ ተግባር በመቆጣጣር የከተማዋን ንጽህና የማስጠበቅ ተግባር ላይ ነበር። እየተስፋፋ የመጣውንና ለሌሎች ችግሮችም ምክንያት የሆነውን የጎዳና ላይ ንግድ ለማስቀረት፤ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ይከናወን የነበረውን የመሬት ወረራና ሕገ ወጥ ግንባታ ለማስቀረት ነበር።

በከተማዋ ይፈጸሙ የነበሩት የደንብ ጥሰቶች እነዚህ ብቻ አልነበሩም። በስፋት ከተለመዱት መካከልም ከመንገድ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የእግረኛውንና የትራፊክ እንቅስቃሴውን ከሚያስተጓጉሉት መካከል ግንባታዎች ሲከናወኑ ለግንባታ የሚውሉ ቁሳቁሶችና ተረፈ ምርቶቻቸውን በመንገድ ላይ በመድፋት፤ የከተማዋን ገጽታ በሚያጠለሽ መልኩ ካለምንም ፈቃድ በግድግዳዎች በኤሌክትሪክና የስልክ ፖሎች ላይ ማስታወቂያዎች መለጠፍ፤ በአዋኪ ተግባራት ማለትም በመጠጥ ቤቶች፤ ሺሻና ጫት ቤቶች መስፋፋት የማህበረሰቡን ጤናና ሰላም የሚረብሹ እንቅስቃሴዎች መስፋፋት፤ በተለይም እነዚህ ተግባራት በትምህርት ቤቶች አካባቢ ሲሆኑ የመማርና ማስተማር እንቅስቃሴውን የሚያደናቅፉ ከመሆናቸው ባሻገር ለትውልድ መጥፋት ቀዳሚ ምክንያት እየሆኑ ነበር።

በሌላ በኩል አዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካም መዲና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆነች ሰፊ ከተማ ናት። ከተማዋ በየወቅቱ እየሰፋች የመጣች በመሆኑ በርካታ ነዋሪዎች የያዘችና የምስራቅ አፍሪካ የንግድ ኮሪዶርም ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች። ከተማዋ ከነዋሪዋ በተጨማሪ ከሌሎች የሀገሪቱ ክልሎችና የውጪ ሀገራት የሚገቡና የሚወጡ በርካታ እንግዶችን በየቀኑ የምታስተናግድም ናት።

ይህንንም መሰረት በማድረግ በከተማዋ የሚስተዋሉ የደንብ መተላለፎችን ጊዜ ሳይሰጡ መቆጣጠር የሚያስፈልግበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ኃላፊነትም በዚያው ልክ እየሰፋና እየጨመረ ሊመጣ በቅቷል።

ይህንንም መሰረት በማድረግ ነበር ካቢኔው አምኖበት የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን እነዚህን ጥሰቶች እንዲቆጣጠርና እንዲከላከል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም እርምጃ እንዲወስድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ተደራጅቶ ሥራውን እንዲጀምር ተደርጓል። በመሆኑም ባለሥልጣኑ ሊኖረው የሚገባው አቅም እነዚህን የተዘረዘሩትን ችግሮችና ሌሎች ወቅት ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ ጥሰቶችን ለመከላከል የሚያስችል እንዲሆን ሲሰራ ቆይቷል።

አዲስ ዘመን፤- የደንብ ጥሰቶች በየወቅቱ መልካቸውን እንደሚለዋወጡ ይታወቃል። ባለሥልጣኑ ይህንን ለመቆጣጠርና ከጊዜ ጋር ለመራመድ የሚያስችል አደረጃጀት አለው ለማለት ይቻላል?

ሻለቃ ዘሪሁን፤- የደንብ ማስከበር ሥራ ከተጀመረ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ተከናውነው ብዙ ውጤቶችም የተገኙበት ነው። በዚህም እንደ ተቋም በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የአደረጃጃት ለውጦች ቢኖሩም አንጻራዊ በሆነ መልኩ እንደ አጠቃላይ ጥሩ ልምድ የነበረው ተቋም ነው። በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ስር ያሉ አስፈጻሚ አካላት በየወቅቱ እየተሻሻለ ያለና የማስፈጸም አቅሙም እያደገ የመጣ ተቋሙ ነው።

ከተደራሽነት ባሻገርም በከተማዋ የሚሰራቸው ሥራዎች በየወቅቱ እየጨመሩ መጥተዋል። በመሆኑም የሲቪል ሠራተኞቹንም ሆነ ሌሎቹን ለተልእኮ ብቁ ለማድረግ በርካታ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች እየተሰጡ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በየጊዜው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የሚሰጡ ስልጠናዎች አሉ።

ከእነዚህም ውስጥ የፓራ ሚሊቴሪ ባለሙያዎች በታወቁ የስልጠና ማዕከላት እየገቡ እንዲሰለጥኑ ይደረጋል። በዚህ ረገድ ባለፉት ተከታተይ ዓመታት ከአዲስ አበባ ፖሊሲ ኮሌጅ ጋር በመቀናጀት አባላቱ በየዓመቱ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል። በተጨማሪ ከከተማ አስተዳደር ጀምሮ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ የሚሰጡ ስልጠናዎችም አሉ። ይህም ሰልጣኞች ሕዝባቸውን በሥነ ምግባር በታነጸ አካሄድ በታማኝነት እንዲያገለግሉ ብቁ የሚያደርጋቸው ይሆናል።

አዲስ ዘመን ፤- የደንብ ማስከበር ሥራ ሲነሳ በደንብ አስከባሪዎች በኩል የሥነ ምግባርና ሙስና ጉዳዮች በተደጋጋሚ እንደ ችግር ሲነሱ ይሰማል። በዚህ ላይ ምን ምላሽ አለዎት ?

ሻለቃ ዘሪሁን፤ ባለሥልጣኑ የሚሰራቸው ሥራዎች በሙሉ መነሻቸውም መድረሻቸውም ሕግ እንዲከበር በማድረግ የማህበረሰብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። በመሆኑም በማንኛውም መልኩ በተቋሙ ሠራተኞች በኩል የሚፈጸሙ የሥነ ምግባር ጥሰቶችም ሆኑ ሙስና ተገቢው እርምጃ የሚወሰድባቸው ይሆናል።

በእኛ በኩል የሥነ ምግባር ግድፈት እንዳይከሰት ሠራተኞቻችን በየወቅቱ እያበቃን አያሰለጠንን እንገኛለን። ይህም በመሆኑ እስካሁን እንደ ተቋም የጎላ ስህተት አልተገኘም። ነገር ግን እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ የሥነ ምግባር ጥሰት እንዲከሰትም ሆነ ለሙስና በር የሚከፈተው በቅድሚያ ሕግ ደንብና መመሪያ ያለ ማክበር አካሄድ ሲኖር ነው። እያንዳንዱ ዜጋ በሕግና በተፈቀደለት አግባብ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ሕጋዊ ነህ ብሎ ሊያመሰግነው እንጂ ሊጠይቀው የሚችል አካል የለም። ይህን አልፎ የተፈጠሩ ችግሮች እንኳን ቢኖሩ ብዙም ሳይለፉ በየደረጃው ላሉ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ ችግሩን መፍታት አጥፊውንም ተጠያቂ ማድረግ ይችላሉ።

ይህም ሆኖ ባለሥልጣኑ የተከሰቱ የሥነ ምግባር ጥሰቶችንም ሆነ ሙስና ለመከላከል ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ካሉት አስራ አንድ ዳይሬክቶሬቶች አንዱ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ነው። ይህ ዳይሬክቶሬት በከተማ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ ክፍሎችም አሉት። እነዚህ ክፍሎች ከማህበረሰቡ በጥቆማ መልክና በቅሬታ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ከማስተናገድ ባለፈ የየራሳቸውን መንገድ በመከተልም ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ ይገኛሉ።

አዲስ ዘመን፤- ለደንብ ማስከበር እንቅስቃሴ የማህበረሰቡ ተሳትፎና ትብብር እንዲሁም የባለ ድርሻ አካላት ሚና ምን ይመስላል?

ሻለቃ ዘሪሁን፤– ከማህበረሰቡ ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለን። ግንኙነታችንም የሁለትዮሽ ሲሆን ማህበረሰቡ እኛ እንዲተባበረን የምንጠይቀውን ብቻ ሳይሆን መሰራት አለበት የሚለው እና ሌሎች ጥቆማዎችንም በየወቅቱ እያደረሰን ይገኛል። በተመሳሳይ በኛም በኩል ከከተማ ጀምሮ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ በየሶስትና ስድስት ወሩ ያከናወናቸውን ተግባራት ለማህበረሰቡ የምናስገመግምበት፤ አፈጻጸማችንን የምናሳይበት መድረክ አለ።

ብዙ ጊዜ የሚደርሰን ምላሽ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ባይኖር ኖሮ አዲስ አበባ አሁን ባለችበት የሥርዓት ደረጃ እንደማትገኝ ነበር። እኛም በመስክ ምልከታችን ወቅት በሥራችን ምን ያህል የደንብና መመሪያ የሕግም ስህተቶችን እየተቆጣጠርን እንደሆነ ስለምናይ ነገሩ እውነት መሆኑን እንገነዘባለን።

በሌላ በኩል የደንብ ማስከበር ሥራ በባህሪው የማይነካው ተቋም የለም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ከ23 ተቋማት ጋር በቅንጅት ስንሰራ የቆየን ሲሆን በቅርቡ ወደ ሰላሳ አንድ አድጓል። ከእነዚህም መካከል ንግድ ቢሮ፤ ቄራዎች ድርጅት፤ መሬት አስተዳደር፤ ትምህርት ቢሮ፤ ሰላምና ጸጥታ፤ ፖሊስ፤ ከተማ ግብርና፤ ሚዲያ ባህልና ቱሪዝም … ይጠቀሳሉ። ባለሥልጣኑ እነዚህን አካላት ለአንድ ወቅት የትብብር ሥራ ብቻ ሳይሆን የእለት ተእለት እንቅስቃሴው አካል አድርጎ የሚያያቸው ናቸው። በመሆኑም በየዓመቱ እቅድ ሲታቀድ ከእነዚህ ተቋማት ጋር የሚኖረው ሁኔታ ከግምት የሚገባና የየተቋማቱም ሃሳብ የሚታከልበት ይሆናል።

አዲስ ዘመን፤- የኮሪዶር ልማቱን ተከትሎ የወጡ ሕጎች መመሪያዎችና ደንቦችን በተመለከተ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ምን ያህል የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰርቷል ?

ሻለቃ ዘሪሁን፤– ተደጋግሞ እንደተነገረው በከተማዋ ኮሪዶር ግንባታ እየተከናወነ ያለው አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ እንዲሁም ለእንግዶች ተስማሚ ለማድረግና ከሌሎች ከተሞችም ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ነው። በኮሪዶር ልማቱ የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ብዙ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት የፈሰሰባቸው የመላው ኢትዮጵያዊ ሀብትና ንብረት ናቸው። ግንባታዎቹም ሆኑ የአረንጓዴ ልማቶች ከወጣባቸው ገንዘብ በላይ ብዙዎች ሀያ አራት ሰዓት እንቅልፍ አጥተው የለፉበት ነው። ከመንገድ ሥራ ጀምሮ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችና የመጸዳጃ ቤቶች ግንባታዎች በሚያስድምም ሁኔታ በመከናወን ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ በመጠቀም ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅም ይሆናል።

ሕዝቡ ልማቱን እንደራሱ እየጠበቀ እና እየተንከባከበ ያለ ቢሆንም ባለሥልጣኑ እነዚህን ውድ ሀብቶች ከጥፋት የመጠበቅ ሕጋዊ ኃላፊነትና አደራ አለበት። የሕዝቡ ልፋትና ትብብርም ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው በሕግ አግባብ ኃላፊነት የተሰጠው አካል ተገቢውን ቁጥጥርና እርምጃ ሲወስድ ነው። ይህም ሆኖ እርምጃ የመውሰድ ሥራ እየተሰራ ያለው ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በስፋት ከተከናወነ በኋላ ነው። እንደ ተቋም ባለሥልጣኑ የደንብ ማስከበር ሥራዎን የጀመረው ግንዛቤ በመፍጠር ነው። በአሁኑ ወቅትም ከዘጠና በመቶ በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ያለው ግንዛቤ በመፍጠሩ ላይ ነው።

በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፤ በትምህርት ቤቶች፤ በትራንስፖርት መሳፈሪያ አካባቢዎች ዛሬም ድረስ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። የእኛን ትምህርታዊ ማስታወቂያዎች በተለያዩ የሚዲያ ዓይነቶችም በየቀኑ ለሕዝቡ ተደራሽ እያደረግን እንገኛለን። በነገራችን ላይ እኛም ያወጣነው ደንብ የሚተገበረው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ቢሆንም የምንሰጣቸው የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ግን በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ እየሆኑ ነው። የከተማ ልማት ሥራ ደግሞ የኮሪዶር ልማትን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱም አካባቢዎች እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም የእኛ ሥራ ለሌሎቹም መሠረት የሚያስቀምጥና ልምድ የሚወሰድበት ነው ማለት ይቻላል። የተሻሻሉ ደንቦችና መመሪያዎችንም ማህበራዊ የትስስር ገጾች ሳይቀሩ እንዲያጋሩት አድርገናል። ይህ ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን፤- ደንብ ተላልፈው ሲገኙ የሚወሰን የቅጣት ክፍያን በተመለከተ የተጋነነና ወጥነት ያለው ሥራ እየተሰራ አይደለም ይባላል፤ በዚህ ረገድ ምን ምላሽ አለዎት።

ሻለቃ ዘሪሁን፤- ከሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ ያለው ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አደረጃጀት፣ አሰራር እና የፓራሚሊተሪ ሠራተኞች አስተዳደር ለመወሰን የወጣ ደንብ ቁጥር 150/2015 (ማሻሻያ) ደንብ ቁጥር 167/2016» ለኮሪደር ልማቱ ብቻ የተዘጋጀ አይደለም። የወጣው ደንብ በመላው የከተማዋ አካባቢዎች የሚተገበር ነው። ይህ ሕግ ለሁሉም የደንብ አስከባሪ ሠራተኞችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንዲዳረስ ተደርጓል። ለምሳሌ አንድ የሲጋራ ቁራጭም ሆነ ሌሎች ወረቀቶችን አላግባብ የጣለ ግለሰብ ሁለት ሺ ብር እንደሚቀጣ በደንቡ ተመላክቷል። ይህ በመላው ከተማዋ ኮሪደር ልማቱ በተገነባባቸው ቦታዎች ጨምሮ የሚተገበር ነው።

የኮሪዶር ልማት ሲባልም አሁን የተሰራው ብቻ አይደለም በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉትንና በቀጣይም በመላው ከተማዋ የሚተገበሩትን የሚያካትትም ነው። በመሆኑም የወጡት ደንብና መመሪያዎችም ትግበራ በመላው ከተማዋ የኮሪዶር ልማቱ በተዳረሰባቸውና በሌሎች ቦታዎችም በሙሉ የሚተገበር ይሆናል። ይህም ሆኖ ሁሉም ሰው ሊገነዘበው የሚገባው የደንቡ መሠረታዊ አላማ ሕዝብን በማሳወቅና በማስተማር ጥፋት እንዳይፈጸም ማድረግ እንጂ ሲያጠፉ መቅጣት አይደለም።

ይህም በመሆኑ እነዚህ ሕጎች ከመውጣታቸው በፊት ከሕዝብ ጋር ውይይት ተደርጎባቸው ነበር። በመሆኑም ለአንድ ቦታ ብቻ ተብሎ የተዘጋጀ ባለመሆኑ የቅጣት ወጥነት አለመኖር ሊከሰት አይቸልም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የተሻሻለው ደንብ ቅሬታ ያለበት ማንኛውም አካል አቤቱታውን እንዴት ሊያቀርብና ሊስተናገድ እንደሚችል በግልጽ አስቀምጧል። በመሆኑም ከሕግ አግባብ ውጪ ተስተናግደናል የሚሉ አካላት በዚያ መሠረት ወይንም በቀጥታ እኛ ቢሮና ለዚሁ ተግባር በክፍለ ከተማና ወረዳ ለተመደቡ አካላት ማሳወቅ ይችላሉ።

ቅጣቱ ከፍተኛ ነው በሚል የተነሳው ሀሳብ ግን ትክክል አይደለም። ቅጣቱ የተጋነነ አይደለም፡፡ እንዲያውም ልማቱ የወጣበትን ወጪ ሳይሆን የሕዝብን አቅምና ማስተማርን አላማ ያደረገ ነው። ልማቱ በጣም ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ግንባታዎችና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የተከናወኑበት ነው። በመንግሥት በጀት በመሆኑ እንጂ በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዱ ነገር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው። በተጨማሪ የሚተላለፉ ቅጣቶች አስተማሪ በመሆን ሌሎችን ወደ ጥፋት ከመግባት የሚታደጉ መሆንም ይጠበቅባቸዋል።

አዲስ ዘመን፤- የተጀመሩ የደንብ ማስከበር ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከማህበረሰቡ ምን ይጠበቃል ?

ሻለቃ ዘሪሁን፤- በቅድሚያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገርን መልካም ገጽታ ሊገነባ በሚችል መልኩ የተገነቡትን የኮሪዶር ልማቶችንም ሆኑ ሌሎች የሕዝብ መገልገያ ንብረቶችን መንከባከብ አጠቃላይ የማህበረሰቡ ኃላፊነት ነው። ከተሰራው ልማት ሕዝብ የማይጠቀምበት ምንም ነገር የለም። መሬት ቢጠበቅ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሕዝብን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው። የአካባቢ ጽዳት ሥራዎችም ሲከናወኑ የሕዝብን ጤንነት የመጠበቅ ሥራ እየተሰራ ነው። ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ሲደረግም የማህበረሰቡ በሰላም ወጥቶ የመግባት፤ የልጆችና የሴቶች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተረጋገጠ ማለት ነው።

በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ የሚከናወኑት ሥራዎች በሙሉ የእሱን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን በመረዳት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ሊሰራ ይገባል። ከሕዝቡ የሚጠበቀው ጥፋትና የሕግ ጥሰቶችን ሲመለከት ለሚመለከተው የሕግ አስከባሪ አካል እንዲያሳውቅ ብቻ አይደለም። ሁሉም ሰው ቤተሰቡንና በአካባቢው ያለውን ሌላ አካል ጥፋት እንዲጠበቅ የማድረግ እና መንግሥት የሚሰራቸውን መሠረተ ልማቶች በአግባቡ እንዲጠቀም ቢያስተምርና ቢመክር ውጤታማ መሆን እንችላለን።

የሥነ ምግባር ጉዳይ በአንድ ወቅት ተሰርቶ የሚቆም እና የሚያበቃ አይደለም። ዛሬ በልምድ ትክክል መስሎን የምናደርጋቸውን የሕግ ጥሰቶች ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ጊዜ ይፈልጋል። ነገር ግን ከተማመርን በአጭር ጊዜ ልናሳካው የምንችለው በጣም ቀላል ነገር ነው። መንግሥት እነዚህን ውብ የሆኑ ልማቶች የሚገነባውና እየገነባ ያለው አሁን ያለውን ትውልድ በማሰብ ብቻ አይደለም። ጥቅሙ ለሚመጣውም ትውልድ ነው። በተመሳሳይ የሥነ ምግባርና ሥርዓት የመያዝ ጉዳይን በተመለከተ የሚሰሩት ሥራዎች ዛሬ ሕግ በማስከበር ሥራ ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆኑ ነገ ራሱ አውቆ ለሕግ ተገዢ የሆነ ሀገሩንና ሕዝቡን የሚወድ ትውልድ ለመፍጠርም ነው። እነዚህ ሥራዎች ደግሞ በአንድ አካል በአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ የሚሳኩ አይደሉም።

ባለፉት ጥቂት ጊዜያት በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን በኮሪዶር ልማቱ በተሰሩ መናፈሻዎች ሲያዝናኑ ጥፋት እንዳያጠፉና ስህተት እንዳይሰሩ ሲቆጣጠሩ እያየን ነው። እነዚህ ልጆች ወደፊት ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ዛሬ ግንዛቤውና እውቀቱን ስለያዙት የሚመራቸውም ሆነ የሚጠብቃቸው አካል አይፈልጉም። ደንብ መመሪያና ሕጎችን ማክበር ለሥርዓት ተገዢ መሆንን ባሕላችን ማድረግ ይጠበቅብናል። ለዚያ ደግሞ መሠረቱ የሚጣለው ዛሬ ላይ ነው። ኃላፊነቱ የተሰጠው ለደንብ ማስከበር ባለሥልጣኑ ቢሆንም ከዚያ በላይ እየተሳተፈ ያለው ማህበረሰቡ ነው። ይህ የሚያስመሰግን ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

አዲስ ዘመን፤- እናመሰግናለን።

ሻለቃ ዘሪሁን፤- እኔም አመሰግናለሁ።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You