የመሠረተ ልማት ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ – የኮሪደር ልማት

የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ከተማዋ ሰፋፊ የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶችን፣ ውብ አረንጓዴ ሥፍራዎችን፣ ያልነበረ ግን እንዲኖር የተደረገ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች / ብስክሌት/ ማሽከርከሪያ መንገድ እንዲኖሯት አድርጓል። ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መንገድ የማዘጋጀቱ ሥራም በእዚሁ ልማት በሚገባ ተሠርቶበታል። በየመንገዶቹና በየአረንጓዴ ሥፍራዎቹ ማረፊያ መቀመጫዎችን ፣ መጸዳጃ ቤቶችን፣ የውሃ አካላትን /ፋውንቴኖችን፣ የቡና መጠጫ ቦታዎችን . ወዘተ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲኖሯት አስችሏል።

የልማቱ ቱሩፋት ዘርፈ ብዙ ነው፤ በዚህ ጽሁፍ ሁሉንም ዘርዝሮ መጨረስ ባይቻልም፣ አንኳር አንኳሩን አንስቶ ማሳየት ግን ይገባል። ከቱሩፋቶቹ አንዱ በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የተካሄደው ሰፊ ሥራ ነው። በከተማዋ መሠረተ ልማቶችን ተቀናጅቶ ባለመሥራት ሳቢያ ፣ በውሃ ፣ በቴሌኮም፣ በመብራት ፣ ወዘተ መሠረተ ልማቶች ላይ ይደርስ የነበረው ጉዳት ከፍተኛ ስለመሆኑ ይታወቃል፣ በዚህ ሳቢያ ከተማዋ የጣችው ሀብት፣ ዜጎች ማግኘት ሲገባቸው ያጡት አገልግሎት ሲታሰብ ደግሞ የልማቱ ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው።

አዲስ አበባ በመሠረተ ልማት በተቀናጀ አግባብ አለመገንባት የተነሳ አዳዲስ መንገዶች በተመረቁ ማግስት ሲቆፈሩባት ኖረዋል፤ አዲስ የተዘረጉ የቴሌኮም፣ የውሃ ፣ ወዘተ መሠረተ ልማቶች ሲሠበሩባት፣ ሀብት ለብክነት ሲዳረግባት ኖሯል።

ይህን ጉዳት ሲያስከትል የኖረ ችግር ለመፍታት መንግሥት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በቅንጅት እንዲካሄዱ የሚያስችል ተቋም እስከ ማቋቋም ደርሶ እንደነበርም ይታወቃል። ይሁንና እሱም እያለ ጥፋቱ ብዙ ነበር። ይህን ችግር የሚፈታ ሥራ በአንዳንድ ዋና ዋና መንገዶች ግንባታ ላይ ቢደረግም፣ አዲስ መንገድ ከመቆፈር፣ የውሃ የቴሌኮም መስመር ከመቆረጥ፣ ወዘተ ብዙም አልተረፈም።

አሁን በኮሪደር ልማቱ ልዩ ልዩ መሠረተ ልማቶችን አቀናጅቶ ለመዘርጋት እየተከናወነ ያለው ተግባር የተጠቀሱትን ችግሮች ከመፍታት፣ ሊባክን ይችል የነበረውን ሀብት ከማትረፍ አኳያ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። መንገዶቹ ሲገነቡ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም፣ የመጸዳጃ ቤት መሠረተ ልማቶች መሬት ውስጥ እንዲቀበሩ ተደርጓል።

በሀገራችን አዲስ አበባን ጨምሮ በ31 ከተሞች ያህል ተግባራዊ እየሆነ ያለው ይህ የኮሪደር ልማት አንዱን የመሠረተ ልማት ለመገንባት በሚካሄድ ሥራ ሌላውን የማፍረስ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ ይረዳል። ግንባታዎች በአንድ ጊዜ የሚካሄዱ በመሆናቸው የከተሞች የመንገድ መሠረተ ልማቶች በተደጋጋሚ የመቆፈር እና የመፍረስ እጣፈንታቸው ቢያንስ እንዲጠብ ያደርጋል። አንዱ መሠረተ ልማት ዘርግቶ ሲጨርስ ሌላው መሠረተ ልማት ለመገንባት ዶማና አካፋ ይዞ የሚመጣበትን ሁኔታ ያስቀራል። በተለይ በኮሪደር ልማቱ በለሙ አካባቢዎች።

አንድ መሠረተ ልማት ለመገንባት ሲባል በሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ በሚደርስ ጉዳት ተገልጋዩ ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ብዙና በቀላሉ ሊታይ የማይገባውም ነው። ለመሠረተ ልማት ግንባታ በሚል ተቆፍሮ ባልተደፈነ ጉድጓድ እግራቸው ገብቶ የተሰበሩ ወይም ሌሎች የጤና ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉ ይታወቃል። መንገዱ መልሶ ባለመገንባቱ ሳቢያ ቦታው ውሃ ሊያቁር፣ ጭቃ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታም እንዲሁ ሰፊ በመሆኑ በእግረኞች እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ችግር ይፈጥራል።

በእግረኛ መንገድ ላይ የተፈጠረውን ጉድጓድ፣ ጭቃና ውሃ ሽሽት እግረኞች ወደ መኪና መንገድ ገብተው ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ በእግረኞች ላይ የመኪና አደጋ ይደርሳል።

በሌላ በኩል ደግሞ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴም ይስተጓጎላል። አደጋን ለመከላከል በሚል በትራፊክ ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያርፋል፤ ይህ ሲሆን ባለጉዳዮች ከጉዳያቸው ሊያረፍዱ፣ መኪናዎች ሊጋጩ የሚችሉበት ሁኔታ ብዙ ነው።

የመሠረተ ልማቱ ጉዳቱ በተሽከርካሪ መንገድ ላይም ይስተዋላል። በዚህ ሳቢያም መኪኖች እቃ ሊሰብሩ፣ ሊጋጩ፣ ጥሩ መንገድ ፍለጋ በሚል እግረኛ መንገድ ላይ ወጥተው ሊሄዱ ሁሉ ስለሚችሉ ችግሩ በጣም ሰፊ ነው።

የከተማ ገጽታ ማበላሸት ድግሞ ሌላው ችግር ነው። በመሠረተ ልማት ላይ በሚደርስ ጉዳት ሳቢያ እግረኞች መንቀሳቀስ የማይችሉባት፣ ተሽከርካሪዎች የተሳለጠ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚቸገሩባት የአዲስ አበባ ከተማ ስትታሰብ ደግሞ ገጽታዋ በእጅጉ ይበላሻል።

የተጠቀሱትን ችግሮች በኮሪደር ልማቱ አማካይነት ለመፍታት እየተሠራ ነው። በከተማዋ ተንሰራፍቶ ከነበረው የመሠረተ ልማት ችግር አኳያ ሲታይ በልማቱ ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል ማለት ያሰኛል፣ ልማቱ ሰፋፊ የእግረኛ፣ የተሽከርካሪ፣ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች መንገድ ወዘተ. በዋና ዋና መንገዶች ላይ በስፋትና በፍጥነት እየተገነቡ መሆናቸው ችግሩን በወሳኝ መልኩ መቀነስ ይቻላል።

የመሠረተ ልማት ግንባታው በትራፊክ እንቅስቃሴ በእግረኞች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት የሚያስቀር ብቻ አይደለም። ከተማዋ በጎብኚዎች እንድትወደድ፣ ነዋሪዎቿ በእረፍት ጊዜያቸው ወጥተው የሚዝናኑባቸው ፣ አላፊ አግዳሚውም የተጓዘ ሳይመስለው ወደፈለገው መድረስ እንዲችል የሚያደርጉ ናቸው።

በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ጭምር የቴሌኮምና የመብራት ገመዶች በተተከሉላባቸው ምሰሶዎች ላይ ገመዶች ተያይዘው የሚታዩበትን ሁኔታም እንዲቀር አስችሏል። መሠረተ ልማቶቹ በኮሪደር ልማት ሥራው በመሬት ውስጥ እንዲቀበሩ ተደርጓል።

መሠረተ ልማቶቹ በዚህ መልክ ከእይታ ውጪ መደረጋቸውና ሥርዓት መያዛቸው ለመንገደኞችና ለተሽከርካሪዎች ብቻ አይደለም ምቹ ሁኔታ የሚፈጠረው። ከተማዋ ለቱሪስቶች ምቹ እንድትሆንና ገጽታዋም እንዲገነባ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ጎዳናዎች አይወጣም፣ የተፈነቃቀለ ድንጋይና ኮረት፣ ጭቃና የታቆረ ውሃ የመንገደኞች ፈተና አይሆኑም። አረንጓዴ ሥፍራዎች፣ አረፍ ማለት የሚቻልባቸው መቀመጫዎች፣ ፋውንቴኖች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶችና ካፍቴሪያዎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች የተካተቱቡት በመሆኑ አካባቢዎቹ በጎብኚዎች ተመራጭ ይሆናሉ።

የኮሪደር ልማቱ በመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳትን የሚያስቀር ብቻ አይደለም፤ ከመሬት በላይ የተዘረጉ የኢትዮቴሌኮም፣ የመብራትና የመሳሰሉት ገመዶችም መሬት ውስጥ እንዲቀበሩ አድርጓል። ገመዶቹ ከቤቶች ጣሪያ ጋር የተያያዙ በመሆኑ ብዙ ጊዜ በገመዶቹ ምክንያት የኤሌክትሪክ አደጋ ሲደርስ ቆይቷል። እዚህም እዚያም የሚተከሉት ምሰሶዎች ብዛትም የመሠረተ ልማቱ ችግር ያለበት መሆኑ ሌሎች ማሳያዎች ናቸው።

በኤሌክትሪክ እና በቴሌኮም ገመዶች ብዙም ሳይርቁ የተተከሉ ዛፎች በተለይ ከመብራት ጋር በተያያዘ አደጋ ያስከትላሉ በሚል የታለመላቸውን ግብ ከማሳካት እንዲቀሩ ተደርገዋል። ዛፎች እንደልባቸው የሚሆኑበትን ሁኔታ ይፈጥራል። በተለይ በኮሪደር ልማቱ ለአረንጓዴ ሥፍራ ልማት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠ እንደመሆኑ መሠረተ ልማቶቹ በመሬት ውስጥ መዘርጋታቸው ዛፎችን በሚገባ ለማልማት ምቹ ሁኔታ ነው።

የኮሪደር ልማቱ ለመንገድ የሚያስፈልጉ መብራቶችን በየት በኩል አልፈው አዚህ ተገኙ በሚያሰኝ መልኩ ገመድ ሳይታይ መንገዶች መብራት በመብራት እንዲሆኑ አድርጓል። መብራት ብርሃን ብቻ ሳይሆን መንገዶች ህንጻዎች ልዩ ልዩ ህብረ ቀለሞች ያላቸውና ከተማዋን ይበልጥ ማስዋብ ያስቻሉ እንዲሆኑ አድርጓል።

የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ልዩ ልዩ መሠረተ ልማቶች ዘመኑን በሚመጥን መልኩ እንዲዘረጉና ከተማዋን በሚገባ እንዲያገለግሉና እንዲያስውቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስቻለ ነው። ይህን ልማት ወደ ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎችም ለማስፋት ሥራዎች ተጀምረዋል። ይህ ሥራ በእጅጉ ይበል የሚያሰኝና ድጋፍ ሊቸረውም የሚገባ ነው።

የከተማዋ የተለያዩ ተቋማት የኮሪደር ልማቱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ነዋሪዎች ብዙ ድጋፍ አድርገዋል። ልማቱ በተስፋፋባቸው አካባቢዎችም ይሄው መደገም ይኖርበታል። መንግሥት የከተማዋን መሠረታዊ ችግር ሆኖ የቆየውን የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን የማሟላትና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ተግባር አሁን ላይ መደገፍ ማለት በልማቱ ውስጥ ዐሻራን ማኖር ነው። በልማቱ ዋንኛው ተጠቃሚ ሕዝቡ እንደ መሆኑ ሕዝቡ ድጋፉን አሁንም አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

በተለይ ልማቱ በሚያተኩርባቸው አካባቢዎች ያለው ነዋሪ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑ በቀደሙት ልማቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች በሚገባ ታይቷል። ይህ አጋርነት በተጠናከረ መልኩ መቀጠል ይኖርበታል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You