ስንቅነሽ አጣለ (ዶ/ር) ይባላሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሥነጽሑፍ እና ቋንቋ የፎክሎር ትምህርት ክፍል ባልደረባ ናቸው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወደ ቻይና ልኳቸው በቤጂንግ ፎሪን ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። የዛሬዋ የሕይወት ገፅ እንግዳችን ለብዙ ሴቶች ምሳሌ መሆን ይችላሉ።
ውልደት እና ትምህርት
ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን የተወለዱት ስንቅነሽ አጣለ (ዶ/ር)፤ ለወላጆቻቸው ዘጠነኛ ልጅ ናቸው። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እዛው ደብረብርሃን የአንደኛም ሆነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ኃይለማርያም ማሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። እናታቸው የተሞናሞኑ የመሬት ከበርቴ ነበሩ። ልክ ስንቅነሽ (ዶ/ር) ሰባተኛ ክፍል ሲደርሱ፤ ደርግ መጥቶ የእናታቸውን ሃብት ወረሰባቸው። ቤተሰቡ በቅንጦት የኖረ በመሆኑ ለተወሰነ ጊዜ ግራ ተጋባ። ስንቅነሽን (ዶ/ር) የሚያስተምሩበት ሁኔታም ጠባብ ሆነ።
በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገቡ ለመላው ቤተሰቡ ሕይወት ፈታኝ ሆነችባቸው። እናት ለውጡን ተከትሎ አካባቢ መቀየር ፈለጉ። አካባቢያቸውን ሲቀይሩ ለስንቅነሽ (ዶ/ር) የሚሆን ትምህርት ቤት በቅርብ ርቀት ማግኘት አልተቻለም። ከሰባተኛ ክፍል በላይ የሚያስተምር ትምህርት ቤት ባለመኖሩ፤ ትምህርትን ለመቀጠል ከእናት መነጠል የግድ ሆነ። ስንቅነሽ (ዶ/ር) ራሳቸውን ማስተማር ግድ ሆነባቸው።
እናት ከተንደላቀቀ ኑሮ ወጥተው ወደ ሥራ ለመሠማራት ጊዜ ፈጀባቸው። ስንቅነሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በተለይ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆነው ቤታቸው ውስጥ ሹራብ እየሠሩ ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ሦስት ቱባ ክር በዘጠኝ ብር ገዝተው፤ የጉልበታቸውን ዘጠኝ ብር ጨምረው ለአንድ ትልቅ ሰው የሚሆን ሹራብ ሠርተው በየሳምንቱ እየሸጡ ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ከመቸገር ይልቅ በትምህርት ቤቱ ታዋቂ ዘናጭ ሆነው፤ አስራ ሁለተኛ ክፍል ደረሱ።
የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ላይ ሳይቀር እየሠሩ መሸጣቸውን ቀጠሉ። በትምህርታቸው ግን እንዳሰቡት ውጤት ማምጣት አልቻሉም። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ፤ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ውጤታቸው ከዲፕሎማ ማስገቢያ አለማለፉ አስከፋቸው። ነገር ግን ለመማር እና ለመቀጠል ወስነው የተመደቡበት ባሕርዳር መምህራን ኮሌጅ ገቡ።
ትዳር እና ትምህርት
ስንቅነሽ (ዶ/ር) ኮሌጅ ከገቡ በኋላ ግን ትምህርት እና እጅ ሥራ አብረው አልሔድ አሉ። ችግር ተፈጠረ፤ ሆኖም ግን በአማርኛ ቋንቋ መምህርነት ከሠለጠኑ እና ዲፕሎማቸውን ከጨረሱ በኋላ፤ ወደ ጊምቢ ኮምፕርሄንሲፍ ሃይስኩል ተመድበው ሲያስተምሩ ቆዩ። በዛው ትዳር መሠረቱ፤ ልጆችም ወለዱ።
ሁለት ልጆች ከወለዱ በኋላ ዲፕሎማቸውን በጨረሱ በሦስተኛው ዓመት፤ ዲግሪ ለመማር እንደሚፈልጉ ተናገሩ። በዛ ጊዜ ማንም አልተቀበላቸውም። የትዳር አጋራቸውም ሆኑ ባልደረቦቻቸው ‹‹ምንም አይሠራልሽም›› እያሉ በፅኑ ተቃወሟቸው። እርሳቸው ግን ሁለት ልጅ ቢወልዱም፤ ‹‹ትምህርት በክረምት ብቻ ነው። ልጆቼን ደግሞ እናቴ እየመጣች ለሁለት ወር ትንከባከባቸዋለች እማራለሁ። ” ብለው ወሰኑ። ለአራት ዓመታት ያህል፤ ለሁለት ወር ክረምት እናታቸው እርሳቸው ቤት እንዲቆዩ አደረጉ። በመጨረሻም የነበራቸውን ዲፕሎማ አሻሽለው በክረምት ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪቸውን ያዙ። በልጅነታቸው በተማሩበት ኃይለማሪያም ማሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበው በመምህርነት ማስተማር ቀጠሉ።
ጊዜውን እያስታወሱ፤ ‹‹የሴትነት ፈተና ብዙ ነው። ትዳር ይኖራል፤ ልጆች አሉ። አንዳንድ ባሎች ራሳቸው ልጆች ናቸው። ሴቶች እንዲያድጉ ላይፈቅዱ ይችላሉ። እኔንም ብዙዎች ‹ይበቃል› ዲፕሎማ ካለሽ ከዛ በላይ ምን ያደርግልሻል’ ሲሉኝ ነበር። የቅርብ የምወዳት ጓደኛዬ ሳትቀር ልትረዳኝ አልቻለችም ነበር። ›› በማለት ማንንም አልሰማም ብለው ትምህርታቸውን እንደቀጠሉ ይናገራሉ። ለትምህርታቸው መግፋትም አበረታች እና ትልቁን ሚና የተጫወቱት እናታቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።
ከመምህርነት ውጪ
ስንቅነሽ (ዶ/ር) ለ14 ዓመት ካስተማሩ በኋላ፤ በሥራ ዝውውር በ1993 ዓ.ም ክረምት አካባቢ ግብርና ሚኒስቴር በሥነጽሑፍ አርታዒነት ተቀጠሩ። ከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ የመምህርነት ሕይወታቸው እዛ ላይ አከተመ። ቆይተውም የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች ባለሙያ ሆነው ሰባት ዓመት አካባቢ እዛው ሠሩ። ነገር ግን ሁኔታውን ሲያስታውሱ፤ የቢሮ ሥራ እና አስተማሪነት በፍፁም የተለያየ ነው። በማለት ለእርሳቸው ከአስተማሪነት ውጪ ሕይወት አሰልቺ ሆኖባቸው መቆየታቸውን ይናገራሉ።
እርሳቸው ግብርና ሚኒስቴር ገብተው ሥራ ከጀመሩ በኋላ፤ ቁጭ ማለት አዲስ ሆነባቸው። ጊዜው የሽግግር ወቅት በመሆኑ በተቋሙ በቂ ሥራ እና መረጋጋት አልነበረም። በግብርና ሚኒስቴር የሥነጽሑፍ ኤዲተር ሆነው በኤክስቴንሽን ክፍል ውስጥ ሲሠሩ፤ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብሎ መዋል አሰለቻቸው። መጽሐፍ እና ጋዜጣ ሲያነቡ ውለው ቤት መግባት አዕምሯቸውን ረበሸው። በዚህ ጊዜ ‹‹ሁለተኛ ዲግሪዬን ብማር ይሻለኛል። ›› ብለው፤ ተቋሙ እንዲያስተምራቸው ጠየቁ። ተቋሙ የሰጣቸው መልስ፤ ‹‹ላለሽበት ክፍል እና የሥራ ሁኔታ ከግብርና ሚኒስቴር አንፃር ዲግሪ በቂ ነው። ስለዚህ ልናስተምርሽ አንችልም። ›› የሚል ምላሽ ተሰጣቸው።
ከተቋሙ በሳምንት ለሦስት ቀን ግማሽ ግማሽ ቀን ፍቃድ ይሰጠኝ ብለው፤ ራሳቸው ከፍለው እንደሚማሩ አሳውቀው ትምህርታቸውን ጀመሩ። ስንቅነሽ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ በዚህ ጊዜ ከትዳር አጋራቸው ጋር ተለያይተው ነበር። ትምህርታቸውን ከመሥሪያ ቤቱ የብድር ተቋም ገንዘብ ተበድረው ከፈሉ። ለብቻቸውን ልጆች ማስተማር፤ የዩኒቨርስቲ ትምህርት ክፍያ ተጨምሮ መኖር ከባድ ሆነባቸው። ይህ ሁሉ ቢሆንም በጥሩ ውጤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ።
ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ግብርና ሚኒስቴር መቆየት የለብኝም ብለው፤ ሦስት ቦታ ለሥራ አመለከቱ። የት ልግባ ብለው ሲያመነቱ በ1997 ዓ.ም ሚኒስቴሩ ቢሮ እንደሚፈለጉ ተነገራቸው። የተፈለጉት የአጠቃላይ የግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የዲስፕሊን ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው እንዲሠሩ ነበር። ይህ ሲነገራቸው ለመልቀቅ መፈለጋቸውን ገለፁ። ለምን ከተቋሙ እንደሚለቁ ሲጠየቁም፤ ምክንያቱም የሚሠሩት ሥራ አለመኖሩን ተናገሩ። የወቅቱ ኃላፊ ሚኒስትር ብቻ አልነበሩም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱ ነበሩ። ከሰዎች ጋር ሲማከሩ ‹‹እርሳቸው የማያዙት የትኛው ተቋም ልትገቢ ነው?›› ብለው ሲያስፈራሯቸው፤ የኮሚቴው ሰብሳቢ ለመሆን ተስማሙ።
ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለሚኒስትሩ ሲሆን፤ ሥራው በጣም ብዙ ፈተና ነበረው። የተወዘፉ ብዙ ጉዳዮችን መሥራት የግድ ሆነ። ሳይሠሩ የበሉትን ለመክፈል ተገደዱ። የተከማቸውን ሥራ ካስተካከሉ በኋላ በድጋሚ መሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ (ቢ ፒ አር) ሥሪ ተባሉ። በዚህ መካከል የሰው ኃይል ምደባው ሲያልቅ ግን ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት አሰቡ። ‹‹ሚኒስትሩ ሹመት ላሰጥሽ ነው›› ቢሉም ስንቅነሽ (ዶ/ር) አልተስማሙም፤ ማስተማር ይሻለኛል አሉ። የሚገኘውን ደመወዝ እንዲሁም ጥቅማጥቅም እና ሌሎችም የወደፊት ዕድሎችን በተመለከተ በጓደኛ ቢመከሩም እምቢ አሉ። እጃቸው ላይ ብዙ ሥራ ነበር። ‹‹ሥራሽስ›› ሲባሉ፤ ጎን ለጎን ያለደመወዝ እሠራለሁ ብለው ለሦስት ወር ሁለቱም ሲሠሩ ቆዩ።
በዛው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፎክሎር መምህርነት ተቀጠሩ። ከግብርና ሚኒስቴር ለቀቁ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለአንድ ዓመት ያህል በመምህርነት ሲሠሩ ቆዩ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2000 ዓ.ም ምርጫ ነበር። ባላደራው ሲያስተዳድር ቆይቶ መደበኛ ምርጫ ሲካሔድ ለምክር ቤት ተወዳድረው የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆኑ።
ሁኔታውን ስንቅነሽ (ዶ/ር) ሲያስረዱ፤ ከዛ በፊት አዲስ አበባ ምክር ቤት አልነበረም። ሕግም የሚያወጣውም ሆነ የሚያስፈፅመው ራሱ ሥራ አስፈፃሚው ነበር። ስለዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ደረጃ ሲቋቋም የመጀመሪያዋ አፈጉባኤ ሆነው ለሁለት ዓመት አገለገሉ። በመቀጠል ለሦስት ዓመት የምክር ቤት አባል ሆነው ቆዩ። ከአፈጉባኤነት ሲለቁ የ3ኛ ዲግሪያቸውን ጀምረው በ2007 ዓ.ም ጨረሱ። በ2008 ዓ.ም ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና የቻይናው ፎሪን ስተዲስ ዩኒቨርስቲ በተግባቦት ስምምነት መሠረት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምር ሰው መላክ ነበረባቸው። እዛ ተልከው ወደ ስምንት ዓመት ሲሠሩ ቆይተዋል።
የባለታሪኳ አርዓያ
የእርሳቸው አርዓያ እናታቸው ናቸው። እንደሚናገሩት ማንም ሊገምት በማይችል መልኩ ለምንም ነገር የማይሸነፉ ጠንካራ ናቸው። የእናታቸው እምነት ምንም ዓይነት ፈተና ሊያጋጥም ይችላል። ናዳዎች ይኖራሉ። ነገር ግን ናዳ ቢመጣም ተቋቁሞ መውጣትን ማዕከል ያደረገ ነው። ስለዚህ ስንቅነሽ (ዶ/ር) ም እንደእናታቸው ናቸው። ፈተና ያስደስታቸዋል። ስለዚህ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ሕይወታቸው በሙሉ ፈተና የተሞላበት ነው። ፈተናውን ማለፍ ደግሞ የእርሳቸው ስኬት መሆኑን ያስረዳሉ።
ሴት መሆን፤ ባለትዳር መሆን ፈተና ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ዋናው አንዲት ሴት ራሷ ለራሷ ከወሰነች ያሰበችበት ትደርሳለች። ሌላው ጉዳይ በዲሲፕሊን መመራት ነው። ችግርም ቢሆን በሥነሥርዓት በመመራት ያልፋል ይላሉ። እርሳቸው ልጆቻቸውን እንዴት እንዳሳደጉ ሲገልፁ፤ የሚባክን ነገር ካለ ገንዘቡ አይበቃም። ሶፍት ሳሙና እና በየወሩ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በየወሩ ገዝተው ለእያንዳንዳቸው ይከፋፈላሉ። ሁሉም የራሱን ጠብቆ እና ቆጥቦ ይጠቀማል። ለምሳሌ ሳሙና ለልጆች እና ለእናት ለአራቱም ይሠጣቸዋል። በዚህ ደረጃ በአግባቡ ሁሉም የሚያስፈልጋቸውን በየግላቸው ይወስዳሉ።
‹‹ልጆቹ ኑሯቸውን እንዲኖር ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን አደርጋለሁ። ዋናው ጉዳይ አይራቡም፤ ነገር ግን እናት ነኝና ጫማ እያጣሁ ለእነርሱ የአራት ሺህ ብር ጫማ አልገዛም። አሁን ሁሉም አድገዋል፤ ትልቅ ሆነዋል። ትንሹ 32 ዓመቱ ነው። ሁሉም በአግባቡ የየራሳቸውን ሥራ እየሠሩ ይኖራሉ። ›› ይላሉ።
የፖለቲካ ፍላጎት
‹‹ የፖለቲካ ፍላጎት የለኝም፤ መሾም እና ፖለቲካ ብፈልግ ኖሮ የግብርና ሚኒስትር ያቀረቡልኝ ጥያቄ እቀበል ነበር። ነገር ግን ማስተማር ይሻለኛል በሚል ወደ ማስተማር ገባሁ። ነገር ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከገባሁ በኋላም፤ አንድ ዓመት አካባቢ እንዳስተማርኩ ምርጫ ቅንጅት አሸንፎ ከተማዋ የምትመራው በባላደራው ነበር። በቃ ተመረጪ ሲሉኝ ለስብሰባ በሦስት ወር አንዴ ብቻ ትገኛለሽ ሲሉኝ ተስማማሁና ፎቶ ሰጥቼ ተመረጥኩ። ›› ይላሉ።
ነገር ግን ቀድሞ እንደተባሉት አልሆነም። አፈጉባኤ ትሆኛለሽ ተባሉ። ሌላ ቦታ መድቡኝ ቢሉም የሚሰማቸው አጡ። አሁንም ሰዎች ሲያማክሩ አስፈራሯቸው። ስለዚህ ስለሥራው እና አሠራሩ ጠየቁ፤ ከፌዴራል ቀጥሎ ምክር ቤት ያላቸው ክልሎች እንጂ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አልነበራቸውም።
ባሕርዳር ሔደው ከባሕርዳር አፈጉባኤ ልምድ ጠየቁ። እነርሱ ከሕገመንግስቱ የተቀዳ የራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ አላቸው። ‘ስጡኝ’ አሉና ማንበብ ጀመሩ። ጽሑፉ በጣም ምርጥ ነበር። ስለዚህ መሥራታቸውን ቀጠሉ። ከንቲባዎቹን በፊርማቸው ካፀደቁ በኋላ፤ ለእርሳቸው ግን ቢሮ አጡ። ስለዚህ አዲስ ጽሕፈት ቤት ማቋቋም፤ የሰው ኃይል የመቅጠር ሥራ ሠሩ። አዋጆችን ማፅደቅ እና ሁሉንም ነገር ቅርፅ ማስያዝ ጀመሩ።
ከዩኒቨርስቲ ወደ አፈጉባኤነት ሲገባ ማስተማሩን ለጊዜው አቁመው ነበር። ከዩኒቨርስቲውም የተሰጡት ለጊዜው በሚል በትውስት ነበር። ለሁለት ዓመት ምክር ቤቱን ሥርዓት እና መልክ ለማስያዝ ጥረት ካደረጉ በኋላ ግን ነገሮች ቅርጻቸውን ቀየሩ። በብዙ መልኩ ያመኑበትን የማይቀይሩ በመሆናቸው እና አንዳንዴም የማያምኑበትን ጉዳይ አይሆንም የሚል አቋም መያዛቸው ከሁኔታዎች ጋር ተግባብተው መቀጠል አቃታቸው።
ስንቅነሽ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ‹‹ሴት ሆኜ የያዝኩት የአንድ ወንድ ቦታ ነው። ስለዚህ ፈተናው ብዙ ነው። በዛ ቦታ ላይ ለመቆየት ጓደኛ ማፍራት፤ ማታ
አብሮ ብርጭቆ ማጋጨት ያስፈልጋል። እኔ ደግሞ እስከ ማታ አራት ሰዓት ሠርቼ፤ ቤቴ የምገባው በጣም ደክሞኝ ነው። ›› ለማንኛውም ሁለት ዓመት ከሦስት ወር አካባቢ ቆይታ በኋላ፤ በሌላ አፈ ጉባኤ ተተካሁ ይላሉ። በጣም ደስ ብሏቸው ወደ ዩኒቨርስቲ ተመለሱ። በዛው ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ጀመሩ።
‹‹በአፈጉባኤነት ሥራዬ ቢሮክራሲው በምን መልክ እንደሚሠራ፤ ለቦታው ምን ዓይነት ሰው እንደሚያስፈልግ አወቅኩኝ። እኔ ደግሞ ለቦታው ምን ያህል እንደማልሆን አውቄያለሁ። አሁን እንደውም ሰው ካላስታወሰኝ ረስቼዋለሁ። ከዛም በኋላ እኔን የተካችኝ ሴት ራሷ ብዙ አልቆየችም። በኋላ ወንድ ሲይዘው ረጋ። ›› የሚሉት ስንቅነሽ (ዶ/ር)፤ ነገር ግን በጉልበት ሳይሆን በአዕምሮ ሥራ ማንኛውም ወንድ ከሚሠራው የተሻለ በዲስፒሊን የመሥራት አቅም አለኝ ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ።
‹‹አንዳንድ ጊዜ የሚያስጠላው ፖለቲካ ላይ ያልሆኑትን ነገር እንደሆኑ አድርጎ ጥላሸት የመቀባት ዝንባሌ ይታያል። በዋናነት ደግሞ ፖለቲካ ሳይሆን ዓላማዬ በትምህርቴ መግፋት ነበር። ስለዚህ አፈጉባኤነት ሲቀር በኃላፊነት ላይ እያለሁ የተሰጠኝን ቤት በደብዳቤ ቤታችሁን ውሰዱ ብዬ አስረክቤያለሁ። እነርሱም ከምስጋና ጋር ደብዳቤያቸውን ሰጥተውኛል። ግብርና ካገኘሁዋቸው ትልልቅ መልካም ነገሮች መካከል አንደኛው ሁለተኛ ዲግሪዬን መማሬ ሲሆን፤ ሌላኛው በ1997 ዓ.ም ከተሠራው የጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ ‹በጊዜው ቅንጅት የድሃ ማጎሪያ ነው፤ ቶሎ ይፈርሳል› የሚል ወሬ በማውራቱ ቤቶቹን የሚወስድ ሰው ጠፋ። ›› የሚሉት ስንቅነሽ (ዶ/ር)፤ ስለዚህ የአዲስ አበባ ዩኒየን 700 ቤቶችን ገዝቶ ለሠራተኛ ማኅበራት ሲያከፋፍል፤ ግብርና የመጣውን ቤት የሚወስደው ሲጠፋ፤ እርሳቸው ግን ባለሦስት እና ባለሁለት መኝታ ቤት ማግኘት ቢችሉም ቅድመ ክፍያውን መክፈል ይከብደኛል ብለው ባለአንድ መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤት አገኙ። አሁንም በዛው ቤት እየኖሩ ነው።
በመጨረሻም የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከቤጂንግ ፎሪን ስተዲ ዩኒቨርስቲ ጋር በገባው ውል መሠረት የአማርኛ መምህር መላክ ነበረበት። አንዲት መምህርት ሔደች። ነገር ግን ሁለት ዓመት አስተምራ ቀጥይ ስትባል አልፈልግም አለች። ምክንያቱም ደመወዙ ትንሽ ነው። ማንም አልፈልግም አለ። ቻይና ያለው የአማርኛ ትምህርት ክፍል ሊዘጋ መሆኑ ተገልፆ እንዲሔዱ ተጠየቁ፤ መጀመሪያ አቅማምተው ነበር፤ በኋላ ቻይና የአማርኛ ትምህርት ክፍል ከሚዘጋ ብለው ሔዱ።
ኑሮ በቻይና
ስንቅነሽ (ዶ/ር) ቻይና ሲሔዱ፤ ዩኒቨርስቲው 101 የዓለም ቋንቋዎች የሚሰጡበት ትልቅ ዩኒቨርስቲ ነው። ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካላት ሀገሮች የሥራ ቋንቋ በትምህርትነት የሚሰጥበት ግቢ ነው። ከአፍሪካ ቋንቋ ሱዋህሊ መሰጠት ከተጀመረ 50 ዓመት ሆኖታል፤ ሐውሳ 40 ዓመት ሆኖታል። አሁን አማርኛ አለ፤ ሶማሌኛም እያስተማሩ ነው፤ የጋና ቋንቋም በዩኒቨርስቲው እየተሰጠ ይገኛል።
ስለዚህ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በቻይና አዲስ ስለሆነ ተማሪዎች ለአንድ አጋማሽ የትምህርት ዘመን ይመርጡና ከተማሩ በኋላ፤ ቆይተው ገና መናገር ሲጀምሩ የትምህርት ጊዜው ያልቅ እና ይሔዳሉ። በደንብ ስላላወቁት ይረሱታል። በሌላ አጋማሽ የትምህርት ዘመን አዲስ ተማሪዎች ይመጣሉ። ይህንን ሲያዩ ትምህርቱ በሚገባው እየሔደ አይደለም። ስለዚህ ለዩኒቨርስቲው ጥያቄ አቀረቡ። እንደሌሎቹ ቋንቋዎች በዲግሪ ደረጃ ይሰጥ ያለበለዚያ ብክነት ነው ሲሉ ጠየቁ። ያለበለዚያ መቆየት እንደማይፈልጉ ሌላ አስተማሪ ሊመጣላቸው እንደሚችል ተናገሩ።
ዩኒቨርስቲው በበኩሉ፤ ‹‹በዲግሪ ዲፓርትመንት ለመክፈት ደግሞ አልችልም። ምክንያቱም የአማርኛ የመማሪያ መጽሐፍ ያስፈልጋል፤ ቢያንስ አንድ አማርኛ የሚችል እና አማርኛ የሚያስተምር ቻይናዊ ያስፈልጋል።›› አለ። ስንቅነሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አማርኛ የሚማር አንድ ሰው ምረጡና ኢትዮጵያ ሄዶ ይማር፤ እኔ ደግሞ የመማሪያ መጽሐፍ አዘጋጃለሁ። በዚህ ከተስማማን ልቆይ ካልተስማማን ወደ ሀገሬ እሔዳለሁ አሉ። ዩኒቨርስቲው ተስማማ።
ሁለት ልጆች ተመርጠው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተላኩ። እርሳቸውም መጽሐፎችን ለአራት ዓመት አዘጋጁ። ተማሪዎቹ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሊመረቁ ሲሉ ግን ኮቪድ ገባ። ኮቪድ ሲገባ መንግሥት የትኛውም ዩኒቨርስቲ ተማሪ እንዳያስመርቅ አለ። ትምህርቱን የጨረሰችው አንዲት ቻይናዊት ነበረች። እሷ ካልተመረቀች እና ቻይና ሔዳ ማስተማር የማትችል ከሆነ ፕሮግራሙ አይከፈትም ተባለ። ስለዚህ ስንቅነሽ (ዶ/ር) መመረቅ አለባት ብለው በብዙ ውጣ ውረድ እርሷ ብቻዋን በልዩ ሁኔታ ተመረቀች።
ፕሮግራሙ ሲጀመር እርሳቸው ደግሞ በኮቪድ ምክንያት ኢትዮጵያ ነበሩ። የኦንላይን ትምህርት ማስተማር ጀመሩ። አማርኛ ቋንቋ የራሱ ፊደል ያለው በኢትዮጵያ ኢንተርኔት አገልግሎት፣ ኤሌክትሪክ እየተቋረጠ ማስተማር የማይሆን ነገር ነው። በራሱ ፈተና ሆነ፤ ስለዚህ ቻይና ለመሔድ ወሰኑ። ቻይና በዛ ጊዜ ማንም ሰው እንዳይመጣ ብላ ነበር። ሆኖም ቪዛ ሰጥተዋቸው እዚህም ሆቴል ከፍለው ማቆያ ከቆዩ በኋላ ቤጂንግ ሔዱ። ቻይና ቤጂንግም በድጋሚ ማቆያ፣ ገብተው ለአንድ ወር ቆይታ በኋላ ከተማሪዎቹ ጋር ተቀላቀሉ። ወደ ሦስት የመማሪያ መጽሐፎች አሉ። ጀማሪዎቹ እና መካከለኞቹ የሚማሩበት መጽሐፍ አዘጋጅተው አስተማሩ። የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አራት ዓመት ጨርሰው የአሁኑ ሰኔ ተመረቁ። አሁን የፊታችን መስከረም አዲስ ተማሪዎች ይቀበላሉ።
የቻይና ባሕል
‹‹እኛ አዕምሮ ውስጥ ያለው ቻይናን የምናይበት ሁኔታ ከባድ ነው። ዋናው ፈተና ቋንቋ ነው። እንግሊዘኛ ተናጋሪ ማግኘት አይቻልም። ገበያ ሄዶ የሆነ ነገር መግዛት አይቻልም። ሁሉም ዕቃ ላይ የሚፃፈው በቻይና ቋንቋ ነው። እስከሚለመድ ይከብዳል። ሌላው ጉዳይ እንደእኔ አይነት ከሰው ጫካ ውስጥ ለወጣ ሰው ይከብዳል። ›› ይላሉ። ለብቻውን መኖር እና መብላት ለማይወድ ሰው ከባድ ነው። ሳያወሩ ምንም ሳይናገሩ መዋል አለ። ማንም ለማንም ምንም አይደለም። በኋላ ግን የሕዝቡ ባሕል እና ቋንቋ ሲለመድ በጣም ምቹ አገር ነው።
ቻይና ምንም የሚያስፈራ ነገር የለም። ሌሊት ሰባት ሰዓት የትኛውም ሰው የፈለገበት ደርሶ መመለስ ይችላል። ሕዝቡ ደግሞ ትንሽ ቋንቋ የሚያውቅ ሰው ካገኘ በደስታ ቶሎ ይግባባል። የበታቼ ነህ የማለት ሁኔታ የለም። ቻይና ዘግታ ስለቆየች በተወሰነ መልኩ ከገጠር የመጡ ቻይናውያን አፍሪካውያንን ወይም አጠቃላይ የውጪ ሰዎችን አይተው አያውቁም። የምድር ባቡር ውስጥ ሁሉም ቻይናዊ ሆኖ አንድ አፍሪካዊ ብቻ ሊኖር ይችላል። እነዛ ሰዎች ያንን ሲያዩ ይደነግጣሉ። ‹‹ ኒሃው›› ወይም ሠላም ሲባሉ ‹‹ኒሃው›› ብለው እየሳቁ ሰላምታ ይሰጣሉ። ሁሉንም ነገር ይረሳሉ።
‹‹እኔም በበኩሌ እኔ የተለየሁ ነኝ ብዬ ራሴን አሳምናለሁ። ሊያዩኝ ፎቶ ሊያነሱኝ ይፈልጋሉ፤ ያንን እንደመጥፎ አላየውም። ሲንደመጥፎ ማየት አደገኛ ነው። ›› ካሉ በኋላ የሚያስቀና የሥራ ባሕል እንዳላቸው ይናገራሉ። ስንቅነሽ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ቻይናዎች ምንም የሌላቸውን ነገር እንዳለ ያደርጋሉ። ወንዝ በሌለበት ወንዝ ይፈጥራሉ። ተራራ በሌለበት ተራራ ይሠራሉ። ዛፍ በሌለበት ዛፍ ያበዛሉ። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሁሉም ነገር አለን። ነገር ግን አልተጠቀምንበትም። እነርሱ ሀገር አንድ ሥራ ከተጀመረ የሚሠራው 24 ሰዓት ነው። ፈረቃ አላቸው። አየራቸው ከባድ ነው፤ ነገር ግን በኃይለኛ ቅዝቃዜ ውስጥ ይሠራሉ። ሌላው ማንኛውም ሰው ለራሱ ኃላፊነት አለበት። እንደኢትዮጵያ አንድ ነጋዴ አጎት ቤት ሳይሠሩ መኖር አይቻልም። 18 ዓመት ከሞላቸው በኋላ ይሠራሉ፤ እንዲሁም ወላጅን ይረዳሉ።
እንደስንቅነሽ (ዶ/ር) ገለፃ፤ በቻይና የሚና መደበላለቅ የለም። ፖለቲከኛው ፖለቲካውን ይሠራል። አስተማሪው ያስተምራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሁሉም ፖለቲከኛ ነው። እነርሱ እንደዚህ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ለመፈትፈት ጊዜም የላቸውም። የትዳር ጓደኛ ለማግኘት እንኳ የሚተያዩበት ጊዜ የላቸውም። የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ወላጆቻቸው ሲቪ ይዘው ፓርክ ይሄዳሉ። በታወቀ ፓርክ በታወቀ ሰዓት ተገናኝተው እሁድ እና ሰኞ ሴት ልጅ ያላቸው የሴት ልጃቸውን ቁመት፣ መልክ የትምህርት ደረጃ እና በአጠቃላይ ገልፀው ያስተዋውቋቸዋል።
በቻይና በሕጻንነታቸው ሐኪም የሚሆነው ፖለቲከኛ የሚሆነው እያንዳንዱ በማስተዋል ችሎታው (በአይ.ኪው) ስለሚለይ ያንኑ ነገር ከታች ጀምረው ይዘው ያድጋሉ። ሌላው አንድ ሰው ዩኒቨርስቲ ገብቶ ዲግሪ ከያዘ ትንሽ ሥልጠና ተሰጥቶት ማንኛውንም ሥራ መሥራት ይችላል ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ አማርኛ ዲግሪ ያላቸው የእኔ ልጆች የሚያስተምሩት እና የሚሠሩት የግድ አማርኛን የተመለከተ ብቻ አይሆንም። ከ2 ወር እስከ ስድስት ወር የሚቆይ ሥልጠና ወስደው የትኛውንም ሥራ ይሠራሉ።
ሌላው በስንቅነሽ (ዶ/ር) የተገለፀው፤ በቻይና የመንግሥት መሥሪያ ቤት መቀጠር በጣም ከባድ ነው። ድሮ የተዘጋጀ ፈተና አላቸው። ያንን ፈተና ያላለፈ መቀጠር አይችልም። ያንን የሚያልፈው በጣም ጥቂት ሰው ነው። ካላገለገሉ እና አለምጣለሁ ካሉ ለአንድ ሰከንድ መቆየት አይቻልም ይላሉ።
ቻይናዎች በዓል የሚያከብሩት በሰፊው ነው። አንድ በዓል ከሦስት ቀን በታች አይከበርም። ታዲያ ቀኖቹን አስቀድመው ከበዓል በፊት በእረፍት ቀናት ያካክሷቸዋል። ለምሳሌ ሐሙስ በዓል ከሆነ ረቡዕ እና አርብ ለማረፍ ከበዓሉ በፊት ያሉትን ቅዳሜ እና ዕሁድን የሥራ ቀን አድርገው ሦስት ቀን ሥራ ይዘጋል። ሦስት ቀን የሆነበት ምክንያት ሰዎች ወደ ተለያየ ቦታ ስለሚሔዱ ነው። በበዓል ጊዜ የሚጎበኝ ነገር ይዘጋጃል። ኢትዮጵያ ውስጥም ጳጉሜን ሰዎች ቀድመው ሠርተው ቢያርፉ እና ስድስት ቀን ወደ ሌላ ቦታ ሔደው እንዲያከብሩ ማድረግ ቢቻል መልካም ነበር ይላሉ።
ስንቅነሽ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ቻይናዎች ባሕላዊ መድኃኒትን የሚጠቀሙት በከፍተኛ ሁኔታ ነው። በቻይና የባሕላዊ ሕክምና ዩኒቨርስቲዎች አሉ። የቻይና የባሕል ሐኪም ለመሆን 12 ዓመት መማር ግዴታ ነው። ሆስፒታሎች ውስጥ ዘመናዊም ባሕላዊም ሕክምና አለ። ታካሚው ከፈለገ ባሕላዊ ካልሆነም በዘመናዊ መንገድ መታከም ይችላል። ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚደረገው የዕፅዋት፣ የጭስ፣ የማሸት እና ሌሎችም ሕክምናዎች አሏቸው። በኢትዮጵያ ግን ባሕላዊውን ሕክምና ወደ ኋላ እየጣልነው ብዙዎቹ አዋቂዎች እየሞቱ እየከሰርን ነው ይላሉ። በእርሳቸው በኩል በዚህ ላይ ጥናት እያካሔዱ መሆኑን በመጠቆም፤ ‹‹የሀገራችንን ባሕላዊ ሕክምና እንዴት ወደ ዘመናዊነት እናምጣ›› የሚለው ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት አለበት ይላሉ።
አማርኛ ቻይና በመሰጠቱ ለሀገር ትልቅ ስዕል ነው። ለዲፕሎማሲ ግንኙነትም ሆነ ለባሕል ልውውጥ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ቋንቋውን ብቻ ሳይሆን ባሕሉንም እናስተምራቸዋለን። ቻይናዎች ለኢትዮጵያ ያላቸው ግምት ትልቅ ነው። አፍሪካ ሲባል የሚያስቡት ኢትዮጵያን ነው። አማርኛ መማራቸው የኢትዮጵያ ሽታ ቻይና ውስጥ እንዲኖር አድርጓል። ስለዚህ ትምህርቱ እንዲቀጥል ሁሉም ሰው ሊያግዝ ይገባል። በቀጣይም አማርኛ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ የሚሆኑት በሙሉ በቻይና ይሰጣሉ እንዲሆን መጣር አለብን ይላሉ።
ያስተማርዋቸው ልጆች በአማርኛ የሠሩት የመመረቂያ ጽሑፍ የሚገርም ነው። አንደኛዋ የኢትዮጵያ ቡና በቻይና ገበያ ያለው ተቀባይነት እና ፈተናዎቹ ምንድን ናቸው? በሚል ሐሳብ ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር ይላሉ። ያነሳቻቸው ነገሮች በጣም የሚገርሙ ናቸው የሚሉት ስንቅነሽ (ዶ/ር)፣ ቡና ለኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ነው። ያንን ቡና ላኪዎች እና መንግሥት ቢጠቀምበት ጥሩ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
ሌላኛው ተመራቂ የቻይና ካምፓኒዎች በኢትዮጵያ የሚያጋጥማቸው ፈተና ምንድን ነው? የሚል ነው። የዜግነት መስፈርቶች ቻይና እና በኢትዮጵያ ያለውን እያነፃፀሩ አጥንተዋል። ስለዚህ ትምህርቱ እየሠፋ ቢሄድ ትልቅ ለቻይናም ሆነ ለኢትዮጵያ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።
ስንቅነሽ (ዶ/ር)፤ ይህን ዕድል በማግኘታቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን አመስግነዋል ። ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በቻይና ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ያገዛቸው መሆኑን ገልፀው፤ ቤጂንግ ፎሪን ዩኒቨርስቲ እንደሀገራቸው እንዲሰማቸው በተለይ የአፍሪካን ስተዲስ ኮሌጅ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም በ2ኛ ዲግሪ ደረጃ የአማርኛ ትምህርት በቻይና ይሠጣል ብለው እንደሚመኙ ገልፀዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም