‹‹ኢጎ›› እና ጠንካራ ማንነት

የሰው ልጅ በክርክር ወቅት ያለማመን አልያም ሽንፈትን አለመቀበል ወይም እዋረዳለሁ ከሚል ፍርሃት ከእኔነት /ego/ የሚመጣ እንደሆነ ሳይንሱ ይናገራል። በሌላ ወገን ደግሞ የሰው ልጅ ያመነበትን ነገር ስህተትም ይሁን ልክ እስከመጨረሻው ድረስ ከታገለ እንደ አቋም ያለው ቆራጥ ተደርጎ ይቆጠራል። ጥያቄው ግን ‹‹ሁለቱን እንዴት አንድ አርጎ ማስታረቅ ይቻላል?›› የሚለው ነው። ለነገሩ ሕይወት ማለት ሁለት ጫፍ ላይ ያሉ ሁለት ነገሮችን ሚዛን መስጠት ነው፤ ብስለት ነው። ሕይወት ደግሞ ሁልግዜ በግራ በቀኝ፣ በፊትና በኋላ፣ በላይና በታች፣ በውስጥና በውጪ በሚያሳዩ ነገሮች የተሞላች ነች።

ለምሳሌ በግራና ቀኝ አንዱ ወደዛ ሌላው ደግሞ ወደዚ ይሄዳል። አንዱ ወደ ሰሜን ሌላው ወደ ደቡብ ይሄዳል። አንዱ ምስራቅ ሌላው ምእራብ ይሄዳል። ስለዚህ እያንዳንዱን ነገር ነጭና ጥቁር፣ ጨለማና ብርሃን እያልን የአቅጣጫና የእይታ ልዩነት እናስቀምጣለን። ሕይወት ማለት ደግሞ በነዚህ ነገሮች መካከል ትናንትናና ነገ ያለ ነገር ነው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች በትክክል የመሄድ ጉዳዮች ናቸው።

አንድ ክርክር በሚነሳበት ግዜ ግትር ብሎ፤ አላምንም ብሎ የሚያስቸግር ተሟጋች ሰው በአንድ በኩል ቆራጥ አቋም እንዳለው ሆኖ ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ግትር፣ ሽንፈት የማይወድ ‹‹ኢጎይስት›› ተደርጎ ይታያል። ታዲያ ይህ ሁለት ተቃርኖ እንዴት ነው ሊጣጣም የሚችለው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። ለዚህ ሁለት ነገሮች አሉ።

የመጀመሪያው ነገር ሁሉም ሰው ጥንካሬው ሲገለበጥ ድካማ ጎኑ ነው የሚሆነው። ይህን ልንቀይረው አንችልም። ለምሳሌ በጣም ቆራጥ የሆነ ሰው እንዳለመታደል ሆኖ ብዙ ግዜ ግትር ነው። በጣም ደግ የምንላቸው ሰዎች ካልተጠነቀቁ ገንዘብ አባካኝ ናቸው። በጣም ቆጣቢ የምንላቸው ሰዎች ደግሞ ስስታም የመሆናቸው እድል ከፍተኛ ነው። በሌላ በኩል በጣም ሰው የሚወዱ፣ ከሰው ጋር የማኅበራዊ ሕይወታቸው የደመቀላቸው፣ ሰው የሚያዝናኑ ሰዎች በይበልጥ ራሳቸው ላይ ትኩረት አያደርጉም። በመጠኑ ዝርክርክ የመሆን እድልም አላቸው።

ስዚህ ለነዚህ ነገሮች ሚዛን መስጠት ያስፈልጋል። አንድ ሰው ግትርና ቆራጥ ስለመሆኑ መለያው የቱ ጋር እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። ‹‹ኢጎይስት›› የሚባልና ራሱን የሚያቅ አቋም ያለው የቱ እንደሆነ መለየት ይገባል። እንግዲህ የመጀመሪያው ሂደት ከሰዎቹ ነገሩን መዋጣት ነው። ወደሃሳቡ መውሰድ ነው። አንድ ሰው ሃሳቡ በራሱ ቆሞ፤ ተሟግቶ ሰውዬው ሃሳቡን ማሳየት ነው ኃላፊነቱ። እናም ያ ሃሳብ በሚሸነፍበት ግዜ እንዴት እሸነፋለሁ ብሎ ዘራፍ! ካለ ከሀሳብ ቀጠና ወጥቶ ወደራሱ ቀጠና ገብቷል ማለት ነው።

ለምሳሌ አንድ ትንሽ ልጅ ከሌሎች አዋቂዎች የተሻለ ሃሳብ ካመጣ አዋቂዎቹ አይደሉም እየተንበረከኩ ያሉት ሃሳቡና ሀሳቡ ተገናኝተው የተሻለው ሀሳብ ሁልግዜ ከፍ ብሎ እንዲወጣ መፍቀዱ ነው። በአብዛኛው እኛ ሃሳባችን ሲነካ እኛ እንነካለን። ሃሳባችን ሲሰበር እኛ እንሰበራለን። አንድ ሃሳብ በራሱ ትክክል ነው ብለን ካሰብን እስከመጨረሻው ድረስ እንሟገትለታለን። ነገር ግን የሆነ ቦታ ላይ ከእርሱ የሚበልጥ ሃሳብ ቢመጣ የእኛ ሃሳብ ተሸንፎ የበታች ቢያስመልሰንም ሃሳቡ ስለተሸነፈ እኛ ከተሸነፈ ሃሳብ ጋር ቆመን ትልቅ ሰው ብንመስል ምን ጥቅም አለው?

እዚህ ጋር ትልቁ ነገር ምንድን ነው፤ ሁል ግዜ ከሚያሸነፍ ሀሳብ ጋር ራስን ማቆም ነው። አንዳንድ ግዜ የሚያሸንፈውን ሃሳብ እኔ ነኝ ይዤ እምመጣው እንላለን። አዎ በርግጥ ሁላችንም ያመጣነው ሃሳብ ሲሸነፍ ቅር ይለናል፤ ይሰማናል። የማይታይ ደም ይደማናል። እምባ በእምባ እንሆናለን። መጨረሻ ላይ ግን ምን ተባለ ለሚለው ነገር ማን አለ ከሚለው በላይ ቦታ የምንሰጥ ከሆነ ሰዎች ሌላ ጉዳዩ ሌላ ይሆናል። ሰዎች ሊሸናነፉ የሚገባው በጉልበትም፣ በሌላ አይነት የኃይል ሚዛን ሳይሆን በሃሳብ ልእልና ነው ብለን ካሰብን የመጀመሪያው ነገር ራሳችን ላይ መስራት አለብን።

ስለዚህ ለራሴ ሀቀኛ መሆን አለብኝ፣ አይምሮዬን ክፍት አድርጌ ሁልግዜ አንድ ሀሳብ ይዤ ስመጣ ከኔ የተሻለ ሃሳብ ሊመጣ እንደሚችል መጠበቅ አለብኝ፣ ማለት አለብን። ለነገሩ ሀሳቡ ላይመጣም ይችላል። ከኔ የተሻለ ሀሳብ ባልመጣበት ሁኔታ ሁሉ ግትር አልባልም ቆራጥ ነው የምባለው፤ ለአቋሜ የቆምኩት ማለት ለተረዳሁት እውነት ነው የቀምኩት፤ ከእኔ የተሻለ እኔ ራሴ ውስጤ ቢያውቀው የእኔ ሃሳብ ቢሆን ኖሮ እንዲያሸንፍ የምፈልገው ከሆነ ያ ሃሳብ ማጎንበስ አለብኝ ማለት ይኖርብናል። ትህትናም የሚለካው ለሀሳብ እንጂ ለሰው በማደር አይደለም። ለዛም ነው አንዳንድ ሰዎች ለሰው ሲያድሩ አድር ባይ የማያምኑባቸውን ነገሮች የማያደረጉ የማይባሉት።

ነገር ግን ‹‹ሃሳቡ እኔ እስከተረዳሁት ድረስ ትክክል ከሆነ ለሃሳቡ አድሪያለሁ›› ማለት ይጠበቅብናል። ባለመረዳት ደገሞ አንዳንድ ሰዎች ዝግ ይሆናሉ፤ አይሰሙም። ድንገት ቢገባኝና ባምንስ ብለው ሁሉ የሚፈሩ ሰዎች አሉ። አይምሯችን ክፍት ካልሆነ ሁልግዜ የያዝነውን ነገር ነው ይዘን የምንቀጥለው። የያዝነውን ነገር ላለመልቀቅ በምንፈራበት ግዜ የምንታወቀው ድምፃችን ሲጮህ፣ ሌሎች ሰዎች እንዲያወሩ ባለመፍቀድ፣ ሀሳባቸው እያሸነፈ ሲመጣ የሰዎቹን ስም በማጥፋት፣ ሰዎቹ ከዚህ በፊት ያጠፉትን ጥፋት በማውጣትና በማውራት ነው። እዚህ ጋር ከሃሳቡ ጋር ሳይሆን ከሰዎቹ ጋር ነው ጉዳያችን።

አንዳንድ ግዜ ደግሞ ሰዎች ላይ ፍርሃት እንለቃለን። እኛ ያልነው ሃሳብ ካልሆነ ሰዎች ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል፣ አዲሱ ሀሳብ እንዴት አደገኛ እንደሆነ እንናገራል። ይህ የሚያሳየው እኛ እየኖርነው ያለነው ለኢጓችን እንጂ ለትክክለኛ ሀሳብ አይደለም ነው ማለት ነው። በዚህ የተነሳ ብዙ ግዜ ብዙ ቤት ውስጥ ባሎች እኔ ያልኩት ብቻ ነው ሲሉ ሚስቶች አይሰሙም ወይም ከሰሙም በኋላ አጣጥለው ይተውታል። ይህን የሚያውቁ አንዳንድ ሚስቶች ባል ሳያውቅ ሃሳቡ የእርሱ እንደሚመስለው በተለያየ መንገድ በሌላ ሃሳብ ላይ ይቆሙና እርሱ የራሱ ሀሳብ ስለሚመስለው ሚስት የምትለውን ሃሳብ እንዲቃወም ያደርጋሉ። መጨረሻ ላይ የተደረገው ሃሳብ የእርሷ ይሆናል።

ይህ የሚሆነው አንዳንድ ሰዎች ከልክ ያለፈ ሽንፈትን ያለመቀበል ሁኔታ ውስጥ ሲገቡ /ኢጎይስት/ ሲሆኑ ነው። አንዳንድ መስሪያ ቤትም እንደዛ ይደረጋል። አለቃው የራሱ ሀሳብ ካልሆነ እንደማያደርግ ሲያውቁ በተለያየ በማይታወቅ መልኩ ሃሳቡ እርሱ ጋር እንዲደርስ ያደርጉና ሰውይው ለብቻው ሃሳቡን ይቀይርና ዘራፍ! ብሎ የእነርሱን ሃሳብ ይዞ ሲመጣ ‹‹አረ አለቃ እንደዚህ ይሆናል እንዴ? ይሄ ነገር ምናምን›› ሲሉ ‹‹በቃ›› ብሎ በእነርሱ ሃሳብ ስር ይሆናል። ይህ ታዲያ አንዳንዴ እንደ ዘዴም ሊታይ ይችላል።

ይህ ግን ሁልግዜ እንደዚህ ነው ማለት አይደለም። ሚስቶችም አንዳንድ ግዜ የራሳቸው ሀሳብ ገዢ እንዲሆን ሲፈልጉ ምግብ ይከለክላል ወይም ሌሎች የተለያዩ ነገሮችን ያደርጋሉ። ለምን? በቃ መጨረሻ ላይ ሰውዬው ቤት ውስጥ ሰላም ለመፍጠር ብሎ የራሱን ሃሳብ ትቶ የሚስቱን ይቀበላል። ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ባህሪይ ነው። ልጆችም ያኮርፋሉ፣ ይጮሃሉ፣ ይንፈራፈራሉ ያለቅሳሉ። ያላቸውን ጉልበት ሁሉ ተጠቅመው የራሳቸውን ሃሳብ ያራምዳሉ።

በዓለማችን ላይ የተከሰቱ አብዛኛዎቹ ጦርነቶች የማን ሃሳብ ይሁን እንጂ ትክክለኛው የማን ሀሳብ ይሁን በሚል የተከሰተ አይደለም። ለምሳሌ በአሜሪካን ሀገር ምርጫ ሊካሄድ ነው። ዲሞክራቶችንና ሪፐብሊካንን ስናይና ስንሰማ ቢያንስ ሁለት እውነት ያለ ነው የሚመስለን እንጂ ለአንድ እውነት ሁለት አይነት ሰው ያለ አይመስለንም። አንዱ ሌላውን አገሩን ለማጥፋት እንድተነሳ አድርጎ ነው የሚያስበው። ፍርሃት ተኮር የሆኑ ነገሮች አሉ። አልፎም ተርፎመም ሃሳቡን ማጥፋት የማይቻል ከሆነ ደግሞ በተለያየ መንገድ የሰውዬውን ስብእና ከማጉደፍ ጀምሮ ሕይወት ለማጥፋት ይሞከራል።

ስለዚህ ሰዎች ለራሳቸው ነው ለሃሳቡ ነው እየተሟገቱ ያሉት ወደሚለው ነጥብ ስንመጣ ከኔ የተሻለ ሀሳብ ካለ ለመለወጥ ‹‹መጀመሪያውኑ ለመስማት ዝግጁ ነኝ ወይ?›› ብሎ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል። አንዳንድ ግዜ ደግሞ በጣም ውስጣችን እምቢ ካለ እስኪ አስቤበት ልምጣ ማለትም ክብር ነው። እኔ እንደሱ አላስብም ያለህን ማስረጃ ስጠኝና ላንብብና አስቤበት ልምጣ ማለት መልካም ነው። የዛን ግዜ ራሳችንን ጥለን መዋረድም ከመሰለን እንኳን እንደዚህ አላሰብኩበትም ነበር ብለን ነገሩን አድንቀን እስቲ ለማንኛውም ላስብበት ማለትን መለማመድ ያስፈልጋል። የመጣው ሃሳብ ግን ምንም ጉድለት የሌለው ከሆነ ትንሽ ትህትና ያስፈልጋል። ለሃሳቡ መገዛት ይገባል።

ባጠቃላይ አብዛኛው ግትርነትና አይነኬነት ሃሳብንና ኤጎን ከማዋሃድና በሃሳብና በማንነት መሃል ለመለየት ካለመቻል የሚመጣ ነው። ሁሌ አሸናፊ መሆን የሌላው ሀሳብ ደፍጥጦ መሄድ እንጂ የተሻለውን ሃሳብ አንስቶ ወደፊት መቀጠል ማለት አይደለም። ከማንም ይምጣ ጥሩውን ሃሳብ ካገኘን በኋላ የሁላችንም ሃሳብ ካደረግነው ሁላችንም አሸናፊ እንሆናለን። ምክንያቱም ውጤቱ የተሻለ ስለሚሆንና ለሁላችንም ስለሚበቃ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ በሃሳብ የሚያሸንፉ ሰዎች ደግሞ ብዙ ግዜ ብልህ አይደሉም። ማሸነፋቸውን ለማሳየት የተሸነፈውን ሰው ደፍጭጨው መሸነፉን አሳውቀው፣ ካልታወቀም ትንሽ ደም በደም አድርገው፣ ሁሉ ሰው አጨብጭቦላቸው የተሸነፈውን ሰው በደምብ እንደተሸነፈ የማድረግ ነገሮች ይታዩባቸዋል። ስለዚህ በሃሳብ የሚያሸንፍ ሰው ተሸናፊውን ሰው ማጣት የለበትም። ልክ የእኛ ሃሳብ እንዳሸነፈ አውቀን ያኛው ሰው መውጪያ ቀዳዳ እየፈለገ እንዳለ ካወቅን ይሄ ነገር ሊሆን ይችላል ወይስ አይችልም እስኪ እናስብበት፤ አንተም ያለከው ሀሳብ እኮ ብዙ ጥቅም አለው። ምን አልባት ሁለቱን ሃሳቦች ብለን ለሌላው ሰው የሆነ የአሸናፊ አባል እንዲሆን የሚጋብዝና ሌሎች ሰዎችን የማይጎዱ መንገዶችን መጠቀም ያስፈልጋል።

እንደዚህ አይነት ሰዎች አንድ አዲስ ሀሳብ ይዘው ሲመጡና ሃሳባቸው አሸናፊ እንደሆነ ሲያውቁ ስብሳባም አይጠብቁም። አንዳንዶች ደግሞ ሀሳቡን የሚገልፁት ስብሰባ ላይ ነው። ሁሉም ሰው አዲስ ነው። ከዛ የሚደፈጨጨውን ደፍጭጨው ከፍተኛውን ድርሻ እነርሱ የወዱ ሆነው ነው ነው መታየት የሚፈልጉት። በርካታ ሰዎች ደግሞ ሀሳቡን መጀመሪያ ለሰዎች ይዘሩትና ከዛ ሁሉም ሰው ሲገባ ያ ሃሳብ አዲስ አይደለም አብዛኛው ሰውም ያንን ሀሳብ ለመቀበል ብዙ አይቸገርም፤ በጣም ጥቂት ሰው ግን ሊቸገር ይችላል። ስለዚህ በሀሳብ ማሸነፍ ስንፈልግ ለሰዎች ደግሞ መሸነፍ መቻል አለብን።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You