በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ የለም። ይህንንም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ አስታውቀል። የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ የሁለተኛው መካከለኛ ዘመን መርሐ ግብር ምሰሶ የሆኑ አራት መሠረታዊ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን እነዚህም በሀገሪቱ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታን መፍጠር፣ የንግድ ሥራዎችን የሚያሳልጡ የሚያቃልሉና ውጤታማነትን የሚያሻሽሉ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን ማሻሻል፣ የዘርፎቹን ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን የማሳደግ እና የመንግሥት የማስፈጸም አቅምን ማጎልበትን ብሎም ማሻሻያዎቹ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን መቀነስና የንግድ ዕድሎችን በማስፋት የግል ሴክተሩ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና ማሳደግ ናቸው።
እነዚህ ምሰሶዎች የፋይናንስ እና መዋቅራዊ ማሻሻያ እርምጃዎቹ ይበልጥ አሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ጠንካራ እና ዘላቂ ወደሆነው የኢኮኖሚ አቅም ለመሸጋገር ሀገሪቷ የምታደርገው ጥረት አካል እንደመሆናቸው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አይኖርም። ለዚህም ሦስት መሠረታዊ ምክንያቶች መኖራቸውን መጥቀስ ይቻላል።
አንደኛው በአሁኑ ወቅት በገበያው ላይ ያለ ከውጪ የገባው ሸቀጥ ከማዳበሪያ፣ ነዳጅ እና ብድር በቀር በፍራንኮ ቫሉታ የገቡትን ጨምሮ አብዛኞቹ በጥቁር ገበያ የምንዛሪ ተመን ተገዝተው የገቡና ከዚህ ቀደም የዋጋ ማስተካከያ የተደረገባቸው ናቸው። በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ መሠረት ገበያ በወሰነው የዶላር ምንዛሪ ተመን ሸቀጦችን ገዝቶ ወደ ሀገር ቤት ለማስገባት ቢያንስ ወራት እንደሚፈጅና ከዚህ አንፃር እየተደረገ ያለው የዋጋ ጭማሪ ምንም ዓይነት ምክንያታዊ መሠረት የለውም።
ሁለተኛው መንግሥት የወሰደው የማሻሻያ እርምጃ ሁለት የተራራቁ ገበያዎችን የማቀራረብ ወይም ኢ-መደበኛ የሆነውን የኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ መደበኛ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲቀየር ያደረገ ሲሆን ይህም ሕገ ወጥ የነበረውን አካሄድ ወደ ሕጋዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ቀይሮታል። ከዚህ አኳያ በተለያዩ ችግሮች ወደ ሕገ-ወጥነት የገቡ ኃይሎች በሕጋዊ መንገድ የሚፈልጉትን ነገር እንዲያገኙ ሁኔታው እየተመቻቸላቸው ወደ ሌላ ሕገ ወጥ ተግባር እንዲገቡ የሚያስገድድ ምንም ምክንያት አይኖርም።
ሦስተኛው ምክንያት የተደረገው ማሻሻያ የንግዱ ማኅበረሰብ ራሱ ሲጠይቀው የኖረው ጥያቄ በመሆኑ ራሱ ለጠየቀው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሲሰጥ ሕገወጥነትን ማበረታታት ተቀባይነት የለውም። ይህንንም በመገንዘብ ወደ ሕጋዊና መደበኛ የኢኮኖሚ ሥርዓት መግባት ይኖርበታል። በነዚህ ሦስት መነሻ ምክንያቶች መንግሥት በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ አላግባብ የምርት እጥረትና ዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ላይ የጀመረውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተደረገበት ምክንያትም በመንግሥት በኩል በግልፅ ተቀምጧል። ከተቀመጠው ምክንያት አኳያም በሸቀጦች ላይ ምንም ዓይነት የዋጋ መጨመር ሰበብ ሊኖር እንደማይችል ተጠቁሟል። ይህ ሲባል ግን ነጋዴው በተለይ ስግብግቡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ሰበብ አድርጎ በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ አይጨምርም ማለት አይደለም። ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ መጨመር ከቶውንም የሚገናኝ ጉዳይ እንዳልሆነ እያወቀ ይህን ሕገ ወጥ ነጋዴው ይህን ሰበብ አድርጎ በሸቀጦች ላይ ዋጋ የማይጨምርበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
በተለይ መጪው አዲስ ዓመት እየተቃረበ ነውና የዓመት በዓል ገበያው ፍጹም ይደራል። በዚህ የግብይት ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት ለመቀበል ኪሳቸውን አራግፈው ነው በጉን፣ ዶሮውን፣ ቅርጫውን፣ እንቁላሉን፣ ቅቤውን፣ አይቡን… ወዘተ የሚገዙት። ሸቀጦቹን መግዛታቸው እንዳለ ሆኖ ታዲያ በሕገ ወጥ ነጋዴዎች ያልተገባ ዋጋ ያለመዘረፍ ዋስትናቸውና በተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጦችን የመግዛት መብታቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል።
ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ሁሌም ቢሆን ሰበብ እየፈለጉ በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ በመጨመር፣ ምርት በመደበቅና እንዳለቀ በማስነገር ሸማቹ ማኅበረሰብ ድንጋሬ ውስጥ እንዲገባና አማራጭ አጥቶ ከእነርሱ ምርቱን እንዲገዛ ነው ማድረግ የሚፈልጉት። ከዚህ በተቃራኒ ፍትሐዊ በሆነ የንግድ ውድድር የሚያምኑና ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች የሚያቀርቡ በርካታ ሕጋዊ ነጋዴዎች አሉ። እነዚህ ነጋዴዎች በሀቀኝነት ምርቶችን ለሸማቾች የሚያቀርቡና የሚገባ ትርፍ የሚያገኙ ናቸው።
ስለዚህ መጪውን አዲስ ዓመት ተከትሎ ብቻ ሳይሆን አሁንም በዚሁ ግርግር ዋጋ ለመጨመር የሚጣደፉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ መንግሥት የማያወላዳ ርምጃ መውሰድና የሸማቹን መብት ማስጠበቅ ይኖርበታል። በተለይ ይህን ለመከታተልና ለመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት አካላት ከምንግዜውም በተሻለ ሁኔታ ሥራቸውን በአግባቡ ሊያከናውኑ ይገባል። በተለይ ደግሞ የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅ የተቋቋመው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ከወትሮ በበለጠ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል።
ሸማቹ ኅብረተሰብም የንግዱ ዋነኛ ተዋናይ ነውና በሸቀጦች ላይ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች ሲደረጉ በዝምታ ማለፍ የለበትም። ይልቁንም በሕገወጥ ነጋዴዎች በኩል እነዚህን ያልተገቡ ድርጊቶች ሲመለከት ለፖሊስ አልያም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሊጠቁም ይገባል። ይህን ሲያደርግም ነው የራሱንም ሆነ የሌሎች ሸማቾችን መብት ማስከበር የሚችለው።
ሕገወጥ ነጋዴዎችም ቢሆኑ የመረጡት መንገድ አዋጭ አለመሆኑና ከትርፉ ይልቅ ኪሳራው በብዙ መንገድ የሚያመዝን መሆኑን በመገንዘብ ሕጋዊውን መስመር በመከተል ምርትና አገልግሎታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ይህም በሸማቹ ማኅበረሰብና በመንግሥት በኩል ያለውን አመኔታ ይጨምርላቸዋል። ሁለንተናዊ ድጋፍና ማበረታቻ ከመንግሥት በኩል ይኖራል ተብሎም ይታሰባል።
ከሁሉ በላይ የመገናኛ ብዙኃን በተለይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዙሪያ በየእለቱ ለማኅበረሰቡ መረጃዎች በማቅረብ በጉዳዩ ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። በየእለቱ የምርቶችን ትክክለኛ የመሸጫ ዋጋ ለአድማጭ ተመልካች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በሸቀጦች ላይ ያልተገቡ ጭማሪዎች ሲደረግም በምርመራ ማጋለጥ አለባቸው።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በቀጣይ ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን ቁልፍ ሚና አለውና ይህን ለማሳካት የሁሉም አካላት ርብርብ ወሳኝ ነው። በዚህ የርብርብ ሂደት ታዲያ አንዳንድ ግለሰቦች ባልተገባ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም። በተለይ ደግሞ ሕገወጥ ነጋዴዎች ይህን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ከዚህ አንፃር ይህን ሀገራዊ ትልቅ ሕልም እውን ለማድረግ ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት። በተለይ በሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ጠንካራ እርምጃዎች ከአሁኑ መወሰድ ይኖርባቸዋል።
ሙዘይን ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም