በመንገዳችን ላይ…

የክረምቱ አየር ‹‹መጣሁ ቀረሁ›› በሚለው ዝናብ ግራ የገባው ይመስላል። ያዝ ለቀቅ የሚያደርገው ቅዝቃዜ ድንገት ብቅ በምትለው ፈዛዛ ጸሀይ እየተዋዛ ነው። የነሐሴ ዝናብ ያረሰረሰው እርጥብ መሬት ጭቃ እንደያዘው አርፍዷል። ዕለቱ ለአብዛኞቹ ምቾት የሰጠ አይመስልም። ዳመናና ጸሀይ ቀኑን የሙጥኝ ብለው መፈራረቅ ይዘዋል።

የምሳ ሰዓት እያለፈ ነው። አብዛኞቹ የቢሮ ሰራተኞች የወጉን አድርሰው፣ ከሻይ ቡና መመለስ ጀምረዋል። ካፊያ ቢጤ ያየው መሬት መልሶ ለጸሀይዋ እጅ ሰጥቷል። ጠፈፍ ማለት የጀመረው መሬት በጭቃና ጎርፍ መልኩን እየቀየረ ነው።

መሀል አራት ኪሎ የኮሪደሩ ልማት ከዳሰሳቸው መንገዶች በአንደኛው አቅጣጫ ላይ እገኛለሁ። ይህ ቦታ ከጥቂት ጊዚያት በፊት እግረኞች የሚተላለፍበት ባዶ መሬት ነበር። ዛሬ ላይ ሜዳው ተቀይሮ በዘመናዊ ደረጃ ተቀይሯል። እሱን አለፍ ብሎ በሚገኘው ዋና መንገድ በተቀመጡ ቄንጠኛ ወንበሮች ላይ አንዳንዶች አረፍ ብለው የልባቸውን ያወጋሉ። ጋዜጣና መጽሀፍ ያነባሉ። ወጪ ወራጁን ይቃኛሉ። የእኔ እግሮች መዳረሻ ግን ከዚህ መንገድ አለፍ ብሎ ከተገነባው አዲስ ደረጃ ላይ ሆኗል። ብቻዬን አይደለሁም። የስራ ባልደረባዬ ከአጠገቤ አለች።

በድንገት ሞቅ ያለው ጨዋታችን ተቋርጦ ትኩረታችንን ከሚስብ አንድ እይታ ላይ አተኮርን። የሁለታችንም ዓይኖች በእኩል መጓዛቸው ያለምክንያት አልሆነም። ስሜታችንን የጋራ ያደረገውን እውነታ አይተን እንደዋዛ ማለፍ አለመቻላችን እንጂ።

ከአዲሱ የእግረኞች መውጫና መውረጃ ደረጃ ላይ አረፍ ያሉ አንዲት እናት። ፊታቸው በወጉ አይታይም። ወፈር ደልደል ያለው አቋማቸው በዕድሜ ጫና በውሎ ድካም መዛሉ ያስታውቃል። ፊታቸውን በአሮጌው ጥላቸው ከለል አድርገውታል። ጠጋ ብለን አስተዋልናቸው። ምቹ አልጋ ላይ እንዳለ ሰው ዕንቅልፍ ሸለብ አድርጓቸዋል።

ወጪ ወራጁ በሚተራመስበት፣ ጩኸት ግርግር በበዛበት አውራ መንገድ ላይ የሰላም ዕንቅልፍ መታሰቡ የጤና ላይሆን ይችላል። የውስጣችንን ጥርጣሬ አውጥተን ጥቂት አሰብንና ጠጋ አልናቸው። ድምጽና ኮቴ በቀላሉ የሚያነቃቸው አይመስልም። ጎናቸው ቆመን ያወጋነውን ሰምተው ደንገጥ አላሉም። ከሸለብታቸው ፈጥነው አልነቁም።

ምርጫ አልነበረንም፣ እንዳይደነግጡም፣ በዕንቅልፉ እንዳይቀጥሉም በዘዴ ቀሰቀስናቸው። እንደመባተት ብለው በድንገት ብንን አሉ። ካበጡ ዓይኖቻቸው፣ ከገረጣ ፊታቸው ጋር በግንባር ተፋጠጥን። እየተሳቀቁ በትህትና ሰላምታ አቀረቡልን። የተዘረጉ እጆቻቸው ከእጆቼ ሲገናኙ ሽክረታቸው የሞረድ ያህል ተሰማኝ።

የጨበጥኩት እጅ በእጄ ሲደርስ ማበጡ ጭምር ታውቆኛል። ወዲያው ዝቅ ብዬ አሮጌ ጫማቸውን አስተዋልኩ። አንዳች ክፍተት ያለው አይመስልም። ሁለቱም እግሮቻቸው ጢም ብለው ሞልተውተዋል። የፊታቸው ገጽታ ጤናማ አለመሆኑ ግልጽ ነው። ውሀ ያዘሉ ዓይኖቻቸው በየአፍታው በሚያረግፉት ዕንባ ጉንጮቻቸው ጠቁረዋል።

ወይዘሮዋ አሁንም አንገታቸውን እንደደፉ ናቸው። ሁኔታቸው ውስጥን ይረብሻል። ለደቂቃዎች በመሀላችን ዝምታ ሰፈነ። የደረቀው ከንፈራቸው በአፋቸው እህል ውሀ እንዳልዞረበት ያሳብቃል። ከአጠገባቸው አረፍ ብለን ጨዋታ ጀመርን። ብዙ የማያወሩት ወይዘሮ ለንግግሩም እየከበዳቸው ነው። እንደምንም የአፍታ ዝምታቸውን ሰብረው ብሶታቸውን ዘረገፉት።

ተወልደው ያደጉት ከአዲስ አበባ ውጭ ነው። ረጅሙን የሕይወት ዘመናቸውን ግን ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ አሳልፈዋል። አቅምና ጤናው በነበራቸው ግዜ ኑሮን ለመግፋት ያልሞከሩት ሥራ የለም። በየሰው ቤት እንጀራ ጋግረዋል፣ በተለያዩ የጉልበት ሥራዎች አድረዋል። ልጆች ከወለዱም በኋላ ይህ አይነቱ ሕይወት ከእሳቸው ጋር ነበር።

አሁን እኚህ ሴት ጉልበት አቅም አንሷቸዋል። ያለ አባት ያሳደጓቸው ልጆች በራሳቸው ሕይወት ኑሯቸውን እየገፉ ነው። እሳቸው እንደሚሉት ለመጀመሪያ ልጃቸው የተለየ ፍቅር አላቸው። እሱም ቢሆን እስከዛሬ ከጎናቸው ርቆ አያውቅም። አቅማቸው በደከመ ግዜ የጎደለውን እየሞላ፣ የቤት ኪራይ እየከፈለ ሲደጉማቸው ቆይቷል።

ወይዘሮዋ ድካም ያጠላበት ፊታቸው ሁሉን ይናገራል። ዕለቱን በእግራቸው ረጅም መንገድ ሲጓዙ፣ ሲኳትኑ ነበር። በየደረሱበት እያረፉ፣ ብርድ ዝናቡን አልፈውታል። ከድካማቸው በኋላ ከተቀመጡበት ስፍራ በዕንቅልፍ ሲናውዙ ቆይተዋል። እውነቱን አልተናገሩም እንጂ ምግብ ያለመቅመሳቸው ግልጽ ነው። መለስ ብለው ስለልጃቸው የጀመሩትን ወግ ቀጠሉ።

ይህ ልጅ መልካም የሚባልና፣ ጥሩ ስነምግባር የተላበሰ ነው። የእናቱን ውለታ ለአፍታም ዘንግቶ አያውቅም። አብሯቸው በነበረ ግዜ ስለውስጣቸው ችግር አስኪነግሩት አይጠብቅም። ፊታቸውን አይቶ ሁሉን ይረዳል። ወጣ ብሎ ራሱን ከቻለ ወዲህም ያሻቸውን ሲያሟላ ‹‹አይዞሽ›› ሲላቸው ነበር።

እሱ ትዳር ይዞ ከቤት ከራቀ ወዲህ ብዙ ጉዳዮች ጎድለዋል። እንደፊቱ መለስ ቀለስ ማለቱን ትቷል። እንደ ልጅ ወግ እናቱን ‹‹እንዴት አደርሽ፣ እንዴት ከረምሽ ብሏቸው አያወቅም። ይህ እውነት ውሎ ሲያድር ችግሩን ማባስ፣ ቀዳዳውን ማስፋት ያዘ። የልጅ እጅን የለመደ ጓዳ እርቃኑን ሊሆን አስገደደ። አሁን ወይዘሮዋ ካለፉት ግዚያት የበለጠ ጨንቋቸዋል። የሚወዱት ልጃቸው ፊቱን እንዳዞረባቸው፣ እንዳልፈለጋቸው እየተሰማቸው ነው። ስልክ ሲያስደውሉ አያነሳም። አለበት የተባለ ስፍራ ሲሄዱ አያገኙትም። ለምን ብለው ሲጠይቁ መልስ ለመስጠት ግዜ የለውም።

የእሱ ባህርይ መለወጥ ዱብዕዳ ቢሆንባቸውም እንዲህ የሆነው ትዳር ከያዘ ሚስት ካገባ ወዲህ ነው ይላሉ። እንዲያም ሆኖ እንደ እናት ያስቡለታል እንጂ አዝነውበት አያውቁም። ሁሌም እሱ ፍለጋ በወጡ ቁጥር እንደ ቀድሞው አቅፎ እንዲስማቸው፣ ‹‹ልጄ›› ብለው እንዲመርቁት ይፈልጋሉ።

እናት ልጃቸው እንደተወ፣ እንደራቃቸው ሲያስቡ ይቆዝማሉ። አሁን በቤት ኪራይ ዕዳ ተይዘዋል። እንኳን ለክፍያ ለዕለት ጉርስ የሚሆን ጥሪት ከእጃቸው የለም። ልጃቸውን ፍለጋ ከቤት ሲወጡ ሁሌም ተስፋን ሰንቀው ነው። ሲመለሱ ደግሞ ውስጣቸው ያዝናል። ፊታቸው ይከፋል። በድካምና በሕመም የደከመው አካላቸው ይዝላል። ይህኔ ባገኙት ጥግ አረፍ ብለው ግዜውን በሸለብታ ያሳልፉታል።

ከአራት ኪሎ ጎዳና ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ስለ ልጃቸው ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሏቸው። ወደ ቤት ሲገቡ ደግሞ ሌላው የአከራዮች ጥያቄ ይጠብቃቸዋል። ደርባባዋ እመቤት ዕለቱን ስናገኛቸው ልጃቸውን ለመፈለግ ከወጡበት ሲመለሱ ነበር።

የዛንዕለትም ፈልገው፣ አላገኙትም። አይቶ እንደተደበቃቸው፣ እንደሸሻቸው እያሰቡ ነው። ልክ እንደኛ ሁሉ የጎስቋላዋ ሴት ሁኔታ ያሳዘናቸው አንዳንድ መንገደኞች ምክንያታቸውን ሳይጠይቁ የእጃቸውን እየጣሉላቸው ያልፋሉ። ማንም ደግሞ ለዚህ ምላሽን የሚሻ አይመስልም። የወይዘሮዋ ገጽታ ያለአንዳች ንግግር ሁሉን ይመልሳል።

ተሰናብተናቸው ጥቂት እንደራቅን ዝናቡ መልሶ ማካፋት ጀመረ። የዘንድሮው ነሐሴ ቅዝቃዜው አይሏል። ሁኔታቸው ቢያሳስበኝ መለስ ብዬ ትልቋን ሴት ቃኘኋቸው። ንፋስ የሚያንገላታው አሮጌ ዣንጥላቸው እንደተዘረጋ ነው። እሳቸው ከተቀመጡበት አልተነሱም። የለበሱትን ነጠላ ወደ እግራቸው እየሳቡ እጥፍ፣ ኩርምት ብለዋል።

ነጎድጓድ አልባው ድንገቴ ዶፍ ያለማስጠንቀቂያ ማውረድ የጀመረው ከባድ ዝናብ ሁኔታዎችን ሲቀይር አልዘገየም። አሁን የወይዘሮዋን ፊት መልሼ ማየት አልቻልኩም። ቢከብድም አስቸጋሪውን እውነት ማምለጥ አይቻልም። ከዚህ በኋላ በእሳቸው ላይ የሚሆነውን መገመቱ አይቸግርም። ዝናቡ፣ ጎርፉ፣ ወጀቡ ከደረጃው ጥግ አረፍ ላሉት ትልቅ ሴት በእጅጉ ይፈትናል።

በቅርቡ በዚህ ጎዳና ያየሁት የእሳቸው እውነታ ወደሌላው የዕለት ተዕለት ክስተት ሊያሻግረኝ ግድ ብሏል። ሁሌም ቢሆን ዥንጉርጉሩ የጎዳና ላይ መልክ ብዙ ሽፍንፍን ሀቆች አሉት። ‹‹እህ ብሎ የሚያዳምጥ ቢኖር ደግሞ እያንዳንዱ በራሱ ማንነት ውስጥ ያልተገለጡ ድርሳናት ባለቤት ሆኖ መገኘቱን ያረጋግጣል።

በአራት ኪሎ ጎዳና ላይ ነኝ። በዚህ መንገድ ከማለዳው እስከ ምሽት፣ ከውድቀት እስከ ንጋት ለዓይን ጠፍቶ ስለ ማያውቀው አንድ ጎልማሳ ላወጋችሁ ነው። ይህ ሰው ከየት እንደመጣ ትክክለኛ አድራሻውን የሚያውቅ የለም። እሱና የክረምት ወቅት በእጅጉ መቆራኘታቸውን ግን በየቀኑ የሚያየው ተመልካች የሚያረጋግጠው ሀቅ ነው።

ልክ እንደ አድራሻው ሁሉ ማንነቱን በስሙ ጠርቶ ለመግባባት ይቸግራል። የሚኖረው በራሱ ዓለም በመሆኑ እሱ ስለሌላው፣ ሌላውም ስለእሱ ግድ ሳይሰጣቸው ዓመታት ተቆጥረዋል። እኔም ብሆን ዛሬን ‹‹እከሌ›› ብዬ በስም የማልጠራውን ሰው ያወኩት ከሁለት ዓመታት በፊት በዚሁ የአራት ኪሎ መንገድ ላይ ነበር።

አስታውሳለሁ ግዜው ልክ እንደ አሁኑ የክረምት ወቅት ነበር። ለሊቱን ሲዘንብ ያደረው ከባድ ዝናብ ማለዳውንም አምርሮ ቀጥሏል። አብዛኛው መንገደኛ አየሩን በሚያሸንፍለት አለባበስ ተጀቡኖ እየተራመደ ነው። እንዲያም ሆኖ በቅዝቃዜው ማየል ፊቱን የጨፈገገው በርክቷል። ከሰርቪስ ወርጄ ወደ መስሪያ ቤቴ በእግሬ መጓዝ ጀምሬያለሁ። ቢሮዬ ለመድረስ ጥቂት እርምጃዎች እንደቀሩኝ ግን ዓይኖቼ እንደዋዛ ከማላልፈው አንድ እውነታ ላይ ተሰክተው ቀሩ።

በመንገዴ፡- ከዋናው የአስፓልት ጠርዝ ኩርምት ብሎ የተኛ አንድ ሰው ይታየኛል። በቅዝቃዜው መላ ሰውነቱ እየተንዘፈዘፈ ነው። እንደቀልድ ከላዩ ጣል ያደረጋት የነጠላ እራፊ በሰውነቱ ተጣብቃለች። ሌቱን ሙሉ ሲዘንብ ያደረው ሀይለኛ ዝናብ እንዳላለፈው ገባኝ።

ይህን ሳስብ ውስጤ ልገልፀው በማይቻለኝ ሀይለኛ ቅዝቃዜ ተዘፈቀ። በሰውየው ሁኔታ እንዳዘንኩ ለደቂቃዎች ካጠገቡ ቆምኩኝ። እኔን ያዩ ጥቂት ሰዎች ለአፍታ አየት እያደረጉት ከንፈራቸውን መጠው ያልፋሉ። እኔም ብሆን ከዚህ የዘለለ የፈየድኩት የለም። ስለማንነቱ የአካባቢውን ሊስትሮዎች ጠየቅሁ። ዓይምሮውን እንደሚያመው፣ ሰዎችን መቅረብ እንደማይወድና ውሎ አዳሩ ከዚሁ ጎዳና ላይ መሆኑን አስረዱኝ። ከነሀዘኔ ወደ ቢሮ ገባሁ።

ማግስቱን ለእሱ ይሆናሉ፣ ብርዱን ይከላከላሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ልብሶች ይዤ ትናንት ካየሁት ምስኪን ሰው አጠገብ ደረስኩ። ጥቅልል ብሎ ተኝቷል። ዝናብ ባይሆንም ቅዝቃዜው እንዳለ ነው። ጠጋ ብዬ እንዳልቀሰቅሰው ስለሱ የሰማሁት እውነታ አስፈራኝ። የዓይምሮ ሕመምተኛ መሆኑና ሰዎችን እንደማይወድ ተነግሮኛል።

በዚህ ሰበብ ግን ዝም አላልኩም። ስለእሱ ሌሎችን ደግሜ ጠየኩ። ‹‹አረ! ችግር የለም›› ሲሉ ከተኛበት ቀሰቀሱት። አልፈራሁትም። የእጆቼን ሥጦታ ከእጆቹ አኖርኩለት። በአክብሮትና በፈገግታ ተቀብሎ ከልብ አመሰገነኝ። ባየሁት ነገር ተገርሜ በሰ ላምታ ተሰናበትኩት።

በማግስቱ በዛው መንገድ ሳልፍ ትናንት የሰጠሁትን ልብሶች ደራርቦ ለብሷቸዋል። ገጽታው ጥሩ ሆኗል። ገና እንዳየኝ ከመቀመጫው ብድግ ብሎ ሰላም አለኝ። ሰላም አልኩት። ከዛን በኋላ ክረምቱ አልፎ በጋው እስኪጋመስ እነዛን ልብሶች ከአካሉ ላይ አላጣኋቸውም።

ውሎ ሲያድር ቀስ በቀስ ተግባባን። ሳገኘው ብዙም ባይሆን የምችለውን ኪሱ አደርግለታለሁ። በምስጋና ተቀብሎ የልቡን ያወጋኛል። ሰዎች እንደሚመቀኙት፣ በእሱ መጠቀም እንደሚሹ እሱ ደግሞ በትዕግስት ማለፍ ልምዱ እንደሆነ ይነግረኛል። ግዜ ሰጥቼ አደምጠዋለሁ።

አንዳንዴ ብዙ ወረቀቶች ይዞ ይሞነጫጭራል። አንዳንዴ ደግሞ ረዘም ያሉ ጽሁፎችን እንደ ማስታወሻ ይከትባል። የእጅ ጽሁፉ ድንቅ የሚባል ነው። አንድ ሰሞን የሚከርምባቸውን ጽሁፎች የት እንደሚያደርሳቸው አይታወቅም። እነሱን ይተውና በስዕል ስራዎች ይጠመዳል። ከቀናት በኋላ ደግሞ በእጆቹ ሌሎች ነገሮች ይተካሉ። እነሱን እንደ ሙዚቃ መሳሪያዎች ተጠቅሞ ይዘፍናል፣ ያንጎራጉራል።

እሱ ሁሌም አለባበሱ የተለየ ነው። ዛሬ በጥሩ ልብስ ከታየ ማግስቱን በነጠላና ቀሚስ ሊገለጥ ይችላል። ጫማዎቹ፣ ልዩ ናቸው። አንዳንዴ ጥሩ ይዞታ ያላቸው የቆዳ መጫሚያዎችን ያደርጋል። አንዳንዴ ደግሞ መልካቸው የተለያየና ጥምረታቸው የተቃረኑትን ይመርጣል።

ይህ ሰው አልፎ አልፎ ድምጹን ከፍ አድርጎ ይቀበጣጥራል፣ ያሻውን ይናገራል። ንግግሩ ግን በአብዛኛው ከራሱ ጋር ብቻ ነው። በዚህ ግዜ የሚያጨሰው ሲጋራ ደግሞ ሽታው ጠንከር ያለና ብዘዎችን የሚረብሽ ሆኖ ይተናል። እንዲህ ባለ ስሜት ውስጥ ሲሆን ከአንደበቱ አለፍ ብሎ ሌሎችን ሊሳደብና ሊያስቀይም ይችላል።

በየቀኑ በተለያዩ አልባሳት የሚታየው የአራት ኪሎው ሰው በአንድ ወቅት ችግሩን የተረዱ አካላት ተቀምጦ በሚውልበት አካባቢ የቆርቆሮ ቤት ሰሩለት። ለስሙ ‹‹ቤት›› ያልኳችሁ ይህ ማረፊያ በአንድ ሰፍራ ተቀምጦ መንቀሳቀስ እንዲችል ሆኖ የተዘጋጀ ነው። ይህ ሰው የትም ሲንከራተት ውሎ ማምሻውን ለዕንቅልፍ ጎኑን ያሳርፍበታል። ዝናብ ውርጩን፣ ያልፍበታል።

እንዲህ ከሆነ ጥቂት ዓመታት በኋላ በአራት ኪሎና አካባቢው የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ተጀመረ። ይህ ልማት እስከዛሬ በስፍራው የቆዩ አላስፈላጊ የሚባሉ እይታዎችን የሚያስወግድ ነው። አጋጣሚው ታዲያ የዚህን ሰው ደሳሳ ቤት አፈራርሶ ለመጣል አልዘገየም።

አንድ ቀን የትም ተንከራቶ ወደ ማረፊያው ሲመለስ ጎጆውን ፈልጎ አጣት። ምርጫ አልነበረውም። እንዲህ በሆነ ማግስት ተመልሶ ከጎዳና ጥግ ወደቀ። ቀድሞ የሚያውቁት አንዳንዶች ከሕንጻቸው በረንዳ ላይ እንዲተኛ ፈቀዱለት። ደስ እያለው ሌቱን እዛው ማሳለፍ ጀመረ።

የዘንድሮው ከባድ ክረምትና ይህ ሰው ዳግም ተገናኝተዋል። አሁን እንደትናንቱ ከለላ የሚሆን ጣራና ግድግዳ የለውም። ብርድ፣ ዝናቡን፣ ጎርፍ ጭቃውን ሊያስተናግድ ግድ ይለዋል።

ከሰሞኑ ቀናት በአንዱ ማለዳ ከዚህ ሰው ጋር ድንገት ተገናኘን። ፊቱ ተጎሳቁሏል ለብሶት የከረመው ልብስ ቁሽሽ ብሏል። የዕለቱ አለባበስ ለየት አለብኝ። በወጉ ጥቁር ሻሽ አስሮ ደማቅ የሴት ሻርፕ ደርቦበታል። አፍንጫው ከወትሮው ሰልከክ ብሎ መታየቱ ጥሩ ሴት ወይዘሮ አስመስሎታል። ሳላስበው ፈገግ አልኩ።

በእጁ የያዘውን ቀጭን ዱላ እያወዘወዘ አጠገቤ ከመድረሱ ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጠኝ። በአንድ እጁ ስለያዘው ቋጠሮ ጠየኩት። በረንዳ ላይ የሚያድርበትን ጓዝ ይዞት እንደሚዞር ነገረኝ።

ጥቂት ደቂቃዎችን ቆመን አወጋን። ጨዋታው የተለመደ አይነት ነበር። ብዙዎች በእሱ እንደሚቀኑ፣ እንደሚመቀኙ ዘረዘረልኝ። ቤተሰቦቹ አሜሪካ መኖራቸውን፣ አብዛኞቹ ዕውቀታቸው ስለሚፈለግ ጠላቶቻቸው በጸጉራቸው ልክ እንደሆኑ አንድ በአንድ ነገረኝ። ግዜ ሰጥቼ በትኩረት አዳመጥኩት።?

እየሰማሁት መሆኑን ሲረዳ የክረምቱን ክብደት እየጠቀሰ የውስጥ ብሶቱን አካፈለኝ። ልቤ እያዘነ፣ እየተረበሸ በአንክሮ ሰማሁት። ግን ይህ ሰው ማነው ? የኋላ ታሪኩስ ምንድነው ተሰናብቶኝ እስኪሄድ ምላሽ ያለገኘሁለት ጥያቄ ነበር።

በነዚህ ባልተነበቡ የሕይወት ገጾች ውስጥ ያሉ ባለ ታሪኮች በራሳቸው ሚስጥራት ቢጠፈሩም ከጀርባቸው አንድ እውነት አለ። ይህን እውነት ቆም ብሎ የሚሰማቸው ቢኖር ችግራቸው ይቀላል። ስለነ እሱ ሌላው ቢያስብ አስከፊው ሕይወት ይለወጣል። እኛ ግን በየቀኑ ከነ ጉዳታቸው ስለሚታዩን ወገኖች ግድ ያለን አይመስልም። ሁሌም በመንገዳችን እያየናቸው እናልፋለን። እነሱም ከነድብቅ ታሪካቸው እንደዋዛ ከዚህች ምድር ያልፋሉ። አዎ! እንደዋዛ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You