የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ለማሻሻል

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ታሪክ አጭር እድሜ ያስቆጠረ ነው። በዘርፉ የሰለጠኑ የሕክምና ባለሞያዎች ቁጥርም አሁን ካለው የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን አይደለም። በአሁኑ ግዜ በኢትዮጵያ 627 የአጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሆኖም የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው 1 የአጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪም ለ10 ሺ ሕሙማን ስታንዳርድ አኳያ ሲታይ ቁጥሩ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በዓለም ጤና ድርጅት ስታንዳርድ መሰረት አሁን ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 12 ሺ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች ያስፈልጋል።

ከዘመናዊ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ጎን ለጎን በኢትዮጵያ በባሕላዊ መንገድ የሚከናወነው ሕክምና ከዘመናዊው የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በገጠር አካባቢ የሚኖረው ማኅበረሰብም ባሕላዊ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና አገልግሎትን ነው የሚጠቀመው። ምንም እንኳን የባሕላዊ አጥንት ሕክምና ዘመናዊውን ሕክምና ከመደገፍ አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ቢነገርም ከባሕላዊ የአጥንት ሕክምና ጋር ተያይዞ ውስብስብ የጤና ችግሮች እየጨመሩ መጥተዋል። ይህ ግን በምን ምክንያት እንደሆነ አስካሁን አልታወቀም። ይህን ምክንያት ለማወቅ ነው ቦሳድ/Bone Setting Associated Disability/ የተሰኘው ሀገር አቀፍ የጥናት ቡድን የሶስት ዓመት ጥናት ያካሄደው።

ዶክተር ኤፍሬም ገብርሃና በሞያቸው የኦርቶፔዲክ እና ትራውማ ቀዶ ሀኪም እንዲሁም የላቀ ትራውማ እና አርትሮፕላስቲ ሰብ እስፔሻሊስት ሲሆኑ በኢትዮጵያ አጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ማሕበር ውስጥ ደግሞ ፕሬዚዳንት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ከአደጋ ጋር በተያያዘ ሰዎች በርካታ የጎንዮሽ ጉዳት ያስተናግዳሉ። እነዚህ ጉዳቶች ምን እንደሚመስሉና እንዴትስ መከላከል እንደሚቻል ግን ከአሁን ቀደም የተሰሩ ዘርዘር ያሉ ጥናቶች አልነበሩም። ለዛም ነው ቦሳድ/Bone Setting Associated Disability/ በተሰኘው ሀገር አቀፍ የጥናትና የምርምር ቡድን አማካኝነት በኢትዮጵያ በአጥንትና መገጣጣጠሚያ ጉዳቶች ዙሪያ የሶስት ዓመት ጥናት የተደረገው።

የጥናቱ ዋነኛ ትኩረት በኢትዮጵያ ከሚከሰቱ የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳቶች ጋር በተያያዘ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ግንባር ቀደም የሕክምና አማራጭ ከሚወሰዱ የባሕል ሕክምና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ውስብስብ የጤና ችግሮችን ለማጥናት ነው። ጥናቱም የተለያዩ ዘዴዎችን /quantitative and qualita­tive/ በመጠቀም ችግሩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት ሞክሯል። በዋናነት አሃዛዊ ጥናቱ ከተለያየ አቅጣጫ መገንዘብ ያስችል ዘንድ በጤና ተቋማት ከሕፃናትና አዋቂ ታካሚዎች እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ውስጥ ካሉ ታካሚዎች መረጃ ሰብስቧል።

ለጥናቱ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎች በጤና ተቋማት ውስጥ ከ1 ሺ 830 ታካሚዎችና በማኅበረሰቡ ውስጥ ከ860 ታካሚዎች የተወሰደ ሲሆን፣ በqualitative ጥናቱ ላይ ደግሞ መረጃዎች ከጤና ባለሞያዎች ማለትም ነርሶች፣ የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሺያሊስት ሀኪሞች፣ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና በጤናው መስክ ካሉ አመራሮች ተወስዷል። በተጨማሪም ከተለያዩ ማኅበራት፣ ባሕላዊ ሕክምና ከሚሰጡ ባለሞያዎች፣ በባሕላዊ ሕክምና ታክመው ድነናል ከሚሉ ታካሚዎችና በዚህ የባሕል ሕክምና የተለያየ ውስብስብ የጤና ችግር ደርሶብናል ከሚሉ ታካሚዎች መረጃ ተሰብስቧል። በጥቅሉ ከ3 ሺ በላይ ባለድርሻ አካላት መረጃ በመስጠት በጥናቱ ተሳትፈዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፣ የቦሳድ/BOSAD/ ጥናት ቡድን በኢትዮጵያ ሊመሰረት የቻለው በሶስት መሰረታዊ ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያውና ዋነኛው በኢትዮጵያ የዘመናዊ አጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና መስፋፋትና በባሕላዊ የአጥንት ሕክምና ምክንያት የሚመጣው ውስብስብ የጤና ችግር መካከል የማይጠበቅ ተቃርኗዊ ግንኙነት መኖር ነው። የኢትዮጵያ አጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ታሪክ ሲታይ ከአስር ዓመት በፊት የስፔሺያሊስት ትምህርት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ የነበረ ሲሆን የነበሩትም ሀኪሞች በቁጥር ከ70 የማይልቁ ነበሩ። ይሁን እንጂ በአሁኑ ግዜ 627 የሚሆኑ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች ያሉ ሲሆን ይህም 352 ስፔሺያሊስት ሀኪሞችንና 275 በመማር ላይ የሚገኙ ሬዚደንት ሀኪሞችን ያጠቃልላል።

የአጥንትና መገጣጠሚያ ህክምና ትምህርትም በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በ10 የተለያዩ የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሺያሊቲ ማስተማሪያ ተቋማት ውስጥ እየተሰጠ ይገኛል። በተመሳሳይ ይህ ዘመናዊ የአጥንት ሕክምና ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ በብዛት ይሰጥ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ክልሎች ይሰጣል። በነዚህ አስር ዓመታት ውስጥ የአጥንት ሕክምና እንደመስፋፋቱ ከባህላዊ አጥንት ሕክምና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ውስብስብ የጤና ችግሮች መቀነስ ሲገባቸው እየጨመሩ መጥተዋል። ይህ ተቃርኖ የማይጠበቅ በመሆኑ ጥናቱን ለማካሄድ አንዱ ምክንያት ሆኗል።

ሁለተኛው ምክንያት በተመሳሳይ ርእስ ላይ የተሰሩ በደምብ የታቀዱና የተነደፉ ጥናቶች እጥረት መኖር ነው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ውስጥ በተመሳሳይ ርዕስ ላይ ጥናቶች ሲታዩ አብዛኛዎቹ በአንድ ተቋም ላይ የተሰሩና መረጃዎቻቸው ወደኋላ ተወስደው የተከናወኑ ናቸው። ከዚህ አንፃር ጥናቱን በታቀደና ብዙ ቦታዎችንና የመረጃ አሰባሰብን ባማከለ መልኩ ተሰርቷል።

ጥናቱን ለማካሄድ የተፈለገበት ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ በጤና ተቋማት ውስጥ ከባሕላዊ ሕክምና ጋር ተያይዘው በየግዜው የሚመጡ አስቀድሞ መከላከል የሚቻሉ የተለያዩ ከፍተኛ ውስብስብ የጤና ችግሮች መታየታቸው ነው። በጤና ተቋማት ውስጥ በየእለቱ በርካታ ታካሚዎች ቀላል የሚባል የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ወደ ባሕላዊ የአጥንት ሕክምና በመሄድ ለተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ተጋልጠው ሲመጡ ማየት የተለመደ ነው። እነዚህ ውስብስብ የጤና ችግሮች መታከም ከሚችሉ እስከ ቋሚ የአካል ጉዳት አልፎ ተርፎም እስከ ሞት ሲያደርሱ ይስተዋላል። የጎንዮሽ የጤና እክሎቹ ታካሚው ምንም አይነት ሕክምና ሳያገኝ እቤቱ ቢቆይ እንኳን ላይከሰቱ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ለማወቅ ጥናቱ ተካሂዷል።

ፕሬዚዳንቱ እንደሚገልፁት፣ የጥናቱ ዋና ዓላማ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሆነ፣ የኢኮኖሚ አቅምን ያገናዘበና ደህንነቱ የተረጋገጠ ዘመናዊ የአጥንትና መገጣጠሚያ አካላት ሕክምና መስጠት እንዲሁም በገጠር ለሚኖሩ ሕፃናት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ነው። ይህን ዓላማ ለማሳካት ጥናቱ የታካሚዎችን የስነ ሕዝብ አወቃቀር፣ በብዛት ወደ ባሕላዊ ሕክምና የሚሄዱ የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳት አይነቶችን በመለየት፣ የችግሩን መስፋፋትና ከተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ጀርባ ያሉ አጋላጭ ሁኔታዎችን በሰፊው ለማጤን ተሞክሯል።

በጤና ተቋም ውስጥ የተሰራው ጥናት ከስድስት የተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ስምንት ሆስፒታሎችን ያካተተ ሲሆን እነዚህም ሐዋሳ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ዋቸሞ፣ ሐሮማያ፣ አሰላና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። ከ100 በላይ የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሺያሊስት ሀኪሞች እንዲሁም ሬዚደንት ሀኪሞችም በጥናቱ ተሳትፈዋል። የኢትዮጵያ አጥንትና መገጣጠሚያ ሀኪሞች ማሕበር ደግሞ የዚህ ጥናት ዋና መሪ ሆኖ ሰርቷል። ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ማሕበር፣ የክልል ጤናና ትምህርት ቢሮዎችም የጥናቱ ተባባሪ አካላት ነበሩ።

ለሶስት ዓመታት በተካሄደው ጥናት ሕፃናትን በሚመለከት ከጤና ተቋም በተሰበሰበ የመረጃ ውጤት መሰረት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ 460 ሕፃናት በዚህ ጥናት ተካተው ሕፃናቱ ከአዋቂዎች በበለጠ ከፍተኛ ለሆኑ ውስብስብ ጉዳቶች ተጋላጭ እንደሆኑ ተረጋግጧል። በሕፃናቶቹ ላይ ከ76 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የአደጋ አይነት የሚይዘው የመውደቅ አደጋ ሲሆን በአንፃሩ በአዋቂዎች ላይ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የመንገድ ትራፊክ አደጋ መሆኑን ጥናቱ አሳይቷል። በሕፃናት ላይ ለከፍተኛ ውስብስብ የጤና ችግር አጋላጭ ከሆኑ ተደጋጋሚ ምክንያቶች መካከል በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሕፃናት 6 ነጥብ 5 እጥፍ፣ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ማኅበረሰቦች የተወለዱ ሕፃናት 3 እጥፍ፣ ክፍት የሆነ ስብራት ያላቸው ሕፃናት 6 እጥፍ እና ወደ ባሕላዊ ሕክምና ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ወደ ጤና ተቋም ደርሰው የተመለሱ ሕፃናት 4 እጥፍ የበለጠ ተጠቂዎች መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል።

አዋቂዎችን በተመለከተ በተሰበሰበ መረጃ ውጤት መሰረት 783 አዋቂዎች በጥናቱ ተካተው ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ታካሚዎች ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩና አብዛኛዎች እጅግ በጣም ቀላል የሚባል ጉዳት አይነት የደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል። ባጠቃላይ ታካሚዎቹ ወደጤና ተቋማት ሲመጡ የተመዘገቡ ውስብስብ የጤና ችግሮች 77 ከመቶ ሲሆን 26 ነጥብ 7 ከመቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ባሕላዊ ሕክምና ቦታዎች ከመሄዳቸው በፊት የጤና ተቋማት ደርሰው የተመለሱ መሆናቸው በጥናቱ ተረጋግጧል። ለውስብስብ የጤና ችግር መከሰት ምክንያት የሚሆኑት ሁለት ዋና ዋና መንስኤዎች ተብለው በጥናቱ የተለዩት በገጠር አካባቢ መኖር 2 ነጥብ 4 እጥፍ እና ከድህነት ወለል በታች መኖር 4 ነጥብ 3 እጥፍ ናቸው።

በማኅበረሰብ ውስጥ የተሰበሰበ መረጃ ጥናት ውጤትም በጥናቱ ይፋ የተደረገ ሲሆን በሲዳማ ክልል የባሕላዊ ሕክምናና ውስብስብ የጤና ችግር ከፍተኛ በመሆኑ በማኅበረሰብ አቀፍ ጥናቱ ላይ የገጠርና የከተማን በማካተት ለማጥናት ተሞክሯል። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ አደጋው የደረሰባቸው 860 ታካሚዎች ቃላ መጠይቅ ተደርጎላቸው 68 ከመቶ የሚሆኑ ውስብስብ የጤና ችግሮች ተመዝግበዋል። ውስብስብ ለሆኑ የጤና ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሚያደርጉ ምክንያቶች ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ 3 እጥፍ፣ መሰረታዊ ትምህርት አለመማር 2 እጥፍ እና ባሕላዊ ሕክምና 4 እጥፍ መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል። በጥቅሉ በገጠር የሚኖሩ ሰዎች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና ባሕላዊ ሕክምና የሚታከሙ ሰዎች ለከፍተኛና ውስብስብ ለሆኑ የጤና ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸው በጥናቱ ተረጋግጧል።

ፕሬዚዳንቱ እንደሚያብራሩት በነዚህ የጥናት ውጤቶች መሰረት ቀጣይ ለሚኖሩ የትግበራ እንቅስቃሴዎች የሚጠቅሙ የተለያዩ ማስረጃዎች የተዋቀሩ ሲሆን እስካሁንም ለሕትመት የሚበቁ አምስት የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ተዘጋጅተዋል። የጥናቱን ውጤቶች ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለማድረስ ስራ እየተሰራ ሲሆን ከነዚህም መካከል ማኅበረሰቡ፣ የተለያዩ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የተለያዩ የጤና ባለሞያዎች ይገኙበታል።

ለንባብ የሚሆኑ የተለያዩ ፅሁፎችን በአጭር ጥራዝ መተግበሪያ ተዘጋጅተው ለአንባቢያን እየተሰራጩ ይገኛሉ። ለስልጠና የሚሆኑ ሞጁሎችም ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ ውለዋል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ለስርጭት የሚውሉ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ፅሁፎች ተዘጋጅተው እየተሰራጩ ይገኛሉ። ዋና ዋና ለትግበራ የሚሆኑ ተለይተው ለትግበራው እንቅስቃሴ የሚሆኑ መመሪያዎችም ተዘጋጅተዋል።

በክልሎች ለሚገኙ የጤና ባለሞያዎችና የትምህርት ቤት ማኅበረሰቦች ስልጠናዎችም እየተሰጡ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሚገኙ ተደማጭና አርአያ ለሆኑ ሰዎች እንዲሁም ባሕላዊ ሕክምና ለሚሰጡ ባለሞያዎች የግንዛቤ ማስጨበጪያና የማነቃቂያ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። የስብራት አደጋ ለደረሰበት ግለሰብ እንዴት የሕክምና እርዳታ መስጠት እንደሚቻል የሚያሳዩ የተለያዩ አስተማሪ ቪዲዮዎችና ከታካሚዎች የሚቀርብ የምስክርነት ማስተማሪያ ፊልም ለመስራት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ግንባር ቀደም ተቋማት መካከል አንዱ ከሆነው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረገው ስምምነት የቦሳድ/BOSAD/ አጭር የንባብ ጥራዝ /booklet/ የማባዛት ስራና ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች በስፋት ተደራሽ እንዲሆን የማድረግ ስራም እየተከናወነም ይገኛል።

በጥቅሉ ከባሕላዊ ሕክምና ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ መከላከል የሚቻሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች እየተስተዋሉ ስለሆነ ለሁሉም ታካሚዎች ተገቢና የተሟላ ሕክምና በመስጠት ሊከሰት የሚችል የአካል መጉደልና ሞትን ለመቀነስ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል። የባሕላዊ ሕክምና አሰራር ሂደትን በማዘመን ተገቢውን ሕክምና ለታካሚዎች መስጠትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ማሻሻል እንደሚገባ ጥናቱ ጠቁሟል።

ሁሉም የተጎዳ አካልን አጥብቆ ባለማሰርና በተደጋጋሚ ባለማሸት ለአካልም ሆነ ለሕይወት አስጊ የሆነን ውስብስብ የጤና ችግር መከላከል እንደሚገባ ጥናቱ አሳይቷል። የሕፃናት ስብራቶች፣ ክፍት የሆኑ (ቁስል ያላቸው) ስብራቶችና መገጣጠሚያ አካባቢ የተከሰቱ ስብራቶች ለከፍተኛ ውስብስብ የጤና ችግሮች ስለሚያጋልጡ ወደ ዘመናዊ ሕክምና ተቋማት ተልከው ተገቢውን ምርመራና ሕክምና ማግኘት እንደሚገባቸውም አመላክቷል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም

Recommended For You