የገጠር ልጅ ነች። በለምለሙ መስክ ስትቦርቅ ያደገች ጉብል። ዕድሜዋ ሲፈቅድ እንደእኩዮቿ ከብቶች እያገደች ከአረም ጉልጓሎው ውላለች። እንጨቱን ሰብራለች ኩበት ከምራለች። የእሷ የማንነት ድር ከሳር ጎጆዋ ይገመዳል። በዚህ ጣራ ስር ለፍቶ አዳሪ ቤተሰቦች አሉ። እርሻን ተስፋ አድርገው በሬን ከመሬት ያመኑ። እነሱ ከዓመት ዓመት ጥረው በላባቸው ወዝ ልጆች ያሳድጋሉ። ንግስቴ አምባቸውም በዚህ ጎጆ ከሁለት ታላላቆቿ ጋር በፍቅር ኖራለች።
ንግስቴ ስለከተማ ህይወት የሰማችው ገና ነፍስ ስታውቅ ነበር። ከተሜነት ለእሷ ውበት ነው፣ከተማ ለእሷ ዕውቀት ነው። የመሀል አገር ሰው ልብሱ የፀዳ ንግግሩ ያማረ ነው ብላ ታምናለች። የልጅነት አዕምሮዋ ውበትና ዕውቀት በእኩል ሲቀበል ኖሯል። ጥቂት ቆይቶ ግን ውስጠቷ ወደ ዕውቀቱ አመዘነ። በመማር መለወጥ እንደሚቻል ገባት። ይህን ስታውቅ ቤቶቿን አጥብቃ ወተወተች። ወላጆቿ ቢያንገራግሩም አላሳፈሯትም። ደብተር አስይዘው ፊደል ትቆጥር ዘንድ ትምህርት ቤት ሰደዷት።
ከትምህርት መዋል ስትጀምር ፊደልን በወጉ ለየች፣ ስሌትን አውቃ ቀምራ ማንበብ መጻፍ ቻለች። ይኼኔ ውስጧ ጥንካሬ ተሞላ፣ ከተሜነት ተምሮ በመለወጥ መሆኑ ገባት። ንግስቴ ትምህርት ቤት ውላ ዕውቀት መሸመቷ አስደስቷታል። ይህ ብቻ ግን የወትሮ ግዴታዋን አላስቀረውም። ለትምህርት ከምትርቅበት አዳጋች ጉዞ በኋላ የቤቱ ሥራ ተከምሮ ይቆያታል። እሱን ለመሙላት ደፋ ቀናው ግዴታዋ ነው።
ለጥናት ደብተሯን የምታነሳው ምሽት በኩራዝ ብርሃን ሆነ። እሱም ፈተና ካልደረሰ በወጉ ላይሳካ ይችላል። የህመምተኛው አባቷ ከአልጋ መዋል ደግሞ ለመላው ቤተሰብ ጫናውን አብዝቶባታል። ይህን የምታውቀው ተማሪ ሸክሙን ከማቃለል ሌላ ምርጫ የላትም።
የልጅነት ዕድሜዋ በጨዋታ የተዋዛ ነበር።
ስምንተኛን ክፍል ስታልፍ ግን ይህ ሁሉ ቀርቶ በዕውቀት መብሰል እንዳለ ገባት። በንግስቴ መንደር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የለም። ቀጣዩን ደረጃ ለመማርም ወደ ሌላ ስፍራ መሄድ ግድ ይላል። አሁን ንግስቴ ከቤተሰብ ተነጥላ ከአካባቢው ልትርቅ ነው። አይቀሬው ጉዞ ሲቃረብ ስንቋ ተዘጋጀ። እሷ ታላቅ ዓላማ አላት። ሩቅ አስባ ቅርብ አታድርም። እናም ቆራጥ መሆን አለባት።
ንግስቴ ተወልዳ ያደገችባትን «ጠዳ» ትታ ወደ ጎንደር ዙሪያ ተጓዘች አዘዞ ከተመች። ይኼኔ ከቤት ርቆ የማያውቀው ልቧ ክፉኛ ተረበሸ። ከወላጆች መለየትና ራስን በራስ ማሳደር ከባድ ሆኖ ታያት። ከስፍራው ደርሳ ቤት ስትከራይና ትምህርት ስትጀምር ግን ይህ ሁሉ ስሜት ትቷት ነጎደ። ከዚህ በኋላ እንደልጅነት መቦረቅ የለም። እንደ ቀድሞውም የጓዳ ሥራ አይቆያትም። የኩራዙም መብራት በአምፑል ብርሃን ተተክቷል።
የዘጠነኛ ክፍል ትምህርት ሲጀመር ጠነከረ። አሁን ነገን የተሻለ ለማድረግ ሌት ተቀን ማጥናት ግድ ይላል። ከዚህ ወዲያ ዕንቅልፍና ስንፍና ቦታ አይኖራቸውም። ይህን ያወቀችው ንግስቴ አብራት ካለችው ባልንጀራዋ ጋር መትጋቷን ቀጠለች። ዛሬን ከወላጆቿ ዘንድ አይደለችምና ለቀለብ የሚሆን ወጪ ያሻታል። ለቤት ኪራይ ለቅባትና ለሌላም ከእጇ ገቢ ማኖር ግድ ይላታል።
ሳምንቱን በትምህርት አሳልፋ ቅዳሜና ዕሁድ ወደ ገጠር ስትወርድ ልክ እንደትላንቱ ጉልበቷን ለሥራ ትከፍላለች። ይህን ካላደረገች ወላጆቿ ይከፋቸዋል። እሷም ብትሆን ለቀለብ ለስንቋ ጥሪት ታጣለች። የንግስቴ የሦስት ዓመታት ምልልስ በጥንካሬ ተዋዝቶ ቀጠለ። የጠዳና የአዘዞ መንገዶችም የተማሪዋን ብርታት ፈትነው ለመልካም ውጤት አደረሷት።
አሁን ንግስቴ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤቷ ሚዛን ደፍቷል። የዓመታት ልፋቷ መቋጫ የሚወሰነው ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። እሷ ይህን ከተማ በዝና እንጂ በዓይኗ አታውቀውም። ስለአገሬው የተነገራት ደግሞ ውስጧን በእጅጉ አደናግሮታል። ነዋሪው በአለባበሱ፣ በአነጋገሩ ከሌሎች ይለያል። በአኗኗርና በአረማመዱም ዘመናዊ ነው ተብላለች።
ተማሪዋ መንገደኛ ጉዞዋን ከመጀመሯ በፊት ደጋግማ አሰበች። መክረሚያዋ ሸገር መሆኑ ካልቀረ ማንነቷን መቀየር ይኖርባታል። በተለይ በአለባበሷ የገጠር ልጅ ልትመስል አይገባም። በንግግሯም ቢሆን እንዲሁ። ከራሷ ጋር በውል የተስማማችው ጉብል በውሳኔዋ ጸንታ ለቤተሰቦቿ ጥያቄ አቀረበች። «ከዚህ በኋላ የከተማ ልጅ ሆኛለሁ፥ ሱሪና አጫጭር ቀሚሶች ይገዙልኝ» ስትል።
ወላጆቿ ባቀረበችው ሃሳብ ተደነቁ ፣ ተገረሙም። ያለችውን ለማድረግ ግን አልተቃወሙም። አቅምና ፍላጎቱ ባይኖራቸውም እሷን ላለማስከፋት የልቧን መሻት ፈጸሙላት። ንግስቴም ምርጫዋ የሆኑትን አዳዲስ ልብሶች ሸክፋ አዲስ ህይወት ከትምህርት ጋር ልትቀበል ወደ አዲስ አበባ ገሰገሰች።
አዲስ አበባ ደርሳ ወደዩኒቨርሲቲው ስትዘልቅ የገመተችውን ሁሉ አላገኘችም። የተባለው እንዳለ ሆኖ አለባበስ ሁሉ ሱሪ ብቻ አልነበረም። ያም ሆኖ ግን አካባቢዋን ለመመሳሰል ስትጣጠር ከረመች። ለጥቂት ጊዜያት ሱሪዎቿን እየቀያየረች ለበሰች። ዘነጠችም፣ ትምህርቱ በርትቶ ጊዜው ሲገፋ ግን ሙከራዋ ሁሉ አስጠላት። የቅርብ ጓደኞቿ እሷን ያለመምሰላቸው እውነታም ወደቀድሞው ማንነቷ ሊመልሳት ግድ ሆነ።
በዩኒቨርሲቲ በአግባቡ የሚያግዝ ከሌለ ህይወት በእጅጉ ይከብዳል። ንግስቴም ብትሆን ከዚህ ፈተና አላመለጠችም። በምትማርበት የፍልስፍና መስክ ውጤታማ ብትሆንም ለዕለት ፍላጎቶቿ እጅ ሲያጥራት ቆይቷል። ቤተሰቦቿ አቅሙ የላቸውምና ይህን ሊያደርጉላት አልቻሉም። ሁሌም ለመማሪያ ቁሳቁስ፣ ለቅባት ለንጽሕና መጠበቂያና ለሌሎችም ገንዘብ ካልተገኘ ፍላጎት አይሟላም። እንዲህ በሆነ ጊዜም ከልብ መከፋትና ማዘኑ አይቀሬ ይሆናል።
ቤንች ማጂ፣ ሚዛን ተፈሪ ያበቀለቻት ሀቢባ ኑረዲን አስተዳደጓ በስርዓት የተቃኘ ነው። እንዲህ ለመሆኗ ደግሞ የፖሊስ አባቷ ማንነት አግዟታል። የፖሊሱ ልጅ ከሕፃንነቷ ሲነገራትና ስታየው ያደገችው ጥንካሬ ብርታት አጎናጽፏታል። በተለይ ዘጠነኛ ክፍል ስትገባ ያዳበረችው ማንነት ለአሁኑ የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ወሳኝ መሆኑን ታምናለች።
አባት የሀቢባ መልካም ህይወት የእሳቸውም ህልም ሆኖ ቆይቷል። ነገን በአሸናፊነት ሊያገኟት ይሻሉና በዕንቅልፍ እንድትሸነፍ በስንፍናም እንድትደክም አይፈልጉም። ዘወትር ከመኝታዋ ቀስቅሰው ለጥናት ሲያዘጋጇትም በውጤቷ እንደምታኮራቸው እርግጠኛ ሆነው ነበር።
የአባትና ልጅ ምኞት እውን ሆኖ ሀቢባ ለመጨረሻው የመልቀቂያ ፈተና ተቀመጠች። ጊዜው ደርሶ ውጤት ሲመጣም ዩኒቨርሲቲ መግቢያውን በብቃት ማግኘቷ ተረጋገጠ። ይኼኔ የጡረተኛው ፖሊስ ደስታ ወሰን ታጣለት። የኑሮ አቅማቸው ዝቅተኛ ቢሆንም በልጃቸው ብርታት ነገ መልካም እንደሚሆን ገምተው ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ።
አሁን ሀቢባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ነች። ለብርቱዋ ተማሪ ያለፉት ዓመታት በጥንካሬና በፈተናዎች የተቃኙ ነበሩ። ሀቢባ ወደዩኒቨርሲቲው ከገባች አንስቶ በርካታ ጉዳዮች ያሳስቧታል። የዓመታት ልፋቷ፣ የወላጆቿ ድካም፣ የአቻዎቿ ተጽዕኖና ሌላም። ህይወትን በዚህ መልክ ማወዳደሯም ለመልካም የትምህርት ውጤት አድርሷታል። በየጊዜው ቤተሰብን ላለማስቸገር ያላት አቋም ግን ወሳኝ በሚባሉ ጉዳዮች ጭምር እንድትቸገር ማድረጉ አልቀረም።
አልፎ አልፎ ከቤተሰብ የሚላከው ገንዘብ ደግሞ ለታሰበው ሁሉ የማይሞላ ይሆናል። ለተማሪ የሚያስፈልገውን ያለመረዳት እውነትም ዋንኛው ችግር ነው። ለትምህርት ከሚያስፈልጉ ቁሶች ባሻገር፣ ለንጽህና መጠበቂያ የሚሆኑትን ያለማግኘትም እንደ ፈተና ይወሳል። ሀቢባ የቤተሰቦቿን የኑሮ አቅም ታውቃለች። እናም ስለምን? ብላ አትጠይቅም። እንደፍላጎቷ እያብቃቃች ዛሬን ደርሳለችና በሆነው ሁሉ አትከፋም።
ምዕራብ ጎጃም ዱርቤቴ ተወልዳ ያደገችው እየሩስ አዱኛ ቀልጣፋና ጨዋታ አዋቂ ናት። እየሩስ ፊደል ለመቁጠር ዕድሉን ያገኘችው ሰባት ዓመት ሲሞላት ነበር። ይህ ዕድሜ ግን ትምህርትን ብቻ ሳይሆን የሥራ ጫናም አሸክሟታል። የገጠር ልጅ ናትና እንደእኩዮቿ የሚፈለግባትን መከወን ግዴታዋ ነው። ቤተሰቦቿ መማሯን ቢፈቅዱም በጥናት ሰበብ እንድትቀመጥ አይሹም። ጥናት ይሉት ቋንቋ ለእነሱ አሰልቺና ዱላ የሚያስነሳ ነበር።
ዘጠነኛ ክፍል ለእየሩስ ራሷን የማወቂያ ጊዜ ሆነ። ከወላጆቿ ርቃ ከተማ መግባቷም ጥንካሬን አላበሳት። በቤተመጻሕፍት በማጥናት ሰፊውን ጊዜ ለትምህርት ሰጠች።
ይህ መሆኑ አስራ ሁለተኛን ክፍል በጥሩ ውጤት እንድታልፍና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እንድትቀላቀል ዕድል ሰጣት።
እየሩስ በዩኒቨርሲቲው የሶሻል አንትሮፖጂ ተማሪ ሆና ተመደበች። የእሷ ምርጫ ባይሆንም ባለችበት መስክ ውጤታማ እንደምትሆን አስባ በትምህርቱ ገፋች። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ስለአዲስ አበባ የሰማችው ሁሉ አስጨንቋታል። በተለይ በዩኒቨርሲቲ የኑሮ ልዩነት ፈታኝ እንደሆነ አውቃለች። ቀሚስ መልበስና የገጠር ልጅ መሆን ነውር መሆኑ ተነግሯታል።
ይህ ወሬ ለወላጆቿም ጭንቀት ነበር። እየሩስ በስፍራው ስትደርስ ደግሞ የመኪናው ብዛትና ግርግሩ አስደነገጣት። ያያት ሁሉ የሚዘርፋት መስሏትም ተደናበረች። ስለ ዩኒቨርሲቲው የተባለው ግን ሀሰት መሆኑን ተረዳች። በግቢው ሱሪ ብቻ ሳይሆን ቀሚስ መልበስም ይቻላል። የዚያኔ የሆነውን ዛሬ ስታስበው በፈገግታ ትሞላለች። ለእሷ ባለፉት ዓመታት ፈተናዋ የነበረው ለጉዳዮቿ መከወኛ እጇ ማጠሩ ነበር።
አንዳንዴ ችግሩ ሲብስ ገጠር መልዕክት ልካ «እርዱኝ» ትላለች። ወላጆቿ ግን ይህን ሲሰሙ ይናደዳሉ። «የሚቆርስ፣ የሚያለብስ አሳዳሪሽ መንግሥት ነውና እኛን አታስቸግሪን» ይሏታል። ይሄኔ ውስጧ ይከፋል። አለማወቃቸውን ተረድታ ግን ከጓደኞቿ ትበደራለች።
ሦስቱንም ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያገኘኋቸው ችግራቸውን ሊያቃልል በሚችል የድጋፍ መርሐግብር ላይ ነበር። በቅርቡ አርቲስት አምለሰት ሙጬ እነሱን ጨምሮ 200 ለሚሆኑ ሴት ተማሪዎች የንጽሕና መጠበቂያ ቁሶችን በስጦታ አበርክታለች።
ተማሪዎቹም ስለተደረገላቸው ስጦታ አመስግነዋል። አብዛኞቹ ዛሬን በችግር ቢያሳልፉም ስለነገው መልካምነት አስበው በጥረታቸው ይቀጥላሉ። ስለነገ ዛሬ ላይ መፈተን በጎ ነው። ስለነገ ዛሬን መበርታት ግድ ነው። ስለነገ ሁሉም ይቻላል። ስለነገ…!
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 3/2011
መልካምስራ አፈወርቅ