ወቅቱ የክረምት ወቅት ነው። ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች ደግሞ ይከሰታሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክረምት ወቅት በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎችን እያስተናገደች ትገኛለች። ይሄ አደጋ ከሰው ሕይወት መጥፋት እስከ ንብረት መውደም በሚደርስ የስጋት ደረጃ የሚገለጽ ነው።
ክረምት በየትኛውም ዓለም ከ እስከ በሚል ተፈጥሮአዊ ሂደት ልኬት አለው። የእኛን ሀገር የክረምት አመጣጥና መሄጃ ብንዳስስ እንኳን ከሶስት ወራት ያልበለጠ እድሜ ያለው ነው። በተለያየ ምክንያት ይሄ ተፈጥሮአዊ ሂደት ጠባዩን ቀይሮ ደስ ባለው ጊዜ መጥቶ ደስ ባለው ጊዜ መሄድን አመሉ አድርጓል። ይሄ የባህሪ ለውጥ እንዳለፈው ጊዜ በረከት ብቻ ሳይሆን መርገምትንም ጭምር ይዞ የመጣ ነው።
ቀደም ባለው ጊዜ ባለው የክረምት ወራት ዝናብ ለልማት፣ ለእርሻ፣ ለመስኖ፣ ለግንባታ እንዲሁም ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚውል ነበር። በዚህም ተናፍቆ ከመጠበቁ ባለፈ ሲወጣም እንዲሁ በናፍቆት ነበር። ይሄ ሂደት ክረምትን ከልማት ጋር አስተሳስረን እንድናርስ፣ እንድንጎለጉል፣ እንድንዘራ፣ ባጠቃላይ ለግብርናው ኢንዱስትሪ እንደዋነኛ ግብዐት ሆኖ ሲያገለግን ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይሄ ተፈጥሮአዊ ሂደት ጠፍቶ አዲስ የወቅቶችን ወረፋ እንድንለማመድ ተገደድን። ይሄ መሆኑ ከልማት ጋር ጥፋትን፣ ስጋትን አብሮ ይዞብን መጥቷል። የዚህ ነጻ ሀሳብ መነሻ ይሄ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽኖ በማስመልከት ነው።
በየዓመቱ የግንቦት ወርን መግባት ተከትሎ የሚመጣው የክረምት ወቅት እንዳለፈው ጊዜ ጊዜውን ጠብቆ ከመምጣትና ጊዜውን ጠብቆ ከመውጣት ባለፈ አዲስ ባህሪዎችን በመላበስ በወገን ላይ ሞት በንብረት ላይ ጥፋት በቋሚው ላይ ደግሞ ከፍተኛ የሕልውና ስጋትን ደቅኗል የሚለው ዜና ከሰማነው ሰንበትበት ብሏል። ወትሮ በዝናብ ወዛቸው የሚታወቁት ሰኔና ሐምሌ ሽንጠ ረዥም ሆነው አዲስ ዓመትን በመሻገር እስከ ሕዳር ግዛታቸውን በማስፋት በሁላችንም ላይ ፍርሀትን ደቅነዋል።
ሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ስሟ መነሳቱ አዲስ ባይሆንም በየጊዜው የምንሰማው የሞትና የተፈጥሮ አደጋ ግን አስደንጋጭ ዜና ሆኖ ወደ እያንዳንዳችን ቤት እየመጣ ነው። ሰሞነኛውን የመሬት መንሸራተት ዜና ብናነሳ እንኳን ብዙ ትንታኔዎችን መጻፍ እንችላለን።
በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ የተከሰተውን እጅግ አሳዛኝ የሆነውን የመሬት መንሸራተት ተፈጥሮአዊ አደጋ ማስታወስ እንችላለን። ብሔራዊ ሀዘን ቀን የታወጀለት ይሄ የዜጎች እልቂት የብዙዎችን ልብ የሰበረ ከመሆኑ በተጨማሪ በርካቶችን ያለ ቤተሰብ፣ ያለወላጅ፣ ያለጠያቂ፣ ያለልጅ እንዲሁም ያለቤትና ንብረት ያስቀረ ነው።
በአደጋው ከ260 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን በርካቶችን ደግሞ ነገን እንዲሰጉ በማድረግ ያለፈ አሳዛኝ ክስተት ነበር። በዚህ አደጋ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የተለያዩ ክልሎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች በያገባኛል ስሜት ርብርብ በማድረግ ለአፈጋው ተጎዥዎች ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል።
የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ ብዙዎች ስፍራው ድረስ በመገኘት የማኅበረሰቡን ስሜት የተጋሩበትን ሁነት ማስታወስ ይቻላል። የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ጨምሮ ሌሎች ወዳጅ ሀገራትን ያሳዘነ እንደነበር ከማጽናኛ መልክታቸው መረዳት ችለናል።
እንዲሁም በካፋ ዞን በዴቻ ወረዳ ሚዲዮ ጎምበራ ቀበሌ በዛው ሰሞን በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ የሶስት ሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፍ ባለፈ የአካል ጉዳት ማድረሱም ተዘግቧል። እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ ግሽሬ ጉዱ ሞና ሆሞ በሚባል አካባቢ እንደዚሁ ተመሳሳይ አደጋ ደርሶ የአስራ አንድ ሰዎች ሕይወት አልፏል።
በአማራ ክልል በደሴ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ‹ጀሜ› ተብሎ በሚጠራ ሰፈር የመሬት መንሸራተት አደጋ መከሰቱ ሌላኛው ሰሞነኛ ወሬ ነበር። እኚህ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ሚዲያ ሽፋን አግኝተዋል መነጋገሪያ ይሁኑ እንጂ በተለያዩ ቦታዎች መሰል አደጋዎች ሊፈጠሩ እንደሚችል ይገመታል። በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎና ሰሜን ጎንደር ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ቄለም ወለጋ፣ በሀረርጌ እና አርሲ ዞኖች፣ በጋንቤላ ተመሳሳይ አደጋ አጋጥሞ የበርካቶች ውድ ሕይወታቸውን ቀስፏል ።
ችግሩ በተከሰተበት አካባቢ ሁሉ መንግስታዊና ግለሰባዊ ድጋፎች እንደቀጠሉ ናቸው። እስከ ነሐሴ መግቢያ ድረስ በጎፋ ወረዳ ብቻ ከ125 ሚሊዮን 886 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ምግብ ነክ ለሆኑ ውሏል። ከ57 ሚሊዮን 843 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ምግብ ነክ ያልሆኑ፣ ከ2 ሚሊዮን 335 ሺህ በላይ የሚልቅ ተመን ለሕክምና ቁሳቁስ በተጨማሪም ተመሳሳይ ወጪን በሚጋራ ተመን የግንባታ ግብዐት ድጋፍ ተደርጓል።
በርግጥ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያየ አካባቢ በክረምቱ አማካኝነት ስጋት አለ። በመሬት መንሸራተት፣ በአፈር ናዳ፣ በጎርፍ እና መሰል ክስተቶች ማኅበረሰቡ ስጋት ላይ ወድቋል። መጪውን ጊዜ ካለስጋትና ሞት ለመቀበል ዛሬ ላይ ቁርጠኛ ስራዎች ያስፈልጋሉ። ያለፈውን ዓመት በዜና ሽፋን ብቻ ባናልፈው ዛሬ ላይ ለዚህ ሁሉ ጥቃት ባልበቃን ነበር። ነገን ዛሬ መስራት የሚለው እሳቤ በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ውስጥም የሚተገበር ነው።
ዛሬ ላይ የምናደርጋቸው ጥንቃቄዎች የነገ መኖር ዋስትናዎቻችን ናቸው። ሁሌ ክረምት በመጣ ቁጥር ሞትና መከራችንን ከመቁጠር ወጥተን ቁርጠኛ የቅድመ ጥንቃቄ ትግበራ ላይ ልንበረታ ይገባል። ሬሳ ከመቁጠር ወጥተን እስኪ ለሕይወት ዋስትና የሚሰጥ አካባቢን እንፍጠር። ቀድመን ብንነቃ፤ ከአደጋ በኋላ የምናደርጋቸው የገንዘብም ሆኑ የቁሳቁስ እርዳታዎች ለቅድመ ጥንቃቄ ከበቂ በላይ ነበሩ። አደጋ እስኪደርስ በሚጠብቅ ልምምድ ውስጥ መሆናችን ነገሮችን አስቀድመን እንዳናይ አድርጎናል።
ርብርባችን ከአደጋ በፊት ቢሆን የበለጠ ያተርፈናል። ከአደጋ ቦኋላ የሚደረግ መረባረብ አንድነታችንንና የእርስ በርስ ድጋፋችንን የሚያሳይ ቢሆንም ለሕይወት ዋስትና አይሰጥም። እንደዚህ አይነት የተፈጥሮ አደጋዎች በቅድመ ጥንቃቄ የሚሸነፉ ናቸው። የማኅበረሰቡን ደህንነት በአስተማማኝነት ለመጠበቅ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እንዲሁም መሰል ስጋቶችን ለማስቀረት እንደመፍትሄ በቀዳሚነት ሊነሳ የሚችለው የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ነው።
በቀጣይም መሰል አደጋዎች ስላለመከሰታቸው ማረጋገጫ የሚሰጠን የለም። ማረጋገጫችን አካባቢያችንን ከመሰል የተፈጥሮ አደጋ ሊጠብቅ የሚችል ሁሉንም አይነት አማራጮችን መጠቀም ነው። አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ሰሞነኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከሰተባቸው የተባሉ ስፍራዎችን በዋቢነት በመጥቀስ እኛ ቸል ብለናቸው እንጂ ከዚህ ቀደም የአደጋ ቅድመ ምልክት አሳይተውን ነበር ሲሉ ተደምጠዋል።
ቸልተኝነት እንደምናየው ዋጋ ያስከፍላል። የምንከፍላቸው ዋጋዎች ደግሞ ከግለሰብ ዘለው ሀገራዊ ማቅ ሊያለብሱ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። የአደጋ ስጋት ስራ አመራር እንዳስታወቀው ባለፈው ወር ብቻ በስድስት ክልሎች በተከሰተው ጎርፍ፣ የመሬት ናዳና መንሸራተት በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ገልጽዋል።
አንድ ሰው ሲሞት ሀገር እየሞተች እንደሆነ ይታሰባል። በመሰል አደጋ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች እጣ ፈንታቸው ምንድ ነው? የሚለው ጥያቄ እንደ ሀገር የሚመለስ የሁላችን የጋራ ጉዳይ ነው። አሁንም ቢሆን የአደጋ ስጋት ያለባቸውንና ቅድመ ማስጠንቀቂያ የታየባቸውን አካባቢዎች በማጤን ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሪዮሎጂ በመጪው ጊዜያት ክረምቱ ተጠናክሮ ስለሚቀጥል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ በመተንበይ ላይ ይገኛል። አደጋ በደረሰባቸው ሆነ የአደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ተገቢው የቅድመ ጥንቃቄ ስራ በመስራት ከአደጋው ራስንና አካባቢን መታደግ ይገባል።
የዝናብ ወቅት ከበጋው በበለጠ ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭነት አለው። መንገዶችን በመሸርሸር፣ በደመናና በዝናብ ሳቢያ መስተዋቶችን በመጋረድ፣ ጎማ በማንሸራተት እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የአደጋው ቁጥር ይጨምራል። ከመሬት መንሸራተቱ እኩል ስናሽከረክርም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግም ይጠበቅብናል። ክረምት በወቅቱ ሲሆን እንጂ ወቅቱን ከልጠበቀ ለእንደነዚህ አይነት መጠነ ሰፊ ችግሮች ሀገርን ይዳርጋል።
በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሳይቀር አሻራው የጎላ ነው። በግብርናው ላይ፣ በትራንስፖርቱ ላይ፣ በኢንዱስትሪው ላይ፣ በቱሪዝሙ ላይ የራሱ አሉታዊ አስተዋጽ አለው። ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ የሚሆነው የቅድመ ዝግጅት ስራ ነው። ችግሮችን የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ አድርጎ ማለፍ በብዙ የምንታወቅበት ነው።
የጎርፍ እና መሰል አደጋዎችን የዛሬ ዓመት እና ከዛ በፊትም ባሉ ጊዜዎችም ሰምተናል። ዛሬም ግን ስለሞትና ስለአደጋ የምናወራ ነን። ለምንድነው ቀድሞ መዘጋጀት ያቃተን? አደጋው ከመከሰቱ በፊት በተዘጋጀ አእምሮና ዝግጁነት ችግሮቻችንን መሻገር ያልቻልነው ለምንድ ነው?።
ክረምት ይዞት ከሚመጣው ጸጋ ጎን ለጎን የሚያደርሰውን አደጋ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ቅድመ በቅድመ ጥንቃቄዎች ልንከላከል ይገባል። ከተቻለ ከአምናው ካልሆነ ከዘንድሮው ተምረን ከርሞን ከስጋት ነጻ የሆነ ማድረግ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ብልህ ከሌሎች የሚማር ነው። ከዚያም ከዛ የምንሰማቸው የአደጋ ዜናዎች አንቂዎቻችን ሳይሆኑ በእኛው መንደር ተከስተዋል።
ካለፈው መማር ወሳኝና ነጻ አውጪ የመፍትሄ አቅጣጫን የሚጠቁም ሆኖ የሚመጣ ነው። በቅድመ ዝግጅት ሙታንን ከመቁጠር ወጥተን የዜጎቻችንን ደህንነት የምናረጋግጥበት ምቹና አስተማማኝ ከባቢን መፍጠር ቀሪ የቤት ስራችን ይሆናል።ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት አበክረው ሊሰሩ ይገባል።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም