የሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ እና በአካባቢው ያንዣበበው አደጋ

አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ በሚለው መጽሃፋቸው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሶማሊያን እንዲህ ይገልጿታል። የሶማሊያ ታሪክ የሚያስደንቅም፤ የሚያሳዝንም ነው። በመሰረቱ ሶማሊያ ሳይጸነስ የተወለደ ሀገር ነው።

ሶማሊላንድ እኤአ በሰኔ 26 ቀን 1960 ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ወጥታ ራሷን ስትችል በደቡብ በኩል የኢጣሊያ ግዛት የነበረችው ሶማሊያም ለአስር ዓመታት ያህል በኢጣሊያ ስር የተባበሩት መንግስታት የሞግዚት አስተዳደር ሆኖ ቆይታ ሀምሌ 1ቀን 1960 ነጻነቷን አገኘች።

ሆኖም የተለያየ የአስተዳደር ብሂልና አካሄድ የነበራቸው ሶማሊላንድና ዋናዋ ሶማሊ ያለምንም ምክክር እና መግባባት እንዲዋሃዱ ተደረገ። ይህም ቅራኔ ፈጠረ። በተለያዩ ጎሳዎች መካከልም በሚኖር ሽኩቻ በመኖርና ባለመኖር መሃል የሚቃትት ሀገር ሆኗል። ›› ሲሉ ሀገሪቱ የቆመችበት መሰረት የረጋ አለመሆኑን ያብራራሉ።

በአጠቃላይም ሶማሊያ ከመመስረቻዋ ጀምሮ ያልጸናች በመሆኑም ዘወትር ግጭትና ሁከት አጥቷት አያውቅም። ይህም ሁኔታ ለአሸባሪዎችና ሰርጎገቦች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም ባሻገር አካባቢው በግጭትና በአለመረጋጋት እንዲታወቅ አድርጎታል።

ሶማሊያ ባለመረጋጋትና በግጭት ውስጥ የምትኖር ሀገር ነች። ከዚያም አልፎ መንግሥት አልባ ሆና ዘመናትን ተሻግራለች። በእነዚህ የመከራ ዓመታት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሶማሊያ ሕዝብ ጎን ተለይቶ አያውቅም።

በፊት ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ተልዕኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግስትም ተረጋግቶ መንግስታዊ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት፤ 60 በመቶ የሚሆነውን የሶማሊያ ክፍል የሚጠብቀውና ከአልሻባብ ጥቃት የሚከላከለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው።

ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጠንካራ መንግሥት እንዲፈጠር መስዋዕትነት ስትከፍል ቆይታለች። አልሻባብ የሁለቱም የጋራ ጠላት መሆኑ ደግሞ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እንዲቆሙ ያስገደደም ነበር።

የኢትዮጵያን የሶማሊያ ግንኙነት ከዚህም በላይ ነው። የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች በሁለት አገሮች የሚኖሩ አንድ ሕዝቦች ናቸው። ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰረ ነው። ወደ 16 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሶማሊያ እ.ኤ.አ. በ2020 ወደ 294 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሸቀጣ ሸቀጥ ከኢትዮጵያ አስገብታለች። የንግድ ልውውጡም እያደገ እንደሚሄድ ይታመናል።

አሁን ያለው የሶማሊያ መንግስት ይህን ሁሉ የተመለከተ አይመስልም። ጭራሹኑ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆኑ ሀገራትን ጭምር በሰላም አስከባሪነት ስም ጋብዞ ወደ ሶማሊያ እንዲገቡ እያደረገ ነው። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ቀንድ አዲስ ስጋት ይዞ መጥቷል።

የጉዳዩን አሳሳቢነት አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ሆኗል።

የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለዚሁ አዲስ ሽግግር እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት ቀጣናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል። ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም ሲል የሁኔታውን አሳሳቢነት ያብራራል።

በአጠቃላይ ሶማሊያ የመረጠችው መንገድ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ብዙ መዘዝ ይዞ የሚመጣ ነው። በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብ የከፈለችውን መስዋዕትነት ከንቱ የሚያስቀርና ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የተከፈለውንም የሕይወት ዋጋ ጭምር ዋጋ የሚያሳጣ ነው።

በሌላም በኩል በኢትዮጵያ ሰራዊት የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ተመናምነው የነበሩት የአልሸባብና የአልቃኢዳ ኃይሎች እንደገና እንዲያንሰራሩና አካባቢውን የሽብር ማዕከል እንዲሆን በር የሚከፍት ነው። ይህ ደግሞ ስጋቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ ጭምር ነው።

የሶማሊያ መንግሥት እየሄደበት ያለውን መንገድ ማጤን ይኖርበታል። በተለይም ለውዝግቡ መነሻ ተደርጎ የሚወሰደውን የባሕር በር ጥያቄ የሶማሊ ሕዝብም ሆነ የቀጣናው ሀገራት ሊረዱት ይገባል። የኢትዮጵያ መንግሥት ወደብና የባሕር በር ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑንና የጎረቤት ሀገራትም ኢትጵያን እንዲተባበሯት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም በግልጽ የተቀበለ ሀገር የለም።

የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆንም ከስነልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሕዝቡ እንዲጋለጥ አድርጎታል። የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል። ለበርካታ መሰረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ይውል የነበረውን ከ1ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕድል ለሌሎች የሰጠች ቢሆንም የተጠቀመችበት ግን ሶማሊላንድ ብቻ ነች። ዋናዋ ሶማሊያም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ የመሆን ዕድል አላት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በፓርላማ ተገኝተው እንዳሉት ‹‹የሶማሊያ መንግሥት በአንድ ሰዓት በረራ እና በአንድ ሰዓት ውይይት ይህን ነገር መልክ ማስያዝ ይችላል። በጣም ቀላል ነገር ነው ።

ምክንያቱም ከሶማሌ መንግሥት ጋር ምንም ጸብ የለንም። የሶማሌ መንግሥት የመረጠው ግን እኛን ከማናገር በየሰፈሩ እየዞረ እኛን መክሰስ ነው። ያለኝ ምክር ብር አታባክኑ ነው። በየሀገሩ ስንሄድ፤ በጣም ብዙ ወጪ ይወጣል፤ ብር ከምናባክን እሱን ሰብሰብ አድርገን አንድ ኪሎ ሜትር ዎክ ዌይ ብንሰራበት፤ አንድ ትምህርት ቤት መቋዲሾ ብንሰራበት ሕዝብ ይጠቅማል።

እኛን ለመክሰስ ሀገር ለሀገር መሄድ አያስፈልግም ። አዲስ አበባ መምጣት ይቻላል። ለመነጋገር ዝግጁ ነን። ሶማሊያ እንድትጎዳ፤ እንድትፈራርስም፤ እንድትበተንም የሚፈልግ መንግሥት አይደለም። ቢሆን ልጆቹን ልኮ አይሞቱም። የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የባሕር በር ጥያቄ ነው። ይሔ ሕጋዊ ጥያቄ ነው። ይሄን በሰላማዊ እና በንግግር መልኩ እንደማንኛውም ኮሚዲቲ/ ሸቀጥ ለመቀበል ኢትዮጵያ ዝግጁ ነች።

ለምሳሌ ወይ ሶማሌ፤ ወይ ጅቡቲ ወይም ሌሎቹ፤ የባህር በር አላቸው፤ ግን እንደ ኢትዮጵያ ሊያመርቱ አይችሉም። እኛ የተሻለ መሬት አለን፤ የተሻለ ውሀ አለን፤ ኢነርጂ ምግብም፤ ከኛ አቦካዶ ከነሱ ውሀውን ብንጋራ ምንም ችግር የለውም። ንግድ ነው።

ተጠቅመው ተጠቅመን አድገው አድገን፤ ተባብረን አብረን ብንሄድ ለሪጅኑ/ለአካባቢው ለልጆቻችንም ጠቃሚ ነው። እናንተ እንዲህ አይነት ጥያቄ አታንሱ ቢባል ግን፤ ጥያቄ አታንሱ ብለህ የምታፍነው ጉዳይ አይደለም፤ እውነት እስከሆነ ድረስ ጊዜውን ጠብቆ ይወጣል።››ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው።

በአሁኑ ወቅት 120 ሚሊዮን ሕዝብ በ2050 አካባቢ ደግሞ በእጥፍ የሚያድግ ሕዝብ ተይዞ “ስለቀይ ባሕር እና ስለ ወደብ አታንሳ፤ ዝም ብለህ ተቀመጥ” የሚል አፋኝ አመለካከት ሊኖር አይገባም። የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ማክበር አሊያም ደግሞ የራሷን የባሕር በርና የወደብ አማራጮች ማክበር ይገባታል። ከሁለቱ ውጭ መሆን ግን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን የሚቀበሉት አይደለም።

ሶማሊያ በሺዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የባሕር በር አላት። ግን ይህ ሁሉ ኪሎ ሜትር ለሶማሊያ ወደብ ሆኖ ሊያገልግል የሚችል አይደለም። ስለዚህም ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች ወደብ ከኢትዮጵያ ጋር ማልማት ትችላለች። ወይንም ደግሞ ለም መሬት ወስዳ በምትኩ ወደብ ልታቀርብልን ትችላለች። ብቻ አማራጩ ብዙ ነው።

ዘይላ ሶማሊያ እንደ ሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባሕር በር ነው። ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች። ለኢትዮጵያ ቅርበት አለው። ከሞቃዲሾ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚርቅ ስለሆነ ሶማሊያ ልትጠቀምበት አትችልም። ስለዚህም መነጋገር ከተቻለ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የዘይላን ወደብ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበትና ሶማሊያም በምትኩ ጥቅም ብታገኝ ሁለቱም ሀገራት አሸናፊ መሆን ይችላሉ።

ከዚህ በተረፈ ግን የኢትዮጵያን ፍላጎት አፍኖ አሸናፊ መሆን አይቻልም። ለሶማሊያ ሕዝብ በርካታ ውለታ ለዋለችው ኢትዮጵያ በየስፍራው እየዞሩ ስም ማጥፋትና በኢትዮጵያ ላይ ሀገራት የተሳሳተ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያን ውለታ የዘነጋ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለሶማሊያ ሰላም ሲል ሕይወቱን ከመገበሩም በሻገር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008 የሶማሊያ መንግሥት ሲቋቋም ቀድማ ኤምባሲ የከፈተችና ዕውቅና የሰጠችው ኢትዮጵያ ናች። በተለያዩ ጊዜያትም በሶማሊያ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች ሲያጋጥሙ የሶማሊያ ሕዝብን በሯን ከፍታ የምትቀበለው ኢትዮጵያ ብቻ ነች። ታዲያ ይህንን ሁሉ ውለታ ለምትውለው ኢትዮጵያ የሶማሊያ መንግሥት በተቃራኒው እየሰራ ያለው ኢትዮጵያን የማጠልሸት እና በኢትዮጵያ ላይ ስጋት የሚደቅን እርምጃ መውሰድ ጉዳዩን እንቆቅልሽ ያደርገዋል።

በተለይም በሰላም አስከባሪ ስም የኢትዮጵያን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ለመፈጸም መሞከሯ የቀጣናውን ችግሮች ከማባባስ ባሻገር ይዞ የሚመጣው አንዳችም መፍትሄ የለም። በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፓርላማ ተገኝተው እንደተናገሩት ፤ የሶማሊያን ሕዝብ ለመታደግ ሲባል ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አጥታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የሶማሌያ ሕዝብ፤ የሶማሌያ ጎሳዎች በአብዛኛው በእኛ ውስጥ ስላሉ ጎረቤት ብቻ ሳይሆን ወንድሞቻችን ናቸው። ለሶማሊያ ሰላም ሞተናል፤ ለሶማሊያ አንድነት ሞተናል። ለሶማሊያ ያለንን ክብር፤ ብልጽግና ከማንም መንግሥታት በላይ አሳይተናል።

ሶማሊያን እንደ ኢትዮጵያዊ ቆጥረን የደገፍነው እኛ ነን። በሶማሌያ አንድነት የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ የለውም። በኛ እና በሶማሌላንድ መካከል የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ለሁሉም ጎረቤቶቻችን ያቀረብነው ጥያቄ፤ ሁሉን ለምነን ጠይቀን ምላሽ ስናጣ ከመለሰልን አካል ጋር ተፈራረምን እንጂ ከሶማሊያ አንድነት ጋር የተያያዘ ጥያቄ አይደለም ብለዋል።

የሶማሊያ መንግሥት ይህን ሁሉ በመዘንጋት ወይም ኢትዮጵያ ውለታ ፊቱን በማዞር ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አብሮ እየሰራ ነው። ከዚያም አልፎ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ወደ ግዛቱ ጋብዟል። ይህ ደግሞ አልሸባብ እንደገና እንዲያንሰራራ እና የሶማሊያ ሕዝብ ዳግሞ ለስቃይ እንዲዳረግ መፍቀድ ነው። ከዚህም አልፎ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የአሸባሪዎች መናኸሪያ እንዲሆን በማድረግ የበለጠ የግጭትና የጦርነት ቀጣና እንዲሆን በር መክፈት ነው።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን  ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You