የኮሪደር ልማቱ ይዞት የመጣውን ትሩፋት ሙሉ ለማድረግ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁርጠኛ አካሄድ በመከተል የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን በኮሪደር ልማቱ በመታገዝ አዲስ እንዲሁም አበባ እያደረገ ይገኛል። ይህ ተግባር ሲከናወን ከተማዋ አዲስ እና ውብ ከመሆኗ በተጨማሪ የተገኙ ሌሎች በጎ ትሩፋቶችም አሉ።

ከእነዚህ ትሩፋቶች አንዱ በኮሪደር ልማቱ የተተከሉ ተክሎች ለዓይን እይታ ማራኪ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለአየር ንብረት መታደስ የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ነው። ሣሩ፤ የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎችን ጨምሮ ዘንባባዎቹ የከተማዋን አረንጓዴ ስፍራ በማሳደግ የሚያበረክቷቸው ሁለንተናዊ አስተዋፅዖ ለመገመት የሚከብድ አይሆንም ።

የኮሪደር ልማቱ ሌላው ትሩፋት የመኪና መንገዱ እንዲሁም የእግረኛው መተላለፊያ ሰፋ ብሎ ስለተሠራ ሹፌሮች በአስፋልት ላይ መኪናቸውን ዘና ብለው ማሽከርከር መቻላቸው ነው። እግረኞችም መኪናን እየተሻሹና ከመኪና ጋር እየተገፋፉ ከመንቀሳቀስ ተገላግለዋል። ይህም በመሆኑ መኪና በአስፋልቱ፤ እግረኛው በጎዳናው በመንቀሳቀሱ የመኪና አደጋ እየተስተዋለ አይደለም።

እኔ በብዛት በምንቀሳቀስበት የኮሪደር ልማቱ በተሠራባቸው በአራት ኪሎ – ፒያሳ መንገድ እና አራት ኪሎ – ቀበና – መገናኛ መንገድ ከዚህ በፊት የማየው የትራፊክ አደጋ አሁን ላይ እያስተዋልኩኝ አይደለም።

እንደውም ቀደም ሲል አብዛኛው እግረኛ ሕግ የማያከብር፤ በፈለገበት ቦታ የሚሻገር፤ እንዲሁም አስፋልት ላይ የሚንቀሳቀስ የነበረው አሁን ላይ በአብዛኛው በእግረኛ መንገድ የሚሄድ፤ የእግረኛ መሻገሪያ እየፈለገ የሚሻገር መሆኑን ለመታዘብ ችያለሁ። ይህም ከኮሪደር ልማቱ የተገኘ ሌላው ትሩፋት ነው። ይህ ትሩፋት በከተማዋ ለመኪና አደጋ መቀነስ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ይሆናል እላለሁ።

ቀደም ባለው ጊዜ ሕግ የማያከብረው አብዛኛው እግረኛ ብቻ ሳይሆን ባለመኪኖችም ነበሩ። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል አራት ኪሎ ከትምህርት ሚኒስቴር አጠገብ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በር ላይ በእግረኛ መንገድ ላይ መኪኖች ተደርድረው ስለሚገኙ እግረኛው ወደ አስፋልቱ ወጣ ብሎ ለመጓዝ ይገደድ ነበር።

መኪኖቹ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በእግረኛ መንገድ ላይ የሚቆዩት ሁሌም ንግድ ባንኩ በሥራ ላይ እስካለ ድረስ መደበኛ የመኪና ማቆሚያ እስኪመስል ድረስ ሃይ ባይ ሳይኖራቸው ባለጉዳዮች እየተፈራረቁ ያቆሙበት ነበር። አሁን እግረኛ በእግረኛ መንገዱ፤ ባለመኪናው በአውራ መንገዱ ይነጉዳል።

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የኮሪደር ልማት በተሠራባቸው ሥፍራዎች አብዛኛው እግረኛ ሕግ እያከበረ ነው የሚሄደው። የመኪና መንገዱን እየተዳፈረ መሄድ አይደለም፣ የብስክሌት መሄጃውን እንኳን አብዛኛው እግረኛ እየተዳፈረ አይሄድም። ብስክሌት እየተንቀሳቀሰበት እንዳልሆነ እያወቀ ክፍት ነው ብሎ አብዛኛው እግረኛ አይሄድበትም፤ ተው አትሂድ የሚለው አሠራሩና ሕሊናው ነው። ሕሊናው የሚያዘው እግረኛ ማግኘት መቻሉ ታዲያ የኮሪደር ልማቱ ትሩፋት ነው አያስብልም ትላላችሁ? ።

ሌላው ትሩፋት ደግሞ በኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገዶች ላይ የተሠሩት የእግረኛ ማረፊያ(መቀመጫ) አግዳሚዎች ናቸው። እነዚህ መቀመጫዎች እግረኛ በሚጓዝበት ወቅት ቢደክመው አረፍ ብሎ ከድካሙ እፎይታ ያገኝበታል፤ አንዳንዶቹ መቀመጫዎች ጥላ ሥር ስለሆኑ አረፍ በማለት ከፀሐይ በመጠለል ማሳለፍ የሚቻልባቸው ናቸው። አስፈላጊም ከሆነ ቁጭ ብሎ ለማሰላሰል መቀመጫዎቹ ምቹ ናቸው።

እዚህ ላይ ልጠቅስ የምፈልገው ጉዳይ መቀመጫዎቹ ከተጠቃሚዎቹ ቁጥር አንጻር መጠነኛ ስለሆኑ ተቋማት በበራቸው ላይ ሆነ አመቺ በሆኑ አቅራቢያቸው ላይ ሁለትም ሆነ ሦስት ማረፊያ የሚሆኑ መቀመጫዎች በማዘጋጀት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸው ቢወጡ መልካም ነው እላለሁ።

የኮሪደር ልማቱ ሌላው ትሩፋት የምለው ደግሞ አራት ኪሎ ትምህርት ሚኒስቴር አጠገብ የተሠራው የውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መንገድ ነው። ይህ የእግረኛ መንገድ የትራፊክ መጨናነቅንና አደጋ ከመቀነስ በተጨማሪ በውስጡ የተለያዩ አገልግሎቶች ማግኘት ማስቻሉ የሚጠቀስ ነው። የተሳፋሪ መጫኛና ማውረጃ ስፍራ መዘጋጀቱም ሌላው ተጠቃሽ ትሩፋት ነው።

በአሁኑ ሰዓት አምስቱም የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከአንዳንድ ጥቃቅን የማጠናቀቂያ ሥራዎች በስተቀር በአብዛኛው ተሠርተው አገልግሎት እየሰጡ ነው። በቅርቡ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ክፍት የተደረገው ከቦሌ ኤርፖርት ጀምሮ መገናኛ – ሲኤምሲ የሚደርሰው የመጀመሪያው ዙር አምስተኛው የኮሪደር ልማት የቀላል ባቡር የሐዲድ መሥመሩ ፈታኝ ቢሆንበትም በርካታ ነገሮችን አካቶ በማየቴ አድናቆቴን በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ። ይህንን እንድንመለከት እና እንድንገለገልበት ላደረጉ ከላይ እስከ ታች ላሉ የልማቱ ተሳታፊዎች ሁሉ ምስጋና አቀርባለሁ።

አድናቆትና ምስጋና በማስከተል የምሰጠው ቢስተካከሉ የምለው፤ የፍሳሽ መቀበያ ቱቦዎች በአንዳንድ ስፍራዎች በሚገባው ልክ ባለመዘጋጀታቸው ዝናብ ሲዘንብ ፍሳሹ ጎርፍ ሆኖ እግረኞችንም ሆነ ተሽከርካሪዎችን እያስቸገረ ስለሆነ ለዚህ የሚሆን ማስተካከያ ቢደረግ መልካም ነው እላለሁ።

ከዚህ በተጨማሪ ለእግረኛ ተብሎ የተሠራው መንገድ አንዳንድ ቦታ ቴራዞው አዳላጭ በመሆኑ ዝናብ ሲዘንብ እያንሸራተተ ሰው ሲጥል አይቻለሁ፤ በተለይ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ኢትሆፍ እና ቲ- ሩም ሕንጻ ፊት ለፊት ያለው የተነጠፈው ቴራዞ እንዳያንሸራትት በሚል በኦክስጅን እየተሞቆ እንዲሻክር ማስተካከያ ሲደረግለት ለማስተዋልም ችያለሁ።

ይህ ከሚሆን ይልቅ በቅድሚያ የማያንሸራትቱ ቴራዞዎች ቢዘጋጁ ኖሮ ሰዎች ከመውደቅ ይድናሉ፤ ተጨማሪ ወጪ ወጥቶ ማስተካከያ ማድረግም አያስፈልግም ነበር። ይሄን የመሰሉ ሁኔታዎች ወደፊት በሚሠሩ የኮሪደር ልማቶች እንዳይከሰቱ ትምህርት መውሰድ ይገባል። በአንዳንድ አካባቢዎች የተሠሩት የመፀዳጃ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቁ ቢሆንም አገልግሎት እየሰጡ አይደለምና በፍጥነት አገልግሎት እንዲሰጡ ቢደረግ መልካም ነው ።

ሌላው ቀደም ሲል ሲነሳ የነበረው እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ የተነገሩት የልማት ሥራዎች ሲሠሩ፤ በልማት የሚነሱ ዜጎች ሳይጉላሉ መሠረተ ልማቱ የተሟላ ምትክ ቤትና ቦታ የማግኘታቸው ሁኔታ እና በማኅበራዊ ኑሯቸውም እንዳይራራቁ አንድ ስፍራ የሚያገኙበት ሁኔታ የመመቻቸት ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You