የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) በአህጉሪቱ የዝንጀሮ ፈንጣጣ የተስፋፋባቸው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ላይ ክትባት ሊሰጥ እንደሚገባ ማዕከሉ ማሳሰቡ፤ የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣን የዓለም የጤና ስጋት ነው ሲል ማወጁ፤ የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል፥ ክትባቱ በቅርቡ መሰጠት እንዲቻል በአግባቡ ለማስቀመጥና ለመጠቀም መዘጋጀቱን መጥቀሱ ለዛሬ መጣጥፌ መነሻ ሆኖኛል፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በዓለም የጤና ድርጅት የሕብረተሰብ ጤና ስጋት መሆኑ ከተገለፀ ጀምሮ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሠራ ነው፤ በዚሁ መሠረት÷ በድንበርና በተመረጡ አካባቢዎች ላይ ቅኝት የማድረግ፣ የልየታ ሥራ፣ በሽታውን መመርመር የሚያስችል የቤተ-ሙከራ አቅምን የማሳደግ እንዲሁም የባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት ሥራ እየተከናወነ ነው። የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በ13 የአፍሪካ ሀገራት መከሰቱን በመግለጽ÷ እስካሁን በኢትዮጵያ በበሽታው የተያዘ ሰው አለመኖሩን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ አረጋግጠዋል፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተብሎ የሚታወቀው ኤምፖክስ በቫይረስ የሚመጣ በሽታ ነው። ምልክቶቹ ትኩሳትና ሽፍታ ሲሆኑ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ወይም ከተበከሉ ቁሳቁሶች ጋር በመገናኘት ሊተላለፍ ይችላል። በሽታው ብዙውን ጊዜ ለክፉ ባይሰጥም፣ ለሞት ሊዳርግ ይችላል። የመከላከያ እርምጃዎች በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪን ማስወገድ እና ንፅህናን መጠበቅ ነው። ክትባቶች እና ሕክምናዎችም አሉት።
በተለያየ ምክንያት በሽታ የመከላከል አቅማቸው ደካማ ለሆነ፣ ለህጻናት፣ ለነፍሰ ጡር ሴቶችና የጤና እክል ላለባቸው ሰዎች ግን ሕመሙ ሊበረታና ሞትን ሊያስከትል ስለሚችል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚተላለፈው ከቁስልና ከሰውነት ፈሳሽ በሚፈጠር ንክኪ እንዲሁም የተበከሉ ቁሶችን በመጠቀም ስለሆነ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
አያድርገውና ወደ ሀገራችን ቢገባ የጤና አጠባበቅ ስርአታችን በወጉ ያልተደራጀና ብዙ የሚቀረው ከመሆኑ ባሻገር የሕክምና አገልግሎት ወይም የክትባት ተደራሽነት ውስንነት ስላለብን ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። ስለሆነም ወደ ሀገራችን እንዳይገባ እየተደረገ ያለውን ጥረት ማጠናከርና ተቋማዊ ማድረግ ይመከራል።
ሌላው ከበሽታው ጋር ተያይዞ የሚፈጠር መገለል በአእምሮ ጤና እና በማህበራዊ ደህንነት ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ስለሚችል፤ የተሳሳተ መረጃም በሕዝብ ዘንድ ፍርሀትን ጎንቁሎ የመከላከል ጥረቱን እንዳያስተጓጉለው እና የማኅበረሰብ ምላሾች ላይ ሳንካ እንዳይፈጥር ከወዲሁ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን ማከናወን ይገባል። ስለ ዝንጀሮ ፈንጣጣ ምልክቶች፣ መተላለፊያ መንገዶችና እንዴት መከላከል እንደሚገባ ሳያሰልሱ ማስተማር ግድ ይላል።
ከሁሉም በላይ የጤና አጠባበቅ መሠረተ ልማትን ወይም የጤና አጠባበቅ ተቋማትን እና አገልግሎታቸውን የዝንጀሮ ፈንጣጣን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዝግጁ መሆናቸውን አበክሮ ማረጋገጥ ያሻል። እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶችን ማዘጋጀትና የምርመራ አቅምን መፈተሽ፤ ለክትባት መዘጋጀት፤ ክትትልና ሪፖርት ማድረግ ያስፈልጋል።
በመከላከል ሒደት ውስጥ የማኅበረሰብ ተሳትፎን ማሳደግ፤ ዓለም አቀፍ ትብብር ማጠናከር ማለትም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር መረጃን፣ ሃብትን እና ተሞክሮን አንሰላስሎ መጠቀም፤ ማንኛውንም ወረርሽኝ በፍጥነት ለመከላከልና ተጽዕኖውን በብቃት ለመቆጣጠር የአደጋ ጊዜ ምላሽ ዕቅዶችን ማዘጋጀት እና መተግበር በኢትዮጵያ ውስጥ የዝንጀሮ ፈንጣጣ የስርጭትን አደጋ ለመቀነስ እና የሕዝብ ጤናን ለመጠበቅ ያግዛል።
የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ዋና ዳይሬክተር ጂን ካሴያ (ዶ/ር) ሰሞኑን እንዳስታወቁት፡፡ ከዚህ በፊት በቫይረሱ ያልተጠቁ ቡሩንዲን፣ ኬንያን፣ ሩዋንዳንና ዑጋንዳን ጨምሮ በትንሹ 13 የአፍሪካ አገሮች በወረርሽኙ ተጠቅተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሽታው ባልነበረባቸው አገሮች በ2024 ብቻ 2,863 በቫይረሱ የተጠቁ ሕሙማን እንደተመዘገቡና ከእነዚህ ውስጥ 517 መሞታቸውን፤ የቫይረሱ ሥርጭት በከፋበት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ጨምሮ፣ በአኅጉሪቱ ያሉ ተጠርጣሪ ሕሙማን ቁጥር በ2022 ከነበረው 7,146 እና በ2023 ከነበረው 14,957 ልቆ በ2024 ወደ 17,000 ከፍ ብሏል፡፡ ይህ የተጠናከረ የቁጥጥር፣ የላቦራቶሪ ምርመራና የንክኪ ክትትል ሥርዓት በሌለበት የተገኘ በመሆኑ ቁጥሩ ከዚህ ሊልቅ እንደሚችልም ይገመታል ብለዋል፡፡
አሁን የተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ የጉዞ ገደብ ከሚጣልበት ደረጃ ባያደርስም፣ የአገሮችን ጥምረትና አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሻ፤ እንደ ካስያ (ዶ/ር)፣ የዝንጀሮ ፈንጣጣ አኅጉሪቱ ከዚህ ቀደም ካስተናገደቻቸው ወረርሽኞች የተለየ አይደለም፡፡ በጤና ሥርዓት ውስጥ የተከሰተ ቀውስ በመሆኑ ግን በትብብር መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ከግንቦት 2022 እስከ ሐምሌ 2023 ድረስ ቫይረሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት የሚሻ ድንገተኛ የማኅበረሰብ ጤና እክል ተብሎ በዓለም ጤና ድርጅት ታውጆ ነበር፡፡ ሆኖም አፍሪካ በዚህ ወቅት ያስፈልጋት የነበረውን አስቸኳይ ድጋፍ አላገኘችም፡፡ በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው ሥርጭት ሲቀንስ በአፍሪካ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዓለም አቀፍ አገሮች አሠራራቸውን መቀየር እንዳለባቸና ከአፍሪካ ሲዲሲ ጋር በቅርበት በመሥራት ለአባል አገሮች ድጋፍ እንዲያደርጉም ቀሪ አቅርበዋል፡፡
በአፍሪካ የቫይረሱን ሥርጭት ለማወቅ በተሠራ ውስን ዳሰሳና በተገኘ ማስረጃ መሠረት ሁኔታው በዳሰሳው ግንዛቤ ከተገኘበት በበለጠ ከባድ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በ2022 ድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና እክል ብሎ ካወጀ በኋላ፣ የታማሚዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ የሕመሙ ሁኔታም ከባድ ነው፡፡ የኤች አይቪ ሕሙማንን ከማጥቃቱ ጋር ተያይዞም የሞት መጠን እየጨመረ ነው፡፡ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመጀመሪያ በሰዎች ላይ የታየው በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እ.ኤ.አ. በ1970 ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቫይረሱ በተለያዩ አገሮች ታይቷል፡፡ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻ ከ15 ሺሕ በላይ በቫይረሱ ሲጠቁ 537 ደግሞ ሞተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ይህንን ጽሑፍ እስካጠናቀርንበት ዓርብ ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) የተጠረጠረም ሆነ የተረጋገጠ ታማሚ እንደሌለ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) በሽታ በዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ አማካይነት የሚመጣ ሲሆን፣ በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት የሚችል በሽታ ነው፡፡ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ ዕብጠት፣ የጡንቻና የጀርባ ሕመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣት ከበሽታው ምልክቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ ልቅ ግብረ ሥጋ ግንኙነትን ጨምሮ ንክኪ የበሽታው መተላለፊያዎች ናቸው፡፡
ጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የቅድመ ዝግጅት፣ የቅኝትና የምላሽ እንዲሁም የድንበር ጤና ልየታና አገልግሎት ሥራዎችን የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያና ምላሽ ማዕከል በማቋቋም እየሠራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በተለይም ደግሞ በኬንያ አዋሳኝ ሦስት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ የመውጫና መግቢያ ኬላዎች እንዲሁም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከወትሮው በተጠናከረ ሁኔታ የቅኝትና የልየታ ሥራዎች እየተተገበረ ይገኛል ብሏል፡፡ በሽታው በቀጥታ ከሰው ወደ ሰው በንክኪ የሚተላለፍ እንደመሆኑ መጠን፣ ምልክቶችን የሚያሳይ ማንኛውም ሰው በአቅራቢያው በሚገኝ የጤና ተቋም ሪፖርት እንዲያደርግ፣ ወይም በ952 እና 8335 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲያደርግ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ስለ ወረርሽኙ እየተሰጠው የሚዲያ ሽፋን እዚህ ግባ የማይባልና በመግለጫ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ሊታረምና ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የግድ ወረርሽኙ ሀገራችን መግባትና ሰዎችን መግደል መጀመር የለበትም። ለመከላከል በስፋት ማስተማርና መቀስቀስ ያሻል። በዚህ ከተግባባን አዘጋገቡ ከተለመደው አሠራር ወጥተው የማብራራት ጋዜጠኝነት መርህን (Explanatory Journalism) መከተል ይመከራል፡፡
የሲኤንኤን “Reliablel Source” አዘጋጅ ብራያን ስቴልተር በዚያ ሰሞን ብዙኃን መገናኛዎች በተለይ ዋና ዋናዎቹ የዩናይትድ ስቴትስ ቴሌቪዥኖች፣ ጋዜጦችና ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን እንዴት እንደዘገቡትና መዘገብ እንዳለባቸው ከሙያው ጎምቱዎች ዳን ራዘርንና ካርል በርኒስቲን፣ ከአንጋፋዎቹ የአሶሼትድ ፕሬስ (ኤፒ) ሳሊ ቡዝቤንን፣ የዎል ስትሬት ጆርናሉን ማት መሪ ጋር መክሮ ነበር፡፡ ይህ ተሞክሮ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝን ለመከላከል ቀምረን ልንጠቀመው ይገባል።
አንጋፋዋ የአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ሳሊ ቡዝቤን ‹‹ወረርሽኝ የማብራራት ጋዜጠኝነት ጎልቶና ገዝፎ የሚወጣበት ትልቅ ሁነት ነው፡፡ (Pandemic is The Olympic of Explanatory Journalism) ብላለች፡፡ ኦሎምፒክ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ፣ ከ200 አገሮች የተወከሉ እስከ 20 ሺሕ የሚጠጉ አትሌቶች የሚሳተፉበት፣ ለአሸናፊ አትሌቶች ከፍ ያለ ዕውቅና ከማስገኘቱ ባሻገር ለቀጣይ ስኬት መስፈንጠሪያ ስለሆነ፣ ለዝግጅቱ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚወጣበት፣ ከዓለም ዋንጫ ባልተናነሰ የስፖርታዊ ውድድሮች ሁሉ ቁንጮ ስለሆነ ነው እንግዲህ የማብራራት ጋዜጠኝነት አልፎ አልፎ ለሚከሰት ወረርሽኝ፣ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ዘገባ ፍቱን መድኃኒቱ ነው ያለችው፡፡ ለመሆኑ የማብራራት ጋዜጠኝነት ምንድነው?
ለአንባቢያን በሚገባ ቀላልና ግልጽ ዓረፍተ ነገር፣ እንግዳ የሆኑ ሐሳቦችንና ውስብስብ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች የሚዘገቡበት የጋዜጠኝነት ዓይነት ነው፡፡ የብሩኪንግስ የኮሙዩኒኬሽን ተባባሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ፋዋል፣ “Explanatory Journalism Cure the Internet?” በሚል ባስነበበን መጣጥፍ፣ የማብራራት ጋዜጠኝነት አንድን ጉዳይ ግልጽ፣ ቀጥተኛና ተደራሽ በሆነ አግባብ መዘገብ ነው፡፡ የዕዝራ ክሌንስን ቮክስ፣ የኒውዮርክ ታይምስ ‹‹ዘ አፕሾት››፣ የቡዝፊድና የብሉምበርጉ ኩይክቴክን በአብነት ይጠቅሳል፡፡ የማብራራት ጋዜጠኝነት በመረጃ ላይ የተመሠረተ ምክንያታዊ ዘገባ ለአንባቢያን ለማድረስ ከማገዙ ባሻገር፣ እግረ መንገድ የኅትመት ጋዜጠኝነትን መሠረታዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ዕገዛ እንደሚያደርግ ያስረዳል፡፡
ሌላው የዚሁ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ቶማስ ኢ ማን ዛሬ እንደ አዲስ የማብራራት ጋዜጠኝነት እየተቀነቀነ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. ከ1985 ጀምሮ ፑሊትዘርን ያሸለመ የጋዜጠኝነት ዘርፍ መሆኑን ያስታውሳል፡፡ መረጃ ማዛባት በገነገነበት በዚህ የኢንተርኔት ዘመን እንደ ፈጣን መፍትሔም እየተወሰደ ይገኛል ይለናል፡፡ ቮክስ ከአምስት ዓመታት በፊት በዲዝኒላንድ ፓርክ የኩፍኝ ወረርሽኝ መቀስቀሱን ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ሁሉ በማሟላትና ግልጽ በሆነ ቋንቋ፣ ሙያዊ አገላለጾችን (ጃርገንስ)፣ ቀላል በሆነ ገለጻ በመተካትና መረጃ ሳያዛባ ያጠናቀረውን ዘገባ ፋዋል በምሳሌነት ይጠቅሳል፡፡
በዘገባው ኩፍኝ በተባለው አደገኛ ተላላፊ በሽታ በክትባት ላይ የተከፈተው የሴራ ዘመቻ የተነሳ ልጆቻቸውን የሚያስከትቡ ወላጆች መቀነስ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰዎች እንቅስቃሴ መጨመር ለወረርሽኙ በፍጥነት መዛመት አስተዋጽኦ እንደነበረው በአብነት ያነሳል፡፡ የማብራራት ጋዜጠኝነት የዜናዎችን ትክክለኛ መሆን አለመሆን ከማጣራት ባሻገር፣ በየደቂቃው የሚዥጎደጎደውን ዜና ከተዘገበበት ዓውድ አንፃር አንባቢ፣ አድማጭ፣ ተመልካችና ተከታይ በቀላሉ እንዲደርሰውና እንዲገነዘበው በማረቂያነት ያግዛል፡፡ በተጨባጭ መረጃና በአኃዝ የበለፀገ የጋዜጠኝነት ዓይነት ቢሆንም ለእውነት ወግኖ ከመሞገት ወደኋላ እንደማይል፣ ፖሊሲዎችን ከታሪካዊ ዓውዳቸውና ከአኃዛዊ መረጃዎች ጋር በማዋሀድ እንደሚያፍታታም ይገልጻል፡፡
የኮሎምቢያ ጆርናሊዝም ሪቪው (ሲጄ አር) ጋዜጠኛ አሌክሳንድሪያ ኔሰን “In a Pandemic, What is Essential Journalism?” በሚለው ጽሑፏ፣ የማብራራት ጋዜጠኝነት አሁን እንደምንገኝበት ዓይነት ክፉ ቀን ሲመጣ ጋዜጠኞች ጠቃሚ መረጃ በማሠራጨት ብቻ ሳይወሰኑ፣ መመርያ ሰጪ በመሆን ወደ ጋዜጠኝነት ጥንተ መሠረታቸው ይመለሳሉ፡፡ አድማጭ ተመልካቹ፣ አንባቢውና የማኅበራዊ ድረ ገጾቻቸው ተከታይ ምን ማድረግ? እንደሌለበት? መረጃና ዕርዳታ ሲፈልግ ማን ዘንድ መደወል እንዳለበት፣ ምን እንደሚፈልግ፣ የት መሄድ እንዳለበት አቅጣጫ ያመላክታል፡፡ በግል፣ በድርጅትና በመንግሥት ሚዲያዎች ስለዝንጀሮ ቫይረስ የሚዘገቡ ዜናዎች ምን ያህል የሚያብራሩ እንደሆነ፣ በእነዚህ አላባውያን አማካይነት መመዘን እንችላለን፡፡
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም