የግንዛቤ እጥረት የሚስተዋልበት የወሊድ ክትትል አገልግሎት

በኢትዮጵያ በዓመት ወደ 14 ሺህ የሚጠጉ እናቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ህይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

እ.ኤ.አ በ2017 በተባበሩት መንግሥታት በወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየውም በየዓመቱ በዓለማችን 295 ሺህ የሚሆኑ እናቶች ከእርግዝና፣ ወሊድና ድህረ ወሊድ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ይሞታሉ። ከእነዚህም ውስጥ 94 በመቶ የሚሆኑት የእናቶች ሞት በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ውስጥ ነው።

የእናቶች ሞት በእርግዝና ጊዜ ወይም ከወሊድ በኋላ ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚከሰቱትን የጤና ችግሮች ወይም በእርግዝናው ምክንያት ሊባባሱ በሚችሉ ብሎም በህክምና አገልግሎት ችግር ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡፡

በእርግዝና እና ወሊድ ጊዜ የሚከሰቱትን የጤና ችግሮች ለመቅረፍም በዋነኝነት የቅድመ የወሊድ እና የድህረ ወሊድ ክትትክ አገልግሎት በትክክለኛ ጊዜ እንዲሁም ብቁ በሆኑ የጤና ባለሙያዎች መሰጠት አለበት።

የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ጤናማ የእርግዝና ጊዜ ማሳለፍ አስፈላጊ ቢሆንም በአብዛኛው በሀገራችን ማህበረሰቦች ዘንድ የቅድመ ወሊድና ድህረ ወሊድ ክትትሎችን በጤና ማዕከላት ውስጥ የመከታተል ባህል ዝቅተኛ ነው፡፡

ታዲያ ለዚህም ዋናው መንስኤ የግንዛቤ እጥረት በመሆኑ ስለ እናቶች የጤና ክትትል አስፈላጊነት በተለያየ መልኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፤ እየተሠሩም ነው፡፡

በጤና ሚኒስቴር ብሄራዊ የእናቶች ጤና ፕሮግራም አስተባባሪ ሲስተር ዘምዘም መሀመድ እንደሚገልጹት፤ እናቶች ነፍሰጡር መሆናቸውን ከባለቤታቸው ውጭ አይናገሩም፡፡ በጤና ተቋማትም ክትትልም የማድረግ ባህላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡

ይህም በዋነኝነት ከግንዛቤ እጥረት እና ከአመለካከት ክፍተት የተነሳ የሚፈጠር በመሆኑ ከዚህ አይነት ባህል ውስጥ የምንወጣበት መንገድ መፈጠር አለበት ይላሉ፡፡

በመሆኑም ነፍሰጡር እናቶችን ተሳታፊ ያደረጉ እዝናኝና አስተማሪ መርሀ ግብሮች መዘጋጀታቸው በቂ ግንዛቤ በመፍጠር እናቶች ወደ ጤና ተቋማት ለመምጣት እንዲወስኑ በማድረግ በኩል ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ነፍሰጡር እናቶችን በማሳተፍ የሚሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እናቶች የጤና ክትትል እንዲያደርጉ መንገድን የሚያመላክት መሆኑን በመጥቀስ፤ መሰል መርሀ ግብሮች አባቶችን የሚያሳትፉበት ዕድል ቢፈጠር የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚረዳ አመላክተዋል፡፡

የቅድመ ወሊድ ክትትል አንዲት እናት ባረገዘች በ12 ሳምንት ወይም 3 ወር ጊዜ ውስጥ ክትትል ማድረግ መጀመር እንደሚኖርባት ጠቅሰው፤ በዚህም የሥነ-ምግብ እና ምክር አገልግሎት፣ የጤና ምርመራ፣ የክትባት፣ የምክር አገልግሎት በመስጠት በእርግዝና ወቅት ጥሩ አቋም እንዲኖራት የሚሠራ መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡

በፊት አራት ጊዜ ብቻ ይሰጥ የነበረው የቅድመ ወሊድ ክትትል አሁን ስምንት እና ከዚያ በላይ የተደረገ ሲሆን፤ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ የእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ሞት በመቀነስ በኩል የበለጠ ውጤት እንዲገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ሲስተር ዘምዘም እንደሚገልጹት፤ ሚኒስቴሩ ሁሉም እናቶች ባሉበት ቦታ የሚመጥናቸውን አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የሰለጠነ ባለሙያ ለማብቃት፣ ግብአት ማሟላት፣ የጤና ተቋማትን ማስፋፋት እየተሠራ ይገኛል። የጤና ተቋማት ተደራሽ ለማድረግም በማይቻልባቸው አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የጤና እና ሥነምግብ ባለሙያ ቀጥሮ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡

የቅድመ እርግዝና፣ ቅድመ ወሊድ እና ድህረ ወሊድ የጤና አገልግሎት በጤና ተቋም እንዲያገኙ ማስቻል መጨረሻው ጤናማ እናትነት የሚቋጭ ነው የሚሉት አስተባባሪዋ፤ ሁሉም እናቶች ይህንን በመገንዘብ ተሳትፎአቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

በዘርፉ መርሀ ግብሮችን የሚያዘጋጀው የታዋቂ ኢቭንትስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል አበራ በበኩላቸው፤ የነፍሰጡር እናቶች የጤና ክትትል ግንዛቤን የማሳደጉ ዓላማ በሀገሪቱ በስፋት እየተስተዋለ የሚገኘውን የእናቶች ህይወት ማለፍን ለመቀነስ ነው፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫው ነፍሰጡር እናቶች የሚሳተፉበት የነፍሰጡር እናቶች የቁንጅና ውድድር እንዲካሄድም ይደረጋል፡፡

ውድድሩ ነፍሰጡሮች ምቾታቸው ተጠብቆ ጊዜ እንዲያልፍ ከማድረግ በተጨማሪ ለተለያዩ ስሜቶች ተጋላጭ የሆነውን የእርግዝና ጊዜያቸውን በተዝናኖት የሚያሳልፉበት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 /2016 ዓ.ም

Recommended For You