ተቋማትን ከማጠልሸት ጀርባ ያሉ ስውር ደባዎች

ጠንካራ ተቋማት የጠንካራ ሀገር መሰረቶች ናቸው። የጠንካራ ተቋማት ባለቤት የሆኑ ሀገራት ጽኑ መሰረት ያላቸው በመሆኑ ሀገርን ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሸጋግራሉ፤ የሀገርን ገጽታ ይገነባሉ፤ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖም ይፈጥራሉ፤ ቋሚ አምባሳደር ሆነውም ሀገርን ያስተዋውቃሉ። በአጠቃላይ የሀገር መለያ ሰንደቅ ዓላማ ተደርገው ይወሰዳሉ።

ይህንኑ በመረዳት ኢትዮጵያም ዘላቂ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት ጥረት በማድረግ ፩ ላይ ትገኛለች። መንግስት በተቀያየረ ቁጥር የማይቀያየሩ፤ ዛላቂነት ያላቸውና በየትኛውም ግዜና ቦታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው የሚያስተዋውቁ ተቋማትን ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። በዚህ ረገድም ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያገኙ ተቋማት ከመኖራቸውም ባሻገር ከወዲሁም የብዙዎችን ቀልብ መሳብ የቻሉና ከኢትዮጵያም አልፈው አፍሪካን ማኩራት የሚችሉ ተቋማትም ብቅ ብቅ እያሉ ነው።

ዓለም አቀፍ እውቅናን ካገኙና ከኢትዮጵያ አልፈው የአፍሪካ ኩራት ከሆኑ ተቋማት ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር የማይዋዥቅና ጥንካሬውንም አስጠብቆ ከዘመን ወደ ዘመን መሸጋገር የቻለ የጠንካራ ተቋማት ምሳሌ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢንዱስትሪው የአቪዬሽን ኦስካር ተብሎ በሚጠራው የስካይትራክስ መድረክ ለ7ኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ሽልማትን አሸንፏል። አየር መንገዱ በተጨማሪም የአፍሪካ ምርጥ የቢዝነስ ክፍል አየር መንገድ ሽልማትን ለ6 ተከታታይ ዓመታት ማሸነፍ ችሏል።

እንዲሁም አየር መንገዱ የአፍሪካ ምርጥ የኢኮኖሚ ክፍል አየር መንገድ ሽልማትን ለ6 ተከታታይ ዓመት ለማሸነፍ በቅቷል። ከዚህ ባለፈም በአፍሪካ የኢኮኖሚ ክፍል ምርጥ ምግብ አገልግሎት ሰጪ አየር መንገድ ሽልማትን አሸንፏል።

ሆኖም ይህ የአፍሪካ ኩራት የሆነው አየር መንገድ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች በተደረገ ቅንጅት ስሙን የማጥፋት ዘመቻ ከተከፈተበት ሰነባብቷል። የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና የማይመኙ ሀገራት ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመተባበር በረባ ባልረባው የአየር መንገዱን ስምና ዝና የማጠልሸት ደባ ውስጥ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፍና ዘመናዊ የአቪየሽን ዘርፍ ነው። በተወዳደረበት መስክ ሁሉ የሚያሸንፍና ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ኩራት የሆነ ተቋም ነው። ሆኖም ከዚህ ግዙፍ አየር መንገድ ጋር ተወዳድረው ማሸነፍ ያልቻሉና አልፎ ተርፎም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መጉዳት የሚፈልጉ ሀገራትና አካላት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአየር መንገዱን ዝና ለማጠልሸት በርካታ ዘመቻዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ጥቂቶቹን ለማስታወስ ሰኞ ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም. ከሱዳን የተነሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን አብራሪዎች “እንቅልፍ ጥሏቸው” መዳረሻቸውን አልፈው እንደነበር የሚያወሳ ዘገባ ተሰራጭቶ ነበር። በተደረገው ማጣራትም ዘገባው ሀሰት መሆኑ ተደርሶበታል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምሥል አንዲት ተሳፋሪ በአየር መንገዱ ሠራተኞች ከአውሮፕላኑ እንድትወርድ ስትጠየቅ እና ተሳፋሪዋ አልወርድም እያለች ከሠራተኞቹ ጋር የምታደርገውን የተካረረ ክርክር የሚያሳይ ምስል ተጋርቶ ነበር። ይህንን ጉዳይ በዋነኛነት ታዋቂው ኬንያዊ የሲንኤንኤን ጋዜጠኛ ላሪ ማዶዎ ጉዳዩን ከልክ በላይ ሲያጦዘው ነበር። ይህ ጋዜጠኛ በዚህ ልክ ጉዳዩን ማጦዙ ከጋዜጠኝነት ሙያው ይልቅ ጉዳዩን መወዳደር የተሳነውን የኬንያን አየር መንገድ በአቋራጭ ለመጥቀም የተደረገ ሴራ መሆኑን ልብ ይሏል።

ሰሞኑን ደግሞ በአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያት ወደ መቀሌ የሚጓዝ የሀገር ውስጥ በረራ ጉዞ መቋረጥን ምክንያት በማድረግ አየር መንገዱን የሚያብጠለጥሉ ሰዎች ስድብና ዛቻ የማህበራዊ ሚዲያው ዋነኛ አጀንዳ ነበሩ።

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን አየር መንገድ ዝና ጥላሸት ለመቀባት የሚደረጉ ጥረቶች በተቀናጀ መልኩ እየተፈበረኩ ነው። ከግለሰቦች አልፎም ሀገራት ጭምር ጥቃቅን ሰበቦችን እየፈለጉ የአየር መንገዱን ዝና የሚያወርዱ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ለመመልከት ችለናል።

ሆኖም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመን ተሻጋሪ ልምድ እና እውቀት ያለው ተቋም በመሆኑ በወሬ የሚረታ ቁመና የለውም። ስለሆነም እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አንግቦ በአፍሪካ ሰማይ ላይ ይነግሳል።

ሌላኛው የስም ማጥፋት ሰለባ እየሆነ ያለው ተቋም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት 116 ዓመታትን ያስቆጠረ ዕድሜ ጠገብ ተቋም ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጀግንነት መለያው፤ ድል ማድረግ ዓርማው ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና የማይደረምሰው ተራራ፤ የማይወጣው አቀበት፤ የማያሸንፈው ጠላት የለም። ይህን እንኳንስ ወዳጅ ጠላትም የሚመሰክረው ነው።

ሆኖም የውጭና የውስጥ ጠላቶች በመቀናጀት የሰራዊቱን ስም ለማጠልሸት ሲሯሯጡ ይታያሉ። ሰራዊቱ ያለመገለጫውና ያለተግባሩ መገለጫ ለመስጠትና ለማጠልሸት የሚሞክሩ የውጭ ጠላቶችና በገንዘብ የተገዙ ባንዳዎች ብዙ ናቸው። ሆኖም ከሕዝብ አብራክ የወጣውና የጀግኖች ስብስብ የሆነው የመከላከያ ሰራዊት በወሬና በአሉባልታ የሚረታና የሚናድ አይደለም።

ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በድል ላይ የድል አክሊል እየደረበ የሕዝብ ጥቅምንና የሀገር ሉአላዊነቱን የማስጠበቅ ቁመና ከምንግዜውም በላይ ጎልብቶ ይገኛል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሕዝብ አብራክ የወጣ በመሆኑ ሁልጊዜም ሕዝባዊና ሀገራዊ ተልዕኮዎችን አንግቦ ይንቀሳቀሳል። የሀገሪቱን ሉአላዊነትን ለማስከበርና የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ መስዋዕትነትን ይከፍላል። በዱር በገደሉ ይዋደቃል። ደሙን ያፈሳል፤ አጥንቱን ይከሰክሳል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ያስቀጥላል።

እንደ አየር መንገድ እና የመከላከያ ሰራዊት ሁሉ የውጭ ጠላቶችና የሀገር ውስጥ ባንዳዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ የተከፈተበት ሌላኛው ተቋም የአባይ ግድብ ነው። የአባይ ግድብ በአፍሪካ ግንባር ቀደሙ የኃይል ማመንጫ ሲሆን ግድቡ ከኃይል ማመንጫነቱ በሻገር የአይበገሬነትና የአልሸነፍ ባይነት ተምሳሌትም ተደርጎ ይወሰዳል።

እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 2003 ላይ ጅማሬው የተበሰረው የአባይ ግድብ ከ15 ዓመታት በኋላ ወደ ፍጻሜው ተቃርቧል። ሆኖም ግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳታጠናቅቅ በብዙ ተደክሟል።

በተለይም የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድር ሁሌም እንከን እንዲኖረው በግብጽ በኩል በብርቱ ሲሰራበት ሰንብቷል። ከመነሻው ጀምሮ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም አይነት የልማት ሀሳብ እንዳይኖራት ለዘመናት ስትባዝን የኖረች ግብጽ፣ የሕዳሴ ግድቡ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ በኢትዮጵያ ላይ የማስፈራሪያና የማስጠንቀቂያ ዶፍ ስታዘንብ መክረሟ የሚታወቅ ነው።

ከማስፈራራትና ከያዙኝ ልቀቁኝ በኋላ ዶሴዋን በመያዝ፤ ‘ ሲሆን ሲሆን ግድቡ እንዳይገነባ በማደርገው ጥረት ከጎኔ ይቆማሉ፤ ካልሆነም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ያሳድሩልኛል’ ወዳለቻቸው አካላትም፤ አገራትም ዘንድ ተንከራትታለች። ይሁንና ኢትዮጵያ በግብጽ ግልምጫም ሆነ ዛቻ እንዲሁም በሌሎቹ አገራት ጫና ከአቋሟ ዝንፍ ሳትል ግንባታዋን ሌት ተቀን ስታስኬደው ከርማለች።

ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ያጋጠማት ፈተና በርከት ያለ ከመሆኑም በላይ በየምክንያቱ ብዙ ነገሮችን እንድታጣ ተደርጋለች። በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ኢኮኖሚዋ እንዲዋዥቅ በብዙ ተጥሯል። ምክንያቱ ሌላ ይምሰል እንጂ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር ባሉ ዜጎቿ ጫና ተፈጥሯል።

ግብጽ የሕዳሴ ግድቡን ወደጸጥታው ምክር ቤት በማመላለስ ኢትዮጵያ በብዙ ጫና ውስጥ እንድታልፍ ከማድረጓም በተጨማሪ ሐሰተኛ በሆነ መረጃዋ፤ አንዳንድ አቅላቸውን በሳቱ አካላት ግድቡ በቦንብ እንዲጋይ እስከማሰብ ተደርሷል። ስለ ዓባይ ግድብ ምንም የማያገባው የአረብ ሊግም በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል።

ከዚህ በሻገርም በሀገር ውስጥ ጭምር ሰዎችን በገንዘብ በመግዛት ሁከትና ረብሻ እንዲስፋፋ እና ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ በብዙ ተደክሟል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶር) ሰሞኑን እንደተናገሩት ከሞላ ጎደል 15ሺ የሚሆኑ በገንዘብ የተገዙ ሰዎች የሕዳሴውን ግድብ ለማስተጓጎል በኢትዮጵያ ተሰማርተው ነበር። እነዚህ ሰዎች በየሚዲያው በመውጣት፤ በየማህበራዊ ሚዲያውና በየዩቱቡ በመገኘት ያልተቋረጠ አሉባልታና ስም የማጥፋት ዘመቻ ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ አሁንም በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ የአባይ ግድብ ከዳር እንዳይደርስ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ሲያደርሱት የነበረውን ተጽዕኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚከተለው ገልጸውት ነበር። ‹‹ሲሚንቶ ከማምረት አጓጉዞ እዚህ ቦታ እስካለው ሥራ 15 ሺህ የሚጠጋ የተለያየ ስም ያላቸው በመነሻነት የኛ የሆኑ፤ ግን የተገዙ፣ የተሸጡ ሰዎች ይሄ ሥራ አሁን ያለበት ደረጃ እንዳይደርስ፣ እንዳይቋጭ ብዙ ጊዜ እና ገንዘብ ሕይወት አጥፍተዋል።

ብዙ አልተናገርንም፤ ምክንያቱም ለንግግር አይመችም። አሁንም ዘርዝሬ አልገልጸውም። ነገር ግን ሰው ለግንዛቤ እንዲያመቸው አንድ ተርባይን ሲመረት፣ ሲገዛ፣ ከፋብሪካው ጅቡቲ እስኪደርስ ያለውን ጣጣ ትቼ ያው ገንዘቡም ችግር ነው። ከተመረተም በኋላ ጅቡቲ ማድረሱም ከባድ ነገር ነው። እሱን ትቼ ከጅቡቲ ወደብ ያለውን ሂደት ጨርሼ እዚህ ቦታ ለማድረስ ምን ያክል ቀን የሚወስድብን ይመስላችኋል፤ በትንሹ 45 ቀናት አካባቢ ይፈጅብናል። አንድ ተርባይን ከጅቡቲ ተነስቶ እዚህ እስኪመጣ በዝቅተኛ 25 ኪሎ ሜትር በቀን ይጓዛል በጣም በከፍተኛ ከተጓዘ 40 ኪሎ ሜትር በቀን ይጓዛል።

በየ40 ኪሎ ሜትሩ እያደረ ነው የሚመጣው፣ ከዚህ ጅቡቲ ስንት እንደሆነ ማስላት ይቻላል። በየ40 ኪሎ ሜትሩ አንድ አንድ ቀን ይፈጅበታል። ትልቅ ነው መኪናው የተለየ ነው። በፍጥነት መጓዝ አይችልም በጣም ሳይፈጥን እንደ ሰው ቀስ እያለ ነው የሚጓዘው አንድ ተርባይን ከጅቡቲ አንቀሳቅሰን እዚህ ለማድረስ 45 ቀናት ይፈጅብናል። ይህ በመደበኛው መንገድ መኪኖቹ ምንም እንቅፋት ሳይገጥማቸው ሲጓዙ ነው።

ነገር ግን ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ተርባይኑ ቀርቶ ሲሚንቶ ከደርባ እዚህ ስናመጣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እያዳንዱን መንገድ አስፓልት ስላልሆነ ለእያንዳንዱ ትራክ ፈንጂ እየለቀመ አልፎ አልፎም አደጋ ሲያጋጥም እየተጋፈጠ ፈንጂ እየለቀመ ነው የሚጓዘው። ከደርባ ተጭኖ ዝም ብሎ እዚህ አይደርስም።

አንዳንድ ጊዜ 20፣30ና 40 መኪና እየጫነ፣ እያዳንዷን መኪና እየፈተሸ ነው ትራንስፖርት አድርገው እዚህ የሚደርሱት። ፈንጂ ስለሚቀበር በየመንገዱ። መሀል ላይ መንገድ ተበላሽቶብን ነበር መንገዶቹ ፒስታ ስለነበሩ ተበላሽተው ጠጋኝ ኮንትራክተር አላገኘንም፣ ብዙዎቹ ኮንትራክተሮች ካለው መሠረታዊ ችግር አንጻር አልፈለጉትም።

መከላከያ መንገድ እየጠገነና እየሠራ ፈንጂ እየለቀመና ትራንስፖርት እያደረገ በየቦታው ደግሞ የሚያጋጥመውን ችግር እየተዋጋ ነው ይህንን ግድብ ያጠናቀቀው። ብዙ አልቅሰንበት፣ ደክመንበት፣ ደምተንበት ነው የሠራነው።››ሲሉ የሁኔታውን አስቸጋሪነት አብራርተዋል።

ሆኖም የእነዚህ ሀገራትና እነሱ የላኳቸው ሰዎች ምኞት ሳይሞላ ኢትዮጵያውያን ግድቡን ወደ ማጠናቀቅ ደረጃ ደርሰዋል። ዛሬ የሕዳሴ ግድብ ወደ ኋላ ከ205 እስከ 210 ኪሎ ሜትር ተኝቷል። ዛሬ የሕዳሴ ግድብ ወደታች ጥልቀቱ መቶ 133 ሜትር ደርሷል። ዛሬ ሕዳሴ ግድብ የጣናን ሀይቅ እጥፍ አድጓል። ጣና እስከ 30 ቢሊዮን ነው። ይሄ 62 ነጥብ አምስት ነው፤ ደብል አድርጓል። የጣና ውሃ ስፋቱ ብቻ ሳይሆን በጣም ሻሎው ነው። 13፣ 14 ሜትር ነው ጥልቀቱ። ይሄ 133 ገደማ ሜትር ጥልቀት አለው። በጣም ጥልቅ ነው ማለት ነው። ወደታችም ወደኋላም ወደጎንም በጣም ሰፊ ስለሆነ የጣናን እጥፍ/ደብል ውሃ ሆኗል።

በአጠቃላይ ከጥንት እስከ ዛሬ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶች ከሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋር ተባብረው ኢትዮጵያን ለመበታተን መሄድ እስከሚችሉት ድረስ ተጉዘዋል። በተለይም ዘመን አመጣሾቹ የኢትጵያ ጠላቶች በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ በመቆም ጉዞዋን ለማደናቀፍ በብዙ ደክመዋል። ጠንካራ ተቋማትን በማጠልሸት የኢትዮጵያን የእድገት ጉዞ ለማሰናከል ከጠላት ጋር አብረው ትውልድ ይቅር የማይለው ደባ ፈጽመዋል።

የውጭና የውስጥ ጠላቶች በአንድነት በማህበር ለሀገሪቱ መደከምና በሂደትም መፈራርስ አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚሉትን ኃይል በማደራጀት፤በማስታጠቅና በማሰልጠን ታሪካዊ ጠላትነታቸውን በገሃድ ሲያስመሰክሩ ነሮዋል::

እነዚህ የውጭና የውስጥ ጠላቶች የዚህን ኩሩ ሕዝብ የዘመናት ዕሴቶች ለመናድ ከመሯሯጣቸውም በሻገር የሀገሪቱ መሰረት የሆኑ ተቋማት እንዲዳከሙና አለፍ ሲሉም እንዲከስሙ በብዙ ሰርተዋል። ሆኖም በጠንካራ አመራርና በኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ጥረት ተቋማቱ ከሀገር ውስጥ አልፈው ለሌሎች ሀገራትም አለኝታ በመሆን የድል አክሊል ተጎናጽፈዋል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You