አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ፤- በድንገት ያጣነው የኪነጥበብ ባለሙያ

ሃገራችን የበርካታ የኪነጥበብ ሰዎች መፍለቂያ ናት:: ያም ሆኖ ግን በሰሩት ልክ ያልተዘከሩና ያደረጉትን አበርክቶ ያህል ያልተወደሱና ያልተወራላቸውም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። ከእነዚህ መካከል ተዋናይ፣ ደራሲና የትያትር አዘጋጅ ኩራባቸው ደነቀ አንዱ ነው።

አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ በ1957 ዓ ም በሐረር ከተማ ልዩ ስሙ ሸንኮር በሚባለው መንደር ውስጥ ነበር የተወለደው። በቤተሰቦቹ የሥራ ዝውውር ምክንያት ወደ አሰበ ተፈሪ የአሁኗ ጭሮ ከተማ በህፃንነቱ በመምጣቱ የቄስ ትምህርቱን፣ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚገባ ተከታትሎ ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግባት የሚያስችል ውጤት በማግኘት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቲያትር ዲፓርትመንትን ተቀላቀለ።

በልጅነቱ የነበረውን ኪነጥበባዊ ዝንባሌና ተሰጥኦውን ያስተዋሉ ቤተሰቦቹም ሆኑ አብሮ አደጎቹና የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚሰጡት ማበረታቻ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታው በድራማ እና በሙዚቃ ክበባት የነበረው ተሳትፎ ላይ ያሳየውን ችሎታ ባጤኑት መምህራን ዘንድ ሁሌም ግንባር ቀደም ተመራጭ ነበር።

በ1970 ዓ.ም የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለ የ01 ቀበሌ የወጣቶች ማኅበር የኪነት ቡድን ሲያቋቁም ቀዳሚ ሆኖ ቡድኑን በመቀላቀል በውዝዋዜ፣ በዘማሪነት እና በድምፃዊነት መሳተፍ ጀመረ።

የኩራባቸው ደነቀ የነፍስ ጥሪ ግን በድራማው ዘርፍ በተዋናይነት መሳተፍ ነበር። በጊዜው በድራማው ዘርፍ የሚሳተፉት በዕድሜያቸው ከፍ ከፍ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና መምህራን ነበሩ። በወቅቱ የኢህአፓ መዋቅር ተመትቶ ከእስር የተፈቱት አባላት “ወጣቱና ትግሉ “ የተሰኘ ቴአትር ወቅቱ ሳያልፍ ለማቅረብ እያዘጋጀ ጥድፊያ ላይ ነበረ።

በዚህ ጊዜ የትምህርት ፈረቃው የከሰዓት በፊት የነበረው ኩራባቸው ደነቀ የቴአትሩ ልምምድ ከሰዓት በኋላ ስለነበር ከትምህርት ቤት እንደተለቀቀ ለምሳ ወደቤት ሳይሄድ በቀጥታ ልምምዱ ቦታ በየዕለቱ በመገኘት ሲለማመዱ ያይ ጀመር። ከጥቂት ቀናት በኋላም አንዱ ተዋናይ እያረፈደ ሲያስቸግር እስኪመጣ የሱን ገፀባህርይ እያነበበ እንዲሸፍንለት አዘጋጁ ታዳጊውን ይጠይቀዋል።

የተዋናዩ ማርፈድ መቅረትም ቀጠለ። ጊዜ የሌለው አዘጋጁ ተጨነቀ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ለመተወን የተራበው ታዳጊ እንደተለመደው ለመሸፈን ሲወጣ ያን ቀን የተውኔቱን ፅሁፍ ሳይዝ ባዶ እጁን ወጣ። ተዋንያኑም አዘጋጁም አላመኑም። ያለምንም መሳሳት ተጫወተው። አዘጋጁ በመደሰቱ ገፀ-ባህሪውን እንዲጫወት አፀደቀለት። ሁሉም አበረታቱት። የቴአትሩ ማቅረቢያ ቀንም ተቆርጦ ለተመልካች ቀረበ። አተዋወኑም በተዋናዩ፣ በአዘጋጁ እና በተመልካቹ ተወደደለት። ከፍተኛ ሞራል እና አድናቆትም ጎረፈለት።

ጉዞ ወደ ዩኒቨርሲቲ

በ1976 ዓ ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናውን ግቢ ስድስት ኪሎ ሲቀላቀል የቴአትር ጥበባት ዲፓርትመንት መኖሩን እንኳ የማያውቀው ኩራባቸው ደነቀ ቀደም ካሉት የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ከሆኑት የአሰበ ተፈሪ ልጆች ‘ አንተማ ቴአትር አርትስ ነው መግባት ያለብህ ‘ በሚል በርካታ አስተያየት ነበር አቀባበል የተደረገለት።

በዓመቱ የዲፓርትመንት ምርጫ ሲያደርግም ሳያወላውል አንደኛ ምርጫው አድርጎ በሞላው የቴአትር ጥበባት የትምህርት ክፍል ተመድቦ በመማር በ1979 ዓ ም በጥሩ ውጤት ለመመረቅ በቅቷል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን የባህል ማዕከል አባል በመሆን በተለያዩ ቴአትሮች ላይ በተዋናይነት በመሳተፍ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አቅርቧል። በ1980 ዓ ም ወደ ሥራው ዓለም የተቀላቀለው ከዘመቻ መምሪያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተመድቦ በዕጣ ወደ ደረሰው ጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር አርባምንጭ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት በጀማሪ የቴአትር ኤክስፐርትነት በመሄድ ነበር።

በአርባምንጭ የነበረው የሁለት ዓመታት ቆይታም የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ወጣቶችን ያበረታታ ነበር። በተለይ ከአርባምንጭ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር ለድራማ ክበብ አባላትና ለከተማዋ አማተር ባለሙያዎች ስለቴአትር ጥበብ በሰጠው ሥልጠና በሙያው የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉና ከተማሪዎቹ ጋር ባሳለፈው ጊዜ ያገኘው ልምድ አንዱ እንደሆነ አበክሮ ይገልፃል።

በአርባምንጭ የነበረው ቆይታ አሁን ላለው ችግርን በፅናት የመቋቋም ጥንካሬ መሠረቱና መልካም እንደነበረ ቢያምንም የነፍሱ ጥሪ ግን መቼ አዲስ አበባ ገብቶ አንዱ ቴአትር ቤት መድረክ ላይ የሚተውንበትን ጊዜ ይናፍቀው ነበር። ይህንንም ሕልሙን ለማሳካት ዝውውር ለመጠየቅ ወስኖ ቆርጦ ይነሳል።

በ1981 ዓ.ም ብቻ የተለያዩ ምክንያቶች በማቅረብ ከአስር ጊዜ በላይ አዲስ አበባ ዋናው መስሪያ ቤት እንደተመላለሰ ይናገራል። በመጨረሻም የመመረቂያ ፅሁፉን የሰራው ‘በኢትዮጵያ የህፃናት ጨዋታዎች ውስጥ የሚገኙ የቴአትር አላባውያን’ በሚል ርዕስ ላይ ስለነበር በወቅቱ አዲስ ለተከፈተው የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ባቀርብ ይቀናኝ ይሆናል በሚል ያደረገው ሙከራ ተቀባይነት አግኝቶ በ1982 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ እንደተመኘው አዲስ አበባ ገባ።

በወቅቱ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከጀርመን ኤምባሲ ጋር በመተባበር ዳይሬክተርና ስቴጅ ማኔጀር ከጀርመን በማስመጣት ‘የዝናቧ እመቤት ‘ የተሰኘ የጀርመን ተውኔት ወደ አማርኛ ተተርጉሞ እየተሰራ ነበር። እዚያ ሄዶ እንዲውል በመታዘዙ በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር እየተገኘ ልምምዱን መከታተል ይጀምራል።

አዘጋጁ ተዋንያኑን እያሰራ እያለ አንዳንድ የተዋንያኑ ስሜቶች ግር ሲሉት የአማርኛው ትርጉም ምን እንደሚል ኩራባቸውን ይጠይቀዋል። የተዛባ ነገር መኖሩን ሲረዳም ከጀርመንኛው ፅሁፍ ጋር እያመሳከረ እንዲያስተካከል እንዲያግዘው በማድረጉ ከዳይሬክተሩ ከፍተኛ የዝግጅት ልምድ እንዳገኘበት ይናገራል።

ከዚያም ሐረር በነበረበት ግዜ በቀበሌው ኪነት ቡድን ያጋጠመው ሁኔታ እዚህም ይከሰታል። ዋናውን ገፀባህርይ የሚጫወተው ተዋናይ እየቀረ በማስቸገሩ ፅሁፉን ይዞ እንዲሸፍን ዳይሬክተሩ ይጠይቀዋል። ከዚያም የቴአትሩ መክፈቻ ጊዜ በመቃረቡ ኩራባቸው ገፀ-ባህሪውን እንዲጫወት በመወሰኑ ልምምዱ ተጠናቆ ይመረቃል።

ከቴአትር ቤቶች ሥራ አስኪያጆች እና ከቴአትር ባለሙያዎች ያገኘው አድናቆትና ማበረታታት ለበለጠ ስኬት ጠንክሮ እንዲሰራ ሞራል ሆነው። ለሕፃናት መተወን የተዋናይ ከባድ ፈተና እንደሆነ የሚመሰክረው ኩራባቸው ይህም ለአዋቂ ተመልካች ቴአትር የመተወን አቅሙን እንዳጎለበተለት ይናገራል።

ከመደበኛ ሥራው ባለው ትርፍ ጊዜ ከሀይሉ ፀጋዬ፣ ከጀማነሽ ሰሎሞን፣ ከስንዱ አበበ፣ ከእፀገነት ተስፋዬ እና ከእናትፋንታ ውቤ ጋር በመሆን ንጋት የቴአትር ኢንተርፕራይዝ የተባለ ድርጅት በመመስረት ‘ቅርጫው’ የተሰኘ ቴአትር ባህል ማዕከል ተሰርተው በራስ ቴአትር አቅርቧል። ተውኔቱ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ታይቶ እጅግ ከፍተኛ አድናቆት ተወዳጅነት በማትረፉ ወደ ሰሜን አሜሪካ ተጋብዞ የሄደ ቴአትር ነበር።

ኩራባቸው በሀገር ፍቅር ቴአትር

ከሁለት ዓመት የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ቆይታ በኋላ ወደ አንጋፋው የሀገር ፍቅር ቴአትር ተዛውሮ በተዋናይነት እና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እየተመደበ በመስራቱ ከፍተኛ ልምድ ማካበት ችሏል።

በተለያዩ የመድረክ፣ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ድራማዎች ላይ በተዋናይነት እየተመደቡ መስራት የዘወትር ተግባሩ ነበር። ከዚህም በሻገር በተለያዩ ቴአትር ቤቶች የተለያዩ የመድረክ ቴአትሮች ማዘጋጀት በከፍተኛ ፍቅር የሚሰራው እና ከፍተኛ እርካታ የሚያገኝበት ዘርፍ ነበር።

የተለያዩ የመድረክ፣ የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ድራማዎችን መፃፍም ሌላው ነፍሱን የሚያረካት ሥራ ነበር። ከዚህ ባሻገርም በተለያዩ ቴአትር ቤቶች በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታዎች እየተመደበ የሰራባቸው ጊዜያትም ቢሆኑ ለሙያውና ለባለሙያው የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት አቅሙ የቻለውን ያደረገባቸው ጊዜያት በመሆናቸው ደስተኛ መሆኑን አርቲስት ኩራባቸው ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሮ ነበር።

በመድረክ ቴአትሮች ላይ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በትወና ከተሳተፈባቸው መካከል በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ‘የዝናቧ እመቤት ‘ እና ‘የገንፎ ተራራ’ ቴአትሮች፤ በሀገር ፍቅር ቴአትር ‘የጨረቃ ቤት’፣ ‘ዓይነ ሞራ’፣ ‘ንጉሥ ሊር’፣ ‘ፍሬህይወት’፣ ‘ጥሎሽ’፣ ‘አሉ’፣ ‘ጣውንቶቹ’፣ ‘ከራስ በላይ ራስ’ እና ‘የሸክላ ጌጥ’ ቴአትሮች፤ በቴአትርና ባህል አዳራሽ ‘የጫጉላ ሽርሽር’ ቴአትር፤ በራስ ቴአትር ‘ቅርጫው’ ቴአትር ይገኙበታል።

ከዳይሬክቲንግ ሥራዎቹ ካዘጋጃቸው የመድረክ ቴአትሮች ሲጠቅስ በሀገር ፍቅር ቴአትር ‘ስጦታ’፣’ጥሎሽ’ እና ‘መዳኛ’ ቴአትሮች፤ በቴአትርና ባህል አዳራሽ ‘ሶስና’፣’አንድ ክረምት’፣ ጥቁሩ መናኝ’ እና የጫጉላ ሽርሽር’ (ዝግጅት በተዋንያን ነበር) ቴአትሮች፤ በራስ ቴአትር ‘ትንታግ’ የተሰኘ ቴአትር በማዘጋጀት በተለይ በዚህ ሥራው የዝግጅት ከፍታውን ያሳየበት መሆኑን ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

ካዘጋጃቸው ሙዚቃዊ ድራማዎች መካከል በተለይ በአንጋፋዋ አርቲስት አስናቀች ወርቁ ሕይወት ላይ ተመስርቶ የተፃፈውና ያዘጋጀው ራሷ አስናቀች ወርቁ በትወና የተሳተፈችበት በራስ ቴአትር በ1990ዓ.ም ለአዲስ ዓመት የቀረበው ‘አስናቀች ኢትዮጵያ’ የተሰኘው ሥራ እጅግ የሚደሰትበት ስለመሆኑ፤ እንዲሁም ‘እስከመቼ’ በሚል ርዕስ በቴአትርና ባህል አዳራሽ የቀረበው ከሸገር ሰርከስ ቡድን አባላት ከቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች ጋር በጋራ የተሳተፉበት ዝግጅቱም አዲስ ልምድ ያገኘበት እንደሆነ ይናገራል።

ከፃፋቸው የሬዲዮ ድራማዎች ‘እናትና ልጆቹ’ የተሰኘው ተከታታይ ድራማ በ1990 ዓ.ም ለ47 ሳምንታት በኤፍ ኤም 96.3 ሬዲዮ ጣቢያ የተላለፈው እና ‘የመጨረሻዋ ሌሊት’ የተሰኘው ደግሞ በብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ ለሁለት ሳምንታት የተላለፈ ነበር።

በተጨማሪም በሀገር ፍቅር ቴአትር በ1994 ዓ.ም ፅፎ ያዘጋጀው ‘መዳኛ’ የተሰኘው የአዘቦት ቀን የቴአትር ድርሰቱ አዳዲስ ቴክኒኮችን የተጠቀመበት እና ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈለት ነበር።

አርቲስት ኩራባቸው በበርካታ የሬድዮ ድራማዎች ላይ በተለይም ደራሲ ሀይሉ ፀጋዬ በፃፋቸውና በቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም በተላለፉት በአብዛኞቹ ተሳትፏል። ለሁለት ሳምንታት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረቡ ‘ጩኒና ቾምቤ’የተሰኘ የሕፃናት ቴአትር እና ‘የማለዳ ጤዛ’ የተሰኘው ድራማ ይገኙበታል።

በተሳተፈባቸው የተመረጡ ጥቂት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ‘ገመና 1’ እና ‘ገመና 2’ ድራማዎች ብዙ አድናቂዎች ያፈሩለት መሆኑንና በተለይም በቅርቡ በሳምንት ሦስት ቀናት በ48 ክፍሎች ቀርቦ በተመልካች ዘንድ ተወዳጅነትን ባተረፈው ‘እረኛዬ’ በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ያሳየውን የትወና ብቃት ብዙዎች እንዲመሰክሩለት ሆኗል።

በሕጻናት እና ወጣቶች ቴአትር ቤት፣ በሀገር ፍቅር፣ አዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ፣ በራስ ቴአትር በትወና፣ በአዘጋጅነት እና በሥራ አስኪያጅነት ሰርቷል። ከቴአትር ባሻገር በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን ድራማዎች ተወዳጅነትን አትርፏል። አርቲስቱ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በኪነጥበብ ውስጥ ሲያሳልፍ ያለውን ዕውቀት ሳይሰስት ያካፈለ፣ ባለሙያዎችን እና ሙያውን አክባሪ እንደነበር ይነገርለታል።

ኩራባቸው ደነቀ ከወይዘሪት አስቴር ታደሰ ጋር በ1985 ዓ.ም በጋብቻ ተሳስሮ ሁለት ወንድና እና አንዲት ሴት ልጆችን ማፍራት ችሏል። ይህ አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያ በድንገት ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሥርዓተ ቀብሩም ነሐሴ 21ቀን 2016 ዓ.ም በቀጨኔ መድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል። እኛም ይህንን የጥበብ ባለሙያ ነፍስ ይመር እያልን ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን እንመኛለን።

ለዚህ ፅሑፍ እንደ ምንጭነት የተለያዩ ማህበራዊ ድህረገጾችን ተጠቅመናል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You