የማይረሳው የአንጋፋዎቹ ውለታ

ኢትዮጵያ የብዙ ስመ ጥር ግለሰቦች ሀገር መሆንዋ የታወቀ ቢሆንም ታሪካቸው በአግባቡ በወረቀት ላይ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው:: በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኙአቸው ዕድሎች በአገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዕውቀት የቀሰሙ ኢትዮጰያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ እሠራርንና አስተሳሰብን በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሁራን እንደ ነበሩ ታሪክ ይነግረናል።

ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልበሩም። በውትድርና፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ኢትዮጵያውያን ብዙዎች ናቸው።

ለዚህ አባባላችን ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑን ደግሞ ሰሞኑን ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ሁለት አንጋፋ የጥበብ ሰዎች ናቸው። አርቲስት መርሃዊ ስጦት እና ድምጻዊ አለማየሁ ፋንታ ናቸው። እነዚህ የጥበብ ሰዎች ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ስጦታ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዘመናት ሲያገልግሉ ኖረዋል። በዚህም የሕዝብን ስሜት ከመግዛታቸውም በሻገር የእነሱን ፈለግ የተከተሉ በርካታ ወጣቶችን ማፍራት ችለዋል። የእነዚህ የጥበብ ባለውለታዎች ታሪክ ሰፊ ሲሆን በዛሬው የባለውለታዎቻችን አምድ በየተራ ከታሪኮቻቸው ጨለፍ አድርገን ለማስታወስ እንሞክራለን፤ በቅድሚያ ከድምጻዊ መርሃዊ ስጦት እንጀምር።

የወርቃማው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ባለውለታ አርቲስት መርዓዊ ስጦት በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደም ቦታ ከሚይዙ አንጋፋ ሙዚቀኞች መካከል አንዱ ናቸው። ከሀምሳ አምስት ዓመት በላይ በቆየበት የሙዚቃ ሕይወቱ በክላርኔትና አልቶ ሳክስ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት በሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲነት በአቀናባሪነት እንዲሁም በኃላፊነት (አመራር) ቦታ ላይ ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል።

የአምባሰሉ ንጉስ የክላርኔት ንጉስ በመባል የሚታወቀው ጋሽ መርዓዊ ስጦት ውልደትና እድገታቸው ከወሎ አምባሰል ልዩ ስሙ ዳቃ ወረዳ ነው። ከአምባሰል ወጥተው በክላርኔት አምባሰልን ወደር በማይገኝለት ሁኔታ በመጫወት በሙዚቃ መድረክ ላይ ነግሰው ኖረዋል። አርቲስት መርዓዊ ስጦት አምባሰልን ሲጫወቱ አይቶ ስሜቱ የማይኮረኮር፣ የማያነባ የለም።

የሙዚቃ ሕይወታቸው የሚጀምረው በ1942 ዓ.ም ገና የ14 ዓመት ልጅ እያሉ የማዘጋጃ ቤት በወቅቱ የሙዚቃ እና ቴአትር ማስፋፊያ “ጎንደሬው ገብረማርያም ” የተሰኘ ቴአትርና የመንገድ ላይ የሙዚቃ ትርኢት (ፋንፋር ባንድ) ለማሳየት ደሴ በመጡበት ወቅት ልባቸው ይሰረቅና እሳቸውም እንደነሱ መሆን እንደሚፈልጉ በመጠየቃቸው አዲስ አበባ ከመጡ እናስተምሮታለን ይሏቸዋል።

ይህ ቃል በጊዜው ከሰጡት ውስጥ አንዱ ተስፋዬ ሳህሉ “አባባ ተስፋዬ ” ነበሩ። እሳቸውም ለአዲስ ዓመት የእንቁጣጣሽ አበባ ስለው በየሹማምንቱ ቤት በማዞር ሀምሳ ብር ይሰበስቡና ወዴት ነህ የሚለው ጥያቄ እንዳያስጨንቃቸው ሆን ብለው ብርድ ልብስ ቀደው ላሰፋ ነው። በሚል ሰበብ ከቤት ይወጣሉ ከአንድ ጣልያናዊ ሹፌር ጋር ተነጋግረው በትሬንታ ኳትሮ ተጭነው ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ።

አጠያይቀውም ቃል የገቡላቸውን ሰዎች ያገኙና በአስራ አራት ዓመታቸው የሙዚቃ ትምህርታቸውን ይጀምራል። ከትምህርታቸው ጋር አንድ ላይ ማደርያና የኪስ ገንዘብ ጭምር ይሰጣቸው ነበር። በወቅቱ ከእሳቸው ጋር አብረው ከነበሩት ሙዚቀኞች መሀል የሳክስፎኑ ንጉሥ ጌታቸው መኩሪያ አንዱ ናቸው። ስድስት ዓመት በዚህ ሁኔታ ካሳለፉ በኋላ የጃንሆይ 25ኛ የብር ኢዩቤልዩ በዓል ምክንያት በማደረግ የአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር የቀድሞ ቀ.ኃ.ስ ቴአትር ቤት ሲቁቋም ከተመረጡት አስራ ሦስት ሙዚቀኞች መካከል አንዱ በመሆን መስራች ሆኑ።

በአርመናዊው አስተማሪና አለቃቸው ሙሴ ነርሲስ በምግባራቸውም ሆነ በትምህርት አቀባበላቸው የሚደነቁት አርቲስት መርዓዊ ከሙሴ ነርሲስ ህልፈት በኋላ የሙዚቃ ክፍሉን ተረክበው ለሰላሳ ዓመታት በአለቃነት አገልግለዋል። በዚህም ወቅት ለአርቲስት ምኒልክ ወስናቸው፣ ለመልካሙ ተበጀ፣ ጠለላ ከበደ፣ ፍቅርተ ደሳለኝ . . . ለበርካቶች ግጥምና ዜማ ደርሰዋል። ሙዚቃ አቀናብረዋል። ከነዚህም ውስጥ የምኒልክ ወስናቸው የእንጆሪ ፍሬ፣ ትዝታ አያረጅም፣ ስኳር ስኳር፣ አፈር አትንፈጊኝ፣ በምድረ ሱዳን ያለሽው፣ ጥቁሯ ጽጌረዳ፣ የመልካሙ ተበጀ፣ ብዕር ብዕር፣ ሰላም ጤና ይስጥልኝ፣ ንቢቱ፣ የፍቅርተ ደሳለኝ ልማት ልማት ሌሎችም ይገኙበታል።

ከዚህም ባሻገር ከ200 የማያንሱ አብዮታዊ መዝሙሮችን፣ ለሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን እና ለሌሎችም በርካታ ታዋቂ ቴአትሮች ማጀቢያ ሙዚቃዎችን ደርሰዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብም የመጀመሪያ የሆነውን የክለቡን መዝሙር የሰሩት አርቲስት መርዓዊ ስጦት ናቸው። በአፄ ኃይለስላሴ፣ በዘመነ ደርግ እና በዘመነ ኢሕአዴግ ጊዜ በተሰራው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ላይ የጋሽ መርዓዊ ትንፋሽ ተቀርጿል! ዜማው በሚሰራበት ጊዜም ኦርኬስትራውን የመምራትና የማስተባበር ሥራውን የሰሩት ጋሽ መራዊ ስጦት ናቸው።

በሙያው All Black People Music Festi­val ጨምሮ በናይጄሪያ፣ በግብጽ በሱዳን፣ በቻይና በራሺያ፣ በአሜሪካ እና ሌሎችም ሀገራት ሀገሩን ወክሎ ተሳትፈዋል። በአሜሪካ ሀገርም ከሙዚቀኛ ያሬድ ተፈራ ጋር በመሆን አምባሰልና ትዝታ ለትውልድ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲተላለፍ በካሴትና በሲዲ አስቀርጸዋል። ለዚህና መሰል አስተዋጽኦ በተለያዩ ጊዜያት ሽልማትን አግኝተዋል።

* ከጃንሆይ የማበረታቻና የመጻህፍት ሽልማት

* በደርግ ጊዜ በማስታውቂያ ሚኒስትር የምስጉን ሰራተኛ ወርቅ ተሸላሚ።

* የዓለም አቀፍ ጎልድ ሜርኩሪ ሽልማት (ሽልማቱ ዓለማቀፋዊና ትላልቅ የዓለም መሪዎችን ጨምሮ ሳይንቲስቶችና ምሁራን የሚሸለሙት ነው)

* ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የወርቅ ሽልማት

* በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ማህበር የክብር ሽልማት ።

* የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር (ባህል ማዕከል) የክብር ዋንጫ ተሸላሚ።

* ከጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለክብር ሜዳሊያ ሽልማት ጥቆቶቹ ናቸው።

ጋሽ መርዓዊ ጡረታ ከወጡም በኋላ ከሙዚቃው ሳይርቁ እስከ ቅርብ ጊዜ ከብሔራዊ ቴአትር ደጅ አይጠፋም። የልብ ሕመም አጋጥሟቸው የትንፋሽ መሳሪያ መጫወት እስከተከለከሉበት ጊዜ ድረስ ክላርኔታቸውን ይዘው መገኘት ባለባቸው ቦታ ሁሉ እየተገኙ ሕዝብን ያስደስቱ ነበር። በሕይወታቸው ከኦርኬስትራው ተነጥለው በየትኛውም ምሽት ክለብ ሰርተው አያውቁም። በተሰጥኦ ያምናሉ። አዳዲስ ወጣቶች በመጡም ጊዜ ካሉበት አድኖ በማግኘት እና በማበረታታት ይታወቃሉ።

አርቲስት መርዓዊ ስጦት ባላቸው ጊዜ ሁሉ ባለተሰጦ ልጆች በማደን ችሎታቸውን እያደነቁ፣ እየመከሩ የሚያበረታቱና ምን አይነት አርቲስት መሆን እንዳለባቸው ምሳሌ በመሆን ጭምር የሚደግፍ የሙያ አባትም ጭምር ናቸው! ለዚህም “የዓለም አቀፍ ሜርኩሪ” ሽልማታቸው ወጣት ባለሙያዎች ባዩት ጊዜ እንዲበረታቱበትና እንዲነሳሱበት በማሰብ በስጦታ መልክ ” ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢሮ እንዲቀመጥ አስረክበዋል።

ሌላኛው የሀገር ባለውለታ ድምጻዊ አለማየሁ ፋንታ ነው። ባህላዊዎቹን የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያዎች በገናን በመደርደር፣ ክራርና መሰንቆን አሳምረው በመጫወት ይታወቃሉ፡ አንጋፋው ሙዚቀኛ አለማየሁ ፋንታ የቀለም ትምህርትን የተማሩ እንዲሁም የድቁና ትምህርትም የነበራቸው ነበሩ።

በ1927 ዓ.ም በወሎ አካባቢ የተወለዱት አንጋፋው የማሲንቆ እና በገና ተጫዋች፣ ድምጻዊ እና የሙዚቃ መምህር አለማየሁ ፋንታ በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል::

አለማየሁ ፋንታ የግጥምና ዜማ ድርሰት፣ ክራር፣ ማሲንቆ እና በገና በመጫወት ይታወቃሉ።

ያላቸውን ጥልቅ ተሰጥዖ እና እውቀትም ለትውልድ በማካፈል ለበርካታ አሥርት ዓመታት በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል።

በተለየ በማሲንቆ አጨዋወታቸው የሚታወቁት አለማየሁ ፋንታ፣ በዓለም ዙሪያ የኢትዮጵያን ባህል ማስተዋወቅ የቻሉ ናቸው።

በዚህም የባህል አምባሳደር የሚል ማዕረግ እንዳገኙ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

ባከናወኑት ተግባር ከዓለም አቀፍና ከሀገር ውስጥም የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙ ነበር።

የባህል አምባሳደር አርቲስት እና የሙዚቃ መምህር አለማየሁ ፋንታ ለ60 ዓመታት በዘለቀ የትዳር ሕይወታቸው 3 ወንዶች እና 3 ሴቶች ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ የልጅ ልጅም ማየት የቻሉ ናቸው።

ድምጻዊ አለማየሁ ፋንታ ከ6 ወራት በፊት በድንገት ወድቀው እግራቸው በመሰበሩ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ስርዓተ ቀብራቸውም ፒያሳ በሚገኘው በገነተ ፅጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ በ9 ሰዓት ተፈጽሟል።

እኛም በዚህ ለሕዝብና ለሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ ሁለቱን አንጋፋ የጥበብ አባቶች ታሪክ በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክረናል፤ ለሀገራቸው ላበረከቱት መልካም አስተዋጽኦ አመስግነናል። ሰላም!

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You