ድል ብቻ ሳይሆን ቁጭትም አንድ ያድርገን

ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት ውስጥ ከኋላቀርነት ለመላቀቅ የምታደርገው ጥረትና የለውጥ መሻት ተቋርጦ አያውቅም። ይህ ጥብቅ ፍላጎት ግን በጥቂት ፈተናዎች ምክንያት ሲገታ የተመለከትንበት ግዜ በርካታ ነው። ከዚህ ውስጥ በውስጥና በውጪ የሚነሳው ግጭትና ጦርነት አንዱ ነው። ጦርነት የኢትዮጵያን ሽንቁሮቿን እየከፈተ የቋጠርነውን ጥሪት ሲያስፈታን ያጠራቀምነውን በረከት ሲያስደፋን፤ ከስልጣኔና ዘመናዊነት ወደኋላ ሲጎትተን ዛሬ ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያውያን በጦርነት የደረሰባቸውን ዘርፈ በዙ ጉድለት የሚያስታውሱት ከሩቅ ሳይሆን ከቅርብ ግዜ ትዝታቸው ጨልፈው ነው። ከከፋው ግጭትና አለመግባባት ወጥተን ወደ ልማት እንድንገባም አያሌ ጥረቶች ተደርጓል።

የሩቁን ትተን የቅርብ ግዜውን ብናስታውስ ሀገር ከዚህ አዙሪት ትወጣ ዘንድ የፌዴራል መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ሲያደርግ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ የሰላም ጥሪዎች ተቀብሎ በተፈለገው ልክ እንደሀገር ላሉብን የፀጥታ ችግሮች ለውይይት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥ ፍቃደኛ የሆነ ኃይል (ከፕሪቶሪያው ስምምነት ውጪ) አልነበረም። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳው የእርስ በእርስ መተማመን መጥፋትና አገር በሚገነባበት የጋራ ትርክት ላይ አለመስማማት ነው። በዚህ ምክንያት ውዱ የሰው ልጅ ሕይወትና አያሌ ሀብት እንዲጠፋ ምክንያት እየሆነ ነው፤ ዛሬም ይህንን የጥፋት መንገድ እየተከተልን ነው።

ከዚህ ቀደም የነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ከሀሳብ የበላይነት ይልቅ በግጭትና በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ማለፍን ምርጫው ያደረገ መሆኑን አብዛኛዎቻችንን ያስማማል። ይኸው ጉዞ በሀገራችን ታሪክ ውስጥም በርካታ ጊዜያት ተደጋግሞ ተመልክተነዋል። ዛሬም በዘመናዊ የፖለቲካ ሂደት ውስጥም ካለፈው ባልተማረ መልኩ ግጭት ላይ ሙጥኝ እንዳለ መዝለቁ አሳሳቢ ነው። በእርግጥ መንግስት ከዚህ አዙሪት እንድንወጣ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን እያደረገ ነው። ይህ ሙከራ ግን በሁሉም ባለድርሻዎች ካልተደገፈ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።

በየትኛውም ሀገር ሆነ ሁኔታ የመሳሪያ አፈሙዝ ዘላቂ ሰላምን አምጥቶ አያውቅም። ሰላም የሁሉም ጉዳዮች ማጠንጠኛ ቋጠሮ ነው። ያለ ሰላም ምንም ነገር ማከናወን አይቻልም፤ ካለ ሰላም ነገ የለም። ግጭት፣ ጦርነት ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ይወስድብናል። ሰላም ከሌለ ሰርቶ መለወጥ ተስፋ ብሎ ነገርም አይኖርም። ሰላምን ለማረጋገጥ ደግሞ የግዴታ ዲሞክራሲያዊ አገርን መገንባትና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ፖለቲካን መከተል ይጠይቃል።

ይሁን እንጂ በአገራችን የሰላም አየር ለማደፍረስ እዚህም እዚያም ፀብ የሚጭሩ በርካቶች ናቸው። የሚከሰቱ ግጭቶች ደግሞ የዜጎች ሕይወት እየነጠቁ፤ የአካል ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ። የንብረት ውድመት እና የዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀል በየግዜው የምንሰማው ዜና ሆኗል። ግለሰቦች ተዘዋውረው ለመስራት ተቸግረዋል፤ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ በየጉድባው ለሚያደቡ ነፍጥ አንጋቢዎች ሲሳይ መሆን ነው።

መንግስት በኢትዮጵያ የሰላም አየር እንዲነፍስ፣ በሙሉ አቅም ወደ ልማትና ብልፅግና እንድንገባ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ ይደመጣል። አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን ከማቋቋም አንስቶ በርካታ ሙከራዎችን እያደረገ ነው። ለዚህ እንደ ምሳሌነት የምናነሳው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ተደጋጋሚ ጥሪ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ጦርነት፣ እርስ በእርስ መገዳደልና መበላላት ይብቃን›› በማለት ልዩነቶች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ አድምጠናል። ለዚህ ጥሪ ቀና ምላሽ መስጠትና በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ለመወሰን አንድ መድረክ መፍጠር ያስፈልገናል።

ከዚህ ባሻገር መንግስት ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት እና የ‹‹ኑ እንመካከር›› ጥሪ የሚበረታታ ቢሆንም ሰፊ የውይይት እና ምክክር መድረክ እንዲፈጠር ደግሞ ተጨማሪ ኃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል። በየግዜው ሆደ ሰፊ በመሆን እና በምክክር ለሚገኘው ውጤት ተፈፃሚነት ያለውን ቁርጠኝነት እና የማስፈፀም ሚና ከፍ በማድረግ ተዓማኒነቱን መገንባት አለበት። መሳሪያ ያነገቡ አካላት ወደ ጠረጴዛ ውይይት እንዲመጡም ተደጋጋሚ የማግባባት ስራ ደጋግሞ መስራት ይገባዋል።

መንግስት በግጭት ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ወደ ምክክር ኮሚሽኑ የውይይት መድረክ እንዲመጡ ከሚያደርገው ጥሪ ባሻገር ኅብረተሰቡም በዚህ ጥረት ላይ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል። ግጭት በሚታይባቸው አካባቢ የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች እና ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል በማስገንዘብ ታጣቂ ኃይሎች ትግላቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እና በሰላማዊ ፖለቲካ እሳቤ እንዲፈቱ ማግባባት ይኖርባቸዋል።

በሚደረጉ የፖለቲካ ምክክሮች በአገር ግንባታ እና ትርክት ላይ አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን ልዩነቶችን ማጥበብ የሚችሉ ሳይንሳዊ መፍትሄዎችን እየተከተሉ ለመሄድ መስማማት አስፈላጊ ነው። በአንዳንድ ጉዳዮችና አጀንዳዎች ላይ ‹‹ላለመስማማት ተስማምቶ›› በሰላማዊ መንገድ ለአብላጫ ድምፅ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ መገዛት በራሱ አንዱ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ መሆኑን ማመን ተገቢ ይሆናል። ይህንን ባህል ሁሉም ኃይሎች እንዲከተሉት ማኅበረሰቡና ተፅእኖ ፈጣሪ አካላት የአመፅን መንገድ የመረጡ አካላትን ለማሳመን ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል።

የሰላም እጦት ሀገርን ከማትወጣው ቅርቃር የሚከት ነው። አሁን ባለው ነባራዊ እውነታ መንግስት ይህንን በመገንዘብ ለሀገር ሰላም ሲል በሩን ለድርድር ክፍት ቢያደርግም ታጣቂ ቡድኖች ወደ ድርድር ለመምጣት ሲያንገራግሩ ይታያል። አንዳንዶች እንዲያውም ጦርነቱ ዋነኛ የገንዘብ ምንጫቸው እየሆነ ነው። በሕዝብ ስም ጫካ የገቡት አካላት የተለያዩ የሀሰት ትርክትን እየፈጠሩ ሕዝብ መንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው ይሰራሉ። ይህ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ማኅበረሰቡ ሊያስገነዝብ መንግስትም ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ እርምት ሊሰጥ ይገባል።

እነዚህ ኃይሎች ግጭት ከቆመ ጥቅማቸው ስለሚያሳጣው የሰላም ጥሪዎች ፍሬ እንዳያፈሩ መሰናክል እየሆኑ ነው። በዚህም እንታገልለታለን ከሚሉት ኅብረተሰብ በተቃራኒ ቆመው ይገኛሉ። እንዲያውም ለሕዝቡ ሞት፣ መፈናቀልና እንግልት ምክንያት እየሆኑ ነው። እነዚህ አካላት ከጥፋታቸው ተቆጥበው እታገልለታለሁ የሚሉትን ማኅበረሰብ የሰላም ፍላጎት በማስቀደም ለውይይት ቅድሚያ ሰጥተው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

መለያየታቸውም ሰላም ቢሰጣቸው ኖሮ ሩሲያ ከዩክሬን፣ ሰርቪያ ከኮሶቮ፣ ሱማሌ ላንድ ከሱማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንም ከሱዳን ጋር ባልተዋጉ፣ ባልተቃቃሩም ነበር። የ1990ው ደም አፋሳሽ የባድመ ጦርነት ባልተከሰተ ነበር። ከልዩነታቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጋቸው ላይ አጥብቀው የሰሩት ሁለቱ ጀርመኖች፣ ሁለቱ የመኖች፣ ወደ ውህደት መምጣታቸውን እናስታውሳለን። እኛ ከዚህ የተሻለ ቁመና ላይ ብንሆንም ለሰላም መስፈን በጋራ በቁጭት ካልሰራ እጣ ፈንታችን ከዚህ የተለየ አይሆንም። በመሆኑም አሁን የሚታየውን ምልክት ቀድመን ልናመክነው ይገባል። ጉዳዩ ‹‹ በእንቁላሉ ግዜ በቀጣሽኝ ኖሮ›› የሚለውን ኢትዮጵያዊ ብሂል የሚያስታውስ ይሆናል።

ኢትዮጵያውያንን እንደ አድዋ አይነት ድሎች ብቻ ሳይሆኑ በየዘመናቱ የተከሰቱ ግጭቶችና የደረሱ ጥፋቶች ያስከተለው ቁጭት አንድ ሊያደርገን ይገባል። ድሎች ብቻ ሳይሆኑ ሽንፈቶችም፣ ቁጭቶችም፣ አደጋዎችም አንድ የማድረግ ኃይል እንዳላቸው አምነን ስህተታችንን ለማረም እንነሳ። የዘጠኝ ወራት የእስራኤላውያን ክፍፍል አንድ መሆን የቻለው በሰሞኑ የሀማስ ጥቃት ነው። ኢንዶኔዣውያን የመከፋፈል ጉዳይ ሲያጋጥማቸው የ2004ቱን ከ200 ሺህ በላይ ሕዝብ ያለቀበትን ሱናሚን ያስታውሱታል። እኛም እንደሀገር እየፈተኑን ካሉት ችግሮች ተምረን ዳግም ለአንድነት ዳግም በጋራ አንድ ኃያል አገርን ለመገንባት መነሳት ይጠበቅብናል።

ችግሮቻችን ለዳግም መተባበርና አንድነታችን መነሳሳት ይሁን አልን እንጂ ከዚያ የተሻሉ እሴቶች ሳይኖሩን ቀርተው አይደለም። ከጤናማው ይልቅ የተጣመመውን፣ ከደጉ ይልቅ ክፉውን፣ ከጥሩው ይልቅ መጥፎውን፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን ማጉላት ሆኖብን፤ አይናችንም፣ ጆሯችንም ወደ እነዚህ ያተኩራል እንጂ እጅግ አኩሪ የአንድነት፣ የመተሳሰብና የአብሮ መኖር ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን። እነዚህን እሴቶቻችንንም ለተቸገርንባቸውና ለተፈተንባቸው ግዜያት ብናውላቸው መልካም ነው።

አድዋ የአንድነታችን ውጤት መሆኑን የተረዳው ፋሺስት ካዘመተብን ጀት እና ታንክ በላይ እርስ በርሳችን እንድንጣላ፣ በጠላትነት እንድንተያይ፣ ጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክትን ፈጥሮ በብሄር፣ በቋንቋ፣ በሀይማኖት እንድንለያይ የተቻለውን ያህል የክፋት ዘር ዘርቶብናል። ይህ ዘር በቅሎና ጎምሩቶ ዛሬም ድረስ ፈተና ሆኖብን ይገኛል። እንዳሰበው በእርስበርስ ጦርነት ከምድረ ገፅ ባያጠፋንም በመጠኑ ግን ተሳክቶለታል።ብዙ የብሄር ነፃ አውጪዎችንም ፈጥሯል። እኛም ልዩነትን ከፍ አድርገነው በመደብ ትግል ሳይቀር፤ ቀኝ ዘመም፣ ግራ ዘመም እየተባባልን፣ በፊደል ሳይቀር ‹‹እናሸንፋለንና፤ እናቸንፋለን›› እየተባባልን፤ ለሽብር ቀለምን ሰጥተን እስከበቃን ድረስ ተጨፋጭፈናል። ለዚህ ነው ከቅዠታችን መንቃት የሚኖርብን።

በራስ ቋንቋ መማር፣ መዳኘት፣ መገብየት ተፈጥሯዊና እጅግ መልካም ሆኖ ሳለ ለርካሽ ፖለቲካዊ ትርፍ አንድ ከሆንባቸው ይልቅ የምንለያይባቸው ጎልተው እየተነገሩን አድገን አንድ ትውልዳችን ለራሱም ለሀገሩም እንዳይጠቅም ሆኖ ተመርዟል።

ይህ እውነታ ግን መላው ኢትዮጵያውያንን እና አብሮ የመኖር እሴታቸውን የሚወክል አይደለም። ከ80 በመቶ በላይ ሕዝባችን ንፁህና ያልተበረዘ፣ የመጣበትንም የክፋት ዘር አላበቅልም ብሎ በአንድነቱ የፀና ባይሆን ኖሮ የተደገሰልን ሴራ ግቡን መትቶ እስከዛሬ ፈራርሰን ነበር። በመሆኑም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልቦና ውስጥ ያለው መልካም ዘር ጥቂት ምሁራን፣ የፖለቲካ ቡድኖች ወስጥም ገብቶ የተደቀነብንን ፈተና ዳግም ድል ልናደርገው ይገባል።

ምስጋና ለኃያሉ ፈጣሪያችንና ክፋትን ውጦ ለሚያስቀረው አስተዋዩ ሕዝባችን ይሁንና ይቺ ሀገር ዛሬ ላይ ደርሳለች። የዛሬውንም ክፋት አልፋ ነገን ታመለክታለች። ለዚህ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ እርስበርስ ያጋመዱን ማህበራዊ እሴቶቻችን እጅግ ትልቅ ዋጋ አላቸው። የእኔም መልእክት እነዚህን ሀብቶቻችንን እንደ አይን ብሌናችን እንጠብቅ የሚል ነው። ማኅበራዊ አደረጃጀቶቻችን እንደ እድር፣ እቁብ፣ ማኅበር፣ ሰንበቴ፣ የጤና ቡድን፣ መድረሳ፣ ሰንበት ትምህርት ቤት፣ መረዳጃ፣ የእንትን ሰፈር ልጆች ማኅበርና የመሳሰሉት ትልቅ አስተዋፆ ስላላቸው አጥብቀን ልንይዛቸው ለትውልድ ልናስተላልፋቸው ይገባል።

እኛ ኢትዮጵያውያን በብዙ መንገድ ጠንካሮች ነን። ከሶስት ሺህ ዘመን በላይ የዘለቀ አገረ መንግስት ታሪክ አለን። እሴቶቻችን እንደ ብዝሀነታችን ብዙ ናቸው። ከልዩነቶቻችን ይልቅ አንድነታችንን የሚያጎሉ ትርክቶች ባለቤት ነን። ሀዘናችን፣ ደስታችን፣ መተባበርና መረዳዳታችን ከሁሉ በላይ ለኢትዮጵያ ያለን ፍቅር ከጋራ ትርክቶቻችን መካከል የሚጠቀሱት ናቸው።

አሁን ልንፈታው የሚገባን የፖለቲካ ባህላችንን ነው። በኢትዮጵያውያን እሴትና ባህል የተገራ፣ ዲሞክራሲያዊና የሰለጠነ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልገናል። ይህ የሚሳካው ደግሞ በጠብ-መንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሰከነ ውይይትና ምክክር ነው። ዲሞክራሲን ማስፈን ከቻልን የመንግስት ተቋማት ሕዝብን እንጂ ጥቂት ግለሰቦችን እንዳያገለግሉ አድርገን ካዋቀርን ነገ ልናያት የምንፈልጋት ታላቅ አገር መገንባት እንችላለን። በመሆኑም ዛሬም የልዩነትን ዓርማ ያነገቡ ከፋፋዮች በግልፅ እንደ ሕዝብ ግን ‹‹በፍፁም አንቀበላችሁም›› ብለን በመግፋት በጋራ እሴቶቻችን ላይ ልናተኩር ያስፈልጋል። አንድነትና የሰለጠነ አገር የሚገነባው በውይይት፣ ይቅር በመባባል፣ በሰጥቶ መቀበል ብቻ ነው። ስለዚህ ለአንድነታችን፣ ለኅብረታችን ስንል የምንሰጠውም የምንቀበለውም ይኑረን! እንደ ድሎቻችን ሁሉ ቁጭቶቻችንም አንድ ያድርጉን!

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You