የዓለም አቀፍ ሥልጣኔ ተነሳሽነት /Global Civilization Initiative (GCI) /ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻይው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ እ.ኤ.አ. መጋቢት 15 ቀን 2023 በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ እና በዓለም የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በከፍተኛ ደረጃ ተካሂዶ በነበረው ውይይት ላይ ቀረበ።
በፕሬዚዳንቱ የቀረበው ይህ መልካም ውጥን ቻይና በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ያዳበረችውን የሥልጣኔ ፍቺና ከዓለም ሀገራት ጋር ያላትን የወዳጅነት መስተጋብር፤ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ያላትን የጎለበተ ልምድ መሠረት ያደረገ ነው።
የዓለም አቀፍ የሥልጣኔ ተነሳሽነትን ከሚያጠናክሩ የተለያዩ ተግባራዊ ተሞክሮዎች መካከል በቻይና እና በአፍሪካ ሥልጣኔዎች መካከል ያለው የጋራ መማማር አርአያነት ያለው ነው።
ተዛማጅ የታሪክ የጽሁፍ መዛግብት እንደሚያመለክቱት ፤ የቻይና እና የአፍሪካ ሥልጣኔዎች በሰፊ የጂኦግራፊያዊ ርቀት ላይ የሚገኙ ቢሆኑም፤ ግንኙነታቸው ከጥንት ከታን ሥርወ መንግሥት ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡
በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ከተቀዳጁ በኋላ የቻይና-አፍሪካ ግንኙነት በዕኩልነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ትብብር ላይ ተመስርቶ ቀጥሏል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ለዓለም ሥልጣኔ ብዝሃነት እና በሥልጣኔዎች መካከል ሊኖር ለሚገባው እኩልነት እውቅና በመስጠት ለዓለም ተምሳሌት ሆነዋል ፡፡
ቻይናውያን እና አፍሪካውያን ተመሳሳይነት ያላቸው ባህላዊ እሴቶች እና ፍልስፍናዎች አሏቸው፤ ሁለቱም የጋራ ጥንካሬን እና በሰላም እና በስምምነት አብሮ መኖርን ያበረታታሉ።
የአፍሪካ ሀገራት የተለያዩ የትብብር አጋሮችን አጥብቀው ከመሻታቸውም በላይ ከተፅዕኖ ነፃ የሆነ የልማት ጥያቄ አላቸው። ጥያቄያቸው ራስን በራስ የማስተዳደር እና ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ነው። የሕዝባቸውን ከውጭ ልምዶች ተጠቃሚ የመሆንን ፍላጎት የሚንጸባረቅበት ነው። ይህ ደግሞ ሁሉን አቀፍ ባህል ካለው ከቻይና ሥልጣኔ ጋር ይስማማል።
ከዚህም ባለፈ ፤ የዓለም አቀፍ ሥልጣኔ ተነሳሽነት በቻይና እና በአፍሪካ ሥልጣኔዎች መካከል ያሉትን የረጅም ጊዜ የጋራ የመማማር መርሆዎችን የሚያረጋግጥ ነው፤ ንቀትን፣ ማንቋሸሽን፣ የሥልጣን/የሃይል የበላይነትንና ጫናን የሚቃወም እና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን የሚደገፍ ነው።
የዓለም አቀፍ ሥልጣኔ ተነሳሽነት የሥልጣኔን ቅርስ እና ፈጠራ አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፤ በቻይና እና በአፍሪካ ሥልጣኔዎች መካከል ቀጣይነት ያለውን የጋራ መማማር ቁልፍ ሚናን የሚጠቁም ነው።
በቻይና እና በአፍሪካ መካከል የሚኖረው መልካም በሆኑ ባህላዊ እሴቶች ላይ የተመሠረተ አዳዲስ ሃሳቦችን የሚደግፍ ፤ ሁለቱ ወገኖች በአዲሱ ዘመን የየራሳቸውን የባህል ጎዳናዎች የሠመሩ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥርላቸው ፤ የቻይና-አፍሪካ የባህል ትብብር አሁን ካለው በበለጠ መልኩ አርዓያነት እንዲኖረው የሚረዳ ነው፡፡
ሴኔጋላዊው ምሁር Cheikh Anta Diop (1923-1986) “ታሪካዊ ተነሳሽነትን የሚወስድ ሕዝብ ብቻ ለራሱ ህልውና አስፈላጊ የሆኑትን ቁሳዊ እና ቁሳዊ ያልሆኑ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚችል ያምን ነበር፡፡ ይህም የፈጠራ ችሎታን፣ የፈጠራ ተነሳሽነትን እና የአዲስ ነገር ፈጠራን ይጠይቃል፡፡ ” ይላሉ፡፡
የዓለም አቀፍ የሥልጣኔ ተነሳሽነት በቻይና እና በአፍሪካ ሥልጣኔዎች መካከል እርስ በርስ ለመማማር አዲስ ተግባራዊ መንገዶችን ከፍቷል። በመጪው ጊዜ ቻይና እና አፍሪካ በፍልስፍና ሃሳቦች እና ንድፈ ሃሳቦች ግንባታ ላይ የጋራ መማማርን ማጠናከር፣ የሃሳብ ልውውጥ እና የርዕዮተ ዓለም ጥምረት መፍጠር ፤ዓለም አቀፋዊ የሥልጣኔ ውይይቶችን ማስተዋወቅ እንዲችሉ የሚያግዛቸው ነው ።
ቻይና እና አፍሪካ የባህል ትብብር መስኮችን በንቃት መመርመርና ማጥናት እንዲችሉ ፤ ቻይና የአፍሪካ ስትራቴጂካዊ አጋር እንደመሆኗ ለባህላዊ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ለባህላዊ ቅርሶች ጥገና እና እድሳት እንዲሁም በአፍሪካ የባህል ሥራዎችን ለማደራጀት ድጋፍ እንድትሰጥ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ነው ።
በቻይና እና በአፍሪካ የባህል ልውውጥ ረገድ በስፋትና በጥልቀት ሊሻሻል የሚገባው ብዙ ሥራ እንዳለ ቢታመንም ፤ ተነሳሽነቱ ወደፊት ቻይና ለአፍሪካ ዘላቂ የባህል ልማትና ዕድገት ባህላዊ ተሰጥኦችን በማበረታታት፣ በቴክኒክ ሙያ ሥልጠና እና በአስተዳደር ልምድ ትብብሯን አጠናክራ እንድትቀጥል ይረዳታል ።
በአሁኑ ጊዜ፣ የተለያዩ ግጭቶች ዓለም አቀፉን በሰላም አብሮ የመኖርን መርህ እና እድገትን ያበላሻሉ። ከዚህ አንጻር በቻይና እና በአፍሪካ መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር የተለያዩ ክፍሎችን እና ቡድኖችን ተሳትፎ ማሰባሰብ እና አካባቢያዊ ሚዛንን ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው፡ ፡ ይህንን አቅም ለመፍጠር ተነሳሽነቱ የሚኖረው ሚና የጎላ ነው።
የዓለም አቀፍ ሥልጣኔ ተነሳሽነት በታሪክ እና በእውነታ ላይ የተመሠረተ፣ የዓለምን የሥልጣኔ ብዝሃነት የሚያከብር፣ የሰው ልጆችን ሁሉ የጋራ እሴቶችን የሚያስተዋውቅ፣ የሥልጣኔን ቅርስ እና ፈጠራ አስፈላጊነትን የሚደግፍ እና ዓለም አቀፍ የባህል ልውውጦችን እና ትብብሮችን የሚያጠናክርና የሚደግፍ ነው፡፡
በተጨማሪም ልዩነቶችን ለማስወገድ እና ጥላቻን ለመቀነስ ሃሳቦችን ያቀርባል፡፡ በቻይና እና በአፍሪካ ሥልጣኔዎች መካከል ሰላምና ልማትን ለማስፈን ቀጣይነት ባለው ሁኔታ አዲስ መነሳሳትን ይጨም ራል፡፡
በዚህ መልኩ በቻይና እና በአፍሪካ ሥልጣኔዎች መካከል እየተፈጠረ ያለው የጋራ መግባባት፣ መደጋገፍ እና የጋራ ልማት በዓለም ላይ ያሉ የተለያዩ ሥልጣኔዎችን አብሮ የመኖርን መርህ የሚያበረታታና ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡
ሊሆንግ ፌንግ- የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ኮሌጅ ዲን ዣንግ ቹንጋይ- የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ኮሌጅ መምህር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም