ደስታና የአእምሮ ሰላም መነሻቸው ከሀገር አረንጓዴ ልብስ ውስጥ ነው

ነሐሴ 17/ 2016 ዓ.ም እለተ ዓርብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ታሪክ ሰራን። ቃል ተግባር ሆኖ በዓለም ታሪክ ማንም ያልቻለውን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ እውን አደረግን። ከዳር እስከዳር በአራቱም ማዕዝን የኢትዮጵያን ስምና ክብር ከፍ ያደረገ ሕዝባዊ ንቅናቄ ግቡን መትቷል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጥሪ ተከትሎ ጀምበር ወጥታ እስክትገባ 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘው እቅድ በአንድነት ከቆሙ ታሪክ መስራት በለመዱ እጆች እውን ሆነዋል።

ካለፈው ጊዜ በልጠንና ከፍ ብለን ዓለም ያልቻለውን የራሳችንን ሪከርድ በራሳችን እውን አድርገናል። ዓለምን ከማስገረም ያልሰነፉ የልማት እጆች በአዲስ ትግበራ ዳግም መጥተዋል። ቃል ወደተግባር ተቀይሮ እንዳለፈው ጊዜ ዘንድሮም ባለታሪክ ሆነናል። ሀገርን ባስቀደመ፣ ትውልድን ታሳቢ ባደረገ እና የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ባንጸባረቀ መንገድ ተንቀሳቅሰን የአዲስ ታሪክ ባለቤት መሆን ችለናል።

‹ነገን ዛሬ እንትከል› ከሚል መነሻ ሀሳብ ጀምረን ፤ ‹የምትተክል ሀገር የሚያጸድቅ ትውልድ› ከፍ ብለን፤ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ባሳተፈና የያገባኛል ስሜትን ባሰረጸ መልኩ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብራችንን በድል ተወጥተናል። በየዓመቱ እያደገ በመጣው የችግኝ ቁጥርና የተሳታፈዎች እንቅስቃሴ በድል ላይ ድልን አስመዝግበናል። የችግኝ ተከላው ኢትዮጵያዊነትን ባስቀደመ፣ ከፖለቲካና ከእኔነት በጸዳ ዐይን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከፍ ያደረግንበት ነበር ማለት ይቻላል። ቃላችንን ወደተግባር ቀይረን በንቃት እና በብቃት እንደምንችል ያሳየንበት ሌላው ደማቅ ታሪካችን ሆኖ አልፏል።

የዘንድሮውን ሳይጨምር ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ 32.5 ቢሊዮን ችግኞችን ተክለናል። በዚህም የደን ሽፋናችን በ2012 ዓ.ም ከነበረበት የ17 በመቶ ወደ 23 በመቶ ከፍ በማለቱ ንቅናቄአችን ፍሬ እያፈራ እንደሆነ ተመልክተናል። በአራት ዓመታት ውስጥ በደን ሽፋኑ ላይ ይሄን ያክል ልዩነትን ከፈጠርን በመጪዎቹ ጊዜ ሊሆን የሚችለውን መገመት አይከብድም።

ስለደን ሽፋን አወራን እንጂ የአረንጓዴ አሻራ ይዞት የሚመጣው በርካታ ጸጋዎች አሉ። ለአብነት ስነምህዳርን ማስጠበቅ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ በግብርና፣ በከተማ ልማት፣ ቱሪዝም ዘርፍ እንዲሁም በኢንዱስትሪውና በሌሎች መስኮችም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑ ይታመናል።

በአረንጓዴ እሳቤ የተቃኙት ያለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የስነምህዳር ታሪክ ውስጥ ከፊት የሚሰለፉ ናቸው። የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ ይወስናሉ የተባሉት ችግኞች አድገው የሚፈለገውን ጥቅምና ግልጋሎት እየሰጡ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ምስክርነት ተሰቷል። ከአካባቢ ጥበቃ ጎን ለጎን የማህበረሰቡ የምግብ ዋስትና በመሆን ጉልህ ድርሻ በማበርከት ይሁንታን ተችሯቸዋል።

አምና በዚህ ሰዓት ታሪክ ሰርተን በድላችን ስናጨበጭብ ነበር። ‹ነገን ዛሬ እንትከል› በሚል መሪ ቃል በአፋር ክልል ጅማሮውን ያደረገው 6.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ የተያዘለት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መሪነት ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ በድል ላይ ድል ያስመዘገብንበት ታሪክ ነው።

የዚህ ንቅናቄ አንድ አካል የሆነው የሐምሌ አስሩ የእለተ ሰኞው ሕዝባዊ ተሳትፎ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ታሪካዊውን ድልን አስመዝግቧል። ዘንድሮም በተመሳሳይ ወቅት፣ በተመሳሳይ ሀሳብ፣ በጋራ እና በአብሮነት መንፈስ በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ተነስተን እቅዳችንን አሳክተናል።

ያሻሻልነውን የራሳችንን ሪከርድ በማስመልከት የዛሬ ዓመት በዚህ ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ‹ፉክክራችን ከራሳችን ጋር ነው። እያንዳንዳችን የራሳችንን ሪከርድ መስበር አለብን፣ ችግር የራሱን ሪከርድ እንዲሰብር ልንፈቅድለት አይገባም። ችግር የራሱን ሪከርድ ከሰበረ ተሸንፈናል ማለት ነው› በማለት መልካም መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

እንደተባለውም ከራሳችን ጋር ተፎካክረን የራሳችንን ሪከርድ በመስበር አዲስ ሀገራዊ ድልን አስመዝግበናል። በአንድነት ስለቆምን ችግር የራሱን ሪከርድ አልሰበረም። በጋራ ስለተራመድን ሽንፈት ወደቤታችን አልገባም። ለዓለም ቅርብ የሆነ እውነት ቢኖር ድሎች የሚመጡት ከአንድነት ሀሳብና ከሕዝባዊ ተሳትፎ ቀጥሎ ነው የሚለው እውነት ነው።

እንደሀገር በምናስበውም ሆነ በምናልመው ሕልም ውስጥ አንድነት እና ሕዝባዊነት ካለ የታሪክ ባለቤት ከመሆን የሚያግደን አይኖርም። ሕልሞቻችን አንድነትን ከለበሱ እንደ አድዋና እንደ ሕዳሴ ግድብ አሁን ደግሞ እንደአረንጓዴ አሻራ ዓለም አቀፍ መደነቅን ነው የሚፈጥሩልን። አንድነትን ያለበሰ ሕልምና ምኞት መነሻ እንጂ መድረሻ የለውም። ሕልሞቻችን ውስጥ ሩቅ የሚወስድ ከብሄር የጸዳ፣ ከእኔነት የራቀ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያስፈልገናል።

ድህነት እና ማጣት ሪከርድ ሰብረው በኋላቀርነት ያቆሙን አንድነት የዋጀው የጋራ እውነት ስላጣን ነው። ዘረኝነት እና የማንነት ጥያቄ አሸናፊ ሆነው ለዝቅታ የጣሉን ኢትዮጵያዊ ቀለማችንን ስላደበዘዝን ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ዓለምን ያስደነቁ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄዎች ችግሮቻችን ላይ ቢደገሙ እንደ አረንጓዴ አሻራ ዓለም በክብር ስማችንን ለመጥራት በቻለ ነበር።

እንደሀገር የተጋረጡብን ፖለቲካዊም ሆኑ ሌሎች ችግሮች እንደአረንጓዴ አሻራ የአንድነት ሀሳብ ይሻሉ። በዓለም አደባባይ ስማችን በክብር የተነሳባቸው አጋጣሚዎች ሕዝባዊ ቀለም ያላቸው ናቸው። በብሄር አስበን፣ በእኔነት ተጉዘን የጋራ ታሪክ መስራት አንችልም። የኢትዮጵያ ከፍታ ያለው፣ የትውልድ እውነት ያለው በጋራ በመቆም ውስጥ ነው። በአረንጓዴ ልማት ከአፍሪካ አልፈን ወንዝ የተሻገርነው ኢትዮጵያን ስላስቀደምን ነው።

ላሉብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ትልቁ መፍትሄ ሆኖ የሚታየኝ ኢትዮጵያ የቀደመችበት የንግግርና የውይይት መድረክ ነው። በአንድነት ለቆመ ማህበረሰብ ለውጥ የትም አለ። ታሪክ ስፍራው አንድነት ውስጥ ነው። በአንድነት ተነስተን የራሳችንን ሪከርድ ሰብረን፣ እንደሀገር ደምቀን ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተናል። እኚህ ሁሉ ደማቅ ስሞች በአንድነት የተማጡ የጋራ መጠሪያዎች ናቸው። አንደ ሀገር ደማቅ ስም ለመጻፍ ኢትዮጵያዊነት የቀደመበት ሀሳብና ተግባር፣ ሙግትና ውይይት ያስፈልገናል።

ከአረንጓዴ አሻራ ሀሳብ እና ንቅናቄ ብዙ መማር እንችላለን። እንዴት መጣ? እንዴትስ ዓለም አቀፍ እውቅናና ክብር ተቸረው? ብለን ስንጠይቅ አንድ እውነት ብቻ ነው የምናገኘው። መነሻ ሀሳቡ ኢትዮጵያዊነት ነው መድረሻው ደግሞ እንዳየነው አንድነት ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዛውም በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ሆነን ይሄን ያክል ለውጥ ማምጣት ከቻልን ችግሮቻችንን በቁጥጥራችን ስር የማናደርግበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አመላካች ነው።

አንገት ያስደፋንን ታሪኮቻችንን አድሰን በአዲስ ስም ለመቆም ቅድሚያ ለሀገር የሚል አመለካከት ያሻናል። ሀገራችንን ባስቀደምን ቁጥር እርባና ቢስ የማንነት ደዌ አይነካንም። ደዌአችን እያጎሳቆለን ያለው ኢትዮጵያዊነትን ትተን ማንነትን መሰረት ስላደረግን ነው። መነሻችንን ኢትዮጵያ አድርገን መድረሻችንን ሉአላዊነት እናድርግ። ያኔ በታደሰ ስም እንቆማለን።

በኢትዮጵያ ስም ብዙ ሆነን ብዙ ችግኞችን ተክለናል። በኢትዮጵያ ስም አንድ ሆነን የአንድነት ታሪክ ጽፈናል። በወንድማማችነት ከቆምን ብዙሀነታችን እና ሕብረብሄራዊነታችን የምንፈልጋትን ሀገር ለመፍጠር ከበቂ በላይ ነው። እድሎቻችንን የደበቅናቸው ራሳችን ነን። የማደግና የመለወጥ ጸጋችን በእኛ መልካም ፍቃድ ውስጥ ነው።

በአንድነት ከቆምን ብዙ ነን። ተያይዘንና ተደጋግፈን ከተነሳን ሩቅ የሚወስድ ኃይል አለን። ይሄን እውነት ለማረጋገጥ ደግሞ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በአንድነት ተክለን በአንድነት ያጸደቅናቸውንና ዓለም አቀፍ አድናቆት ያገኘንባቸውን የአረንጋዴ አሻራ ንቅናቄ ማየቱ በቂ ነው።

በአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኝ መትከል አንድነት ከመሆን ሌላ ስም የለውም። እስኪ ይሄን ክብርና ሞገስ በመለያየት ውስጥ ቆማችሁ አስቡት..ምንም ነው አይደል? እውነት ነው ምንም ነው። ክብር የሰጠን አንድነታችን ነው። ፊተኝነትን ያጎናጸፈን አብሮነታችን ነው።

የአረንጓዴ እሳቤ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ጥሩ መነሻ ጥሩ ንቃት ነው እላለው። ራሳችንን አድሰን የታደሰች ሀገር ለመፍጠር ከመነሻነት አልፎ እንደመድረሻ ሊያገለግለን የሚችል ጽንሰ ሀሳብ ነው። ጀምረን በውብ ፍጻሜ ጨርሰናል። አስበን በውብ ንቅናቄ ቋጭተናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሄራዊ ኩራታችን እየሆኑ ከመጡ ንቅናቄዎች ውስጥ አንዱ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት ዓመታት ውስጥ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እያሳየነው ባለው ህዝባዊ ንቅናቄ ለብዙዎች መነሻና መደነቂያ መሆናችን ይታወሳል። ከዓለም ቀዳሚ ከመሆን ባለፈ ስምና ክብር፣ ሙገሳና አድናቆት ያገኘንበት ነበር።

ካለፈውና ዘንድሮ ከተገበርነው ሕዝባዊ እውነታ በመነሳት ሀገራችን ምን እንደሚበጃት መረዳት አይከብደንም። የሚበጀን በአንድ ጀምበር እልፍ ችግኞችን እንደተከሉ እጆች በጋራ መቆም ነው። የሚበጀን ኢትዮጵያን የጉዳያችን አንደኛ አድርገን ወደፊት መራመድ ነው። እንደ ሀገር ብዙ ጸጋና በረከት አለን። ተፈጥሮ ለእኛ አድልታ በብዙ ባርካናለች። ይሄ እድል ዋጋ አውጥቶ እድገት እና ብልጽግናን የሚሰጠን ኢትዮጵያ በሚል የብዙሀን ስም ሲታጀብ ነው።

በጎ በሆነ ከራሳችን አልፎ ለሌሎች በሚተርፍ ሀሳብ እና ንቅናቄ ከትላንት ወደዛሬ መጥተን ብዙ ለውጦችን እያየን ነው። ዓለም መልስ ላጣለት የአየርንብረት ለውጥ የበኩላችንን በማድረግ ጽናታችንን አሳይተናል። ልክ እንደዛሬው ሁሉ መጪውም ጊዜ ይሄን በመሰለው ሕዝባዊ ንቅናቄ በድል ላይ ድል እንደሚሆን ካየነው እውነታ መረዳት ይቻላል።

ሀገራችን የሚያስፈልጋት ለውጥና አድናቆት እያገኘንበት እንዳለው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ አንድነት የታከለበት ኢትዮጵያዊነት ነው። በአንድነት ቆመን ዓለምን አስደንቀናል። በአንድነት ተነስተን ለብዙዎች መደነቂያ ሆነናል። ልክ እንደዚህ እንደሀገር የተፈጠሩብንን ችግሮችም በአንድነት በመቆም መመከት ልንማረው የሚገባ ትልቁ ቁም ነገር ነው።

አረንጓዴ አሻራ ከችግኝ መትከል ባለፈ ብዙ እውነታዎችን የገለጠልን ክስተት ነው። ታሪክ የሰራንባቸውን ዘመኖች መለስ ብለን ብናይ በአንድነት የቆምንባቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። በተቃራኒው ዘርና ብሄር እየቆጠርን ማንም ባልኖረው የድህነት እና የኋላቀርነት መውደቃችን መለያየታችን የፈጠረው እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው።

በየትኛውም መመዘኛ ቢታይ አረንጓዴ አሻራ አንድ ትርጓሜ ነው ያለው እርሱም ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የማክበር እና የማበልጸግ ጉዳይ ነው። በጋራ የተነሳነውም ይሄ እውነት ስለገባን ነው። ሌሎች አንድነት ያጣንባቸው እንዲገቡን የሚያስፈልጉ እውነታዎችም አሉ። በአንድነት ቆመን ይሄን ያክል የድል እና የክብር ስምን ከተቀዳጀን በመለያየት ያባከናቸው ጊዜአቶች ሊቆጩን ይገባል። በአንድነት እጅ ጀምበር ወጥታ እስክትገባ ዓለምን ማስደነቅ ከቻልን ጀምበር ወጥታ እስክትገባ መከራ ያሳዩንን ችግሮቻችንንም በቁጥጥራችን ስር ማድረግ እንደምንችል ምልክት የሰጠን ንቅናቄ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ እሳቤ በኢትዮጵያዊነት ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት የሚያበቃ ነው። መነሻውና መድረሻው ሀገርና ሕዝብ ትውልድም ነው። ከዚህ ውጪ ምንም ሊሆን የማይችል ቢሆን እንኳን ልክ የማይሆን አስተሳሰብ ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ በሆነው በዚህ ብሄራዊ ንቅናቄ ላይ እንዳለፈው ጊዜ ድል ቀንቶን በድል ተመልሰናል። የሚቀረን ድህነት ነው። የሚቀረን በጋራ ችግሮቻችን ላይ በጋራ መዝመት ነው።

አረንጓዴ አሻራ የሀገር ቡሉኮ ነው። ገላችን እንዳይበርደው የላመ እና የጣመ እንደምንበላውና የደለበ እንደምንለብሰው ሀገርም እንዳይበርዳት አረንጓዴ አስተሳሰብ ያሻታል። አረንጓዴ አሻራ የሀገር ልብስ ነው። ደስታና የአእምሮ ሰላም መነሻቸው ከሀገር አረንጓዴ ልብስ ውስጥ ነው። ቸር ሰንብቱ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You