ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊነት

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ገብቶ ከነበረበት አጣብቂኝ መውጣት እንዲችል የለውጡ መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት እንደ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያሉ እርምጃዎችን ሲወሰድ ቆይቷል። በተለይ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ በማድረግ አዲስ ተስፋ መፈንጠቅ አስችሏል። በእነዚሁ ዓመታት የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገትም ይህንኑ ያመለክታል።

ከ2010 እስከ 2015 በጀት ዓመታት በማአካይ 7 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል። አሁን ደግሞ ይህን ለውጥ ለማስቀጠል ሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረግ ውስጥ ገብታለች። ለእዚህም የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት የሚያስችል ድርድር ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋርም ሲደረግ ቆይቶ በቅርቡ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በርካታ የኢኮኖሚ መዛነፎችን ሊያስተካክልና ልማቱን ሊያጠናክር እንደሚችል ታምኖበታል። በዚህ ውስጥም የጥቅል ሀገራዊ የምርት ዕድገት ሊያስመዘግብ እንደሚችል፤ የብድር ሚዛን መዛነፍንና የዋጋ ንረትን መከላከል እንዲሁም ሌሎች ኢኮኖሚ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳም ተጠቁሟል።

ማሻሻያው አሁን ወደ ሙሉ ትግበራ ይግባ እንጂ የዚሁ አካል የሆኑ እርምጃዎች ቀደም ሲል አንስቶ ሲወሰዱ መቆየታቸውን መንግሥት አመልክቷል። ከእርምጃዎቹ መካከል ለሀገር ውስጥ የንግዱ ማህበረሰብ ብቻ ክፍት የነበረውን የችርቻሮና ጅምላ ንግድ ሥራ ለውጭ ባለሀብቶችም ክፍት መደረጉ፣ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠሩ ሕግ ማውጣቱ ይገኙበታል።

ሌላው ማሻሻያው ወደ ትግበራ ሲገባ ሊያጋጥም የሚችለውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት በተለይ በቂ የዘይት አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ሠርቷል፤ የዘይትን ዋጋ ማረጋጋትም የተቻለው አንድም ይህን የዘይት ምርት ወደ ገበያ ማስገባት በመቻሉ ነው።

የማሻሻያ ትግበራው በዋናነት በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ ለማሳካትና ሁለንተናዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሆነ ይጠበቃል። ማሻሻያው ለየዘርፉ ይዞት የመጣው ቱሩፋት ብዙ ነው። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይህንኑ አረጋግጠዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዋናነት ከሚደግፋቸው መካከል የንግዱና የኢንቨስትመንቱ ዘርፎች ሊጠቀሱ ይችላሉ። በተለይም የውጭ ንግድን የበለጠ የሚያሳልጥና የተሻለ የማድረግ፣ እንዲሁም የውጭ ባለሀብቶችም ጭምር እንዲሳተፉበት የሚያስችል ሰፊ ዕድል እንዳለው እነዚሁ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያመለክታሉ።

በመሆኑም በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የሚበረታቱበትን ሰፊ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ኢንቨስትመንት ይስፋፋል። ሰፊ ኢንቨስትመንት ደግሞ በርካታ የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚውን ያነቃቃል። የውጭ ባለሀብቶችን መሳቡም ሳይታለም የተፈታ ነው።

በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓትን ምርጫ የሌለው አማራጭ አድርጎ የወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬን ከጥቁር ገበያው ቁጥጥር ነጻ እንደሚያደርገው ታምኖበታል። ይህን ለንግዱም፣ ለሌሎች ልማቶችም ወሳኝ የሆነ ሀብት በነጻ ገበያ እንዲመራ መደረጉ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።

ማሻሻያው ይህን ሁሉ ቱሩፋት ይዞ ቢመጣም፣ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል መንግሥትም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም አመላክተዋል። መንግሥትም መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን አያይዞ እንደሚሠራ አስታውቋል።

እንደተባለውም ጤናማ ባልሆነው የንግድ ሥርዓት ሳቢያ ችግሮቹ ወዲያኑ ታይተዋል። አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። መንግሥት ይህን ዋጋ የሚያረጋጋ እርምጃ እንደሚወስድ ከማስታወቅ ባሻገር አቅርቦት ላይ እየሠራ ይገኛል። አቅርቦቱን ተከትሎም የዘይት ዋጋ እንደተረጋጋም ታይቷል።

በሌላም በኩል መንግሥት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓትን ተግባራዊ ሲያደርግ ፈታኝ ሁኔታዎች ሊገጥሙት እንደሚችሉ በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በኩልም ሲጠቆም የነበረ ቢሆንም፤ ተግዳሮቶቹ አፍጠው ቢመጡም፣ ትግበራው ቀጥሏል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚገጥሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ የታለመለትን ዓላማ ከግብ ማድረስ እንዲቻል መንግሥትና መላው ሕዝብ ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ በተደረገ ማግስት የተፈጠረውን የገበያ አለመረጋጋት፣ የምርት እጥረትና የሸቀጦች የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ለዚህም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከብሔራዊ የንግድ ተቋማት የጸረ ሕገወጥ ንግድና ገበያ መቆጣጠሪያ የጋራ ኮሚቴ ጋር በመሆን እርምጃ እየወሰደ ነው።

ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተገኘው መረጃ መሠረትም በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማት ላይ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከእስራት ጀምሮ ፈቃድ የመሰረዝና የማሸግ እርምጃ ተወስደዋል። የንግድ ተቋማቱ እርምጃ የተወሰደባቸው ያላግባብ ዋጋ ከመጨመራቸው፣ ምርት ከመደበቃቸው ጋር በተያያዘ ነው። በተደረገው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ዘይት፣ በዱቄት፣ ስኳር፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንችና መሰል ምርቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ ታይቷል።

የዋጋ ንረቱን ለመከላከልና ገበያውን ለማረጋጋት መንግሥት በቀጣይም ይህንኑ የቁጥጥርና ክትትል ሥራውን አጠናክሮ በመቀጠል ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ማምጣት እንዳለበት ይታመናል። በተለይም ዘላቂ የሆነ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታትና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶችን ለመጠገን የአቅርቦት መዋቅሩን በሚገባ ማስፋትና እዛ ላይ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊና የግድ እንደሆነ ባለሙያዎች እያስገነዘቡ ናቸው።

አሁን አንዳንድ አቅርቦቶች ቢደረጉም የዜጎችን ፍላጎት ማርካት አልተቻለም። ስለዚህ በአቅርቦት ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ተመጣጣኝ የሆነና ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ ዕድገት ለማምጣት በአቅርቦት ላይ ከመሥራት ባለፈ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሠረቱ የውጭ ምንዛሪ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የአስተዳደር ችግሮችን የመፈታቱ ሥራም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ይፋ በተደረገ ማግስት ነጋዴው ምርት መደበቅና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ውስጥ ገብቷል። ይህም በኑሮ ውድነት ጫና ትከሻው ጎብጦ ለሚንገዳገደው ሸማች ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደገፍ›› ሆኖበት ሰነባብቷል። አሁንም ድረስ ከዛሬው ይልቅ የነገው የከፋ እንደሚሆን በብርቱ ስጋት የገባውን ሸማች ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የሸቀጦች ዋጋ መናርና የምርት ስወራ ወደፊትም ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ሰቅዞ ይዞታል።

ከዚህም መረዳት የሚቻለው መንግሥት እርምጃውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከስጋቱ ይልቅ ይዞ የሚመጣው ትሩፋት የላቀ እንደሆነ በተደጋጋሚ እንደገለጸው ሁሉ፤ በቀጣይም ይህንኑ ማድረግ ይኖርበታል። በቁጥጥርና ክትትል ስራው እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ከመቀጠል በተጓዳኝ በአቅርቦት በኩልም ዘይት በማቅረብ ዋጋ ማረጋጋት እንደቻለ ሁሉ ሌሎች ምርቶችን በማቅረብም የዋጋ ማረጋጋቱን ሥራ በሁሉም ምርቶች ላይ እንዲታይ ማድረግ መቻል ይኖርበታል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሊያነቃቃ እንደሚችል በመንግሥትም በብዙዎች ዘንድም ታምኖበታል። በቀጣዮቹ አራትና አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ ስምንት በመቶ ያህል ያድጋል፤ የዋጋ ንረት ወደ 10 በመቶ የተጠጋ ይሆናል፤ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 11 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ዕዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ እንደሚልና የወጪና የገቢ ንግድ ዋጋም ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚያድግ ይሆናል። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም እንዲሁ ወደ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ከፍ የሚል ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ክምችት 10 ቢሊዮን ዶላር (የ3.3 ወራት የገቢ ሸቀጦችን ወጪ ለመሸፈን የሚበቃ) እንደሚሆን ተመላክቷል።

እነዚህ ትንበያዎች በቀጣይ ዓመታት በማሻሻያው ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን የኢኮኖሚ ሽግግር ደረጃ የሚያመለክቱ በመሆናቸው ለተግባራዊነቱ መንግሥትን ጨምሮ እያንዳንዱ ዜጋ በብርቱ ሊተጋ ይገባል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You