የኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል። አልፎ አልፎ ከሚከሰት አለመግባባትና ግጭት ባሻገር ስኬታማ የሚባል የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ትስሰሮችን ፈጥራ እስካሁን መቆየት ችላለች። ቀጣናው የተረጋጋ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድም ትታወቃለች። የሰላም አስከባሪ ሃይሎችን በመመደብ ግጭትና ጦርነት ባለባቸው እንደ ሶማሊያና ሱዳን ባሉ ሀገራት በማሰማራት የወሰደችው ሃላፊነትም ከዋና ዋናዎቹ ሚናዎቿ መካከል የሚጠቀስ ነው።
ኢኮኖሚውንም ብንመለከት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት በተለይም ጎረቤቶቿ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ በአፍሪካ ህብረት፣ በኢጋድ በሌሎች መሰል የግንኙነት መድረኮች ላይ ስትሞግት ቆይታለች። ነፃ የንግድ ኮሪደር በሀገራቱ መካከል እንዲኖር ለማስቻልም ያላሰለሰ ጥረት አድርጋለች። ከምእራባውያን ተፅእኖ የተላቀቀ የእርስ በእርስ ንግድ ትስስር መፍጠር አፍሪካን ከኋላቀርነት ለማላቀቅ ፍቱን መድሃኒት መሆኑን፤ ለማስገንዘብና ትብብር እንዲፈጠር ለማስቻል ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርጋለች፤ አሁንም እያደረገች ትገኛለች።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በጎረቤት ሀገራትና በአፍሪካውያን መካከል በሚከሰት የብሄራዊ ጥቅም ግጭት እና ፖለቲካዊ ልዩነት ሳቢያ የሚደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ አፍሪካዊ መፍትሄ መፈለግ ነፃና ሉአላዊት አህጉርን ለፍጠር ያስችላል የሚል ፅኑ እምነትም አላት። ለዚህ ነው ይህንን መርህ አጥብቃ በመያዝ አቋሟን ስታራምድ የቆየችው። ከጎረቤት ሀገሮቿና እንደ ግብፅ ካሉ በቀጣናው ላይ ልዩ ፍላጎት ካላቸው ሀገራቶች ጋር በአፍሪካ ማእቀፍ ውስጥ መፍትሄ ለመፈለግም ተደጋጋሚ ጥረቶችን ለማድረግ ሙከራዎችን ታደርጋለች።
ኢትዮጵያ ‹‹ብሄራዊ ጥቅሞቼ ናቸው›› ካለቻቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ‹‹የባህር በር የማግኘት ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብት›› እንዲሁም ‹‹የአባይ ወንዝን በፍትሃዊነት በጋራ የመጠቀም አጀንዳ›› ቀዳሚዎቹ ናቸው። እነዚህ ሁለት አጀንዳዎች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ነፃነት ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ እንደሚያረጋግጡ ታምኖባቸዋል።
አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥትም ሆነ ያለፉት መንግሥታት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እነዚህን አጀንዳዎች እውን ለማድረግ የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የዓባይ ግድብ እውን መሆን እና ግንባታው መጀመር ለዚህ ርምጃ እንደ ምሳሌ ልንወስደው እንችላለን። ከዚህ ባሻገር አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኘው በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥትም የዓባይ ግድብን ማጠናቀቅ እንዲሁም ሕጋዊ መሠረትን በተከተለ አግባብ የባህር በር እንድታገኝ ለማስቻል በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ይሄ ተግባር አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ እየተፈፀመ ያለ ጉዳይ አይደለም። የዓባይ ግድብ ሥራ ለማጠናቀቅ ከሚያስፈልገው አቅም ጀምሮ ‹‹ግድቡ ብሄራዊ ጥቅማችንን ይነካል›› ባሉ እንደ ግብፅ ባሉ ሀገራት ፈታኝ ጉዳዮች በየጊዜው ይገጥሙታል። ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ ድርድሮች፣ እሰጣ ገባዎችን ሀገራችን አስተናግዳለች። እስካሁን ባልተጠናቀቀው በዚህ ድርድርም አያሌ ፖለቲካዊ ትርፎች እና ድሎች የተገኙ ቢሆንም የተቋጨና የተደመደመ ነገር የለም።
ግብፅ በጠረጴዛ ዙሪያ ከሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ባሻገር ኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጫናዎችን ለማድረግ የማትፈነቅለው ድንጋይ የማትጎነጉነው ሴራ የለም። በተደጋጋሚ ጊዜ የሚደረጉ የድርድር መድረኮችን ከማቋረጥና እንዳይካሄዱ እንቅፋት ከመሆን ጀምሮ ‹‹ፍላጎቴን እውን ያደርግልኛል›› ያለችውን አማራጮች ሁሉ አሟጣ እየተጠቀመቸ ትገኛለች። ከዚህ ስልት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች በእርሷ (በግብፅ) ጎራ እንዲሰለፉ የማድረግ እንቅስቃሴ አንዱ ነው። ‹‹ይሄንን ስልት በምን መልኩ ተፈፃሚ እያደረገችው ይሆን?›› የሚለውን ከዚህ እንደሚከተለው በማስቀምጠው አመክንዮ ለማስረዳት እሞክራለሁ።
ኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎቷን እና ሁለንተናዊ እድገቷን ለማረጋገጥ ‹‹ቁልፍ ማስፈፀሚያዎቼ ናቸው›› ብላ ካስቀመጠቻቸው ጉዳዮች መካከል በተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብት የተደገፈው የባህር በር ባለቤት የመሆን ጥያቄ አንዱ ነው። ይህን ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ ደግሞ የቀይ ባህር ተጋሪ ጎረቤት ሀገራት ቀና ምላሽና ሚና ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ ይህንን ፍላጎቷን ማንሸራሸር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት (ከሱማሌ ላንድ በስተቀር) ሁሉም ሀገራት በጎ ምላሽ ሲሰጡ አልተስተዋለም። እንዲያውም አጀንዳውን የመልማትና ሕጋዊ መብትን የመጠየቅ ሳይሆን ‹‹የጠብ አጫሪነት›› አድርገው በመውሰድ ከፍተኛ ቁጣና ንዴትን እያንፀባረቁ (እንደ ሱማሌ አይነቶቹ) ይገኛሉ። አንዳንዶቹም ከዚህ ቀደም በወደብ ኪራይ ሲያገኙት የነበረውን የደለበ ጥቅም እንደሚያሳጣቸው በማመን ከጥያቄው በተቃራኒ በመቆም የኢትዮጵያን የእድገት ግስጋሴ ለመግታት ከሚማስኑት ተርታ ተሰልፈው ተመልክተናቸዋል።
ከላይ ያነሳነው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄና የጎረቤት ሀገራት አሉታዊ ምላሽ ደግሞ ለግብፅ አዲስ የሴራ ጉንጉን እንድትጠልፍ ቀዳዳ ከፍቶላታል። ‹‹የዓባይ ወንዝን ድርሻ ጠቅልዬ ካልወሰድኩ›› በሚል እብሪተኝነት አንዴ ስታብጥ አንዴ ደግሞ ስትተነፍስ የምትታየው ግብፅ ኢትዮጵያን በማተራመስና ከጎረቤት ሀገራቶች ጋር በመነጠል እቅዷን ተግባራዊ ለማድረግ ደፋ ቀና ስትል እየታየች ነው። ለዚህ ፍላጎቷ መሳካት ደግሞ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄና የአንዳንድ ሀገራት አሉታዊ ምላሽ የተመቻቸ አጋጣሚን ፈጥሮላታል። ለመሆኑ ግብፅ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እያደረገች ትገኛለች?
ግብፅ በዓባይ ጉዳይ ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን የምትፈልጋቸው የቅኝ ዘመን ውሎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የኢትዮጵያን እጅ መጠምዘዝ ትፈልጋለች። ከዚያ በተጨማሪ በቀይ ባህር ላይ ኢትዮጵያ ሚና እንዳይኖራት ትሻለች፤ ይህንን ደግሞ በቀጥታ ማድረግ አልቻለችም። በመሆኑም እንደ ሁለተኛ አማራጭ ኢትዮጵያን በወታደራዊ አቅም ማስፈራራት፣ ከበባ ለማድረግ መሞከር፣ ጎረቤት ሀገራትን ከኢትዮጵያ በተቃራኒ እንዲቆሙ ማባበል፣ ለፍላጎቶቻቸው እውን መሆን (የባህር በር ጥያቄ የተመለከተ) ሁነኛ አጋርና ደጋፊ እንደሆነች ማሳየት የመሳሰሉት ርምጃዎች እየተከተለቻቸው ከሚገኙ ስልቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ለዚህ ጉዳይ የቅርብ ጊዜ ማስረጃዎችን እንደሚከተለው ለማንሳት እንሞክር።
ከሰሞኑ ግብፅና ሶማሊያ ወታደራዊ ስምምነት ማድረጋቸውን ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰምተናል። በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን ምንም እንኳን ሙከራው የተሳካ ባይሆንም የምታራምደውን ፖሊሲ የሚያስፈፅጽምላት መንግሥት ለመመስረት ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች። ከሁሉ በላይ ግን በኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄና ተፈፃሚነት ዙሪያ ከፍተኛ ተቃውሞ እያነሳች በምትገኘው ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ አማካኝነት ሰፊ የሴራ በር እየከፈተች ነው። ለዚህ ደግሞ በሶማሊያ ምድር የጦር ካምፕ ለማቋቋም የጀመረችው እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ነው።
ግብፅ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራቶች ጋር ለማቃቃር ጥቃቅን ስንጥቆች እየፈለገች እየተወሸቀች ነው። በተለይ ከቀይ ባህር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ እንደተገለለች እንድትቆይ ትሻለች። ለዚህ እንዲበጃት ደግሞ እንደ ሶማሊያ ላሉ ሀገራት ተቆርቋሪና መብት አስጠባቂ ሆና ብቅ ብላለች። ይሄ ለኢትዮጵያ ጠንካራ የጠብ አጫሪነት መልእክት ያዘለ ነው። ለዚህ ነው ለግብፅ ተቀያያሪ ስልት ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስፈልገው። ለመሆኑ ከፊት ለፊት በዲፕሎማሲና በድርድር እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ ፍላጎቶቿን አስጠብቃለሁ በማለት የምታደናግረውና ከጀርባ ደግሞ ድብቅ አጀንዳ በመያዝ ሴራ ለምትጎነጉነው ግብፅ ማርከሻ መፍትሄው ምን ይሆን?
የመጀመሪያውና ዋንኛው ጉዳይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራቶች ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ለማጠናከ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ነው። በተለይ በባህር በር ጉዳይ ኢትዮጵያ የማንንም ሉዓላዊነት የመዳፈር አሊያም ጥቅምን የማሳጣት ሳይሆን የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ፍፁም ሕጋዊና ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ለማስጠበቅ ጥረት እያደረገች ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ተከታታይ ውይይቶችንና ማብራሪያዎችን እንዲሁም ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነቶችን ማድረግም ይጠበቅባታል። ይሁን እንጂ ይህ መንገድ የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም በሚጎዳ መንገድ መፈፀም የለበትም። እንደሚታወቀው ‹‹ግብፅ በግልፅ ከኢትዮጵያ ጋር የጥቅም ግጭት ውስጥ ናቸው›› ብላ ከምታስባቸው ጎረቤቶቿ ጋር ያለውን ልዩነት ይበልጥ ለማስፋት እየሠራች ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው በመሄድ ከእነዚህ ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን ሊያጠናክር በሚችል መንገዶች ላይ ንግግር መጀመር ይኖርባታል።
ሌላውና መሠረታዊው ጉዳይ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄና ፍላጎት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድን መፈለግ ነው። ለዚህም ሕጋዊ መንገድን የተከተለ የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ የባህር በር የማግኘት መብትን የሚያስጠብቅ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ ጫናዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ ሲቻል ግብፅ ሆኖ ማየት የማትሻውን የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ባለቤትነት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማስፈን ይቻላል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የሚኖራት ተፅእኖ ማደግ ለጎረቤት ሀገሮች ዋስትና እንጂ ስጋት እንደማይሆን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የግብፅ ቀጣናው ላይ ማንጃበብ ረብ የለሽ ማድረግ ያስችላል።
እንደሚታወቀው ከዛሬ 14 ዓመት በፊት የዓባይ ግድብን መሠረተ ድንጋይ ስናስቀምጥ የግብፅ መንግሥት ቁጣና ጫጫታ ጎልቶ ይሰማ ነበር። ማስፈራሪያና ዛቻውን፣ ወታደራዊ ጡንቻን ለማሳየት ይደረግ የነበረውን ሩጫ፣ ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት አግኝቶ ኢትዮጵያን ከዓለም መድረክ ላይ ለማስገለል የነበረውን ውክቢያ፣ ለጉድ ነበር። እንዲያውም ያንን ሁሉ የተመለከተ ‹‹ዛሬ ግድቡ ይጠናቀቃል›› የሚል ግምት አልነበረውም። ይሁን እንጂ ውሻው እንደጮህ ግመሉም ጉዞውን እንደቀጠለ እዚህ ደርሰን እውነታውን ተመልክተናል።
ዛሬስ? ዛሬም ከዚህ የተለየ ነገር እንደሌለ የግብፅ መንግሥት እንዲገነዘብ ማድረግ ያስፈልጋል። በወታደራዊ ስምምነትና ከበባ፣ ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በማቃቃር፣ በዓለም አቀፍ ክስና እሩጫ የሚቀየር አቋም አለመኖሩን ማስረገጥ ይገባል። ‹‹የባህር በር ይገባኛል›› ጥያቄ በዚህ ውዥንብርና ሁካታ የሚቆም አለመሆኑን ኢትዮጵያውያን ግልፅ ማድረግ ይጠበቅብናል። መንግሥት የጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል አለበት። በብዙ ጩኸት መካከል ዓባይን መገደብና ሃይል ማመንጨት እንደቻልነው ሁሉ የባህር በር ፍላጎታችንንም ከጎረቤቶቻችን ጋር ሳንቃቃር እና ብሄራዊ ጥቅማችንን ሳንጎዳ እንደምናሳካ ማሳየት ይኖርብናል።
ይህ ሲሆን ቀደምት ከአባቶቻችን ጀምሮ ልናሳካው የምንሻው የአፍሪካውያንን መተባበር፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትብብር፣ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትና በጋራ የመልማት ህልም እውን ማድረግ እንችላለን። ከሁሉ በላይ ግን ሁሌም በኋላ ቀርነታችን፣ በድህነታችን እና በራሳችን የተፈጥሮ ሀብት ገዝፋ በመውጣት የበይ ተመልካች እንድንሆን ለምትሻው ግብፅና ለተቀያያሪው የሴራ ስልቷ የማንበገር መሆናችንን በድጋሚ የምናሳይበት ይሆናል። ሰላም!!
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም