ለምግብ ዋስትና መጠበቅና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ተስፋ የተጣለበት የዶሮ ርባታ

ኢትዮጵያ ለእንስሳት ርባታ ምቹ ሥነ-ምህዳርና የአየር ጠባይ እንዳሏት ይታመናል። ሀገሪቱ በከብት ሀብቷ በአፍሪካ በአንደኛነት ከዓለም ደግሞ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተሰልፋ የምትታይበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል።

ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሕዝቧን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና መጫወት ላይ የተሠራው ሥራ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ ይታመናል። ይህንን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ሥራ መሥራት ያስችል ዘንድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ከተጀመረ ወዲህ በተለይ ምርታማነት ማሳደግ ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የመርሃ ግብሩ መጀመር በተለይም በግለሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናንና የምግብ ሥርዓትን በማረጋገጥ ረገድ አወንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ይህም በመሆኑም ዘንድሮ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንቁላል በስፋት መመረት መቻሉንና ህብረተሰቡም እንቁላል በአነስተኛ ዋጋ እንደልብ ማግኘት እስከመቻል መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። ምርታማነቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተም ነው ።

ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የዝግጅት ክፍላችን ባካሄደው የመስክ ምልከታ በተለይ የመኖ አቅርቦትና የቅድመ ወላጅ ጫጩት ዶሮን እንደልብ ማግኘት ላይ አምራች ግለሰቦችም ሆኑ ኢንተርፕራይዞች የተቸገሩበት ሁኔታ ስለመኖሩ ተረድተናል።

አምራቹ በተደጋጋሚ የሚገጥመውን ችግር በመፍታትና በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ የውጭ ምንዛሬን በመታደግም ሆነ ተጨማሪ የገቢ አማራጭ በመፍጠር ላይ ምን እየተሠራ ነው ስንል የጠየቅናቸው የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋት መርሃግብር እንደ ሀገር ከተጀመረ ወዲህ የዶሮም ሆነ አጠቃላይ የእንስሳት ሀብቱን በተጨባጭ ጥቅም ላይ ማዋልና የዜጎችን ሕይወት መለወጥ የሚያስችል ውጤት እየተመዘገበ ነው።

መንግሥት በዋናነት ዝርያ ማሻሻል፤ የመኖ እና የዶሮ ጫቹት ስርጭት እንዲሁም መሰል ግብዓቶችን አቅርቦት ማሻሻል ላይ ሰፊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ በዚህም በየአመቱ የሚገኘው ምርት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ብለዋል።

‹‹እንደሀገር ለዘርፉ በተሰጠው ሰፊ ትኩረት በ2014 ዓ.ም ላይ 26 ሚሊዮን የዶሮ ጫጩት ለአርቢዎች አሰራጭተናል፤ ዘንድሮ ደግሞ ይህንን ቁጥር በሶስት እጥፍ በማሳደግ 72 ሚሊዮን ጫጩት አሰራጭተናል›› በማለት ዶክተር ፍቅሩ ይናገራሉ። በዚያው ልክም እንቁላልና የዶሮ ስጋም በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ልዩነቶችን ማሳየታቸውን ይጠቅሳሉ።

በ2014 ዓ.ም 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን እንቁላል መመረቱን አስታውሰው፤ በ2016 ላይ ደግሞ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን እንቁላል ማምረት መቻሉን ያስረዳሉ። ዘንድሮ ለማምረት ታቅዶ የነበረው 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን እንደነበር አመልክተው፤ መሃል ላይ ከእንቁላል ዋጋ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ችግር የእቅዱን 94 በመቶ ብቻ ማሳካት መቻሉን አስገንዘበዋል።

በዶሮ ስጋ ምርት ረገድም ከዚህ ቀደም እንደሀገር የነበረው የማምረት አቅም እስከ 90 ሺ ቶን ይደርስ እንደነበር አስታውሰው፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምርትና ምርታማነት ማሻሻል ላይ በተደረገው ርብርብ በ2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ 205 ሺ ቶን የዶሮ ስጋ ማቅረብ መቻሉን ሚኒስትር ዴኤታው ይጠቅሳሉ። ይህም ከቀድሞው ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ የጨመረ መሆኑንና ለዘርፉ ትልቅ ስኬት እንደሆነም ተናግረዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ የዶሮ መኖ ማቀነባባሪያ ፋብሪካዎች በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ በብዛት የሚገኙ ቢሆንም፣ በሌሎች አካባቢዎች መሰል ፋብሪካዎች ባለመኖራቸው አምራቾች እዚህ ድረስ ለመምጣት የሚገደዱበት ሁኔታ ነበር። ይህም የማምረቻ ወጪያቸውን ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ በምርት ዋጋ ላይ የራሱ አሉታዊ ሚና ነበረው።

ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር መጀመር ጋር ተያይዞ እያንዳንዱ ክልል ቢያንስ አንድ ማቀነባበሪያ እንዲኖረው በመንግሥት አቅጣጫ ተቀምጧል። በዚህም መሠረት በቅርቡ አሶሳ ላይ የተመረቀውን ጨምሮ ቦንጋ፣ ጅግጅጋና በሌሎችም የክልል ዋና ከተሞች ላይ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎቹ እንዲተከሉ ተደርጓል።

‹‹ከእነዚህም በተጨማሪ ሃዋሳና ቢሾፍቱ ላይ በግልም ሆነ በኢንተርፕራይዞች ደረጃ የተቋቋሙ በርካታ ማቀነባበሪያዎች አሉ። ባህርዳር ላይ ደግሞ ትልቅና ኤክስፖርት ደረጃ የሚያደርግ ትልቅ የመኖ ፋብሪካ ተከፍቷል›› የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም በመሆኑ አምራቾቹ ርቀት መጓዝ ሳይጠበቅባቸው በአቅራቢያቸው መኖ እያገኙ ምርታማነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻላቸውን አስታውቀዋል። አዳዲስ ማቀነባበሪያዎችን ከመትከል ጎን ለጎን ነባሮቹም ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል መንግሥት የቅድመ ወላጅ ዶሮ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ በማስገባት ለአርቢዎች ያከፋፍል እንደነበር ዶክተር ፍቅሩ ያስታውሳሉ። ‹‹እንደሚታወቀው እነዚያን የቅድመ ወላጅ ጫጩቶች ለማስገባት ደግሞ ከፍተኛ የሚባል የውጭ ምንዛሬ እጥረት ስለነበር በዚህ ሁኔታ ምርታማነትን በታሰበው ልክ ለማሳደግ ፈታኝ ነበር፤ ትልልቅ አምራቾችም በተደጋጋሚ የሚያነሱትም ይህንን ችግር ነበር›› ይላሉ። ይህንን ችግር በዘላቂነት መፍታት ያስችል ዘንድ መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጉን ይጠቁማሉ። በተለይም እነዚህ አምራቾች ድጋፍ እንዲያገኙ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት በኩል ለብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ ተፅፎ ዶላር በተሻለ መልኩ እንዲያገኙ ሲደረግ እንደነበር ይጠቅሳሉ።

‹‹በዚህም ከውጭ የሚመጡት ወላጅ ዶሮዎች (ፓረንት ስቶክ) ቁጥር ጨምሯል፤ ግን አሁንም ቢሆን በድጋፍ የሚደረገው አሠራር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል አልነበረም›› ይላሉ። በየጊዜው ወላጅ ዶሮ ከውጭ የማስገባቱ ሂደት ኢትዮጵያ ሁሌም በሌላ ሀገር ምርት ላይ ጥገኛ ሆና እንድትቀጥል የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር አምራቾችን የሚያበረታታ አለመሆኑን ያነሳሉ።

ይህንን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚድሮክ ቢዝነስ ግሩፕና ከውጭ የቅድመ ወላጅ ዶሮ አምራች ኩባንያ ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ የቅድመ ወላጅ ስቶክ ፋርም ግንባታ ከሰሞኑ ማስመረቋን ያመለክታሉ። ‹‹ይህ ሃዋሳ ሻላ ላይ ቢሻንጉራቻ አካባቢ በኤልፎራ የሚሠራ ፋብሪካ ግንባታው ተጠናቆ የቅድመ ወላጅ ጫጩት ለማምረት ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈጥረዋል። ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ የራሳችን የቅድመ ወላጅ ጫጩት ፋርም እንዲኖረን በማድረግ ፈር ቀዳጅ ነው›› ይላሉ።

የቅድመ ወላጅ ዶሮ ፋብሪካው መከፈቱ እንደሀገር የነበረውን ፍላጎት ከማርካት ባለፈ ወደፊት ከዚህ በላይ በመሥራት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም በመንግሥት በኩል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዳሉ። ‹‹ይህ ፋብሪካ በአንድ ጊዜ ወደ ስድስት መቶ ሺ ጫጩቶችን የመያዝ አቅም ይኖረዋል። እያንዳንዳቸው ከሚጥሉት እንቁላል ጋር ሲደመር በሚሊዮን የሚቆጠር ዶሮ ለማምረት የሚያስችል ነው፤ ይህም ከሀገር ውስጥ ፍላጎት አልፎ ለውጭ ገበያም ለማቅረብ የሚያስችል ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።

ግብርና ሚኒስቴር ኢቢሲን ጠቅሶ በማህበራዊ ድረገፁ ላይ እንዳሰፈረው፤ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አማካኝነት የተገነባው የቅድመ ወላጅ (Grand­parent) ዶሮዎችን በማምጣት በኢትዮጵያ በርካታ ዶሮዎች እንዲመረቱ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ይኸው በሃዋሳ ከተማ አቅራቢያ ሻሎ እርሻ በመባል በሚታወቀው የሜድሮክ ኩባንያ የኤልፎራ የዶሮ ማዕከል የቅድመ ወላጅ ዶሮ (Grandparent Generation Chicken Farming) ከፍተኛ የእንቁላል እና የስጋ ምርት መስጠት የሚችሉ የዶሮ ዝርያዎችን በመጠቀም ጥራት ያለው የዶሮ ስጋ ምርት እና እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በከፍተኛ መጠን ማምረት ያስችላል።

በዘገባው እንደተመለከተው፤ በእድገት ጥራት፣ በሽታ በመከላከል እንዲሁም ከፍተኛ የእንቁላልና የስጋ ምርት ያለው የዶሮ ስጋ ምርት እና እንቁላል ምርት በመስጠት የሚታወቁ ጥራት ያላቸው የዶሮ ዝርያዎችን በመጠቀም በሚከናወነው በዚህ በዓይነቱ ዘመናዊ የዶሮ ርባታ ዘዴ በርካታ ሀገራት ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህ ረገድ ከእ.ኤ.አ ከ1920 ጀምሮ በቅድመ ወላጅ ዶሮ ርባታ የተሰማራው ኢቪያገን ኩባንያ ውጤታማ የእንቁላል እና የስጋ ዶሮዎችን አምርቶ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ግንባር ቀደም ነው። ኩባንያው በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና በእሲያ በሚገኙ ከ100 ሀገራት በላይ ገበያውን በበላይነት መቆጣጠር ችሏል።

ኤልፎራ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የቅድመ ወላጅ ዶሮ ሥርዓትን ወደ ሥራ በማስገባት በአጠቃላይ 150 ሚሊዮን ዶሮዎችን በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዝግጅት ማጠናቀቁን ነው የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ማስታወቁንም በዘገባው ተመላክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ፋብሪካውን በጎበኙበት ወቅት እንደገለፁት፤ በሌማት ትሩፋቱ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት የምግብ ሉዓላዊነት አረጋግጣ ከልመና ትገላገላለች።

ማዕከሉ ከሀገር አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ገበያ ውስጥ ቁም ነገር ያለው ሥራ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረው፤ ከ90 እስከ 100 ሚሊዮን የዶሮ ጫጩት መፈልፈል እንደሚችል ጠቁመው፤ ‹‹‘ኢትዮጵያ ሰጪ እንጂ ለማኝ መሆን የለባትም’ የሚለውን ሃሳብ ማሳኪያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል›› ብለዋል። የሌማት ትሩፋት አካል የሆነው የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ ማዕከል በሀገር ደረጃ የምናልመውን በተሟላ መልኩ ለማሳካት ያስችላል›› በማለትም ገልፀዋል።

አሁን ላይ 80 ሚሊዮን ዶሮ በሀገር ደረጃ የማራባት አቅም እንዳለው ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከስድስት ወር በኋላ ከ90 እስከ 95 ሚሊዮን ዶሮ ማርባት እንደሚቻልም ይጠቁማሉ። ‹‹ዘንድሮ 80 ሚሊዮን ዶሮ በማቅረብ አሳክተናል›› ብለው፤ በሚቀጥሉት ዓመታት 150 ሚሊዮን የዶሮ ጫጩት ለማድረስ እየተሠራ መሆኑንም ይጠቁማሉ። ይህ ቁጥር ሀገሪቱ ካላት አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት አኳያ በቂ ባለመሆኑ መሰል ሥርዓቶች መዘርጋታቸው ተገቢና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት ተናግረዋል።

ለዶሮ እርባታ ኢትዮጵያ ያላት የአየር ጠባይ ምቹ መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ምቹ ሁኔታ ወደ ጥቅም መቀየር ያስችል ዘንድም በርካታ ዘመናዊ የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ ማዕከሎችን ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል። ‹‹ከአራትና አምስት ዓመታት በኋላ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ጫጩቶችን የማስፈልፈል አቅም ላይ እንደርሳለን›› በማለትም አክለዋል። ለዚህም በቂ የሆነ መኖ አስፈላጊ በመሆኑ ከሦስት ሺ ሄክታር በላይ ማሳ ላይ መኖ እየተመረተ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በጥቂት ሀገራት በብቸኝነት የተያዘው የቅድመ ወላጅ ዶሮ ርባታ በኢትዮጵያ ለመጀመር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጪነት፣ በወዳጆች ትብብርና በሚድሮክ ድጋፍ የቅድመ ወላጅ ዶሮ ርባታ ማሽን ሰሞኑን በማዕከሉ መተከሉን በዘገባው ተመልክቷል። በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሃዋሳ ከተማ የተቋቋመው ይህ ፕሮጀክት የውጭ ምንዛሬ ወጪን በማስቀረትና የሌማት ትሩፋትን በመደገፍ አስተዋፅኦው ከፍተኛ ስለመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውንም ጠቅሷል። በዋናነት ግን የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ለመቀየር መሠረት እንደሚጥልና ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You