ተግባረ ዕድ ኮሌጅ – በጥራት ሥራ አመራር ሽልማት

የዛሬው የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በእጅ ሙያ ትምህርት ለማሠልጠንና ሀገሪቷ የሚያስፈልጓትን የቴክኒክ ባለሙያዎች ለማፍራት በሚል በ1934 ዓ.ም እንደተቋቋመ ታሪክ ያስረዳል። ኮሌጁ የሥልጠና ሥራውን ‹‹ሀ›› ብሎ ሲጀምር ለሥልጠና የሚመጡ ወጣቶች ትምህርት ቤቱን ለመቀላቀል ምንም አይነት የቀለም ትምህርት ደረጃ አይጠየቁም ነበር። በመኪና ማሽከርከር፣ በመኪና እድሳት፣ በብየዳ፣ በግንበኛነት፣ በአናፂነት፣ በኤሌክትሪክና በብረት ሥራ ነበር ለመሠልጠን ወደ ኮሌጁ የሚመጡት።

ሠልጣኞች በስልጠና የሚቆዩበት ጊዜ መጀመሪያ ለሶስት ወራት የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ግን ወደ ስድስት ወር እንዲራዘም ተደርጓል። በኮሌጁ የመጀመሪያ ሁለት ምሥረታ ዓመታት ትምህርቱ የሚሰጠው በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ብቻ ነበር። በከሰአቱ ክፍለ ጊዜ ደግሞ ተማሪዎች ጂምናስቲክ እንዲሠሩ ይደረጋል። ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የሚመለመሉ ሠልጣኞች ትምህርት ደረጃ ወደ አምስተኛና ስድስተኛ ክፍል ከፍ እንዲል ተደረገ። እንዲህ እንዲህ እያለ ለሶስትና ስድስት ወራት ይሰጥ የነበረው ሥልጠናም በ1938 ዓ.ም ወደ ሶስት አመት እንዲራዘም ሆነ። በፈረንሳይኛ ይሰጥ የነበረው ትምህርትም ወደ እንግሊዝኛ ተቀየረ።

ከ1942 እስከ 1950 ዓ.ም ወደ ኮሌጁ መግቢያ መመዘኛ ስምንተኛ ክፍል ማጠናቀቅን እንደመስፈርት የተጠቀመበትና የሥልጠና ጊዜው ወደ አራት አመት የተራዘመበት ወቅት ነበር። እነዚህ ዓመታት ሠልጣኞች በሥልጠና ቆይታቸው ለሥራ ብቁና ለውድድር ዝግጁ ሆነው እንዲወጡ ለማድረግ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ተመድበው ለግማሽ ቀን መማር የጀመሩባቸው ወይም የትብብር ሥልጠና የወሰዱባቸው ታሪካዊ አመታት ናቸው።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የስምንት ሲደመር አራት /8+4/ ሥልጠና ፕሮግራም እስከ 1971 ዓ.ም ሲሠራበት የቆየ ሲሆን፤ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል በተደረገው የአስር ሲደመር ሁለት /10+2/ የሥልጠና መርሃ ግብር እንዲተካ ተደርጓል። ሆኖም ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ተግባረዊ የተደረገው የ10+2 መርሃ ግብር ሠልጣኞችን በበቂ ሁኔታ አጠቃላይ እውቀትና ክሂሎት ከማስጨበጥ አንፃር በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ወደ 10+3 ከፍ እንዲል ሆነ።

ይህ መርሃ ግብር ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 1980 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ወደ አዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ገብቶ ለመማር 10ኛ ክፍልን ከማጠናቀቅ ባሻገር የተሻለ ትምህርት ደረጃ ማስመዝገብና መልካም ሥነ ምግባር መያዝን ይጠይቅ ነበር። የአዲስ አበባ ተግባረ እድ ትምህርት ቤት በሀገር አቀፍ ደረጃ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ተቀርፆ ወደ ተግባር ከተገባበት እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ ለበርካታ ዓመታት በአጠቃላይ በ8 የሙያ ትምህርት መስኮች ሠልጣኞችን እየተቀበለ በማስተማር የሚታወቅ ብቸኛው የከተማዋና የሀገሪቱ አንጋፋ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ተቋም ነው።

የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከተመሠረተበት 1934 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ጊዜ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሠልጣኞችን በማሠልጠን በከተማዋ አዲስ አበባ፤ እንዲሁም እንደ ሀገር ይታይ የነበረውን የሠለጠነ የሰው ሃይል እጥረት በመቅረፍ ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። 1994 ዓ.ም በኮሌጁ ታሪክም ሆነ እንደ ሀገር የሙያ ሥልጠናና የቀለም ትምህርት በአዋጅ እንዲለያዩ የተደረገበት ወቅት ነበር። በዚህም የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቀርፆ ከተገባበት 1994 ዓ.ም ጀምሮ የሚሰጣቸውን የሥልጠና ዘርፎች በማሳደግ የኮሌጅነት ደረጃን መያዝ ችሏል።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከሙያ ትምህርት ጎን ለጎን ይሰጣቸው የነበሩትን የቀለም ትምህርቶች በመተው ሙሉ በሙሉ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎችን ብቻ መስጠት ጀምሯል። የቅበላ መስፈርቱም በ10ኛና በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተኛ በሚወሰን ውጤት ሆነ። በ10+1፣ 10+2 እና 10+3 ከሰባት በማያንሱ ዲፓርትመንቶች በተለያዩ የሙያ መስኮች ከ3 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ሠልጣኞችን በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት ክፍለ ጊዜ አሠልጥኖ ባለሙያዎችን እያስመረቀ በጊዜ ሂደት አልፏል።

ኮሌጁ መንግሥት ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት አዋጭ በሆኑ የሥልጠና ዘርፎች ላይ በማተኮር እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ በ10+3 የማሠልጠን ትግበራ ሲፈፅም ቆይቶ በመቀጠል የቅበላ መስፈርት እንደተጠበቀ ሆኖ ሥልጠናው በደረጃ እንዲሆን በመደረጉ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 5 ድረስ በሙያ አብቅቶ ማስመረቅ ችሏል። በተለያዩ ጊዜያት በከተማ፣ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሥልጠና ሂደትና በሌሎች መስፈርቶች ተወዳድሮ በአሸናፊነት፣ በአንደኛ ደረጃ በማጠናቀቁ እንደ ሽልማት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የሥልጠና ክፍሎች ማስፋፊያ ሥራዎችን እንዲያከናውን በማሰብ ሁለት ጂ+7 ህንፃዎች እንዲገነቡለት ተደርጓል።

ኮሌጁ የሚያሠለጥናቸው ሠልጣኞች በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራ ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖራቸው ወደ ልህቀት ማእከልነት ለማደግ የሚያስችለውን አቅም መገንባት ችሏል። ወቅታዊ የሠልጣኞች የቅብላ አቅሙም በመደበኛው፣ በማታውና በቅዳሜና እሁድ ሥልጠና መርሃ ግብር በዘጠኝ የሥልጠና ዘርፎች በአጠቃላይ 8ሺህ ሠልጣኞችን የማሠልጠን አቅምን ገንብቷል። ከሰሞኑ ደግሞ ይህ አንጋፋ ተቋም የ82ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን እያከበረ ባለበት ወቅት በምስራቅ አፍሪካ፤ ብሎም በመላው አፍሪካ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ይበልጥ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለውን የISO 9001/2015 የጥራት ሥራ አመራር ሰርተፍኬት ሽልማት አግኝቷል።

የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ግሩም ግርማ እንደሚናገሩት፣ ኮሌጁ ባለፉት 82 ዓመታት ከተመሠረተባቸው ዓላማዎች አንፃር ሲመዘን ከ120ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ወቅቱ የሚፈልገውን ሥልጠና በመስጠት፣ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂን በማሸጋገር፤ በአራቱ ድጋፍ ማአቀፎች ደግሞ ለኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ በመስጠት ምርትና ምርታማነታቸውን ማሻሻል የሚችሉበትን ሥርዓት ሲያግዝ ቆይቷል፤ አሁንም ይህንኑ ሥራ እያከናወነ ይገኛል። በተያዘው በጀት አመት ኮሌጁ ከከተማ አስተዳደሩ የተሰጡትን ዋና ዋና ተልእኮዎችና ሰፋፊ ሥራዎች በስኬት ከመወጣት በተጨማሪ፤ የሪፎርም ሥራዎችን ወደ ተግባር በማስገባት ቁልፍ ስኬቶችን አስመዝግቧል።

ከእነዚህ የሪፎርም ተግባራት መካከል የተቋሙን ገፅታ ትርጉም ባለው መልኩ የሚቀይር ሥራ ተከናውኗል። በሌላ በኩል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መቀነስና የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን የሚያስችል ሥራ ተከናውኗል። ኮሌጁ በ82 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን በመተግበር፣ የደምበኞችን ፍላጎት ማእከል መነሻ በማድረግና እርካታቸውን መዳረሻ በማድረግ ከላይ የተጠቀሰውን የጥራት ሥራ አመራር ሰርተፍኬት ሽልማት ማግኘት ችሏል።

በሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር አነሳሽነት ታህሳስ 2015 ዓ.ም ወደ ሥራ ከተገባበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች በኮሌጁ ተሠርተዋል። የተቋሙን ገፅታ ከመቀየር፣ አሠራርን ከማሻሻል፣ የሠራተኞችን አቅም ከማሳደግ አንፃር ብዙ ልፋት የሚጠይቁ ሥራዎች ቢኖሩም በዚህ ረገድ ስኬታማ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል። ኮሌጁ የጥራት አመራር ሥርዓት በመተግበሩ ምክንያት በስትራቴጂክ እቅዱ ያስቀመጠውን ራእይ ከማሳካት ባሻገር ለኮሌጁ ማህበረሰብ የኩራት ምንጭ ከመሆንና ለተጨማሪ ተልእኮ ተፈፃሚነት ይበልጥ መነቃቃት ከመፍጠሩም ባሻገር የኮሌጁንና ሠልጣኞቹን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይትና ተአማኒነት የሚያሳድግ መሆኑ ተነግሮለታል።

የኮሌጁ አሠራር ከምንም በላይ በቢሮክራሲ ውስጥ የሚሠራውን፣ እያንዳንዱን ሥራና የሚወሰነውን ውሳኔ ተገማችና ግልፅ ፍሰት ያለው ሥራን መሥራት የሚያስችል በመሆኑ የተገልጋዮችን እንግልት ከመቀነስም በላይ አሁን ላይ ፈታኝ የሆነውን የደምበኞችን እንግልት በመቀነስ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን እንደ አንድ የመንግሥት ተቋም ዜጎች በመንግሥት ተቋማት ላይ ያላቸውን እምነት የመጨመር ሚና ለመወጣት ያግዘዋል።

በርግጥ እንዲህ አይነቱ የሪፎርም ሥራ ለኮሌጁ የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አይደለም። ኮሌጁ እድሜውንና ገናናነቱን የሚመጥኑ ከዚህ የላቁ ሥራዎች የሚጠበቁበት እንደመሆኑ መጠን፣ እንደ አመራርም ሆነ እንደ ሠራተኞች በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መአዛ አበራ እንደሚናገሩት ከሆነ የአዲስ አበባ ተግባረ እድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ባሳየው ከፍተኛ የሥራ አመራር ብቃት ነው ይህን ሽልማት ያገኘው። የአመራር ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ፣ በተቋም ውስጥ ያለውን የአሠራር ሥረዓት ማዘመን፣ በዓለም አቀፍ የአሠራር ሥርዓት መቅረፅ፤ እንዲሁም የመምህራንና የማኔጅመንቱን አቅም የመገንባትና በዚህ የአሠራር ሥርዓት ውስጥ ማለፍ ግድ ይላል። ስራንና ትጋትንም ይጠይቃል።

ከዚህ አንፃር የተግባረ እድ ፖሊ ቴኪኒክ ኮሌጅ ላሳየው ቁርጠኛ አመራር የሚገባውን የሥራ አመራር ጥራት ሽልማት አግኝቷል። ይህም ለሌሎች መሰል ተቋማት አርያ የሚሆን ነው። ይህ በISO 9001/2015 የአሠራር ሥርዓት ውስጥ ማለፍ ምርትና ምርታማነትን የሚጨመር፣ ወጥ የሆነ አሠራር በኮሌጅ ውስጥ እንዲኖር የሚያስችል፣ የደምበኛን እርካታ የሚጨምር፣ የአሠራር ሥርዓትን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያድግ የሚያስችልና የተቋሙን ውጤታማነት የሚጨምር ነው። በዚህ የአሠራር ሥርዓት ውስጥ ማለፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎትን ጭምር ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችል ነው።

በርካታ የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በኢትዮጵያ እንደመኖራቸው ልክ እንደ ተግባረ እድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ሁሉ በእንዲህ አይነቱ የአመራር ሥርዓት ውስጥ ማለፍ የአሠራር ሥርዓታቸውን እንዲያዘምኑ፣ ደምበኞቻቸውን እንዲጨምሩና በአገልግሎት አሰጣጥ እንዲረኩ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ትምህርት እሚወስዱበት ነው። ይህንን ተሞክሮ ሌሎች ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ወስደው ወደ ተግባር መለወጥ ይኖርባቸዋል። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅትም አገልግሎት ለመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ ነው።

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ድርጅት የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን ብቻ አይደለም እውቅና የሚሰጠው። ተቋሙ ሌሎችም የትምህርት ማኔጅመንት ሥርዓት ISO 21001 ሰርተፍኬት ይሰጣል። ይህም አሁን ኮሌጁ ላገኘው የሥራ አመራር ጥራት ሽልማት ድጋፍ ሆኖታል። በቀጣይም ሌሎች ሰርተፍኬቶችም አሉና ኮሌጁ በዚህኛው ሽልማት ሊዘናጋ አይገባም። ከዚህ አንፃር አሠራሩን ከዓለም አቀፍ አሠራር ሥርዓት ጋር በመፈተሽ በዛ አሠራር ሥርዓት ውስጥ በማለፍ ትጋቱን መጨመር ይኖርበታል።

የአዲስ አበባ ሥራና ክሂሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር አበራ ብሩ እንደሚሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሳታፊ ለመሆን ተወዳዳሪነትና ብቃት ይጠይቃል። ለጥራትና ለተወዳዳሪነት ደግሞ ወሳኙ ነገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላትና እነርሱን መተግበር የግድ ይላል። ከዚህ አንፃር እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉ የሥራ አመራር ስልቶችንና ሥርዓቶችን ለመተግበር ከጊዜ ወደ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በጅምር ላይ ቢሆንም ለውጥ እየታየ መጥቷል።

ከዚህ በፊት በተለያዩ የማኔጅመንት መሣሪያዎች፣ ካይዘንም ይባል በሌላ አይነት አኳኋኖች ሲደረጉ የነበሩ ነገሮችን እንደማሳያ መውሰድ ይቻላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በድፍረት የተገባባቸውና ውጤት የተገኘባቸው ጉዳዮች ቢኖሩ የጥራት አመራር ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ነው። ይህን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ከሆኑ ተቋማት መካከል ደግሞ አንዱ የአዲስ አበባ ተግባረ እድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አንዱ ነው። ይህ የሚያሳየው እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጥራትና ውድድር ላይ የተመሠረተ ምርትና አገልግሎትና ብቃት ያለው የሰው ሃይል ማቅረብ፤ እንዲሁም ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት እንደተሰጠው ያሳያል።

እነዚህን የጥራት ሥራ አመራር መሣሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ የተፈለገውም አንደኛ ከጥራት አንፃር የሚሰለጥኑ ወጣቶችና ሴቶች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው። ሁለተኛውና ዋናው ጉዳይ ደግሞ ኢንዱስትሪዎችን ለማብቃት እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ነው። በተለይ ኢንተርፕራይዞችን በተሟላ ሁኔታ ድጋፍ ለመስጠት መጀመሪያ አስፈላጊ የሚባሉ ሥርዓቶችን በተቋም ውስጥ መተግበርና ማሸጋገር ያስፈልጋል። ሶስተኛውና አሁን ላይ እየተገባበት ያለው ጉዳይ አገልግሎት ማቅረብና ምርት ማምረት ሲሆን፤ ምርትና አገልግሎቶችን ከድጋፍ በዘለለ ለገበያው ለማቅረብ የጥራት ሥርዓት አመራሩ አቅራቢዎች ጥራት ያላቸውንና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል። ከዚህ አንፃር ISO 9001/2015ን ተግባራዊ ማድረግ እንደ ትልቅ ስኬት ይቆጠራል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You